Wednesday, July 24, 2024

[የክቡር ሚኒስትሩ ባለቤት ሐዘን ለመድረስ ጎረቤት ተገኝተው ለቀስተኛው በሙሉ የሚያወራው ነገር አልገባ ብሏቸው ወደ ቤታቸው ከተመለሱ በኋላ ባለቤታቸውን ስለጉዳዩ እየጠየቁ ነው] 

 • ጎረቤታችን ሐዘን ለመድረስ ብሄድ ለቀስተኛው በሙሉ በሹክሹክታ ያወራል። ግን የሚያወሩት ነገር ሊገባኝ አልቻለም።
 • ምንድነው የሚያወሩት?
 • እኔ ምን አውቄ?
 • እንዴት? የሚያወሩትን ምንም አልተሰማሽም?
 • እኔ እንድሰማ የፈለጉ አይመስልም ግን …
 • ግን ምን?
 • አዋጁ… አዋጁ ሲሉ ይሰማኛል።
 • የምን አዋጅ?
 • እኔ ምን አውቄ?
 • ሌላ ምንም አልሰማሽም?
 • ሌላ ምን?
 • አዋጁ… አዋጁ ከሚለው ሌላ?
 • አልፎ አልፎ…ሊወርሱ ነው …እነሱም እንደ ደርግ ሊወርሱ ሲሉ ይሰማኝ ነበር።
 • እ…ገባኝ
 • ምንድነው?
 • ስለምን እንደሚያወሩ ገባኝ።
 • ስለ ምንድነው የሚያወሩት?
 • ሰሞኑን ለፓርላማ የቀረበ አዋጅ አለ፣ ስለ እሱ ነው የሚያወሩት።
 • የምን አዋጅ ነው?
 • የንብረት ማስመለስ አዋጅ ነው።
 • የምን ንብረት?
 • መንግሥት ምንጩ ያልታወቀ ንብረትንና በወንጀል ጥፋተኝነት ላይ ያልተመሠረተ ንብረትን እንዲወርስ የሚፈቅድ አዋጅ ነው።
 • እንዴት አድርጎ ይወርሳል …አልገባኝም?
 • ምኑ ነው ያልገባሽ?
 • መንግሥት ጥፋተኝነትን ሳያረጋግጥ እንዴት መውረስ ይችላል?
 • ምክንያታዊ ጥርጣሬ ሲኖረው
 • ምን ማለት ነው?
 • ምኑ?
 • ምክንያታዊ ጥርጣሬ ማለት?
 • ያው ጥርጣሬ ነው፣ ነገር ግን?
 • ግን ምን?
 • ከጥርጣሬ ትንሽ ከፍ ይላል።
 • አልገባኝም?
 • ማንኛውም ሰው ይጠረጠራል አይደል?
 • አዎ።
 • ይኼኛው ግን ማንኛውም ሰው ከሚጠረጠረው ጥርጣሬ ትንሽ ከፍ ይላል።
 • እንዴት?
 • ሰው አይደለማ የሚጠረጥረው።
 • እና ማነው?
 • መንግሥት።
 • ታዲያ ለምን ምክንያታዊ ጥርጣሬ ተባለ?
 • ሌላ ምን ሊባል ይችላል?
 • መንግሥታዊ ጥርጣሬ ማለት ይቻላል።
 • ያው እኮ ናቸው፡፡
 • ያው ማለት?
 • የቃላት ልዩነት እንጂ ተመሳሳይ ናቸው።
 • በምንድነው የሚመሳሰሉት?
 • በትርጉም።
 • እንዴት?
 • መንግሥታዊ ጥርጣሬ ነው ከተባለ
 • እ…
 • ምክንያታዊ ነው ማለት ነው።
 • ማን ነው ምክንያታዊ?
 • መንግሥት።
 • እሱን እንኳ ተወው?
 • እንዴት?
 • ሳናጣራ አናስርም…. ብላችሁ አልነበረም?
 • አዎ። መጀመሪያ ላይ እንደዚያ ብለን ነበር።
 • ቢሆንም ሳታጣሩ አስራችኋል፣ አሁን ደግሞ…
 • እ…አሁን ደግሞ ምን?
 • ጠርጥራችሁ ልትወርሱ ነው።

[ሚኒስትሩ ሶፋ ላይ እንቅልፍ ጥሏቸው እየተወራጩና አልፎ አልፎም በእንቅልፍ ልባቸው ‹‹ገና ይቀረኛል›› እያሉ ሲያወሩ የሰሙት ባለቤታቸው ቀስቅሰው አነቋቸው] 

 • እስኪ በስመ አብ በል? ምንድነው እንዲህ ያስጨነቀህ?
 • እ…. አይ ጭንቀት አይደለም።
 • ታዲያ ምንድነው? ፊትህ ሁሉ ተለዋውጦ ስትጮኽና ስታወራ ነበር እኮ?
 • ብዙ አወራሁ እንዴ?
 • ስትለፈልፍ ነበር እንጂ!
 • የማወራው ይሰማ ነበር?
 • ይሰማ ነበር? ስትበጠብጥ ነበር እንጂ።
 • ምን እያልኩ ነበር?
 • ምን እንደሆነ ምን አውቄ ብቻ ‹‹ገና ይቀረኛል›› እያልክ ስትወራጭ ነበር።
 • ገና ይቀረኛል ብቻ ነው ያልኩት?
 • ሁለት ዓመት አለኝ እያልክ ነበር ደጋግመህ የምታወራው። ደግሞ ፀጥ ትልና ገና ይቀረኛል ስትል ነበር።
 • ይህን ብቻ ነው የሰማሽው?
 • በዚያኛው ጫፍ የሚያዋራህንማ እንዴት እሰማለሁ?
 • አትቀልጂ ባክሽ።
 • ግን ማነው?
 • ምኑ?
 • እንዲህ ያስጨነቀህ? ማለቴ ጉዳዩ ምንድነው?
 • ቅዠት ነዋ። ሌላ ምን ይሆናል።
 • ይህንን ነገር በእውንህም ስትለው ሰምቼ አውቃለሁ።
 • መቼ? ምን ብዬ?
 • ሰሞኑን በቴሌቪዥን በተላለፉ ስብሰባዎች ላይም ገና ሁለት ዓመት ይቀረናል እያልክ በተደጋጋሚ ስታወራ ነበር። ምናልባት ይገናኝ ይሆን እያልኩ ሳስብ ነበር።
 • ምን ያገናኛቸዋል?
 • ምኖቹ?
 • ህልምና ቴሌቪዥንን የሚያገናኛቸው ነገር አለ?
 • እዚያም እዚህም ያልከው ነገር ቢመሳሰልብኝ ነዋ። ግን ከማን ጋር ነው?
 • ምኑ?
 • አሁን ተኝተህ ስታወራ የነበረው?
 • አንድ የውጭ አገር ባለሥልጣን ይመስለኛል። አዎ እንደዚያ ነው።
 • ግን እኮ ስታወራ የነበረው በአማርኛ ነው?
 • እሱም ያዋራኝ የነበረው በአማርኛ ይመስለኛል።
 • ማን? የውጭ አገር ባለሥልጣኑ?
 • አዎ።
 • አይ… ምናልባት አስተርጓሚው ይሆናል።
 • አንቺ ደግሞ…
 • ምነው?
 • ነገሩ ቅዠት መሆኑን ዘነጋሽው እንዴ? ይልቅ የምጠጣው ውኃ ስጪኝ?
 • እሺ… እንዲያው ግን እንዲህ ከምትጨነቅ ብትተወውስ?
 • ምኑን?
 • ይቀረኛል ያልከውን?
 • በፍጹም። ገና ሁለት ዓመት አለኝ!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ለቀድሞ የሕግ ታራሚዎች የቆመው ሰው ለሰው

የደርግ መንግሥት ደጋፊዎችና የሥልጣን ተጋሪዎች፣ ከከፍተኛ የቀድሞ መንግሥት ባለሥልጣናት...

ባይደን ከምርጫ ራሳቸውን ካገለሉ በኋላ የዴሞክራቱን መድረክ የተቆጣጠሩት ካማላ ሃሪስ

የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ኮቪድ መያዛቸው በተነገረ ሳምንት ነበር...

‹‹በዶናልድ ትራምፕ ላይ የተቃጣው የግድያ ሙከራ የተቋማችን ውድቀት ማሳያ ነው››

የአሜሪካ ደኅንነት አገልግሎት (Secret Service) ዳይሬክተር ኪምበርሊ ቺትል ለኮንግረስ...

አደራውን ለመጠበቅ ዕድል ያላገኘው ቅርስ ባለአደራ

የኢትዮጵያ ቅርስ ባለአደራ ማኅበር ከተመሠረተ ሦስት አሥርት አስቆጥሯል፡፡ ማኅበሩ...

የአሸንዳ ጨዋታዎች ‹‹ዕቡነይ››

በነሐሴ በጉጉት የሚጠበቀውን የአሸንዳን በዓል ምክንያት በማድረግ፣ ሙዚቃዊ ከትግራይ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

[ክቡር ሚኒስትሩ የቅርብ ወዳጃቸው ከሆነች አንድ ባለሀብት የተደወለላቸውን ስልክ አንስተው በኮሪደር ልማቱ ላይ የምታቀርበውን ቅሬታ እየሰሙ ነው]

ክቡር ሚኒስትር እኔ የኮሪደር ልማቱ ላይ ተቃውሞም ሆነ ጥላቻ እንደሌለኝ የሚያውቁ ይመስለኛል? በዚህ እንኳን አትታሚም።  የእውነቴን ነው ክቡር ሚኒስትር። አውቃለሁ ስልሽ? ለኮሪደር ልማቱ አዋጡ ሲባልም ያለማመንታት አምስት ሚሊዮን...

[ክቡር ሚኒስትሩ በችግኝ ተከላ ፕሮግራም ላይ ሳይገኝ ከቀረው አንድ የተቋማቸው ባልደረባ የሆነ የተቃዋሚ ፓርቲ አባልን አስጠርተው እያናገሩ ነው]

ለምንድነው በዚህ አገራዊ ፋይዳ ባለው ፕሮግራም ላይ ያልተገኘኸው? ክቡር ሚኒስትር ህሊናዬ አልፈቀደልኝም። መቃወምና መተቸት ብቻ ውጤት የሚያመጣ መስልዎህ ከሆነ ተሳስተሃል። አልተሳሳትኩም ክቡር ሚኒስትር? ቆይ የመጀመሪያ ዓመት የችግኝ ተከላ...

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚያከብሯቸው አንድ የቀድሞ ጉምቱ ፖለቲከኛ ስልክ ተደውሎላቸው እያወሩ ነው]

አንዳንድ ነገሮች ቢያሳስቡኝ ነው ቀጠሮ ሳልይዝ ላነጋግርህ የፈለኩት ክቡር ሚኒስትር፡፡ እርስዎማ ቀጠሮ መያዝ አያስፈልግዎትም፣ ምን ገጠመዎት? እኔማ ምን ይገጥመኛል አንተኑ ልጠይቅህ እንጂ? ምን? እውነት ለመናገር የማየው ነገር አሳስቦኛል፡፡ ይንገሩኝ...