Tuesday, July 16, 2024

ሕግ የማጥቂያ መሣሪያ እንዳይሆን ጥንቃቄ ይደረግ!

የሕግ መሠረታዊ ዓላማ ዜጎችን ከማናቸውም ዓይነት ጥቃቶች መጠበቅ፣ ለሕይወታቸውና ለንብረታቸው ከለላ መስጠትና በሥርዓት እንዲኖሩ ማድረግ ማስቻል ነው፡፡ በዚህ መሠረት ሁሉም ዜጎች በሕግ ፊት እኩል መሆናቸውን በማረጋገጥ ለሕግና ለሥርዓት ተቃራኒ የሆኑ ድርጊቶችን ማስወገድ የመንግሥት ኃላፊነት ነው፡፡ እ.ኤ.አ. በ1948 በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የፀደቀው ሁለንተናዊ የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌ፣ በአባል አገሮች በሙሉ ተግባራዊ እንዲደረግ ግፊት የሚደረግ ሲሆን መንግሥታትም የሕጎቻቸው አካል እንዲያደርጉት ይፈለጋል፡፡ የተመድ ድንጋጌ ሰዎች በዘር፣ በሃይማኖት፣ በቀለም ልዩነት፣ በፆታና በሌሎች ልዩነቶች መድልኦና መገለል ሳይደርስባቸው ሕይወታቸውን በሰላም መምራት አለባቸው ይላል፡፡ ማንም ሰው በአገሩ መንግሥት አሠራር በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መሳተፍ አለበት ሲልም ይደነግጋል፡፡ በዚህ መሠረት ሕጎች ሲወጡ ዜጎች በቀጥታም ሆነ በተወካዮቻቸው በኩል ድምፃቸውን እንዲያሰሙ ዕድል ማግኘት አለባቸው ማለት ነው፡፡ ሕግና ሥርዓት ሲኖር ሰዎች መብቶቻቸውን አይገፈፉም፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ በተደጋጋሚ ስለሕግ የበላይነት፣ በሕግና በሥርዓት ስለመኖር ያልተነገረበት ጊዜ የለም፡፡ ዜጎች በአገራቸው ከቦታ ወደ ቦታ ተዘዋውረው የመሥራት፣ የመኖርና ሀብት የማፍራት መብታቸው የሚከበረው መንግሥት በሕግ የተሰጠውን ኃላፊነት ሲወጣ ነው፡፡ ኃላፊነቱን ለመወጣት የተለያዩ አዋጆችን፣ ደንቦችንና መመርያዎችን ማውጣትም ይጠበቅበታል፡፡ መንግሥት ሕግ ሲያወጣ ለሕዝብ ጠቃሚ መሆኑ መረጋገጥ አለበት፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ በርካታ ችግሮች አሉ፡፡ ለምሳሌ ግብር መሰወር፣ የመሬት ወረራ፣ በጀት መዝረፍ፣ በጥቁር ገበያ መነገድ፣ ኮንትሮባንድና የመሳሰሉት ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል እንዳይኖር ከፍተኛ ሚና ይጫወታሉ፡፡ በእነዚህ ሕገወጥ ድርጊቶች ውስጥ ከለላ ተሰጥቷቸው በስፋትና በጥልቀት የሚሳተፉም ሞልተዋል፡፡ ስለዚህ ሕግ ሲወጣ ‹‹ከኑግ ጋር የተገኘ ሰሊጥ አብሮ ይወቀጥ›› ዓይነት የስህተት ዕርምጃ እንዳይወሰድ ጥንቃቄ ያስፈልጋል፡፡ አጋጣሚው ለጥቃት መሣሪያነት መጠቀሚያ እንዳይሆን ማሰብ የግድ ነው፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ ሕግን ለማጥቂያ መሣሪያነት እንዲውል ማድረግ ከተለመደ ሰንበት ብሏል፡፡ ለአብነት በዘመነ ኢሕአዴግ ከምርጫ 97 በኋላ ሦስት አደገኛ አወዛጋቢ ሕጎች መውጣታቸው አይዘነጋም፡፡ እነሱም የሚዲያ፣ የበጎ አድራጎት ማኅበራትና የፀረ ሽብርተኝነት ሕጎች እንደነበሩ ይታወሳል፡፡ በምርጫ 97 ወቅት ኢሕአዴግ በሕዝብ ድምፅ የደረሰበትን ከባድ ምት በኃይል ለማስቆም ሲል፣ እነዚህን ሦስት አፋኝና አገሪቱን ወደ መቀመቅ የከተቱ ሕጎች ተግባራዊ ሲያደርግ ነበር ተቃውሞው ከዳር እስከ ዳር የተስተጋባው፡፡ ሚዲያውን በማሽመድመድ አማራጭ ድምፆች እንዳይሰሙ በአፋኙ ሕግ የማስፈራሪያ ወጥመድ ዘረጋ፡፡ የበጎ አድራጎት ማኅበራት የመብት ትምህርቶች (አድቮኬሲ) ላይ መሰማራት እንዳይችሉ የገቢ ምንጫቸውን የሚያደርቅ ሕግ ደነገገ፡፡ በፀረ ሽብርተኝነት ሕጉ ይቃወሙኛል የሚላቸውን ዜጎች እያንዳንዱን እንቅስቃሴቸውን እያነፈነፈ፣ በሐሰተኛ ክስ በመታገዝ እስር ቤቶችን በታሳሪዎች ሞላ፡፡ ሕግ የማጥቂያ መሣሪያ ሲሆን ውጤቱ ይህ ነው፡፡

በ2007 ዓ.ም. በጀመረው ሕዝባዊ ተቃውሞ መነሻ ወደ ሥልጣን የመጣው አዲሱ የለውጥ አስተዳደር፣ ለሕዝብ ብሶቶችና ምሬቶች ምላሽ ለመስጠት የሪፎርም ዕርምጃዎች ሲወስድ እነዚህ ሕጎች የመጀመሪያዎቹ ተሰናባቾች ነበሩ፡፡ ሦስቱም አፋኝ ሕጎች በከፍተኛ የዜጎች ተሳትፎ ምክክር ተደርጎባቸው አንፃራዊ ነፃነት የሚሰጡ ሕጎች እንዲወጡ መደረጉ አይዘነጋም፡፡ የለውጡ ባቡር ጉዞውን በአባጣ ጎርባጣ ሐዲድ ላይ አድርጎ ኢትዮጵያ በከፍተኛ ወጀብ ውስጥ እያለፈች ስትሆን፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተከታታይ እየወጡ ያሉ ሕጎች በብዙዎች ዘንድ አሉታዊ ስሜት እየፈጠሩ ነው፡፡ መንግሥት ሁሉንም ሰዎች በአንዴ ማስደሰት ወይም ማስከፋት እንደማይቻለው ሁሉ፣ ሕጎች ሲወጡም ሆነ ውሳኔዎች ሲተላለፉ የአዋጭነት ጥናት ማድረግ ግን ይጠበቅበታል፡፡ በሕዝብና በመንግሥት መካከል ሊኖር የሚገባው መተማመን ሲሸረሸር ለምን ማለት ተገቢ ነው፡፡ የሰሞኑ የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅ የፈጠረው መደናገርና ሥጋት ሊጤን ይገባል፡፡ በተጨማሪም የተጨማሪ እሴት ታክስ አዲሱ አዋጅም እንዲሁ፡፡

ባለፉት ስድስት ዓመታት ኢትዮጵያ እያለፈችባቸው ያሉ ከባድ ችግሮች ጥለዋቸው የሚያልፉ ጉዳቶች ይታወቃሉ፡፡ በትግራይ፣ በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች የተካሄዱና እየተካሄዱ ያሉ አውዳሚ ጦርነቶች በአገርና በሕዝብ ላይ ያደረሱት ጉዳት ይታወቃል፡፡ ከዚህ ቀደም በተለያዩ አካባቢዎች በተፈጸሙ ጥቃቶችና ውጊያዎች የተፈጠሩ ጉዳቶች የፈጠሩት ቁርሾ የሚዘነጋ አይደለም፡፡ እነዚህ ሁሉ መከራዎች በደረሱባት አገር ውስጥ ለዘለቄታዊ ሰላም የሚያግዙ ንግግሮች እንዲደረጉ መድረኩን ማመቻቸት፣ እንዲሁም በውጊያ ውስጥ ካሉና በተለያዩ ምክንያቶች ካኮረፉ ወገኖች ጋር ተቀራርቦ ለመወያየት የሚያስችሉ አማራጮች ላይ ትኩረት አልተደረገም፡፡ ይልቁንም ከዛሬ ነገ የተሻለ ነገር የሚጠብቁ ወገኖችን ጭምር ለአመፅ የሚጋብዙ ድርጊቶች ሲስተዋሉ ቆም ብሎ ማሰብ ይገባል፡፡ በተለይ የሚረቀቁ ሕጎች ለሕዝብ ጥቅምና ለአገር ህልውና የሚኖራቸው ፋይዳ ይታሰብበት፡፡ ሕጎች ሲረቀቁ ከሥጋትና ከጥርጣሬ ይልቅ ተስፋ ይጫሩ፡፡

ዜጎች በአገራቸው ደስተኛ ሆነው እንዲኖሩ መንግሥት ከማንም የበለጠ ኃላፊነት አለበት፡፡ ሕጎች ሲወጡ ከምንም ነገር በላይ የዜጎችን አማካይ ፍላጎት መጠበቅ ይኖርባቸዋል፡፡ ሕጎች ጥቂቶችን ተጠቃሚ እያደረጉ ብዙኃኑን እንዳያስከፉ መንግሥት መጠንቀቅ አለበት፡፡ በዜጎች መካከል ልዩነት እንዳይፈጠርና በእኩልነት ላይ የተመሠረተ ግንኙነት እንዲኖር፣ ሕጎች ሚዛናዊና የሁሉንም ወገኖች ፍላጎት ያካተቱ እንዲሆኑ ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ሕጎች ከማንኛውም ዓይነት የፖለቲካ ጫና ነፃ ሆነው ሲወጡ አተገባበራቸው አስቸጋሪ አይሆንም፡፡ የፖለቲካ ጫና ሲበረታ ግን ከሕግነት ይልቅ የጉልበት አጀንዳ አስፈጻሚ ይሆናሉ፡፡ ከዚህ ቀደም አወዛጋቢ የነበሩ ሕጎች ያስከተሉት ጥፋትና ጉዳት እየታሰበ፣ እንደገና ወደ እዚያ ዓይነቱ መራር ትውስታ ላለመመለስ ይታሰብበት፡፡ በሕግና በሥርዓት መተዳደር ለአገር ህልውናም ሆነ ለሕዝብ ደኅንነት በጣም ጠቃሚ ስለሆነ፣ ሕግ የማጥቂያ መሣሪያ እንዳይሆን ጥንቃቄ ይደረግ!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ሚዲያው በሕዝብ የህሊና ችሎት ከተዳኘ በቂ ነው!

መሰንበቻውን ድንገት ሳይታሰብ ያለ ማስጠንቀቂያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ...

የባህር በር ጉዳይ

በታምሩ ወንድም አገኘሁ ድሮ ድሮ ገና ልጅ ሆኜ ፊደል እንደቆጠርኩ...

አገሩ ፖለቲካዊ ስክነትና መደማማጥ ያስፈልገዋል

በንጉሥ ወዳጀነው    ኢትዮጵያ የሁላችንም የጋራ ቤት ነች፡፡ ‹‹ጥያቄዬ ተመለሰልኝ››፣...

የመንግሥት የሰብዓዊ መብት ተቋም ለምን የመንግሥት ሚዲያን ማስተማር አቃተው

በገነት ዓለሙ የአገራችን የ2016 የበጀት ዓመት መሰናበቻና የአዲሱ የ2017 በጀት...

በነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ሳቢያ አጠቃላይ ገበያው እንዳይታመም ትኩረት ይደረግ!

መንግሥት ነዳጅን ከመደጎም ቀስ በቀስ እየወጣ ነው፡፡ ለነዳጅ የሚያደርገውን...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ሚዲያው በሕዝብ የህሊና ችሎት ከተዳኘ በቂ ነው!

መሰንበቻውን ድንገት ሳይታሰብ ያለ ማስጠንቀቂያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የተገኙበት የሚዲያ ሽልማት ሥነ ሥርዓት መካሄዱ ይታወሳል፡፡ ‹‹ለብሔራዊ ጥቅም መከበር ለሠሩ የአገር ውስጥና የውጭ...

ከሕዝብ ጥቅምና ፍላጎት ተፃራሪ ላለመሆን ጥንቃቄ ይደረግ!

ኢትዮጵያ ውስጥ ድብልቅልቅ ስሜት የሚፈጥሩ በርካታ ሁነቶች ማጋጠማቸው አዲስ ነገር ባይሆንም፣ በዚህ ወቅት ከተለያዩ ፍላጎቶችና ዓላማዎች ጋር የተሸራረቡ ሥጋት ፈጣሪ ችግሮች በብዛት እየተስተዋሉ ነው፡፡...

መንግሥት ቃሉና ተግባሩ ይመጣጠን!

‹‹ሁሉንም ሰው በአንዴ ለማስደሰት ከፈለግህ አይስክሬም ነጋዴ ሁን›› የሚል የተለምዶ አባባል ይታወቃል፡፡ በፖለቲካው መስክ በተለይ ሥልጣነ መንበሩን የጨበጠ ኃይል ለሚያስተዳድረው ሕዝብ ባለበት ኃላፊነት፣ በተቻለ...