Wednesday, July 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊመሠረተ ልማት ያልተሟላላቸው የኮንዶሚኒየም ቤት ዕድለኞች የጣሪያና ግድግዳ ግብር ክፈሉ መባላቸውን ተቃወሙ

መሠረተ ልማት ያልተሟላላቸው የኮንዶሚኒየም ቤት ዕድለኞች የጣሪያና ግድግዳ ግብር ክፈሉ መባላቸውን ተቃወሙ

ቀን:

በ2011 ዓ.ም. የ40/60 የጋራ መኖሪያ ቤት ዕድለኛ የሆኑ ሰዎች የመሠረተ ልማት ሳይሟላላቸው የጣሪያና የግድግዳ ግብር ክፈሉ በመባላቸው ትክክል አለመሆኑን በመግለጽ ቅሬታቸውን አሰሙ፡፡

በለሚ ኩራ በሻሌ ሳይት የ40/60 የጋራ መኖሪያ ኮንዶሚኒየም ቤት የደረሳቸው ዕድለኞች፣ ምንም ዓይነት የመሠረተ ልማት ሳይሟላላቸው የጣሪያና የግድግዳ ግብር እንድትከፍሉ የሚል ትዕዛዝ ከገቢዎች ቢሮ በጽሑፍ እንደደረሳቸው ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ ዕድለኛ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

ከ2015 ዓ.ም. ጀምሮ የጣሪያና የግድግዳ ግብር ክፈሉ እንደተባሉና በወቅቱም ለለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ቅሬታቸውን ማስገባታቸውን ገልጸው፣ በአሁኑ ወቅት በሁሉም ብሎኮች እስከ ሰኔ 30 ቀን 2016 ዓ.ም. ድረስ ክፍያ እንድትፈጽሙ የሚል ማስታወቂያ ክፍለ ከተማው መለጠፉን አስረድተዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ መሠረተ ልማት ያልተሟላላቸው ባለዕድለኞች የጣሪያና የግድግዳ ግብር እንደማይከፍሉ በተለያዩ መድረኮች መናገራቸውን፣ ነገር ግን የለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ‹‹ከላይ የተላለፈ ትዕዛዝ ነው›› በሚል ምክንያት ክፍያውን ሁሉም ባለይዞታዎች እንዲከፍሉ እያደረገ መሆኑን አክለው ገልጸዋል፡፡

በሻሌ ሳይት የሚገኙ የጋረ መኖሪያ ቤቶች ውኃ፣ ሊፍት፣ መንገድና  ሌሎች መሠረተ ልማቶች ያልተሟላላቸው ናቸው የሚሉት ባለይዞታው፣ የጣሪያና የግድግዳ ካልከፈላችሁ ኤሌክትሪክ ይቆረጥባችኋል እንደተባሉና ከባድ ችግር ውስጥ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

የጋራ መኖሪያ ቤቶቹ ሙሉ ለሙሉ ሳያልቁ ከቤት ኪራይ ሽሽት የተወሰኑ ሰዎች መግባታቸውን ገልጸው፣ በራሳቸው ወጪ አንዳንድ የግንባታ ሥራዎች ማከናወናቸውን ተናግረዋል፡፡

በሻሌ ሳይት የሚገኙ አብዛኞቹ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ዕድለኞች የባንክ ዕዳ እንዳለባቸው ጠቅሰው፣ መንግሥት መሠረታዊ ነገሮች ያልተሟሉላቸውን የጋራ መኖሪያ ቤት ዕድለኞች የጣሪያና የግድግዳ ግብር የዕፎይታ ጊዜ ማራዘም ይኖርበታል ብለዋል፡፡

የጣሪያና የግድግዳ ክፍያ ሲፈጸም የኮንዶሚኒየም ቤቶች እንዳሉበት የቦታ ሁኔታ ደረጃ አንድ፣ ደረጃ ሁለትና ደረጃ ሦስት በሚል አሠራር ተፈጻሚ እንደሚሆን፣ ነገር ግን አሁን በበሻሌ ሳይት የተሰጠው የደረጃ ሁኔታ ከብሎክ ብሎክም የሚለያይ መሆኑን አክለው ገልጸዋል፡፡

በተመሳሳይ ሌላው የጋራ መኖሪያ ቤት ዕድለኛ እንደገለጹት፣ የመሠረተ ልማት ሳይሟላ የጣሪያና የግድግዳ ክፈሉ መባሉ አግባብ አይደለም በማለት ቅሬታቸውን ተናግረዋል፡፡

በተለይ በርካታ ሰዎች አንዳንድ ጉዳዮችን ለማስፈጸም ለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ሲሄዱ፣ የጣሪያና የግድግዳ ግብር አልከፈላችሁም ወይ የሚል ጥያቄ እንደሚቀርብላቸው ገልጸዋል፡፡

ጉዳያቸውን በተመለከተ ለቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን ለለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ደብዳቤ እንዲጽፍላቸው ጥያቄ አቅርበው፣ በጥያቄያቸው መሠረትም ኮርፖሬሽኑ ደብዳቤ ለለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ቢጽፍም ተቀባይነት እንዳላገኘ አስረድተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት የተለያዩ አገልግሎቶችን ለማግኘት ወደ ክፍለ ከተማው ሲሄዱ ከ2015 ዓ.ም. ጀምሮ የጣሪያና ግድግዳ የከፈላችሁበትን ካላሳያችሁን አናስተናግድም የሚል ምላሽ እንደሚሰጣቸው አስረድተዋል፡፡

በተደጋጋሚ የለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ገቢዎች ጽሕፈት ቤት ድረስ በመሄድ ሁኔታውን ለማስረዳት ሙከራ ማድረጋቸውን፣ ጽሕፈት ቤቱም ለእኛ የደረሰን ነገር የለም የሚል ምላሽ እንደሰጣቸው አክለው ገልጸዋል፡፡

በበሻሌ ሳይት ውስጥ የሚገኙ አንዳንድ ባለዕድለኞች በፍራቻ ብቻ የጣሪያና የግድግዳ ግብር መክፈላቸውን ተናግረው፣ ጉዳዩም ጥርት ያለ መፍትሔ እንዲኖረው ለሚመለከታቸው የተለያዩ የመንግሥት ተቋማት ለማድረስ በሒደት ላይ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡

ከዚህ በፊት የአዲስ አበባ ከተማ አስተደደር ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች ጉዳዩን በተመለከተ እንደገለጹት፣ የመሠረተ ልማት ያልተሟላላቸው የጋራ መኖሪያ ቤቶች የጣሪያና የግድግዳ ግብር እንዳይከፍሉ ተደርጓል፡፡

የጋራ መኖሪያ ቤቶች የመሠረተ ልማት ሳይሟላ ወደ ቤታቸው ያልገቡ ባለዕድለኞች ግብር ክፈሉ ማለት አግባብነት እንደሌለው የጠቀሱት ከንቲባዋ፣ ይህንንም ያደረጉ የመንግሥት ሠራተኞች እንዲቀጡ ተደርጓል ብለው ነበር፡፡   

መሠረታዊ አገልግሎቶች ያልተሟላላቸው የጋራ መኖሪያ ቤቶች የጣሪያና የግድግዳ ክፍያን በተመለከተ፣ የከተማውን የገቢዎች ቢሮ ለማነጋገር በተደጋጋሚ ጥረት ቢደረግም አልተሳካም፡፡    

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ የሠራተኞች ማኅበር አመራር ጋር እየተወያዩ ነው]

ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም! በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት። አዎ።...

የሱዳን ጦርነትና የኢትዮጵያ ሥጋት

የሱዳን ጦርነት ከጀመረ አንድ ዓመት ከአራት ወራት አስቆጠረ፡፡ ጦርነቱ...

ግለሰብ ነጋዴዎችን በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ለማድረግ ያለመው ረቂቅ አዋጅ ተከለሰ

በምትኩ የንግድ ተቋማት በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ይሆናሉ...

አሳርና ተስፋ!

ከቱሉ ዲምቱ ወደ ቦሌ ጉዞ ልንጀምር ነው፡፡ ገና ከመንጋቱ...