Wednesday, July 24, 2024

መንግሥታዊ ተቋማት ውስጥ የተንሰራፋው ሌብነት ልዩ ትኩረት ይሻል!

በየዓመቱ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከበጀት ረቂቅ በፊት መቅረብ የነበረበት የፌዴራል ዋና ኦዲተር ግኝት ሪፖርት ማክሰኞ ሰኔ 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ዘግይቶ ሲቀርብ፣ እንደተለመደው የባለበጀት መንግሥታዊ ተቋማት ውስጥ የሚስተዋሉ ችግሮች ተዘርዝረዋል፡፡ ከችግሮቹ መካከል ውዝፍ ተሰብሳቢ ገንዘብ መበራከት፣ በመረጃ ዕጦት ትክክለኛነታቸውን ማረጋገጥ ያልተቻለና ማስረጃ ሳይቀርብ በወጪ የተመዘገቡ ሒሳቦች ማጋጠም፣ ከደንብና ከመመርያ ውጪ ያላግባብ ክፍያዎች መፈጸም፣ የግዥ አዋጅና ደንብ ያልተከተሉ ግዥዎች መፈጸማቸው፣ ከሥራ ለተሰናበቱ ሠራተኞች ደመወዝ መክፈል፣ በአማካሪ መሐንዲሶች ሳይረጋገጥ ለግንባታዎች ክፍያ መፈጸምና ሌሎችም በኦዲት ግኝቱ ተካተዋል፡፡ ከላይ የተጠቀሱትና ሌሎች በርካታ ቢሊዮን ብሮች የባከኑባቸውና የተዝረከረኩባቸው መንግሥታዊ ተቋማት፣ በአገር ላይ ምን ያህል ከባድ ኪሳራ እያስከተሉ እንደሆነ በቀላሉ መረዳት ይቻላል፡፡ ምንም እንኳ መሻሻል ያሳዩ ተቋማት ቢኖሩም የብዙዎቹ ችግር ግን አገር እየጎዳ መቀጠሉ እስከ መቼ ያስብላል፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ በሁሉም የፖለቲካና የኢኮኖሚ ዘርፎች ውስጥ የተሰገሰገው ሌብነት አደብ እንዲገዛ መደረግ አለበት፡፡ በየዓመቱ በፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት የኦዲት ግኝት ሪፖርት ከሚቀርብባቸው ባለበጀት መንግሥታዊ መሥሪያ ቤቶች ብዙዎቹ፣ ጤነኛ ያልሆነ የፋይናንስና የክዋኔ አፈጻጸም እንዳለባቸው በተደጋጋሚ ስማቸው ይነሳል፡፡ በጣም በተሻለ ደረጃ ላይ መገኘት የሚገባቸው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጉዳይ ደግሞ በእጅጉ አነጋጋሪ ነው፡፡ ይህ ችግር ከፌዴራል አልፎ በሁሉም ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች የሚንፀባረቅ ሲሆን፣ ጠንከር ያለ ዕርምጃ መወሰድ ቢጀመር ብዙዎቹ የተቋማት ኃላፊዎች ለእስር ይዳረጉ ነበር፡፡ ከሆስፒታሎችና ከክሊኒኮች ግንባታ፣ ከትምህርት ተቋማት ግንባታና ማስፋፊያ፣ ከመንገድና ከሌሎች መሠረተ ልማቶች ግንባታና ዝርጋታ፣ ከሕዝብ አገልግሎት መስጫዎችና ከተለያዩ የልማት ሥራዎች የሚዘረፈው የሕዝብና የአገር ሀብት ጥቂቶችን እያደለበ፣ ብዙኃኑን ከድህነት ወለል በታች እያደረገ እንደሆነ ፀሐይ የሞቀው ሀቅ ነው፡፡

ለመጪው በጀት ዓመት እንዲውል ታስቦ በቅርቡ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የ971.2 ቢሊዮን ብር በጀት ሲሆን፣ የፌዴራል መንግሥት ከአገር ውስጥ የገቢ ምንጮችና ከውጭ ዕርዳታ በአጠቃላይ 612.7 ቢሊዮን ብር ገቢ እንደሚሰበሰብ በዕቅድ መያዙ ተገልጿል፡፡ በተጨማሪም ባለበጀት መሥሪያ ቤቶች የተመደበላቸውን በጀት ለታለመለት ዓላማ በቁጠባና በላቀ ውጤታማነት ጥቅም ላይ ማዋል እንዳለባቸው ከፍተኛ ግንዛቤ መያዝ እንዳለበት፣ የሚፀድቀውን በጀት የመንግሥትን የፋይናንስ፣ የግዥና የንብረት አስተዳደር ሕጎችንና ሥርዓቶችን ተከትለው ሥራ ላይ ማዋል እንደሚጠበቅባቸው፣ ይህንንም ለማረጋገጥ የክትትልና የቁጥጥር ሥራውን በማጠናከር ከሥርዓቱ ውጪ ለሚደረግ የበጀት አጠቃቀም ተጠያቂነትን የማረጋገጥ እንቅስቃሴ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ማሳሰቢያ መሰጠቱ ይታወሳል፡፡ ማሳሰቢያው መልካም ሆኖ ሳለ ለዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ሪፖርትና መወሰድ ስላለበት ሕጋዊ ዕርምጃ ምክረ ሐሳብ ሲሰጥ ግን ሰሚ ያለ አይመስልም፡፡

የአገሪቱ በጀት በዚህን ያህል መጠን ተሠርቶ ሲቀርብ ግዙፍ ቢመስልም የውጭና የአገር ውስጥ ብድር ዕዳ ክፍያ፣ ለዓመታት የዘለቀ ባለድርብ አኃዝ የዋጋ ግሽበት፣ በተለያዩ ግጭቶች የወደሙ መሠረተ ልማቶችን መልሶ ለመገንባት፣ የፌዴራል መንግሥት ወጪዎች፣ የክልል መንግሥታት ድጋፍ፣ በሰላም ዕጦት ምክንያት የምርትና አገልግሎቶች መቋረጥ፣ የበጀት ጉድለትና የመሳሰሉት ተግዳሮቶች አሉበት፡፡ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ሰላም ቢሰፍን ሊኖረው የሚችለው ዕምቅ አቅም አሁን ካለው በላይ ገቢ ማመንጨት ከማስቻሉም በላይ፣ የተለያዩ የተጋረጡ ፈተናዎችን በቀላሉ ለመሻገር ምቹ ሁኔታዎች ይፈጠሩለት ነበር፡፡ በአሁኑ ጊዜ ሙስና የሚባለውን ሰንኮፍ በልዩ ትኩረት መንቀል የሚያስችል አቅም እያለ፣ በውል በማይታወቅ ምክንያት ግን ሌብነት ከመቼውም ጊዜ በላይ ከፍቷል፡፡ የሙስና አከርካሪው የሚመታው እያባበሉ በማስታመም ሳይሆን ግንዱን በመቁረጥ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ የሕግ የበላይነትን በተግባር ማሳየት ይጠይቃል፡፡

በመንግሥታዊ ተቋማት ውስጥ መረን የተለቀቀው ሙስና የተገልጋዮችን መብት ከመጋፋት ነው የሚጀምረው፡፡ ሥልጣንን ላልተገባ ዓላማ የሚገለገሉበት የጥቅም ቁርኝት ያስተሳሰራቸው ግለሰቦች ከላይ እስከ ታች አሰፍስፈው የሚጠብቁት፣ በተሰጣቸው ኃላፊነት የሚፈለግባቸውን አገልግሎት ለመስጠት ሳይሆን ተመን ያወጡለትን ጉቦ በጥሬ ብርና በሞባይል ባንኪንግ ለመሰብሰብ ነው፡፡ በተለያዩ መሥሪያ ቤቶች ጉዳያቸውን ለማስፈጸም የሚሄዱ ተገልጋዮች በተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎች ብሶታቸውን ቢያሰሙም አዳማጭ አላገኙም፡፡ ይልቁንም ጉቦ እየጠየቁ መብቶቻቸውን የሚነፍጓቸው ግለሰቦች እንዳሻቸው እንዲሆኑ በመደረጋቸው፣ ጉዳይ ያለባቸው ብዙዎች የማይችሉትን ላለመጋፋት ሲሉ የተጠየቁትን መክፈል አቋራጩ መንገድ ነው ይላሉ፡፡ በጥቅም የተሳሰሩ ግለሰቦችም አለቃና ምንዝር ሆነው በሕዝብ ላብና ዕንባ ሲቀልዱ፣ የተቋማቱ ዓመታዊ ሪፖርት ግን በሐሰተኛ መረጃዎች ተቀባብቶ ‹‹ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ›› የሚሉትን ምሬት አዘል ምፀት ያስታውሳል፡፡

መንግሥት የተለያዩ ፕሮጀክቶቹ በጥራትና በፍጥነት እየተከናወኑ ለአገልግሎት ብቁ የመሆናቸውን ሚስጥር በኩራት ሲናገር፣ እንዲህ ዓይነቱን የሌብነት ገመና እያጋለጠ ብልሹ አሠራሮችን ከሥራቸው ለምን እንደማይነቅላቸው ግራ ያጋባል፡፡ መንግሥታዊ ተቋማትን እንደ ነቀዝ ከሚበሉ ሌቦች በተጨማሪ፣ በሕዝብ ላይ እያላገጡ ኪሳቸውን ሲሞሉ የሚውሉት ዝም የሚባሉበት ምክንያት ግልጽ አይደለም፡፡ በተለይ የሕዝብ አገልግሎት መስጫ ተቋማት በቀላል ምልከታ ብቻ ምን ሲሠራባቸው እንደሚውል መረጃ መሰብሰብ ይቻላል፡፡ ጠንከር ያለ ጥናት ቢከናወን ደግሞ ማን ምን እንደሚሠራ ያለ ብዙ ልፋት መረዳት አያቅትም፡፡ ‹‹ማስረጃ ይቅረብ እንጂ ሕጋዊ ዕርምጃ ይወሰዳል›› በሚል ማስተዛዘኛ ለሌቦች ሽፋን እንዲሰጥ ከማድረግ ይልቅ፣ በአሁኑ ጊዜ ብዙ የሚነገርላቸውን ቴክኖሎጂዎች በመጠቀም የሕዝቡን ምሬት የሚገልጹ ማስረጃዎችን በቀላሉ ማግኘት አይከብድም፡፡ መንግሥታዊ ተቋማት ውስጥ የተንሰራፋው ሌብነት አደብ የሚገዛው ልዩ ትኩረት ሲሰጠው ብቻ ነው!   

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ የሠራተኞች ማኅበር አመራር ጋር እየተወያዩ ነው]

ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም! በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት። አዎ።...

የሱዳን ጦርነትና የኢትዮጵያ ሥጋት

የሱዳን ጦርነት ከጀመረ አንድ ዓመት ከአራት ወራት አስቆጠረ፡፡ ጦርነቱ...

ግለሰብ ነጋዴዎችን በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ለማድረግ ያለመው ረቂቅ አዋጅ ተከለሰ

በምትኩ የንግድ ተቋማት በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ይሆናሉ...

አሳርና ተስፋ!

ከቱሉ ዲምቱ ወደ ቦሌ ጉዞ ልንጀምር ነው፡፡ ገና ከመንጋቱ...

የአገሪቱን የፖለቲካ ዕብደት ለማርገብ የኦሮሞ ፖለቲከኞች ሚና ምን ይሁን?

በያሲን ባህሩ   የኦሮሚያ ብልፅግና      በአገር ደረጃ የብሔር ፖለቲካ በሥራ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የፖለቲካ ፓርቲዎች ከእንቆቅልሽ ጨዋታ ውስጥ ውጡ!

በወርኃ ሚያዝያ ተካሂዶ የነበረው ውይይት ቀጣይ ነው የተባለው መድረክ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩንና የተፎካካሪ ፓርቲዎችን እንደገና ሰኞ ሐምሌ 15 ቀን 2016 ዓ.ም. አገናኝቶ ነበር፡፡ መንግሥትን የሚመራው...

ለልዩነት ዕውቅና የማይሰጥ ፖለቲካ ፋይዳ ቢስ ነው!

በፍርኃትና በሥጋት የተኮማተረ አገር ለመለወጥም ሆነ ለማደግ ዝግጁ መሆን አይችልም፡፡ አጉል ድፍረትና ምግባረ ብልሹነት በተንሰራፋበት ስለነፃነት መነጋገር አይቻልም፡፡ ፍርኃት እንደ ወረርሽኝ አገር ምድሩን አዳርሶ...

ለሕዝብ መሠረታዊ ፍላጎቶች ልዩ ትኩረት ይሰጥ!

በዚህ ዘመን ለሰው ልጅ የሚያስፈልጉ ነገሮች ብዛታቸው እየጨመረ ቢመጣም፣ በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ግን መሠረታዊ የሚባሉ ፍላጎቶች ከመቼውም ጊዜ በላይ ትኩረት ሊቸራቸው ይገባል፡፡ በአሁኗ ኢትዮጵያ...