Wednesday, July 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናአረንጓዴ አሻራ ከአገሪቱ ዓመታዊ በጀት እስከ አንድ በመቶ ድርሻ እንዲኖረው የሚያደርግ ረቂቅ...

አረንጓዴ አሻራ ከአገሪቱ ዓመታዊ በጀት እስከ አንድ በመቶ ድርሻ እንዲኖረው የሚያደርግ ረቂቅ አዋጅ ለፓርላማ ቀረበ

ቀን:

  • 2017 ዓ.ም. እስከ 5.6 ቢሊዮን ብር በጀት ሊመደብ ይችላል

የፌዴራል መንግሥት በየዓመቱ ከአገር ውስጥ ገቢ ምንጭ ከሚመድበው ዓመታዊ በጀት ውስጥ ከ0.5 በመቶ እስከ አንድ በመቶ ያህል፣ ለአረንጓዴ አሻራና ለተጎሳቆለ መሬት ማገገሚያ ልዩ ፈንድ እንዲሰጥ የሚደነግግ ረቂቅ አዋጅ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀረበ።

በ2017 በጀት ዓመት ይሰበሰባል ተብሎ ከተገመተው ጠቅላላ የመንግሥት ገቢ 563.64 ቢሊዮን ብር፣ ከግብር እና ግብር ነክ ካልሆኑ ገቢዎች ይሰበሰባል ተብሎ መታሰቡ፣ በቅርቡ በገንዘብ ሚኒስቴር ይፋ መደረጉ ይታወሳል።

ለፓርላማው የቀረበው ረቂቅ አዋጅ ባለበት ሁኔታ ከፀደቀ ልዩ ፈንዱ ከ2.8 ቢሊዮን ብር እስከ 5.6 ቢሊዮን ብር የሚደርስ በጀት፣ ከመንግሥት ብቻ ሊቀርብለት እንደሚችል ያሳያል።

ሰኔ 13 ቀን 2016 ዓ.ም. የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሦስተኛ ዓመት የሥራ ዘመን 33ኛ መደበኛ ስብሰባ የቀረበው የአረንጓዴ አሻራና የተጎሳቆለ መሬት ማገገሚያ ልዩ ፈንድን ለማቋቋምና አስተዳደሩን ለመወሰን የወጣ አዋጅ የሚል ስያሜ የተሰጠው ረቂቅ አዋጅ፣ ልዩ ፈንዱን ማቋቋም አስፈላጊ ሆኖ የተገኘው የተቀናጀ ቋሚና ዘላቂነት ያለው የአገር ውስጥ የፋይናንስ ምንጭ በመመደብና በማሰባሰብ ሁሉም ክልሎች ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ተጠቃሚ የሚሆኑበትን አሠራር መቀየስ ተገቢ ሆኖ በመገኘቱ እንደሆነ ያብራራል።

ልዩ ፈንዱ ዘጠኝ ዓላማዎች ሲኖሩት ከእነዚህም መካከል የተጎሳቆለ መሬት በተፈጥሮና በመልሶ ማልማት መርህ በመታገዝ እንዲያገግም በማድረግ፣ የደን ልማትና የደን መልሶ ማልማትን መደገፍ፣ የአገሪቱን የካርቦን ልቀት ቅነሳ ግብ እንዲሳካ አስተዋጽኦ ማድረግ፣ እንዲሁም የከተማ ማስዋብና አረንጓዴ ልማት ሥራዎችን መደገፍ የሚሉ ይገኙበታል።

የልዩ ፈንዱ የፋይናንስ ምንጮች የመጀመሪያው የፌዴራል መንግሥት ከሚመድበው በጀት፣ በሁለተኝነት ደግሞ የልማት አጋሮች፣ የሲቪክ ማኅበረሰቦች፣ እንዲሁም የግል ዘርፍ ከሚሰጡት ድጋፍ እንደሆነም በረቂቅ አዋጁ ተጠቅሷል።

የፌዴራል መንግሥት ከሚመድበው በጀት የሚሰበሰበው ገንዘብ ለልዩ ፈንዱ በተከፈተ የባንክ ሒሳብ በየሦስት ወሩ በገንዘብ ሚኒስቴር ተቀማጭ እንደሚሆን ሲገለጽ፣ በሁለተኛ ደረጃ ከሠፈሩት ምንጮች የሚደረገው ድጋፍ የሚተዳደርበት አኳኋን ደግሞ የገንዘብ ሚኒስቴር በሚያወጣው መመርያና የአሠራር ሥርዓት እንደሚወሰን ተብራርቷል።

የልዩ ፈንዱን የሀብት ክፍፍልና አለቃቀቅ በተመለከተ የሠፈረው ድንጋጌ፣ መንግሥት የሚመድበው ዓመታዊ በጀት የገንዘብ ሚኒስቴር በሚያወጣው መሥፈርት መሠረት ለፌዴራል መንግሥትና ለክልሎች ይደለደላል ይላል።

ለክልሎች ከሚደለደለው በጀት ላይ የእያንዳንዱን ክልል ድርሻ ለመወሰን የሚያገለግለውን የገንዘብ ሚኒስቴር አዘጋጅቶ እንዲፀድቅ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ይቀርባል ሲል፣ ሆኖም ለመሸጋገሪያነት የፌዴሬሽን ምክር ቤት ያፀደቀው ጠቅላላ የበጀት ድጋፍ ቀመር በጥቅም ላይ ሊውል እንደሚችል ይገልጻል።

በረቂቅ አዋጁ መሠረት ከተደለደለው ዓመታዊ የሀብት ድርሻ ላይ በየሦስት ወሩ ወደ ተጠቃሚ አካላት ገንዘብ ሊተላለፍ የሚችለው የሥራ አፈጻጸምን መሠረት በማድረግ፣ ክልሎች ተጓዳኝ በጀት ሲመድቡና በክልሉ ለሚተገበሩ ፕሮጀክቶች ፈሰስ ሲያደርጉ ይሆናል ተብሏል።

ከዚህ በተጨማሪም ክልሎች የሚመድቡት ዝቅተኛ ተጓዳኝ በጀት ተፈጻሚ የሚሆነው በተጓዳኝ በጀቱ መጠን ላይ በረቂቅ አዋጁ የልዩ ፈንዱ አስፈጻሚ አካላት በሚል የተዘረዘሩት የገንዘብ ሚኒስቴር፣ የግብርና ሚኒስቴር፣ የፕላንና ልማት ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ደን ልማት፣ እንዲሁም በክልሎች የገንዘብ ቢሮዎች መካከል በሚደረግ ምክክር የጋራ ስምምነት ላይ ሲደረስና በየክልሉና በከተማ አስተዳደሩ ምክር ቤቶች ሲፀድቅ እንደሆነም ተገልጿል።

እስከ በጀት ዓመቱ መጨረሻ ድረስ ሳይተላለፍ የቀረ ገንዘብ በቀጣዩ ዓመት ለልዩ ፈንዱ ከሚመደበው በጀት ጋር ተደምሮ እንደሚደለደልም ተጠቁሟል።

የልዩ ፈንዱ ተጠቃሚ አካላት ተብለው የተጠቀሱት በልዩ ፈንዱ የሚደገፉ ፕሮጀክቶችን የሚያስፈጽሙ የፌዴራል መንግሥት አካላትና ክልሎች ቀጥተኛ ተጠቃሚ በሚል ሲገለጹ፣ ለልዩ ፈንዱ አስተዳደር የሚቋቋም ዓብይ ኮሚቴ በሚያወጣቸው መመዘኛዎች መሠረት ሌሎች አካላት ተጠቃሚ ሊሆኑ እንደሚችሉም ተጠቅሷል።

በዚህ ረቂቅ አዋጅ ክፍል ሦስት ስለልዩ ፈንዱ አስተዳደር አንቀጽ 11 ላይ በቀረበው ድንጋጌ መሠረት የልዩ ፈንዱ ዓብይ ኮሚቴ አስፈጻሚ አካላት ተብለው የተዘረዘሩት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች፣ የኢትዮጵያ ደን ልማትና የክልሎች የገንዘብ ቢሮዎች የበላይ ኃላፊዎች እንደሚዋቀር ሲገለጽ፣ የገንዘብ ሚኒስቴርና የግብርና ሚኒስቴር እንደ ቅደም ተከተላቸው ሰብሳቢና ምክትል ሰብሳቢ እንደሚሆኑ፣ የሚመለከተው የሥራ ክፍል ደግሞ የፈንዱን አስተዳደራዊ ሥራዎችን እንደሚያከናውንና ጸሐፊ በመሆንም እንደሚያገለግል ተገልጿል።

ዓብይ ኮሚቴው ልዩ ፈንዱ አጠቃቀሙና አተገባበሩን የሚቆጣጠር ሲሆን የልዩ ፈንዱን የፕሮግራም ማዕቀፍ፣ ስትራቴጂና መመርያዎችን ማፅደቅ፣ የሚደገፉ ፕሮጀክቶችን ማፅደቅ፣ አጠቃላይ አፈጻጸሙን መገምገም፣ መቋረጥና መሰረዝ በሚገባቸው ፕሮጀክቶች ላይ መወሰን፣ መመዘኛዎችን በማውጣት ተጨማሪ አካላት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ፣ እንዲሁም የልዩ ፈንዱን የኦዲት ሪፖርት ውጤት ማዳመጥ፣ በሪፖርቱ መሠረት ተገቢው ዕርምጃ መወሰዱን ማረጋገጥ በረቂቅ አዋጁ የተሰጠው ሥልጣንና ተግባር ነው።

ዓብይ ኮሚቴው ስብሰባ በዓመት አንድ ጊዜ እንደሚያካሂድ ሆኖም አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ በሰብሳቢው በማንኛውም ጊዜ አስቸኳይ ስብሰባ ሊጠራና ሊደረግ እንደሚችል የተገለጸ ሲሆን፣ ማንኛውም ስብሰባ ላይ ከግማሽ በላይ አባላት ከተገኙ ምልዓተ ጉባዔ እንደሚሆንና ውሳኔ የሚተላለፈው ደግሞ በስብሰባው ከተገኙት አባላት በአብላጫው ድምፅ ሲደገፍ እንደሆነም ተገልጿል። ነገር ግን ድምፅ እኩል በእኩል የተከፈለ እንደሆነ የሰብሳቢው ድምፅ ወሳኝ ይሆናል።

ልዩ ፈንዱን የማስተዳደር ዓብይ ኮሚቴውን በሰብሳቢነት የመምራት ሥልጣን የተሰጠው ገንዘብ ሚኒስቴር፣ ልዩ ፈንዱ ለአምስት ዓመት የሚመራበት አገራዊ ፕሮግራም ማዕቀፍ በየአምስት ዓመቱ ተዘጋጅቶ ለዓብይ ኮሚቴው እንዲቀርብ እንደሚያደርግ ተጠቅሷል።

የገንዘብ ሚኒስቴር ከተጠቃሚ አካላት የሚቀበለውን የሒሳብ ሪፖርት በማጠቃለል የልዩ ፈንዱን ሒሳብ ዘግቶ የበጀት ዓመቱ በተጠናቀቀ በሦስት ወራት ውስጥ፣ በፌዴራል ዋና ኦዲተር ወይም የፌዴራል ዋና ኦዲተር በሚወክለው ኦዲተር እንዲመረመር የማድረግ ኃላፊነትም ተሰጥቶታል።

የፌዴራል መንግሥት ለልዩ ፈንዱ የሚመድበው የበጀት አጠቃቀም የኦዲት ምርመራ ውጤት የበጀት ዓመቱ ባለቀ በስድስት ወራት ውስጥ ለዓብይ ኮሚቴው ይቀርባልም ተብሏል።

የአረንጓዴ አሻራና የተጎሳቆለ መሬት ማገገሚያ ልዩ ፈንድን ለማቋቋምና አስተዳደሩን ለመወሰን የወጣ አዋጅ ከፀደቀ፣ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ለማስፈጸም የሚያስችል ደንብ ሊያወጣ እንደሚችል ሲገለጽ፣ የገንዘብ ሚኒስቴር ደግሞ የወጡ ደንቦችን ለማስፈጸም የሚያስችል መመርያ እንደሚያወጣ ተመላክቷል።

የአረንጓዴ አሻራና የተጎሳቆለ መሬት ማገገሚያ ልዩ ፈንድን ለማቋቋሚያና ለማስተዳደር ለፓርላማ የቀረበው ረቂቅ አዋጅ ለግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ተመርቷል።

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ የሠራተኞች ማኅበር አመራር ጋር እየተወያዩ ነው]

ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም! በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት። አዎ።...

የሱዳን ጦርነትና የኢትዮጵያ ሥጋት

የሱዳን ጦርነት ከጀመረ አንድ ዓመት ከአራት ወራት አስቆጠረ፡፡ ጦርነቱ...

ግለሰብ ነጋዴዎችን በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ለማድረግ ያለመው ረቂቅ አዋጅ ተከለሰ

በምትኩ የንግድ ተቋማት በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ይሆናሉ...

አሳርና ተስፋ!

ከቱሉ ዲምቱ ወደ ቦሌ ጉዞ ልንጀምር ነው፡፡ ገና ከመንጋቱ...