Sunday, July 14, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልየዒድ አል አድሃ ቀናት

የዒድ አል አድሃ ቀናት

ቀን:

ዛሬ በሕዝበ ሙስሊሙ ‹የመስዋዕት በዓል› በመባል የሚታወቀው የዒድ አል አድሃ አረፋ  እየተከበረ ነው። አረፋ በእስልምና ትልቅ ቦታ ከሚሰጣቸው በዓላት አንዱ ነው።  ስለ በዓሉ ጥንተ ነገር  በአንድ መጣጥፍ  እንደተገለጸው፣ ነቢዩ ኢብራሂም  ልጃቸውን ኢስማዒልን ለአላህ ትእዛዝ በመታዘዝ ለመሰዋት ያደረጉትን ፈቃደኝነት የሚዘክር ነው።የኢብራሂም የእምነት ፈተና ታሪክ በቁርኣን ውስጥ መጠቀሱ፣ በዓሉ የእምነትን፣ የአምልኮና የመስዋዕትን አስፈላጊነት ለማስታወስ እንደሚያገለግል ተገልጿል።

የዒድ አል አድሃ ቀናት | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
ዒድ አል አድሃ ከዓመታት በፊት በአዲስ አበባ ስታዲየም ሲከበር

እስላማዊው ቅዱስ ቀን ዓረፋ፣ በዓመተ ሒጅራ መሠረት በጨረቃ አቆጣጠር በ12ኛው ወር ዙልሂጃ 10ኛ ቀን – ዘንድሮ በፀሐይ ሰኔ 9 ቀን 2016-  ላይ ውሏል፡፡ ክብረ በዓሉ ከዋዜማው እስከ ማግስት  ይዘልቃል።

‹‹ዓረፋና ዒድ አል አድሃ›› በሚል በተዘጋጀ አንድ ጽሑፍ እንደተመለከተው፣ ‹‹ዒድ አልአድሃ በመታዘዝ የተገኘ የድነት መገለጫ ነው፡፡ እነዚህ ቀናት አደምና ሐዋን ከጥፋት በዓረፋ ጊዜ ያገናኘ፣ ነቢዩላህ ኢብራሂምም መሥዋዕትነት በፈጣሪ መዳኑን ያረጋገጡላቸው ተምሳሌቶች ናቸው፡፡››

የዒድ አልአድሃ ቀናት ዳግም ከፈጣሪ ጋር መታመንን የሚያስገኙ ኢስላማዊ አስተምህሮ በዓላት ናቸው፡፡ የዓረፋ በዓል የሐጂ ሥነ ሥርዓት የሚከናወንበት በዘጠነኛው ቀን ሲሆን፣ ማግስቱ 10ኛው ቀን ደግሞ ዒድ አልአድሃ የስግደትና  ሶላት በዓል ነው፡፡

የዒድ አል አድሃ ቀናት | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር

‹‹ዓረፋ ማለት ቀኑ ነው፡፡ አደም እና ሐዋ በጀነት ሲኖሩ እንዳይነኩ የተከለከሉትን በዲያብሎስ አማካይነት ስተው ወደ ምድር በተሰደዱበት ጊዜ ሁለቱም ተለያይተው ነበር፡፡ ለበርካታ ዓመታት ተለያይተው ከኖሩ በኋላ ሳዑዲ ዓረቢያ ውስጥ ዓረፋት በሚባል ቦታ የተገናኙበትም ነው፤›› ይላል መጣጥፉ፡፡

‹‹ሁለቱም ‘አረፍ’ ተባባሉ፡፡ አረፍ ማለት ‘አወቅከኝ? አወቅሽኝ?’ ማለት ነው፡፡ ይህን መሠረት በማድረግ መላው የእስልምና ሃይማኖት ተከታይ በዚህ በ9ኛው ቀን በቦታው በመዋል ከፍተኛ መንፈሳዊ ጸጋን መጎናጸፍ እንደሆነ ያምናል፡፡ የሒጅራ ጉዞ ከእስልምና ሃይማኖት አስተምህሮዎች አንዱ ነው፡፡ ተከታዮችም ወደእነዚህ ቅዱስ ቦታዎች በሕይወት ዘመናቸው ቢያንስ አንድ ጊዜ እንዲሄዱ ያዝዛል፡፡ በሐጂ ሥነ ሥርዓት ‘ረብ’ የሚባሉ ጠጠሮችን ይወረወራል፤ የጌታ ሰው ነቢዩ ኢብራሂም ለአምላካቸው ያላቸውን ታዛዥነት ለመገምገም ሰይጣን ፈትኗቸው ነበር፡፡ በዚህ ተራራ ላይ በመሆን ክፋቱን ጠጠር በመወርወር አባሮታል፡፡ ይህን ለማስታወስ አሁንም ጠጠር ይወረወራል፡፡ ሐጂ ሐዋና አደምን ያገናኘበት ወቅት መዘከሪያ ነው፡፡››

የዒድ አል አድሃ ቀናት | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
በበዓሉ ለእርድ
ከሚቀርቡ አንዱ
በግ ነው

በእስልምና የጨረቃ አቆጣጠር የመጨረሻ ወር በዙልሂጃህ 10ኛው ቀን  ላይ  የሚውለው ኢድ አል አድሃ፣ ከአምስቱ የእስልምና ምሶሶዎች አንዱ የሆነው የመካ የሐጅ ጉዞ ፍፃሜ ነው። የወሩ  መጠርያ  ‹‹ዙልሂጃህ››  ትርጉሙ የሐጅ ወር ማለት ነው፡፡በዚህ ወር ሙስሊሞች ወደ መካ ካባ ይዘልቁበታል፡፡

‘ዐንደርስታንዲንግ ዒድ አል አድሃ’ (Understanding Eid al- Adha) በተሰኘ መጣጥፍ  በበዓሉ ስለሚፈጸሙ ሥርዓቶች እንደሚከተለው ገልጿል:-

“የኢድ አል-አድሃ ማዕከላዊ ሥነ ሥርዓት ቁርባኒ ነው። የእንስሳት መስዋዕትነት፣ በተለይም ፍየል፣ በግ፣ ላም ወይም ግመል ይፈጸማል። ከዕርዱ አንድ ሦስተኛው ለድሆች እና ለችግረኞች ይሰጣል፣ አንድ ሦስተኛው ከጓደኞችና ከዘመዶች ጋር ይካፈላል፣ ቀሪው አንድ ሦስተኛው ለቤተሰቡ ይሆናል። ይህ የመስጠት ተግባር በጎ አድራጎትን፣ ያለው ለሌለው ማካፈልን ያመለክታል።

ሙስሊሞች ቀኑን የሚጀምሩት በመስጊድ ወይም በአደባባይ በሚደረግ ልዩ የጸሎት አገልግሎት ነው። ከጸሎቱ በኋላ ብዙውን ጊዜ የመስዋዕትነትን፣ የልግስናን እና የእምነት እሴቶችን የሚያጎላ ስብከት ይከተላል።

ባህላዊ ገጽታ

ዒድ አል አድሃ  አረፋ  የማኅበረሰብ የደስታ ጊዜ ነው። ቤተሰቦች አንድ ላይ እንዲሰባሰቡና እንዲያከብሩ ያስችላቸዋል። ሰዎች ምርጥ ልብሳቸውን ይለብሳሉ፣ ጓደኞቻቸውን እና ዘመዶቻቸውን ይጎበኛሉ። ከበዓሉ ምግቦች ጣፋጮችን ጨምሮ  እንደየባህሉ ይቋደሳሉ።

በኢትዮጵያ በዓሉ ከሚከበርባቸው አካባቢዎች አንዱ የስልጤ ዞን ነው።  ስለ አከባበሩ የቅርስ ባለሥልጣን ባህላዊ ቅርሶች ምዝገባ ድርሳን ላይ የሚከተለው ሰፍሯል፡፡

‹‹አረፋ ገና ከመድረሱ ቀደም ብሎ በእያንዳንዱ ቤተሰብ  ዝግጅቱ ይጀመራል። ሴቶች ቅቤ፣ ቅመማ ቅመምና ቆጮ ያዘጋጃሉ፣ አባወራዎች ለእርድ የሚሆን ሠንጋና የማገዶ እንጨት ያቀርባሉ፡፡ ልጃገረዶች ቤቶቹን በተለያዩ የማስዋቢያ ቀለማት በመጠቀም ይቀባሉ፣ ግቢን ያፀዳሉ፡፡ በበዓሉ በተለያዩ አካባቢዎች የሚኖሩ ተወላጆች ለወላጆቻቸው ስጦታ በመያዝ ወደየአካባቢያቸው  ይገባሉ፡፡

‹‹በአረፋ ወደ ቤተሰቡ ያልመጣ በሕይወት እንደሌለ ይቆጠራል፡፡ ቤተሰብንም ሥጋት ላይ ይጥላል፡፡ የአረፋ በዓልን በስልጤ ልዩ ድምቀት የሚሰጠው በበዓሉ ሰሞን የሚጀመረው የልጃገረዶች ጭፈራ ነው፡፡ በየመንገዱ ያሉ ልጃገረዶች ከአካባቢያቸው ራቅ ብለው በመሄድ በነፃነት የሚጫወቱበትና የሚጨፍሩበት ወንዶች ወጣቶችም በመሄድ አብረው ሲጫወቱ ለወደፊት የምትሆን የትዳር አጋራቸውን የሚያጩበት ወቅት ነው፡፡ በዚህም የአረፋ በዓል በአብዛኛው የመተጫጫ የጋብቻ ወቅት ነው፡፡

‹‹በበዓሉ ዋዜማ የሚከበረው የሴቶች አረፋ ሲሆን የወንዶች ደግሞ የበዓሉ ስግደት በሚከናወንበት ዕለት ነው፡፡ በሴቶች አረፋ ክልፋን (የተከተፈ ጐመን) አተካና (ቡላ፣ አይብና ቅቤ) የተለመዱ ባህላዊ ምግቦች ናቸው፡፡ እርዱ የሚከናወነው በበዓሉ ዕለት በሽማግሌ ከተመረቀ በኋላ ነው፡፡ የአረፋ በዓል ብሔረሰቡ ከፍተኛ ትኩረት የሚሰጠውና ዝግጅት የሚያደርግበት የተለያዩ የቤተሰብ አባላት የሚገናኙበት ስጦታ የሚለዋወጡበት ትዳር ያልያዘ የሚተጫጭበት፣ ትዳር የሚመሠርቱበት በዓል በመሆኑ አስፈላጊና ጠቃሚ ነው፡፡

‹‹ጉራጌና የባህል እሴቶቹ›› በሚል ርዕስ በታተመ መጽሐፍ  እንደተገለጸው፣ አረፋ የእስልምና እምነት ተከታይ የሆኑ የጉራጌ ተወላጆች ከየሚኖሩበት የተለያዩ አካባቢዎች ወደ የትውልድ ቀያቸው የሚመለሱበትና በዓሉን ከወላጆችና ከቤተዘመድ ጋር በመሆን የሚያከብሩበት ታላቅ በዓል ነው፡፡

‹‹ለአረፋ በዓል የሚደረገው ዝግጅት በዓሉ ከመድረሱ ቀደም ብለው ባሉት ወራት ውስጥ የሚጠናቀቅ ይሆናል፡፡ በዚህም እናቶች ለበዓሉ የሚሆን መጪ (ምርጥ) ቆጮ፣ ቅቤ፣ ሚጥሚጣ …ወዘተ ሲያዘጋጁ፣ ሴቶች ልጆቻቸው ደግሞ የመኖሪያ ቤቶችን በማስዋብ፣ የመመገቢያ ቁሶችን በማጽዳትና ሌሎች ለበዓሉ የሚያስፈልጉ ቅድመ መሰናዶዎችን በማሟላት ሥራ ይጠመዳሉ፡፡

‹‹ልክ እንደ ሴቶቹ ሁሉ ወንዶቹም ለአረፋ በዓል የሚያከናውኗቸው የሥራ ድርሻ አላቸው፡፡ ለማገዶ የሚሆን እንጨት ፈልጦ ማዘጋጀት፣ ለእርድ የሚሆን ከብት ማቅረብ በአባቶችና በወንድ ልጆቻቸው የሚከወን ይሆናል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የአረፋ በዓል ቀደም ሲል ተጫጭተው የቆዩ የሚሞሸሩበት፣ ሌሎች ደግሞ በቀጣዩ ሦስት ጉልቻ ለመመሥረት የትዳር ጓደኛቸውን የሚመርጡበትና በባህሉ መሠረት የሚያጩበትም ጭምር መሆኑንም ተወላጆች ያስረዳሉ፡፡

‹‹ሌላው የአረፋ በዓል ያለው ማኅበራዊ ፋይዳ በተጣሉ ሰዎች መሀል እርቀ ሰላም እንዲወርድ የማስቻል ብቃቱ ይሆናል፡፡ ከበዓሉ በፊት የተቀያየሙ ባልና ሚስት፣ ልጅና ወላጅ፣ ጎረቤታሞች …ወዘተ በአረፋ ሰሞን ‹‹ይቅር›› ተባብለው ሰላምን ያወርዳሉ፡፡ ለበዓሉ የተዘጋጀውን አብረው በመብላትና በመጠጣት ይደሰታሉም፡፡

‹‹የበዓሉ ማኅበራዊ ፋይዳው ከአራቱም ማዕዘናት በዓሉን ለማክበር ወደ ትውልድ አካባቢው የመጣው ሙስሊሙ የጉራጌ ተወላጅ በቤተሰባዊና ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ መክሮ ለተለያዩ ችግሮች መፍትሔዎችን የሚሻበት መሆኑ ይሆናል፡፡ የቤተሰብ ሕይወት እንዲሻሻል ‹ምን ይደረግ?› በአካባቢው ልማት እንዲስፋፋ ‹ምን እንሥራ?› ብለው ለበዓሉ እትብታቸው ወደ ተቀበረበት ምድር የተመለሱት በአንድነት ከቤተሰብና ከማኅበረሰቡ ጋር ይመክራሉ፡፡ መፍትሔዎችንም ያበጃሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሚዲያው በሕዝብ የህሊና ችሎት ከተዳኘ በቂ ነው!

መሰንበቻውን ድንገት ሳይታሰብ ያለ ማስጠንቀቂያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ...

የባህር በር ጉዳይ

በታምሩ ወንድም አገኘሁ ድሮ ድሮ ገና ልጅ ሆኜ ፊደል እንደቆጠርኩ...

አገሩ ፖለቲካዊ ስክነትና መደማማጥ ያስፈልገዋል

በንጉሥ ወዳጀነው    ኢትዮጵያ የሁላችንም የጋራ ቤት ነች፡፡ ‹‹ጥያቄዬ ተመለሰልኝ››፣...

የመንግሥት የሰብዓዊ መብት ተቋም ለምን የመንግሥት ሚዲያን ማስተማር አቃተው

በገነት ዓለሙ የአገራችን የ2016 የበጀት ዓመት መሰናበቻና የአዲሱ የ2017 በጀት...