Wednesday, July 24, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በአየር ንብረት ለውጥ የሚከሰቱ ተባዮች በሆርቲካልቸር ምርቶች ላይ ችግር እየተፈጠሩ መሆኑ ተገለጸ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በዓለም አቀፍ ደረጃ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ዕፅዋትን የሚያጠቁ ተባዮች በሆርቲካልቸር ምርቶች ገበያ ላይ ጫና መፍጠራቸው ተገለጸ፡፡ የሆርቲካልቸር ምርቶችን የሚገዙ የአውሮፓ ኅብረት አገሮች የቁጥጥር ሥርዓታቸውን በማጠናከራቸው በላኪዎች ላይ ችግር እየተፈጠረ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡

በሆርቲካልቸር ምርት ጥራትና ደኅንነት ላይ ያተኮረ ብሔራዊ የምርት ጥራት ምዘና ጉባዔ ሰኔ 13 ቀን 2016 ዓ.ም. ሲካሄድ የተገኙት የኢትዮጵያ ግብርና ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ድሪባ ኩማ (አምባሳደር) ገልጸዋል፡፡

የግብርና ባለሥልጣን ወደ ውጭ የሚላኩ የግብርና ምርቶች የተቀባይ አገሮችን መሥፈርት ያሟሉ መሆናቸውን የሚያረጋግጥ የአውሮፓ አገሮች በአየር ንብረት ለውጡ ምክንያት በተፈጠሩ ተባዮችና በሌሎችም ምክንያቶች የቁጥጥር ሥርዓታቸውን በማጠናከራቸው፣ ኢትዮጵያም ከሚያወጡት የቁጥጥር ሥርዓት ጋር የሚመጣጠን አመራር መገንባት እንደሚገባት አስረድተዋል፡፡ ይህን ማድረግ ካልተቻለም አሁን ባለው ሁኔታ የአውሮፓ አገሮች የኢትዮጵያን ላኪዎች ከገበያ ውጪ ሊያደርጉ ይችላሉ ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ወደ ውጭ ከምትልካቸው ምርቶች 80 በመቶ የሚሆነው የግብርና ሲሆን፣ በተለይ አበባ፣ ቡና፣ እንዲሁም እንደ ሰሊጥ ያሉ የቅባት እህሎችና ጥራጥሬዎች ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የሚያስገኙ በመሆናቸው ባለሥልጣኑ ባለው አቅም ቁጥጥር እያደረገ መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ አብራርተዋል፡፡

የአውሮፓ ኅብረት ከዚህ ቀደም አውጥቶት በነበረው ሪፖርት እ.ኤ.አ. ከ2018 ወዲህ ‹‹የእሳት ራት›› የተሰኘው ተባይ በአበባ ምርት ላይ በከፍተኛ መጠን በመገኘቱ፣ አገሮቹ የቁጥጥር ሥርዓታቸውን ማጠናከራቸውን ማስታወቁ ይታወሳል፡፡ ወደ አውሮፓ አገሮች ከሚላከው የአበባ ምርት ምርመራ ይደረግ የነበረው አምስት በመቶ በሚሆነው ላይ ብቻ ስለነበረ፣ በተባዩ መከሰት ምክንያት ምርመራውን ወደ 25 በመቶ ከፍ ማድረጉ አይዘነጋም፡፡

በተለይ እንደ ስፔን፣ ፈረንሣይና ጣሊያን ያሉ የኅብረቱ አገሮች ‹‹የእሳት እራት›› የተሰኘው ተባይ ወደ አገራቸው ከገባ በሰብሎቻቸው፣ በተለይም በፍራፍሬ ምርቶቻቸው ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንደሚያስከትል ገልጸው ነበር፡፡    

ተቀባይ አገሮች የጥራት የቁጥጥራቸው መጠን በመጨመሩ ለጥራት ቁጥጥሩ የሚወጣው ወጪ የሚሸፈነው በአበባ በላኪ አገሮች ወይም በአምራቾች መሆኑ ጉዳቱን ከፍተኛ እንደሚያደርገው መነገሩ ይታወሳል፡፡ 

የአውሮፓ ኅብረት በኢትዮጵያ ላይ ያስተላለፈው የጥራት ቁጥጥር መጠን በዚህ የሚቆም አይደለም ያሉት የኢትዮጵያ የሆርቲካልቸር አምራቾችና ላኪዎች ማኅበር ፕሬዚዳንት አቶ ቴዎድሮስ ዘውዴ፣ ከሚላኩ ምርቶች ላይ የሚገኘውን ተባይ መቀነስ ካልተቻለ የፍተሻ መጠኑ መጨመሩ አይቀርም ብለዋል፡፡

ማኅበሩና ባለሥልጣኑ ይህን ታሳቢ አድርገው ባለፈው አንድ ዓመት ከስድስት ወራት ባከናወኗቸው ሥራዎች፣ እ.ኤ.አ. በ2020 ወደ አውሮፓ አገሮች ከተላኩ የአበባ ምርቶች ለ23 ጊዜያት ተባዩ መገኘቱንና በ2023 ወደ ስምንት መቀነስ መቻሉን ገልጸዋል፡፡ ነገር ግን ይህም በቂ አለመሆኑን አስረድተዋል፡፡

በቁጥጥር ሥርዓቱን ለማጠናከር አቅም መገንባት ስለሚያስፈልግ ኩባንያዎች በራሳቸው አቅም ቁጥጥር እንዲያደርጉ ማስቻል እንደሚገባ፣ ይህንን ማድረግ ካልተቻለ ዋነኛ በሚባሉ የገበያ መዳረሻዎች የሚኖረው ተፎካካሪነት እንደሚቀንስና ሁሉም የሚመለከታቸው አካላት ተቀናጅተው መሥራት እንደሚኖርባቸው አሳስበዋል፡፡

የግብርና ሚኒስቴር መረጃ እንደሚያሳየው እ.ኤ.አ. በ2022/23 ከአበባ፣ ከፍራፍሬና ከአትክልት የወጪ ንግድ 658 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘት ተችሏል፡፡ ይህንን ገቢ ከፍ ለማድረግም የሁሉንም ዘርፎች ርብርብ የሚጠይቅ መሆኑ በጉባዔው ላይ ተገልጿል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች