Sunday, July 14, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናአስተዳደሩ ኦዲት ለማድረግ ዕግድ በጣለበት የማኅበር ቤቶች መሬት ላይ አስቸኳይ ውሳኔ እንዲሰጥ...

አስተዳደሩ ኦዲት ለማድረግ ዕግድ በጣለበት የማኅበር ቤቶች መሬት ላይ አስቸኳይ ውሳኔ እንዲሰጥ ጥያቄ ቀረበ

ቀን:

በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ በቱሉ ዲምቱና በዓለም ባንክ አካባቢዎች በ1996 ዓ.ም. በሕጋዊ መንገድ ተደራጅተው የመኖሪያ ቤት መሥሪያ መሬት የተሰጣቸው የማኅበር ቤቶች፣ እስካሁን ኦዲት ተደርጎ ግኝት ባለመቅረቡና ውሳኔ ባለመሰጠቱ፣ ንብረታቸውን እንዳያንቀሳቅሱ የተደረገበት ምክንያት በአስቸኳይ ውሳኔ እንዲሰጥበት፣ ለከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ ጽሕፈት ቤት ጥያቄ ማቅረቡን፣ የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም አስታወቀ፡፡

ዕንባ ጠባቂ ተቋም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽሕፈት ቤት የጋራ መኖሪያ ቤቶች ኅብረት ሥራ ማኅበራት ያቀረቡትን አቤቱታ መርምሮ ተገቢውን የመፍትሔ ሐሳብ እንዲሰጥበት፣ ከወር በፊት ግንቦት 27 ቀን 2016 ዓ.ም. በደብዳቤ ጥያቄ ማቅረቡ ታውቋል፡፡

የማኅበር ቤቶችን ጉዳይ በተመለከተ ከ2013 ዓ.ም. ጀምሮ ኦዲት ለማድረግ ከንቲባ ጽሕፈት ቤቱ ዕገዳ በመጣሉ፣ ንብረታችንን እንዳናንቀሳቅስ አድርጎናል የሚል ቅሬታ ከማኅበር ቤቶቹ እንደደረሰው የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም የምርመራ ኃላፊ አቶ መንግሥቱ ቀኜ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

የማኅበር ቤቶችን ጉዳይ በተመለከተ መፍትሔ ያልተሰጠበትን ምክንያት በአሥር የሥራ ቀናት ውስጥ ከበቂ ማብራሪያና ማስረጃ ጋር የከንቲባ ጽሕፈት ቤቱ ምላሽ እንዲሰጥበት ጥያቄ ማቅረቡን አስረድተዋል፡፡

በአሥር የሥራ ቀናት ውስጥ ምላሽ ካልተሰጠ ተቋሙ በአዋጁ መሠረት ሁለተኛ የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ ለመጻፍ እንደሚገደድ ገልጸው፣ ማኅበራቱም ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ ጉዳዩ እንዲታይላቸው የከንቲባ ጽሕፈት ቤቱ በር ማንኳኳታቸውን አቤቱታቸውን ባቀረቡበት ወቅት መናገራቸውን አብራርተዋል፡፡

ለከንቲባ ጽሕፈት ቤቱ የቀረበው ጥያቄ አዎንታዊ ምላሽ ካገኘ ምላሻቸው አሳማኝ ነው የሚለውን፣ እንዲሁም ከተቋሙ ሥልጣን ጋር የሚጋጭ ነገር አለው ወይ የሚለው ታይቶ ወደ ውሳኔ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

ከ1996 ዓ.ም. ጀምሮ ሕጋዊ የመሬት ይዞታ አግኝተን ግንባታ ከጀመርን በኋላ፣ በመሀል ‹‹የተሰጣችሁን መሬት በምን ዓይነት መንገድ እንደወሰዳችሁ በኦዲት እናጣራለን›› ከተባልን፣ አራት ዓመታት ሆኖናል ሲሉ የማኅበር ቤቶች አባላት ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ሥር 901 የማኅበር ቤቶች እንዳሉ የተናገሩት አባላቱ፣ ከእነዚህ ማኅበራት ውስጥ የዛሬ ሁለት ዓመታት አካባቢ 217 ያህሉ ብቻ አገልግሎት እንዲያገኙ መደረጉን ገልጸዋል፡፡

ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽሕፈት ቤት ኦዲት ማድረግ ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ በተደጋጋሚ ጉዳዩ ምን ላይ እንደደረሰ ጥያቄ ማቅረባቸውን አስረድተዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት የቤታቸውን ካርታ አስይዘው መበደርም ሆነ መሸጥ እንደማይችሉ፣ በተደጋጋሚ የከንቲባ ጽሕፈት ቤት ኦዲቱ ስላለቀ በቅርቡ ችግራችሁ ይፈታል የሚል ምላሽ እንደሚሰጣቸው ተናግረዋል፡፡

በማኅበር ቤቶቹ ላይ ዕግድ ከመውጣቱ በፊት ለቤት ግንባታ የሚሆን የግብዓት ዋጋ የተሻለ እንደነበር የገለጹት አባላቱ፣ የችግሩን አሳሳቢነት በመረዳት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽሕፈት ቤት ሁኔታውን ማጤን ይኖርበታል ብለዋል፡፡

በአጠቃላይ በአንድ ማኅበር ውስጥ 12 አባወራ አባላት እንዳሉ፣ ሁሉም 94 ካሬ መሬት ይዞታ እንዳላቸውና ሕጋዊ ሰነድ ያሟሉ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ችግሩ እንዲፈታላቸው ለሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም በደብዳቤ አቤቱታ ማቅረባቸውን ገልጸው፣ አቤቱታቸው ምላሽ የማያገኝ ከሆነ ለተለያዩ መንግሥታዊ ተቋማት ለማሳወቅ ዝግጅት ማድረጋቸውን ጠቁመዋል፡፡

የማኅበር ቤቶቹን ጉዳይ በተመለከተ ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽሕፈት ቤት ጥያቄ ለማቅረብ በተደጋጋሚ ጥረት ቢደረግም ሳይሳካ ቀርቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሚዲያው በሕዝብ የህሊና ችሎት ከተዳኘ በቂ ነው!

መሰንበቻውን ድንገት ሳይታሰብ ያለ ማስጠንቀቂያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ...

የባህር በር ጉዳይ

በታምሩ ወንድም አገኘሁ ድሮ ድሮ ገና ልጅ ሆኜ ፊደል እንደቆጠርኩ...

አገሩ ፖለቲካዊ ስክነትና መደማማጥ ያስፈልገዋል

በንጉሥ ወዳጀነው    ኢትዮጵያ የሁላችንም የጋራ ቤት ነች፡፡ ‹‹ጥያቄዬ ተመለሰልኝ››፣...

የመንግሥት የሰብዓዊ መብት ተቋም ለምን የመንግሥት ሚዲያን ማስተማር አቃተው

በገነት ዓለሙ የአገራችን የ2016 የበጀት ዓመት መሰናበቻና የአዲሱ የ2017 በጀት...