Wednesday, July 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ለቀድሞ የኢትዮጵያ ጦር ሠራዊት የቆመው የብርጋዲየር ጄኔራል ለገሠ ፋውንዴሽን

የቀድሞ የኢትዮጵያ የጦር ሠራዊት አባላት ለአገራቸው የሕይወት መስዋዕትን ለመክፈል የወደዱ፣ ለአገራቸው ክብር ዘብ የቆሙና ውለታን የዋሉ ናቸው፡፡ እነኚህ የአገር ጌጦች በአገሪቱ በተከሰተው የሥርዓት ለውጥ ከሥራቸው ተፈናቅለው፣ የሚበሉትና የሚጠጡት አጥተው፣ ሕይወት ፊቷን አዙራባቸውና አገርም ውለታቸውን ዘንግታ፣ ጧሪና ደጋፊ አጥተው ጎዳና ስለመውደቃቸው የአደባባይ ሐቅ ነው፡፡ ‹‹የብርጋዲየር ጄኔራል ለገሠ ፋውንዴሽን›› እነዚህን የአገር ባለውለታ ከወደቁበት ለማንሳትና ድጋፍ ለማድረግ በጄኔራል ለገሠ ተፈራ እህት ወ/ሮ ሙሉብርሃን ተፈራ የተመሠረተ ነው፡፡ የአየር ኃይል ጄት አብራሪው ጄኔራል ለገሠ ተፈራ፣ በቀድሞው የኢትዮጵያ መንግሥት (1967-1983) ዘመን የኅብረተሰብአዊት ኢትዮጵያ ጀግና ሜዳይ የየካቲት 1966 1ኛ ደረጃ ኒሻን ተሸላሚ ነበሩ፡፡ ጄኔራል ለገሠ፣ ሶማሊያ ኢትዮጵያን በምሥራቅና በደቡባዊ ምሥራቅ ግንባሮች በወረረችበት ወቅት (1969-1970) በተዋጊ ጄት አብራሪነት ወደር የሌለው ጀግንነት የፈጸሙ ናቸው፡፡ በወቅቱ በነበረው ውጊያ አውሮፕላናቸው ተመትቶ በመውደቁና በመያዛቸው ለ11 ዓመታት በሶማሊያ በእስር አሳልፈዋል፡፡ የጄኔራል ለገሠ ፋውንዴሽን ስለተመሠረተበት ዓላማ፣ በሚያከናውናቸውና በቀጣይ ሊሠራቸው ስላቀዳቸው ተግባራት የድርጅቱን መሥራችና ሥራ አስኪያጅ ወ/ሮ ሙሉብርሃንን የማነ ብርሃኑ አነጋግሯቸዋል፡፡

ለቀድሞ የኢትዮጵያ ጦር ሠራዊት የቆመው የብርጋዲየር ጄኔራል ለገሠ ፋውንዴሽን | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር

ሪፖርተር፡- ድርጅታችሁ ትኩረት አድርጎ የሚንቀሳቀሰው ምን ላይ ነው?

ወ/ሮ ሙሉብርሃን፡- ድርጅታችን ትኩረት አድርጎ እየሠራ የሚገኘው የቀድሞ ወታደሮችን በመደገፍ ላይ ነው፡፡ በአንድ ወቅት ሕይወታቸውን ለአገራቸው ለመስጠት የወደዱና ይህንንም በተግባር ያሳዩ የቀድሞ ወታደሮች ከነቤተሰቦቻቸው ዛሬ ሜዳ የወደቁ፣ የተረሱና አስታዋሽ ያጡ ሆነዋል፡፡ መቄዶንያ የአረጋውያንና የአዕምሮ ሕሙማን ማዕከል ውስጥ ተጠልለው ከሚገኙ ግማሽ ያህሉ እኚሁ የቀድሞ ወታደሮች ናቸው፡፡ በመሆኑም የቀድሞ የኢትዮጵያ ወታደሮችንና ቤተሰቦቻቸውን አቅም በፈቀደ ሁሉ ከጎናቸው ቆሞ ለማገዝና ለመደገፍ ድርጅቱን መሥርተናል፡፡

ሪፖርተር፡- ድርጅታችሁ ግንቦት 28 ቀ ን 2016 ዓ.ም. በመቄዶንያ ለሚገኙ የቀድሞ ጦር ሠራዊት አባላት የምሳ ግብዣ አድርጓል፡፡ ይህን ለማድረግ ምን አነሳሳዎት?

ወ/ሮ ሙሉብርሃን፡- በመቄዶንያ ግቢ ከሚገኙ፣ ግማሽ ያህሉ የቀድሞ የጦር ሠራዊት አባላት በመሆናቸው አዝኛለሁ፡፡ ወንድሜ የእነርሱ አንድ አካል የነበረ እንደመሆኑና በሌላ በኩል ደግሞ አገሩን እንደሚወድ ዜጋ ሁኔታው የሚያስቆጭ ነው፡፡ በመሆኑም ከቀድሞ አጋሮቻቸው ጋር ምሳ ማብላት ለሕይወታቸው ትልቅ ቴራፒ ነው ብለን በማመን ፕሮግራሙን አዘጋጅተናል፡፡ ፕሮግራሙን በየዓመቱ በማድረግ፣ በቴሌቪዥን የሚያዩቸውንና የትግል አጋሮቻቸው የነበሩ ጄኔራሎችን እየጋበዝን የቀድሞ ጊዜያቸውን፣ ውሏቸውን፣ ሕይወታቸውንና ትዝታቸውን እንዲጨዋወቱ እናደርጋለን፡፡ ይህ ዛሬም አጠገባቸው ሰው እንዳለና እንዳልተዘነጉ እንዲያስቡ ያደርጋቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- የብርጋዲየር ጄኔራል ለገሠ ተፈራ ፋውንዴሽን መቼ ተሠረተ? እስካሁንስ ያከናወናቸው ተግባራት ምንድናቸው?

ወ/ሮ ሙሉብርሃን፡- ድርጅቱ የተመሠረተው በቅርብ ነው፡፡ ገና በጅምር ያለ ተቋም ቢሆንም ትልቅ ራዕይን ሰንቆ እየተንቀሳቀሰ ነው፡፡ በየቦታው የተጣሉ፣ የወደቁ፣ ያልተዘመረላቸውና ለአገር ታላቅ ጀብዱ የፈጸሙ ወታደሮች አሉ፡፡ ለገሠ ተፈራ እና ጥቂቶች ብቻ አይደሉም ኢትዮጵያን ከመወረር ታድገው ለዚህ ያበቋት፡፡ በርካታ ጀግኖች አሉ፡፡ ስለሆነም እነርሱን እየፈለግን አይዟችሁ በማለት እያበረታታንና ታሪካቸውን እየዘከርን እንገኛለን፡፡ ትውልዱም ከጀግነታቸውና ከሥራቸው እንዲማር ፕሮግራም ቀርፀን እንሠራለን፡፡ በተጨማሪም በሕይወት የሌሉ የሠራዊት አባላት ቤተሰቦችንም የመደገፍ ዕቅድ አለን፡፡

ሪፖርተር፡- ብርጋዲየር ጄኔራል ለገሠ ተፈራን ትውልድ እንዲዘክራቸውና በሥራዎቻቸውም እንዲታወሱ በማድረግ ረገድ ድርጅታችሁ ምን እየሰራ ነው?

ወ/ሮ ሙሉብርሃን፡- ድርጅቱ በስሙ መመሥረቱ በራሱ፣ እሱን ለመዘከር የምናደርገው ጥረት አንዱ አካል ነው፡፡ ጄኔራል ለገሠ ሕይወቱ ካለፈ አሁን ስምንት ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ በአዲስ አበባና በክፍለ አገር ለተለያዩ ግለሰቦች ሐውልት ቆሞላቸው አይቻለሁ፡፡ ለገሠ ተፈራ በውትድርናው ዓለም ለፈጸመው ጀብዱ ሐውልት ሊታነጽለት የሚገባው ሰው ነበር፡፡ ለዚህ ታላቅ የአገር ባለውለታ በስሙ አንድ ነገር ባለመሰየሙ ይህን ድርጅት ለስሙ መጠሪያ ልንቋቋም ችለናል፡፡ በተጨማሪም ከልጅነቱ ጀምሮ የተጓዘባቸውን የሕይወት ምዕራፎች የሚዳስስ ዘጋቢ ፊልም በማዘጋጀት ላይ ነን፡፡  ግለታሪኩን የሚያስቃኝ መጽሐፍም እየተጻፈ ነው፡፡ ሁለቱም በቅርቡ ይመረቃሉ ብለን እንጠብቃለን፡፡ መታሰቢያ እንዲቆምለት ከሚመለከታቸው የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ጋር እያደረግነው ያለው ጥረት በጎ ምላሽ እያገኘ ነው፡፡ በቅርቡ ይፋ ይሆናል ብለን እንጠብቃለን፡፡

ሪፖርተር፡- ስለጄኔራሉ የአገር ፍቅር የሚያስታውሱትን ቢነግሩኝ?

ወ/ሮ ሙሉብርሃን፡- ጄኔራል ለገሠ የቤተሰባችን የበኩር ልጅ ነው፡፡ እኔ አምስተኛ ታናሹ ነኝ፡፡ ሶማሊያ እስር ቤት ለ11 ዓመት ታስሮ በነበረ ጊዜ ፈልጌ ያገኘሁት እኔ ነበርኩ፡፡ በሕይወት በነበረበት ወቅት ‹‹የእኔን ሕይወት›› የምታስቀጥይው አንቺ ነሽ ይለኝ ነበር፡፡ ይህ ንግግሩ በጊዜው ምን ማለት እንደሆነ አልገባኝም ነበር፡፡ አሁን ነው እየገባኝ የመጣው፡፡ ድርጅታችን የለገሰን ሰባተኛ ሙት ዓመት ዘክሯል፣ ሐውልቱን ዘመናዊ በሆነ መለኩ በግላስ እንዲሠራ አድርጓል፡፡ አልባሳቱንና ሜዳሊያዎቹን ትውልድ እንዲማርበት ለአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አበርክቷል፡፡ ለገሠ አገሩንና ሕዝቡን እጅግ የሚወድ ሰው ነው፡፡ ከኢትዮጵያ በፊት የራሱን ሞት የሚመርጥ ነበር፡፡ ብቻዬን ሆኜ እሱን ባስታወስኩ ቁጥር ሳይኖር የሞተው ወንድሜ የሚል ሐሳብ ይመጣብኛል፡፡ ሕይወትን ከውትድርና ውጪ አያውቃትም ነበር፡፡ ሙሉ ዕድሜውንና ዘመኑን ለአገሩ የሰጠ ነው፡፡ ከእስር ቤት በተፈታ ጊዜ የምትፈልገው አገር መርጠህ መኖር ትችላለህ ሲባል ‹አገሬ ወይም ሞቴ› ብሎ ወደ ኢትዮጵያ የተመለሰ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በሶማሊያ እስር ቤት ጄኔራሉን ፈልጌ ያገኘሁት እኔ ነኝ ብለዋል፡፡ እንዴት አገኟቸው?

ወ/ሮ ሙሉብርሃን፡- ጊዜው ትንሽ ራቅ ያለ ነው፡፡ ለገሠ በኢትዮ ሶማሊ ጦርነት በአየር ኃይሉ ውስጥ ተሳታፊ እንደነበር አውቃለሁ፡፡ ወዲያው ግን ደብዛው ጠፋብኝ፡፡ ያኔ እኔ ሰሜን አሜሪካ ነበርኩ፡፡ ከአባታችን ጋር በተለያየ ጊዜ ስናወራ ‹ያልቀበርኩትን ልጅ ሞተ ብትሉኝም አላምንም› ይል ነበር፡፡ ድምፁ ለረዥም ጊዜ በመጥፋቱ እኔም ሆንኩኝ መላ ቤተሰብ ዘወትር የምንብሰለሰልበት ጉዳይ ሆነ፡፡ በዚህ ሁኔታ እያለሁ ዘሃራ የምትባል ሶማሊያዊት ጓደኛ ነበረችኝና ወደ አገሯ ስትሄድ፣ ወንድሜ ይኑር፣ ይሙት የሚታወቅ ነገር የለም፡፡ ፈልገሽ የምታገኚው ከሆነ ይህንን ደብዳቤ ስጪው ብዬ ከራሴ ሁለት ፎቶ ጋር ጨምሬ ሰጠኋት፡፡ ያቺ ሴት ከሁለት ወር በኋላ ወደ አሜሪካ ስትመለስ ከእርሱ የተጻፈ ደብዳቤ ይዛ መጣች፡፡ በወቅቱ ከታሰረበት የእስር ቤት ክፍል መውጣት አይፈቀድለትም ነበር፡፡ ሶማሊያዊቷ ግን ከክፍሉ ጠዋትና ማታ እየወጣ ጸሐይ እንዲሞቅ፣ የተሻለ ምግብ እንዲያገኝና የሚተኛበት ፍራሽ እንዲገዛለት አደረገች፡፡ ቤተሰቦቿ በሚሊተሪው ውስጥ የሚያገለግሉ በመሆናቸው ‹የጓደኛዬ ወንድም ነው፣ ተንከባከቡት› በማለቷ የፈለገው ሁሉ እንዲቀርብለት ሆነ፡፡ ከእስር ከተፈታ በኋላ ተገናኝተን ስናወራ ‹የዘሃራ እኔ ወደምገኝበት እስር ቤት መምጣት ለእኔ የብርሃን ያህል ነው፡፡ ትዕግሥቴን በጨረስኩበትና ራሴን ላጥፋ በምልበት ወቅት የደረሰችልኝ ናት› ብሎኛል፡፡ ለለገሠ ከእኔ በላይ ነፍስ የዘራችበት ዘሃራ ነች፡፡ ይህች ሴት ለእኔ ብቻ ሳይሆን ለአገርም ባለውለታ እንደሆነች ይሰማኛል፡፡

ሪፖርተር፡- የጄኔራል ለገሠ የቀብር ሥነ ሥርዓትና የመቃብር ቦታን በተመለከተ የተፈጠረ ነገር ነበር ሲባል ሰምቻለሁ፡፡ በወቅቱ የሆነው ምን ነበር?

ወ/ሮ ሙሉብርሃን፡- ‹አገሬ ኢትዮጵያ ሞኝ ነሽ ተላላ፣ የሞተልሽ ቀርቶ የገደለሽ በላ› እንደተባለው ነው፡፡ አስክሬኑን ከአሜሪካ ፍታት አስደርገን ከእህትና ወንድሜ ጋር ይዘን መጣን፡፡ እዚህም ቤተሰቦቻችን ቤት አርፎና ፍታት ተደርጎለት ወደ ቀብር ቦታ (ሥላሴ ካቴድራል) አስክሬኑ እየተሸኘ ሳለ የጀርመኗ መራሄተ መንግሥት አንጄላ መርኬል ትመጣለችና ወደ ሥላሴ መሄድ አትችሉም ተባለን፡፡ ሲጀመርም ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን እንዳይቀበር ብዙ ክልከላ ሲደረግብን ነበር፡፡ ከፈለጋችሁ ‹ፉካ› ውስጥ ቅበሩት ነበር ያሉን፡፡ የካ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን የእናትና አባቴ የተሠራ ፉካ ስለነበር ተመልሰን እዚያ ለመቅበር በምንሄድበት ወቅት ወንድሜ ተሯሩጦና እዚያም  እዚያም ብሎ በስንት ትግል ሥላሴ እንዲቀበር ተደረገ፡፡ ለመቃብር ቦታ ሃያ አምስት ሺሕ ብር ከፍለን የአገር ክብር የሆነውን ጀግና በአገሩ ላይ አስክሬኑ እንዲንገላታና እንዲቀበር ሆነ፡፡ ወንድሜ ኖሮም ሞቶም የከፋው ሰው እንደሆነ ነው የማምነው፡፡ በቅርብ የሚወጣውና በሕይወቱ ዙሪያ የተዘጋጀው መጽሐፍ ‹‹ሳይኖር የሞተው ወንድሜ›› የሚል ርዕስ የተሰጠው አንዱ በዚህ ምክንያት ነው፡፡ ለገሠ፣ መኖር አልቻለም፣ መቀበር አልቻለም፣ ዕድሜውንም በእስር ቤት ነው የኖረው፡፡ መቼ ኖረ? ለአገሩ ብቻ ቁም ነገር ሠርቶ ያለፈ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በጄኔራሉ ግለ ታሪክ ዙሪያ የተዘጋጀው መጽሐፍና ዘጋቢ ፊልም ሕዝብ ጋር መቼ ይደርሳሉ?

ወ/ሮ ሙሉብርሃን፡- መጽሐፉም፣ ዘጋቢ ፊልሙም በማለቅ ላይ ናቸው፡፡ ሁለቱንም በእኩል ጊዜ ለማስመረቅ አስበናል፡፡ በተጨማሪም በድሬዳዋ ከተማ በስሙ እንዲሰየሙ የጠየቅናቸው ነገሮች አሉ፡፡ በድሬዳዋ የሚገኘው የአየር ኃይሉ የሚሊተሪ ሳይንስ አካዴሚ በስሙ እንዲሰየምና ኤርፖርቱም በስሙ እንዲጠራ ጠይቀናል፡፡ በስሙ የሚጠራ ትምህርት ቤት ገንብተን ለማስረከብም ሐሳብ አቅርበናል፡፡ ለገሠ የጀንግነት ገድል የፈጸመው ድሬዳዋ ላይ በመሆኑ ይህንን ለማስፈጸም እንቅስቃሴ ጀምረናል፡፡ በዚህ ዙሪያ ከከተማዋ የመንግሥት አካላት በጎ ምላሽ አግኝተናል፡፡ ዘንድሮ ያቀድናቸው እንደሚሳኩና ለውጤት እንደሚበቁ እምነት አለኝ፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

አደራውን ለመጠበቅ ዕድል ያላገኘው ቅርስ ባለአደራ

የኢትዮጵያ ቅርስ ባለአደራ ማኅበር ከተመሠረተ ሦስት አሥርት አስቆጥሯል፡፡ ማኅበሩ በእንጦጦ ተራራማ ቦታዎች በአደራ በመንግሥት በተረከበው 1,300 ሔክታር መሬት ላይ የተለያዩ አገር በቀል ዛፎችን በመትከል...

ብዝኃ ትምህርቱን ‹ስቴም› ለማስረፅ

ስሜነው ቀስቅስ (ዶ/ር) የስቴም (Stem) ፓውር ግብረ ሰናይ ድርጅት የኢትዮጵያ ዳይሬክተርና የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የቴክኖሎጂ አማካሪ ናቸው፡፡ በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የማስተርስና የፒኤችዲ...

‹‹እውነታውን ያማከለ የሥነ ተዋልዶ ጤና ግንዛቤን ማጠናከር ያስፈልጋል›› ደመቀ ደስታ (ዶ/ር)፣ በአይፓስ የኢትዮጵያ ተወካይ

በሥነ ተዋልዶ ጤና ጉዳዮች ላይ በመሥራት በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚንቀሳቀሰው አይፓስ፣ የኢትዮጵያን ሕግ መሠረት አድርጎ በሴቶች የሥነ ተዋልዶ ጤና ከጤና ሚኒስቴርና ከክልል ጤና ቢሮዎች...