Wednesday, July 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊበትግራይ ክልል ለ13 ወረዳዎች የተበላሸ የምግብ እህል መሠራጨቱ ተረጋገጠ

በትግራይ ክልል ለ13 ወረዳዎች የተበላሸ የምግብ እህል መሠራጨቱ ተረጋገጠ

ቀን:

  • የዕርዳታ እህሉን ያቀረበው ድርጅት በሕግ ይጠየቃል ተብሏል

በትግራይ ክልል ያጋጠመውን የረሃብ አደጋ ለመከላከል የተቋቋመው የአደጋ ጊዜ ምላሽ ሰጪ ግብረ ኃይል፣ ለ13 ወረዳዎች የላከው የምግብ ዕርዳታ የተበላሸ በመሆኑ እንዳይሠራጭ መታገዱ ገተለጸ፡፡

ግብረ ኃይሉ ዕርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ዜጎች የሚያቀርበው 25 ሺሕ ኩንታል የዕርዳታ እህል መግዛት የሚያስችል ገንዘብ ከተሰበሰበ በኋላ ጨረታ በማውጣት እንደሚገዛ ለሪፖርተር የገለጹት የግብረ ኃይሉ የኮሙዩኒኬሽን ባለሙያ አቶ ኢሳያስ ታደሰ፣ በአሁኑ ዙር የነበረው አሠራርም ይህ እንደነበር ገልጸዋል፡፡

ለዕርዳታ የሚውለውን በቆሎ ለማቅረብ 19 ድርጅቶች የጨረታ ሰነዱን በመግዛት የተጫረቱ መሆናቸውንና ከእነዚህ ውስጥም አራቱ ዋጋቸውን አስገብተው አማኑኤል ብርሃነ የእህል ምርት ውጤቶች ጅምላና ችርቻሮ ንግድ ጨረታውን ማሸነፉን የገለጹት አቶ ኢሳያስ፣ የቀረበው የናሙና እህልና ለወረዳዎቹ የተሠራጨው ግን የተለያየ ነበር ብለዋል፡፡

በውሉ መሠረት ድርጅቱ 25 ሺሕ ኩንታል በቆሎ ለማቅረብ ስምምነት ላይ መድረሱንና በመጀመሪያ ዙር ለ13 ወረዳዎች እንዲላክ የተደረገው 9,280 ኩንታል በቆሎ እንደነበር ገልጸው፣ ‹‹ለወረዳዎቹ ከደረሰ በኋላ የዕርዳታ ኮሚቴው እህሉን ለማከፋፈል ሲዘጋጅ መበላሸቱን በመረዳቱ ሪፖርት ተደርጓል፡፡ የተላከው እህል ባለበት ታሽጎ እንዲቆይ በማድረግ ለዕርዳታ ፈላጊዎች እህል መግዣ ገንዘብ በጥሬው መከፋፈል እንዳለበት ተወስኗል፤›› ብለዋል፡፡

ለወረዳዎቹ ከተላው የዕርዳታ እህል የተበላሽ ሆኖ የተገኘው በስህተት ተቀላቅሎ የተላከ ነው ለማለት የማያስደፍርና በርካታ መሆኑን፣ እህሉን ያቀረበው አማኑኤል ብርሃነ የእህል ምርት ውጤቶች ጅምላና ችርቻሮ ንግድን በሕግ ለመጠየቅ የምግብና መድኃኒት ቁጥጥርና ክትትል መሥሪያ ቤት ተጨማሪ ምርመራ እንዲያደርግ ጉዳዩን ማስረከባቸውን ጠቁመዋል፡፡

ከጦርነቱ ወዲህ በትግራይ ክልል የሚገኙ የዕርዳታ ፈላጊዎች ቁጥር ከፍተኛ እንደሆነ የክልሉ መንግሥት በተደጋጋሚ ሲገልጽ ይደመጣል፡፡ ለዚህም ጦርነቱ ይዞት ከመጣው ሰብዓዊ ቀውስ በተጨማሪ፣ በክልሉ ከባድ የሚባል የድርቅ አደጋ ማጋጠሙ ሌላው ምክንያት ነው፡፡ የተረጂዎችን ቁጥር በሚመለከት የአደጋ ሥጋትና ሥራ አመራር ኮሚሽን ቁጥሩ ተጋኖ እንደሚገለጽና ለፖለቲካ ዓላማ ማስፈጸሚያነት እየዋለ ነው ማለቱ ይታወቃል፡፡

ባለፈው ሳምንት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የአደጋ ሥጋትና ሥራ አመራር ኮሚሽንን የመስክ ምልከታ ባደረገበት ወቅት፣ የትግራይና የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ተፈናቃዮች የተበላሸ የዕርዳታ ምግብ እየቀረበላቸው እንደሆነ ቅሬታ አቅርበውልኛል ማለቱን መዘገባችን ይታወሳል፡፡

ሆኖም የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የአደጋ ሥጋትና ሥራ አመራር ኮሚሽን የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ጋሻው ሹሞ፣ የተበላሸ የምግብ ዕርዳታ እየቀረበልን ነው የሚል ቅሬታ እንዳልደረሳቸው ለሪፖርተር ገልጸው ነበር፡፡ ‹‹ጊዜው ያለፈበት ወይም የተበላሸ የምግብ ዕርዳታ አቅርበን አናውቅም፡፡ እንዲህ ዓይነት ቅሬታም አልቀረበልንም፤›› ካሉ በኋላ፣ ‹‹በክልላችን ያሉ ተፈናቃዮች የተወሰኑ ስለሆኑ እዚያ አካባቢም የደረሰ ቅሬታ የለም፤›› ማለታቸው አይዘነጋም፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ የሠራተኞች ማኅበር አመራር ጋር እየተወያዩ ነው]

ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም! በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት። አዎ።...

የሱዳን ጦርነትና የኢትዮጵያ ሥጋት

የሱዳን ጦርነት ከጀመረ አንድ ዓመት ከአራት ወራት አስቆጠረ፡፡ ጦርነቱ...

ግለሰብ ነጋዴዎችን በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ለማድረግ ያለመው ረቂቅ አዋጅ ተከለሰ

በምትኩ የንግድ ተቋማት በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ይሆናሉ...

አሳርና ተስፋ!

ከቱሉ ዲምቱ ወደ ቦሌ ጉዞ ልንጀምር ነው፡፡ ገና ከመንጋቱ...