Wednesday, July 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜና‹‹በመንግሥት ሠራተኞች አዋጅ ውስጥ የብሔር ተዋፅኦ መካተቱ በአተገባብሩ ላይ ፖለቲካዊ ጫና ያመጣል››...

‹‹በመንግሥት ሠራተኞች አዋጅ ውስጥ የብሔር ተዋፅኦ መካተቱ በአተገባብሩ ላይ ፖለቲካዊ ጫና ያመጣል›› የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ዋና ዕንባ ጠባቂ

ቀን:

በሥራ ላይ ያለውን የመንግሥት ሠራኞች ረቂቅ አዋጅ በማሻሻል እንደ አዲስ ተዘጋጅቶ በቀረበውና ውይይት እየተደረገበት በሚገኘው ረቂቅ አዋጅ ውስጥ፣ የብሔር ተዋፅኦ የሚል ድንጋጌ ማካተት፣ በአተገባብሩ ላይ ፖለቲካዊ ጫና ያመጣል ሲሉ የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ዋና ዕንባ ጠባቂ አስታወቁ፡፡

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውይይት እየተካሄደበት ባለው ረቂቅ አዋጅ ላይ እንደ ተብራራው፣ ሥራ ላይ ያለውን አዋጅ ቁጥር 1064/2010 ለማሻሻል ካስፈለጉ ዋና ዋና ምክንያቶች መካከል የብሔር ብሔረሰቦች፣ የአካል ጉዳተኞች፣ የፆታ ተዋፅኦና የመሳሰሉትን ብዙኃነትና አካታችነት ማገናዘቡ ነው፡፡ ‹‹ኢትዮጵያን የሚመስል›› የመንግሥት ሠራተኞች ስብጥርን ከግምት ውስጥ ያስገባ የመንግሥት አገልግሎትና አስተዳደር ሥርዓት መገንባት አስፈላጊ መሆኑም ተገልጿል፡፡

የመንግሥት ሠራተኞች የሰው ኃይል ምልመላና መረጣ በግልጽ፣ በውድድርና በብቃት (ሜሪት) ላይ እንዲመሠረት፣ ሥራን ውጤታማ ለማድረግ የሚያስችል የአሠራር ሥርዓት ለመዘርጋት፣ የተገልጋዩን ማኅበረሰብ ፍላጎትና ጥያቄ በአጥጋቢ ሁኔታ ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል ሥርዓት ለመዘርጋት፣ የመንግሥትን የመፈጸም ብቃት ለማጎልበት፣ የዜጎችን ፍላጎት የሚያረካና ዓለም ወደ ደረሰበት የዕድገት ደረጃ ሊያሸጋግር የሚያስችል የፌዴራል መንግሥት ሠራተኞች አዋጅ ማውጣት አስፈላጊ በመሆኑ እንደሆነም ተብራርቷል፡፡

ይሁን እንጂ ሲቪል ሰርቪሱን በውድድርና በብቃት (ሜሪት) ላይ እንዲመሠረት ማድረግና የብሔር ተዋፅኦ የሚባሉት ጉዳዮች አብረው የማይሄዱ መሆናቸውን በመግለጽ ማስተካከያ እንዲደርግበት አስተያየታቸውን የሚሰጡ አሉ፡፡

በጉዳዩ ላይ ሪፖርተር ጥያቄ ያቀረበላቸው የፐብሊክ ፖሊሲና አስተዳደር  ባለሙያውና የኢትዮጵያ የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ዋና ዕንባ ጠባቂ እንዳለ ኃይሌ (ዶ/ር)፣ በረቂቅ አዋጁ ሲቪል ሰርቪሱ ኢትዮጵያን መምሰል አለበት ተብሎ መቅረቡ ‹‹የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦችን መምሰል አለበት የሚል አንድምታ ሲኖረው፣ ነገር ግን ሲቪል ሰርቪስ የብሔር ተቋም አይደለም፤›› ብለዋል፡፡

አንድ የሲቪል ሰርቪስ ዋነኛ መርሁ ገለልተኛ፣ ሙያንና ብቃትን መሠረት ባደረገ መንገድ እንጂ በብሔር ተዋፅኦ የሚሰባጠር ተቋም ሊሆን አይገባም ያሉት ዋና ዕንባ ጠባቂው፣ ይህ መሠረታዊ ስህተትና የሲቪል ሰርቪሱን አጠቃላይ ቁመናና ተልዕኮ የሚሸረሽር ነው ሲሉ አስረድተዋል።

የአንድ አገር ሲቪል ሰርቪስ ሲቋቋም የትኛውም የመንግሥት ሥርዓት ቢመጣና ቢሄድ ነፃ፣ ገለልተኛና ሥነ ምግባርን የተላበሰ ቁመና ኖሮት በሙያውና በዕውቀቱ የመንግሥትን ፖሊሲና ስትራቴጂ እንዲፈጽም ራሱን ችሎ እንዲቋቋም መደረግ እንዳለበት አስረድተዋል፡፡ አክለውም የመንግሥት ሠራተኛ የመንግሥትን ፖሊሲ የመፈጸምና የማገልገል ግዴታ ያለበት ፈጻሚ በመሆኑ፣ አንድ የሲቪል ሰርቪስ ተቋም ዕውቀትና ሙያን መሠረት ያደረገ ካልሆነ የታሰበውን አገልግሎት ለመስጠት አዳጋች ይሆናል ብለዋል።

በመሆኑም ብሔርን አንዱ የመለያ መሥፈርቱ አድርጎ ወደ ቅጥር ከተገባ የፖለቲካ ጣልቃ ገብነትን እንደሚያመጣና የባሰ ወደ ሌላ ችግር ውስጥ እንደሚያስገባ፣ የብሔርን ተዋፅኦ በአዋጅ ደንግጎ ወደ ሥራ በሚገባበት ወቅት ሁሉም ብሔረሰቦች የውክልና ጥያቄ እንደሚያነሱ፣ ጥያቄውን ለመመለስ ሲባል ደግሞ አንድም አካታች የሚል አሠራር ለመተግበር ሙያ፣ ክህሎትንና ዕውቀትን አደጋ ውስጥ እንደሚከት ገልጸዋል፡፡ በሌላ በኩል ሁሉንም ብሔረሰቦች ላሳትፍ በሚባልበት ጊዜ ያልተካተቱ በመኖራቸው ምክንያት ሌላ የፖለቲካ ጥያቄ እንዲያነሱ ያደርጋል ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ ከ90 በላይ ብሔረሰቦችና ከ80 በላይ ቋንቋዎች እንዳሉ ሰነዶች መኖራቸውን፣ ዘጠና ብሔረሰቦች ካልተካተቱ ሲባል የመንግሥት ሠራተኛ ከዕውቀትና ከብቃቱ በበለጠ የብሔረሰብ ውክልናው አመዝኖ አገልግሎት በብቃት መስጠት እንደማይቻል አዋጁ ለሕዝብ ውይይት ክፍት ከተደረገበት ጀምሮ አስተያየት የሰጡ  አሉ፡፡

በቅርቡ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በረቂቁ ላይ በተካሄደ ውይይት ከኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) የተወከሉ ከፍተኛ የሕግ ባለሙያዋ ሰዊት ዘውዱ በሰጡት አስተያየት፣ በሲቪል ሰርቪስ አዋጁ ኢትዮጵያን የሚመስል ተቋም እንዲሆን የብሔር ስብጥር ቢካተት ተብሎ የቀረበው ለአድልኦ አሠራር የሚዳርግ መሆኑን ተናግረው ነበር፡፡

በተመሳሳይ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፐብሊክ ሰርቪስ የሰው ሀብት ልማት ቢሮ የሰው ሀብት ሥራ አመራር ድጋፍ ክትትልና ቡድን መሪ አቶ አብርሃም ደግፌ፣ ብዝኃነት በሕጎች ውስጥ መካተቱ መልካም መሆኑን ገልጸው በሲቪል ሰርቪስ ዘርፍ ውስጥ ብዝኃነት መግባቱ ግን አገልግሎት አሰጣጡ የሚፈለገውን የሰው ኃይል በዕውቀትና በብቃት እንዳይገባ ያደርጋል የሚል ሥጋታቸውን መግለጻቸው ይታወሳል፡፡

ከዚህ ቀደም ያጋጠማቸውን ጉዳይ ለማሳያነት ሲያነሱ፣ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደደር ‹‹አካታችነት›› በሚል አሠራር የሠራተኛውን ብቃት፣ ልምድና ብዝኃነት በአንድነት ማስኬድ አለማስቻሉን ተናግረዋል፡፡ በዚህም ችግር የተነሳ ለአንድ የሥራ መደብ ለፈተና ከተቀመጡ መካከል አንዱ ተፈታኝ ከፍተኛ ውጤት አምጥቶ ቦታው የሚገባው የነበረ ቢሆንም የብሔረሰብ ተዋፅኦው ኮታ በመሙላቱ፣ ‹‹ብታልፍም አታገኝም›› ተብሎ ያ የሥራ መደብ ክፍት ሆኖ እንደተቀመጠ አስረድተዋል፡፡ ይህ አካሄድ መንግሥት በሲቪል ሰርቪስ ዘርፉ ለውጥ አመጣለሁ ከሚለው አስተሳሰብ ጋር የሚቃረን ሙያንና ብቃትን ችግር ውስጥ የሚከት መሆኑን ተናግረው ነበር፡፡

 ዋና ዕንባ ጠባቂው እንደሚሉት የተሻለው መፍትሔ መንግሥት ሁሉም ብሔረሰቦች ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ከተፈለገ እኩል የትምህርት ዕድል ያላገኙት እንዲያገኙ ማድረግ፣ ከዚያም ባለፈ በሲቪል ሰርቪሱ አዎንታዊ በሆነ መንገድ ለሴቶች የተለየ ነጥብ እንደሚሰጠው ዕድሉን ማግኘት አለባቸው ለሚባሉት ብሔረሰቦች የተወሰነ ነጥብ በመስጠት ማካተት ይቻል ይሆናል ብለዋል፡፡

የብሔረሰቦች ውክልና በፌዴሬሽን ምክር ቤት ነው የሚሉት እንዳለ (ዶ/ር)፣ በሲቪል ሰርቪስ በዕውቀታቸውና በብቃተቻው ተወዳድረው አገርን በነፃነትና በገለልተኝነት ቦታውን መያዝ ያለባቸው ዜጎች እኩል ዕድል እንዲያገኙ መደረግ እንዳለበት ገልጸው፣ የሲቪል ሰርቪሱ በብቃትና በቴክኖሎጂ ታግዞ የግሉን ዘርፍ ዜጎች የሚፈልጉትን አገልግሎት መስጠት በሚችልበት ቁመና ላይ መገኘት አለበት ሲሉ አስረድተዋል።

ከብሔር ይልቅ ሙያዊ ብቃቱና ችሎታው ያለው ሠራተኛ አስፈላጊ መሆኑን በምሳሌ ሲያስረዱ፣ በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የተቀጠሩ የውጭ አገሮች ዜጎች ምን ብሔር ውስጥ ሊመደቡ ነው የሚል ጥያቄ አንስተዋል፡፡ ‹‹መረጃዎች እንደሚያሳዩት በኢትዮጵያ የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ከሚያስተምሩ መምህራን መካከል ከ1,500 በላይ የህንድ ዜጎች ይገኛሉ። በመሆኑም መመዘኛው ሙያዊ ብቃት አላቸው ወይም የላቸውም የሚለው እንጂ፣ ከየት ብሔር መጣህ የሚል ከመጣ የሚያስኬድ   አይደለም፤›› ብለው፣ ዕሳቤው በተግባር ሊሞከር ይችላል ነገር ግን የትም ሊያራምድ አይችልም ሲሉ አክለዋል፡፡

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በተካሄደው ስብሰባ ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ወ/ሮ ስመኝ ውቤ፣ ‹‹ኢትዮጵያ የብዙ ብሔር ብሔረሰቦች አገር ናት፡፡ በመሆኑም የብዙ ብሔረሰቦች መኖሪያ በሆነች አገር በምንም ዓይነት የፌዴራል መንግሥት ተቋም ውስጥ ሠራተኛ የሌለው ብሔር አለመኖሩ ተቀባይነት የለውም፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ 17 ብሔር ብሔረሰቦች በፌዴራል ተቋማት አንድም ሰው የሌላቸው ናቸው፣ በመሆኑም ወደፊት የመንግሥት የሠራተኛ ቅጥር ሲካሄድ እዚህን የኅብረተሰብ ክፍሎች ታሳቢ ሊያደርግ ይገባል፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ የሠራተኞች ማኅበር አመራር ጋር እየተወያዩ ነው]

ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም! በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት። አዎ።...

የሱዳን ጦርነትና የኢትዮጵያ ሥጋት

የሱዳን ጦርነት ከጀመረ አንድ ዓመት ከአራት ወራት አስቆጠረ፡፡ ጦርነቱ...

ግለሰብ ነጋዴዎችን በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ለማድረግ ያለመው ረቂቅ አዋጅ ተከለሰ

በምትኩ የንግድ ተቋማት በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ይሆናሉ...

አሳርና ተስፋ!

ከቱሉ ዲምቱ ወደ ቦሌ ጉዞ ልንጀምር ነው፡፡ ገና ከመንጋቱ...