Wednesday, July 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ጭርታው!

ሰላም! ሰላም! ወገኖቼ በሙሉ ሰላማችሁ ይብዛ፡፡ ሰላም ለሁላችሁ ይሁን፡፡ ያው እንደምታውቁት ያለፈውን በጭፍን ማክፋፋት ወይም በፍቅር ማሞገስ፣ ያለውን በጥላቻ ማጠልሸት ወይም ሸብረብ እያሉ ማዳነቅ ምንም ፋይዳ እንደሌለው የማውቀው እኔ ደላላው አንበርብር ምንተስኖት፣ በምክንያታዊነት ለመራመድ ‹ወደፊት› ብዬ ወደ ሥራዬ ተሰማርቻለሁ። ዘመኑን አማነውም አላማነውም፣ መንግሥትን አማረርነውም አሞገስነውም፣ መዓልትና ሌቱ መምሸት መንጋቱን መቼ ይተዋል? እንዲያው ነው ልፋታችን እባካችሁ፡፡ በዚህ ቀኑ በንዳድ አቅል በሚያስትበትና ሌቱ ውርጩ ሸንቋጭ በሆነበት የሰኔ ወር እንጀራ ፍለጋ ተፍ ተፍ እያልኩ ነው፡፡ መንግሥት በጋው ተጋምሶ የጀመረው የኮሪደር ልማት ላይ ሲያተኩር፣ እኔ ደግሞ ልማቱ ያፈናቀላቸውን ወገኖች ቦታ ለማስያዝ ላይ ታች እላለሁ፡፡ ልፋቱ እኩል አይቆጠርም እንጂ የእኔም እኮ ከኮሪደሩ ልማት አያንስም ነበር፡፡ ምን ያደርጋል አስተዋዋቂ አጣሁ፡፡ ይህንን ብሶቴን የሰማው ምሁሩ የባሻዬ ልጅ፣ ‹‹ልብህ እንደ ተራራ ቢያብጥ ወኔ ካልጨመርክበት ፋይዳ የለውም…›› ብሎ ሞራሌን ሊያነሳሳ ሲሞክር ሳቅኩኝ፡፡ ድንቄም ልበ ተራራ!

በቀደም አንዱ አስተዛዛኝ መሳይ ተፈናቃይ ዘመዱን በተመለከተ፣ ‹‹ምንስ ቢሆን አሁን በዚህ ክረምት ወዳጅ ቀርቶ ጠላትስ ቢሆን ቤትህን ልቀቅ ማለት ተገቢ ነው?›› እያለ ለአዛውንቱን ባሻዬ ሲያዋያቸው፣ ‹‹ወይ አንተ ድሮና ዘንድሮ አንድ መሰለህ? ዘመኑ በቴክኖሎጂ ተራቆ አገር ምድሩ የተቆለለ ቆሻሻ ሲመስል የዘመኑ ሰው ትዕግሥት የለውም፡፡ ‹በድሮ በሬ ያረሰ የለም› እንዲሉ ምሬትህን ጣሪያ ስታስነካው በፀረ ልማትነት ተፈርጀህ እንደ ቆሻሻ ናፋቂ ትታያለህ፡፡ ይልቁንስ ከዘመኑ በረከት ለመቋደስ ዘዴው ላይ መረባረብ ይሻላል…›› ብለውት ከምሁሩ ልጃቸው ብሰው ተነተኑለት። ሰውዬው የባሻዬን ትንተና ሰምቶ ሲያበቃ፣ ‹‹ወቸው ጉድ ዘንድሮ ልጁም አዋቂውም ነው እንዴ ቃላት እያቀነባበረ የሚያነቃን፡፡ ወጣቶቹስ ይሁን በትምህርትም በቴክኖሎጂውም የሚያገኙት መረጃ ስላለ ነው፡፡ እርስዎ ግን ከዳዊትዎ ላይ ተነስተው ይህንን ሁሉ ትንተና ከየት አመጡት እባክዎ…›› ሲላቸው፣ ‹‹አንተ ሞኝ ዕውቀቱ ሁሉ ያለው መዝሙረ ዳዊት፣ መጽሐፈ ምሳሌና መክብብ፣ የሐዋርያው ጳውሎስ መልዕክቶች ውስጥ ሆኖ ሳለ ምኑ ነው የሚገርምህ…›› እያሉ ሲስቁበት፣ ሳቃቸው ከእኛ ሠፈር እስከ ዋሽንግተን ዲሲ ድረስ የሚሰማ ይመስል ነበር፡፡ ከተጋነነ ይቅርታ!

አንድ ደንበኛዬን ቀጥሮኝ ስለነበር ተገናኝተን በገጠመው ጉዳይ አጀብ እየተባባልን ወደ ጉዳያችን በእሱ ዘመናዊ ‹ጄቱር› ተሽከርካሪ ጉዞ ጀመርን። ትንሽ እንደ ሄድን ጨዋታችንን አቁመን በስሱ ተከፍቶ ወደ የምንሰማው ኤፍኤም ሬዲዮ ሁለታችንም ጆሯችንን ቀሰርን። ተናጋሪው እየደጋገመ ስለመጪው ዓመት ትሪሊዮን ብር ሊደርስ ትንሽ ስለቀረው በጀት ረቂቅ ወሬ ይጀምራል። ያወራል እንጂ አይጨርስም። በመሀል ደግሞ የውጭ ዝነኞችን በጣልቃ እያስገባ ሳለ ደንበኛዬ በጣም ተናዶ፣ ‹‹እሺ እንደ ዜና ይወራ ግድ የለም። ትንታኔ ውስጥ መግባት ምን አገባንና እኛ? በዚያ ሜሲ አለ። በዚህ ሮናልዶ አለ። ሪሃና፣ ሻኪራ፣ ቢዮንሴ፣ ምንትሴ… መቼ ነው እነዚህ ሰዎች ስለእኛ ኑሮ የሚያወሩት? ምናለበት ግን ሚዲያችን ቀልዶ ባያስቀልድብን?›› አለ። ‹‹እንዴት?›› አልኩት ጥቂት ላናግረው። ቀልብ በጠፋበት ዘመን ከቀልቡ ሆኖ የሚያወራ ሰው ጥቂት በመሆኑ፣ በሰማው ነገር እጅግ ተቆርቁሮ ሳየው ከልቡ መሆኑ ስለገባኝ። እሱም ግራ ገብቶት፣ ‹‹እንዴት?›› አለኝ ዞር ብሎ ዓይቶኝ። እኔም ቀልጠፍ ብዬ ልመልስለት ስዘጋጅ አንድ ነገር ትዝ አለኝ፡፡ ፖለቲካ ነዋ፡፡ ወሬ የሚጣፍጠው እንደ ምሁር ፖለቲካ ጣል ሲያደርጉ አይደል!

‹‹ምን መሰለህ ይህንን ጉዳይ ከአጠቃላዩ የአገር ተጨባጭ ሁኔታ አንፃር ብንተነትነው ምን ይመስልሃል?›› ስለው እሱም ራሱን እየነቀነቀ፣ ‹‹ስንት ለሐሳብና ነፃነትና ዕድገት የሚታገሉ ወገኖችን እያከሸፈ እንዲህ ያሉትን የኅብረተሰብ ንቃተ ህሊና ከማጎልበት፣ ጨርሶ የሚያኮስስ ረብ አልባ ዘገባ የሚዘግቡትን ዝም መባላቸው ነዋ። ስንት ቁምነገር ማውራት በሚገባን ሰዓት፣ ስንት ልንነጋገርባቸው የሚገቡን ጉዳዮች እያሉ ወጣቱ በኳስ ተጫዋቾች የጫማ ቁጥር፣ በፊልም ተዋናይ የአልጋ ልብስ ቀለም ሲደነቁር መዋል አለበት? አዲሱ ትውልዱ ራዕዩና ዓላማው ተዋናይነትና አዝማሪነት ብቻ ሲሆን ዝም ይባላል? መንግሥትስ በዚህ ተጨባጭ ሀቅ የሚዲያ ነፃነት አለ ብሎ እንደ መከራከሪያ ይዞ ሊሟገት ይገባዋል? ኧረ ተወኝ እባክህ…›› አለኝ በረጅሙ ተንፍሶ። ‹ኧረ በደንብ ተንፍስ› አልኩ እኔም በልቤ። ትችትና አስተያየት ቅፅል እያሰጡ እንካ ሰላንቲያ በሚያስነሱበት አገር፣ ወደ ውስጥ ተናግሮ ወደ ውስጥ ተንፍሶ እንዴት ይኖራል? እንዴትም!

ጉድና ጉዳ ጉዱን እዚህና እዚያ ስባክን እያየሁ ከአንደኛው ጉዳይ ወደ ሌላው እዘላለሁ። በድለላ ሙያ ከተሰማራችሁ ‹ያልተገላበጠ ያራል› የሚሉት አባባል በደንብ እንደሚሠራ ታረጋግጣላችሁ። ዳሩ የዘመኑ ሰው እንዲህ ያለውን ሥራ ማነቃቂያ አባባል የሚሞክረው አጉል አጉል ቦታ ሆኗል። እስኪ አስቡት ሕዝብ ለማገልገል ተሹሞ እንደ መዥገር የሰው ደም ሲመጥ፣ የትውልድ አርዓያና ተምሳሌት ለመሆን በቃል ኪዳን ታስሮ ትዳር መሥርቶ ሲያበቃ ከአንዷ ወደ ሌላዋ ሲገለባበጥና ተነካክቶ ሲያነካካ ምን እንዲባል አይጨንቅም? ስል የሰማኝ አንድ ወዳጄ፣ ‹‹በጣም እንጂ፣ ደግነቱ በቤተሰብና በትዳር ላይ ያለውን የሞራል ዝቅጠት ለመታደግ ራሱን የቻለ ‹ፀረ ወዲያ ወዲህ› የሚባል ኮሚሽን ባይቋቋምም፣ በሙስናው በኩል ፀረ ሙስና የሚባለው ኮሚሽን ካልተጠናከረ ጥቅሙ አይታየኝም…›› አለኝ። ታዲያ አፋችንን ሞልተን በሚጀመረው መልካም ተግባር ጮቤ እንዳንረግጥ፣ የምንጀምረው እንጂ የምንጨርሰው እንደ ኮሪደር ልማቱና ፓርኮች እጅግ ጥቂት ነው። ቢሆንም እንዳስጀመረን ያስጨርሰን ማለት ወግ ነው!

በወርኃ ሰኔ ሥራ ቀዝቅዞ  ወዲያ ወዲህ እያልኩ ስዘዋወር ያገኘሁት ሥራ ያው የቤት ድለላ ሆነ። ምን ይደረግ ቤት በሌለበት አገር ቤት ፈላጊው በዝቶ እኮ ነው። አንዱ ታዋቂ ቤቱን ለመሸጥ ያቀረበውን ዋጋ ስሰማ ሄጄ ለማየት ጓጓሁ። የተባለውን ቤት ሄጄ ሳየው የተጠሩት ሚሊዮን ብሮች ያንሱታል እስክል ድረስ አስገራሚ ነበር። ወዲያው ቢቀናኝ የማገኘውን ረብጣ ሳሰላው ሐሴት ያቁነጠኝጠኝ ጀመር። በጠፋ ሥራ ገዥ ይገኛል ብዬ ካሰላሁት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ሁለት ደንበኞች ሲገጥሙኝ ግን ከሚገባው በላይ ድንግጥ አልኩላችሁ። ምን አስደነገጠህ አትሉኝም? በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ በሚገኘው የኅብረተሰብ ክፍል ልክ፣ ሚሊዮን ምንም የማይመስለው የኅብረተሰብ ክፍል መበራከቱ ነዋ። ‹ካፒታሊዝም ይሉሃል ይኼ ነው!› የሚለው ምሁሩ የባሻዬ ልጅ ስላቅ ምፀት አዘል አባባል ጆሮዬ ላይ ደወለ። ይኼኔ አንድ ወሬ የጠማው ሰማኝ መሰል፣ ‹‹ታዲያስ ዕድገት የለም ትላላችሁ፣ ግን ይኼው ሚሊዮን በግለሰብ ደረጃ አስቆጠርናችሁ…›› ብሎ ገላመጠኝ። ምን ትሉታላችሁ? የሰውዬው ንግግር ደንበኛዬ ጆሮ ጥልቅ አለ መሰል፣ ‹‹ምንድነው የሚለው?›› ብሎ ጠየቀኝ። እኔም የተናገረውን ስደግምለት፣ ‹‹ተወው እባክህ ሞኝና ወረቀት ያስያዙትን መቼ ይለቅና?›› ብሎ ተረተበት። ለተረት ማን ብሎን!

ሥራዬን ጨራርሼ ኮሚሽኔን በስልኬ ተቀባብዬ ሌላ ቀጠሮ ይዤ ሳበቃ ወደ ቤቴ ገሰገስኩ። ሠፈር ስደርስ ከባድ ዝምታ ነግሷል። ግራ ገብቶኝ ወደ ቤቴ ሮጥኩ። ልክ በሩን ከፍቼ ስገባ ባሻዬና ማንጠግቦሽ ግቢ ውስጥ ቆመው ወግ ይዘዋል። ‹‹ባሻዬ? ምን እግር ጣለዎት?›› አልኳቸው  ካፖርቴን እያወለቅኩ። ‹‹ጭር ሲልብኝ ጊዜ እዚህ ይሻላል ብዬ መጣሁ…›› አሉኝ የአባትነት ፈገግታቸው በቅንነት ፊታቸውን እያበራው። ሳቅ አልኩና በጣም ሳልቀርባቸው ከጎናቸው ስቆም፣ ‹‹በክረምቱ ችግር ይከፋል አሉ። ቀለብ አላችሁ ለመሆኑ? ጠንቀቅ ብላችሁ ተንቀሳቀሱ። መቼም ከላይ ትዕዛዝ ከመጣ መመለስ ባይቻልም መጠንቀቅ አይከፋም…›› ብለው ማንጠግቦሽን እያዩ ሲናገሩ፣ መቼ ከላያችን ላይ ተነቅሎ እንደሚጠፋ በማይታወቀው የኑሮ ውድነት ምክንያት በጭንቀት ልፈነዳ ደረስኩ። በስንቱ እንጨነቅ!

ባሻዬ ደግሞ መተንፈሻ ሲያገኙ ወጉን ይችሉበታል። ‹‹አዬ ባሻዬ በምናችን ልንችለው አምላክ እንዲህ ያለውን ነገር በእኛ እንዲሆን ይፈቅዳል?›› ብላቸው፣ ‹‹ኧረ እውነትህን ነው። በአንድ በኩል ቀማኛውና ምቀኛው፣ በሌላ በኩል ከራስ ጥቅም ውጪ ምንም በማይታያቸው ጉዶች ምክንያት የሰላማችን መናጋት፣ እልፍ ስትል የአመለካከትና የአስተሳሰብ መዛባት እያሰቃኙን መቼ አገገምን? ጭራሽ ከቀዬ መፈናቀል ተጨምሮበትማ ስንቱን እንቻል?›› በማለት የተናገሩት ውስጤ ቀርቷል። ‹ስንቱን እንቻል?› ብለን የምንተወው ሳይሆን የምንታገለው መብዛቱ ይገርማል፡፡ የኑሮ ውድነት የሚባለው መቅሰፍት ዙሪያችንን በየቀኑ እየከበበ መላወሻ እያሳጣን፣ መፍትሔውን ፈልጎ ለማግኘት ግን ዳተኝነት ወይም መዘናጋት ይስተዋልብናል፡፡ ይህ አልበቃ ብሎን ሰላማችን ተቃውሶ የዓለም መጠቋቆሚያ መሆናችን ያናድዳል፡፡ ጡጦውን እንደተቀማ ሕፃን ከሚያለቅሱ ፖለቲከኞች ጀምሮ አገሪቱን ለመዝረፍ እስካሰፈሰፉ ተከታዮቻቸው ድረስ የሚሰማው ይሉኝታ ቢስነት ያስደንቃል፡፡ እኔ በደላላ ጭንቅላቴ ይህንን ታዝቤያለሁ፡፡ እናንተም የራሳችሁን ትዝብት ጨምሩበት፡፡ ጉዳት የለውም!     

በሉ እስኪ ነገር ሳናመጣ  እንሰነባበት። ያንን ጉደኛ ቤት ካሻሻጥኩና ደህና ኮሚሽን ካገኘሁ በኋላ ልክ አልነበርኩም። ሲሸልስ፣ ባንኮክ፣ ዱባይ፣ ካሪቢያን ወይም ባሃማስ ደሴቶች ሄዶ መዝናናት አምሮኝ ነበር። ይህችን የነተበች ካፖርቴን በአዲስ ቀይሬ መዘነጥ ልቤ ቋምጦ ነበር። ከዚያ ‹ቤትሽን ከቤቴ ላይ አንሺልኝ› ከሚባልበት መንደር ወጥቼ አፓርትመንት መከራየትም አሰኝቶኝ ነበር። ምን ያደርጋል ዕድሜ ለኑሮ ውድነት እንኳንስ እኔ ምስኪኑ ደልቃቃዎቹም የግንባታ ግብዓቶች ተወደውባቸው እጅና እግራቸው ታስሮ ተቀምጠዋል፡፡ እነሱን ሆኜ ሳስበው ግን ዕንባ ያስመጣል፡፡ ቁርስ ዱባይ፣ ምሳ ለንደን፣ እራት ኒውዮርክ እያሉ ዓለምን ሲያስሱ የነበሩ ‹ምስኪን› ወገኖቼን ሳስብ አዘንኩ፡፡ ጎበዝ አንዳንዴም በድሎት ውስጥ ለነበሩ እንዘን እንጂ፡፡ መተዛዘን ለመቼ ነው? ምቀኝነት ያተረፈልን መጨካከን ስለሆነ ሥራ ለሚፈጥሩልን ወገኖችም እንዘን፡፡ በበኩሌ ምቀኝነት ስለሚያስጠላኝ ማዘኔን የምገልጸው በሐዘን ነው፡፡ ሐዘን ወደ ደስታ ይቀየር ዘንድ አንድ ላይ ሆነን ወደ ፈጣሪያችን አቤት እንበል፡፡ ይጠቅመናል እንጂ አይጎዳንም!

አሁን ሳስበው አጉል ዓይን ውስጥ መግባት ደግሞ እንደምታውቁት ከዓይን ያጠፋልና አርፌ እንደ ወትሮዬ በጊዜ ወደ ተለመድችዋ ግሮሰሪ አመራሁ። አንገቴን በኩራት ቀና አድርጌ ስገባ ግሮሰሪያችን ቀዝቅዛለች። ባለቤቱም በገበያው መቀዛቀዝ ተጨንቆ መንፈሱ ቀዝቅዟል። ከደጅ አየሩ አንዴ ይወብቃል ሌላ ጊዜ ይቀዘቅዛል። ውስጥ ደግሞ ‹ሙዱ› ቀዝቃዛ ነው። ጥቂት ቆይቶ ምሁሩ የባሻዬ ልጅ ከች አለ። ሁለታችን ብቻ ያላበው ቢራ ይዘን እያንቆረቆርን፣ ‹‹አንበርብር ይኼን ፍራ…›› አለኝ። ‹‹የቱን?›› ስለው፣ ‹‹ይኼንን ጭርታ…›› አለኝ። ‹‹ለምን እፈራለሁ? እንዲያውም የመሠልጠን ምልክት ነው፡፡ ይኼ የሚያሳየው የቁጠባ ባህላችን የማደግ ጅማሮ ምልክት ነው…›› አልኩት የግሮሰሪዋ ባለቤት እንዳይሰማኝ ድምፄን ዝቅ አድርጌ። ‹‹የእኛ ባህሪ በአንድ ጊዜ ተቀይሮ? የድንጋጤ ሽሽትን የቁጠባ ሥልጣኔ አልከው? እውነት ኖሮን ነገን አስበንና ለነገ ተጨቀን እያልከኝ ነው? መልስልኝ እንጂ ራሳችንን እየቆጠብን ወይስ ከኑሮ ውድነት እየተቆጠብን?›› ሲለኝ ከመመለስ ይልቅ እኔ ራሴ ተቆጠብኩ። ግን ጭርታው ምንድነው? ወበቁ ወይስ ብርዱ ነው? የእውነት ጥንቃቄ ነው? እኔ እንጃ፡፡ ለማንኛውም ለጭርታውም ግራና ቀኝ እየተስተዋለ። መልካም ሰንበት!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት