Wednesday, July 24, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

‹‹በኢትዮጵያ በቶሎ ሊተገበሩ ከሚገባቸው አስገዳጅ የኢንሹራንስ ዓይነቶች አንዱ የሞርጌጅ ቤት ግዥ ነው›› ወ/ሮ መሠረት በዛብህ፣ የኢንሹራንስ ኢንስቲትዩት ባለሙያ

ተዛማጅ ፅሁፎች

/ መሠረት በዛብህ በኢትዮጵያ የፋይናንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ በኩባንያ መሪነት ከሚጠቀሱ ጥቂት እንስቶች መካከል አንዷ ናቸው፡፡ ባለፉት አሥራ ሦስት ዓመታት ታዋቂውን የኢንሹራንስ ባለሙያ አቶ ኢየሱስ ወርቅ ዛፉን በመተካት የኅብረት ኢንሹራንስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ በመሆን ኩባንያውን በመምራት ላይ ይገኛሉ፡፡ 26 ዓመታት በላይ በዘርፉ ልምድ ያላቸው / መሠረት የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪውን የተቀላቀሉት በኒያላ ኢንሹራንስ ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅነት በመሆን ነው፡፡ የኅብረት ኢንሹራንስ ኦፕሬሸን ማናጀርና ምክትል ሥራ አስኪያጅ በመሆንም ሠርተዋል፡፡ በኢትዮጵያ ብቸኛው የጠለፋ መድን ኩባንያ በመሆን የሚጠቀሰውን የኢትዮጵያ ጠለፋ መድን አክሲዮን ማኅበርን በቦርድ ሊቀመንበርነት እየመሩም ነው፡፡ ቀደም ብሎም የኢትዮጵያ መድን ሰጪዎች ማኅበር ፕሬዚዳነት በመሆን አገልግለዋል፡፡ በዘርፉ የጎላ አስተዋጽኦ ያላቸው / መሠረት በቅርቡ በአፍሪካ የዓመቱ ምርጥ የኢንሹራንስ ኩባንያ መሪ በመባል ዕውቅና አግኝተዋል፡፡ / መሠረት የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኢኮኖሚክስ ወስደዋል፡፡ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ደግሞ በቢነስ አድሚኒስትሬሽን አግኝተዋል፡፡ SCI (UK) በቻርተርድ ኢንሹራንስ ኢንስቲቲውትም ተመርቀዋል፡፡ ዳዊት ታዬ በኢትዮጵያ የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ከወ/ መሠረት ጋር ያደረገው ቆይታ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

ሪፖርተርከሰሞኑ በአፍሪካ ደረጃ ዕውቅናና ሽልማት ማግኘትዎን በማንሳት ጥያቄዬን ልጀምር፡፡ የአፍሪካ ምርጥ የኢንሹራንስ የሥራ መሪ በመባል ዕውቅና እንዴት አገኙ? ምንስ አስዋጽኦ ስላበረከቱ ነው ይህንን ዕውቅና ያገኙት?

/ መሠረት፡-  ሽልማቱን ያገኘሁት የአፍሪካ ሪ-ኢንሹራንስ ኮርፖሬሽን ከሚባለውና የአፍሪካ አባል አገሮች ካቋቋሙት ኩባንያ ነው፡፡ ይህ ኩባንያ በየጊዜው በተለያዩ ዘርፎች ሽልማቶችን ይሰጣል፡፡ የዓመቱ ምርጥ ኩባንያ፣ የዓመቱ ምርጥ ዋና ሥራ አስፈጻሚና በመሳሰሉት ዘርፎች ባለሙያዎችን፣ የሥራ መሪዎችንና ኩባንያዎችን በመመዘን ብልጫ ላመጡ ተወዳዳሪዎች ዕውቅና ወይም ሽልማት ይሰጣል፡፡ ኩባንያው በየዘርፉ ለሚወዳደሩ ግብዣ በማድረግ እንዲሳተፉ ያደርጋል፡፡ እኔም በዚህ ውድድር ውስጥ ገባሁ። የሚጠየቁ መሥፈርቶችንም ከእነ ሙሉ መረጃው አቀረብኩ። ከዚያ በኋላ አፍሪካ ሪ-ኢንሹራንስ ኮርፖሬሽን ከተወዳዳሪዎቹ መካከል የመጨረሻዎቹን ስድስቱን  ለመለየት ከ40 በላይ አባላት ላሉት የዳኞች ኮሚቴ ላከ፡፡ ከዚያ ውስጥ አንዷና ብቸኛዋ ሴት እኔ ነበርኩ፡፡ ከእኔ ጋር የመጨረሻው ተወዳዳሪዎች የነበሩት  ከኬንያ፣ ታንዛኒያና ናይጄሪያ የመጡ ነበር፡፡ ሽልማቱም በተደረገ ኮንፈረስ ላይ ተሰጠኝ፡፡ 

ሪፖርተርእንዲህ ያሉ ዕውቅናዎች በሥራ አፈጻጸም ውጤት ጭምር የሚገኙ ናቸው፡፡ ዕውቅና ያገኙበትም አንዱ ምክንያትም ለኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ ባበረከቱት አስተዋጽኦ ነው፡፡ በግልም ሆነ በቡድን የኢትዮጵያ የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ ዕድገት ምን አድርጌያለሁ ብለው ያምናሉ? 

/ መሠረት፡- አንደኛ የምሠራበት ኩባንያ ላይ ሰዎች በሙያቸው ጠንካራ ሆነው እንዲወጡ ለየት ባለ መንገድ እሠራለሁ፡፡ ሒውማን ሪሶርስ ላይ ብዙ ከሠራህ ነው ኩባንያህም ኢንዱስትሪውም አገርም የሚያድገው፡፡ በዚህ ረገድ ብዙ ሥራዎችን ሠርቻለሁ ብዬ አምናለሁ፡፡ በኩባንያችን ውስጥ የኩባንያውን ዕድገት ለማስቀጠል  ከምሠራው ሥራ ባሻገር በመድን ሰጪዎች ማኅበር በኩል ለኢንዱስትሪው ይበጃሉ ያልኳቸውን ሥራዎች ስሠራ ቆይቻለሁ፡፡ አሁንም እየሠራሁ ነው፡፡ በተለይ የኢትዮጵያ መድን ሰጪዎች ማኅበርን በፕሬዚዳንትነት፣ ከዚያም የሥራ አስፈጻሚ አባል በመሆን ኢንዱስትሪው ያስፈልጉታል ያልኳቸውና ያመንኩባቸውን ሥራዎች በአግባቡ ተወጥቻለሁ ብዬ አስባለሁ፡፡ ይህ ግን በግሌ ብቻ ሳይሆን በጋራ ጭምር የሠራኋቸው ናቸው፡፡ በማኅበራችን በኩል በተቻለ መጠን ኢንሹራንስን ለማሳደግ እንሠራለን፡፡ የምናደርገው ጥረት ያሰብነውን ያህል እየሄድንበት ባይሆንም አሁንም እየሠራን ነው፡፡ ስለዚህ አስተዋጽኦዬ በተለያየ መንገድ ሊገለጽ ይችላል፡፡ ከምመራው ኩባንያ አንፃር ከወሰድክም ኩባንያህን እያሳደክ ከሄድክ አገርን እንዳሳደክ የሚቆጠር ነው፡፡ በቢሮ አካባቢ የሠራተኞችን ክህሎት እንዲያድግ በተደጋጋሚ ሥልጠና በመስጠትና ሠራተኞችን በማብቃቱ ረገድ ትኩረት እንሰጣለን፡፡ በዚህ ጥሩ የተሳካልን ይመስለኛል፡፡ እንዲህ ባለ መንገድ ያሠለጠናቸውና ከእኛ የሄዱ እስከ ዋና ሥራ አስፈጻሚ የደረሱ አሉ፡፡ ይህ ደግሞ ያስደስተናል፡፡ 

ሪፖርተርበኢትዮጵያ የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ ረዘም ላለ ጊዜ በሥራ መሪነት  ቆይተዋል፡፡ በዚህ ልክ አንድ የኢንሹራንስ ኩባንያን የመራች ሴት ሥራ አስፈጻሚ  የለም፡፡ አሁን ደግሞ በአኅጉር ደረጃ ምርጥ የሥራ መሪ በመባል ዕውቅና ያገኙበት ሙያ ጭምር ነውና ኢንዱስትሪውን በደንብ እንደሚያውቁት ይታመናል፡፡ እስኪ በእርስዎ ምልክታ የኢትዮጵያን የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ እንዴት ይገልጹታል?

/ መሠረት፡- የኢትዮጵያ የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ ብዙ ሥራ የሚፈልግ ነው፡፡ ብዙ ነገሮች ይቀሩታል፡፡ በኢንዱስትሪው ውስጥ ያለውን ክፍተት ለመሙላትና ያለበትን ደረጃ ከፍ ለማድረግ ግን አሁን የተሻለ ነገር እየመጣ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ ይህም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ብዙ ጊዜ የምናቀርበውን ጥያቄ በመመለስና በተሻለ መልኩ እየሰማንም ስለሆነ የሚሻሻሉ ነገሮች እንደሚኖሩ ይሰማኛል፡፡ በዋናነት የኢንሹራንስ ዘርፉ አሁን ካለበት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ወጥቶ ራሱን በቻለ ኮሚሽን ይተዳደር የሚለው የዓመታት ጩኸታችን አሁን ሰሚ አግኝቶ ረቂቅ ሕግ በፓርላማው እጅ ላይ ነው፡፡ ሕጉ መጀመሩ ተስፋ የሚሰጥ ነው፡፡ ይህ እራሱን የቻለ የኢንሹራንስ ኮሚሽን ሲቋቋም በራሱ መንገድ ኢንዱስትሪውን የሚያሳድጉ ሥራዎች ይሠራሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ከሪሰርች ጀምሮ ኢንዱስትሪን የሚመለከቱ የተለያዩ ተግባራትን በነፃነት ለመሥራትና የተሻለ አገልግሎት ለማምጣት የሚያስችል በመሆኑ አሁን የሚታየው ሁኔታ ይለወጣል፡፡ ኮሚሽኑ ከመንግሥት ቁጥጥርና በጀት ውጭ በኢንሹራንስ ኩባንያዎች የሚቋቋም ነውና በዘርፉ ላይ አድምቶ ለመሥራት ዕድል ይሰጣል፡፡ ኮሚሽኑ ለሙያው ትኩረት ሰጥቶ እንዲሠራ በሚያስችል ደረጃ የሚቋቋም ከመሆኑ አንፃር ለባለሙያዎች በቂ ገንዘብ የመክፈል አቅም የሚኖረው ጭምር ነው፡፡ የዚህ ኮሚሽን መቋቋም ለኢትዮጵያ የኢንሹራንስ ኢንዱትሪ ዕድገት ተስፋ የምናደርግበት ነው፡፡ አሁን ባለው አሠራር ኢንዱስትሪውን የሚቆጣጠሩ ባለሙያዎች የመንግሥት ተቀጣሪዎች በመሆናቸው በኢንሹራንስ ኩባንያዎች ውስጥ ከሚሰሩ ባለሙያዎች ያነሰ ክፍያ ነው የሚከፈላቸው፡፡ ኮሚሽኑ ሲቋቋም ግን ጥሩ የሚከፈላቸው ባለሙያዎች የሚሰባሰቡበት ይሆናል። ኢንዱስትሪውን የተሻለ ለማድረግ በመንግሥት ፖሊሲ መደገፍ ሌላው አስፈላጊ ጉዳይ ነው። በሌላው አገር እንደምናየው ዓይነት ለውጥና ዕድገት ለማምጣት የፖሊሲ ውሳኔዎች ያስፈልጉታል፡፡ ለምሳሌ በኢትዮጵያ ሦስተኛ ወገን ተብሎ የሚጠቀሰውን እንውሰድ፡፡ ይህ የኢንሹራንስ ሽፋን በመኪና የመድን ሽፋን አንዷና ትንሽ ነገር ነች፡፡ ይህ እንኳን ትልቅ አቴንሽን ተሰጥቶት የሚሠራ ነው፡፡ ሦስተኛ ወገን በመንግሥት በኮሚሽን ደረጃ የሚመራ ነው፡፡ ለዚህ የመድን ሽፋን የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ከፍተኛ የሆነ ገንዘብ ነው የምንሰጣቸው፡፡ የሚከፍሉት ክፍያም ትንሽ ነው፡፡ እንደዚህ ዓይነት ነገሮች ሊታሰብባቸው ይገባል፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ የኢንሹራንስ አገልግሎት ተነጣጥሎ ነው ያለው፡፡ በአንድ በኩል ሦስተኛ ወገን ተብሎ አንድ የሚሠራ ሥራ አለ፡፡ እንደገና ደግሞ የሜዲካል ይባልና በሌላ የመንግሥት ተቋም የሚመራ የኢንሹራንስ ሽፋን አለ፡፡ ማይክሮ ፋይናንሶችም ማክሮ ኢንሹራንስ ብለው የሚሰጡት የመድን ሽፋን አለ፡፡ ይህ የሚያሳየው ኢንዱስትሪው እንዲህ ባለ የተበታተነ ሁኔታ የሚሠራ መሆኑን ነው፡፡ ስለዚህ ኢንሹራንስ በራሱ ተሰብስቦ በአንድ ቦታ በባለሙያዎች እንዲሠራ ስላልተደረገ የሚጠበቀው ለውጥ አልመጣም፡፡ እስካሁን ትናንሽ ነገሮች እዚያም እዚህም ተበታትኖ የሚሠራ ሥራ ስለነበር እንዲህ ያሉ ችግሮችን ይህ ኮሚሽን ሊፈታ ይችላል ተብሎ ይታሰባል፡፡ ይህ ሲሆን የእኛም አገር የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ ያድጋል ብዬ እጠብቃሁ፡፡ 

ሪፖርተርየኢትዮጵያ የኢንሹራንስ ገበያ ለየት ያለ ፀባይ ይታይበታል ተብሎ በተደጋጋሚ የሚገለጽ ነገር አለ፡፡ የዕድገት ምጣኔው አነስተኛ መሆኑ ብቻ ሳይሆን ከሌሎች አገሮች በተለየ ሁኔታ የሕይወት የኢንሹራንስ ሽፋኑ ሕይወት ነክ ካልሆነው በእጅጉ ያነሰ መሆኑ ነው፡፡ በዓለም ላይ ዝቅተኛ የሕይወት ኢንሹራንስ የሚሰጥባት አገር ኢትዮጵያ መሆኗ ይጠቀሳል፡፡ በሌሎች አገሮች ግን የሕይወት ኢንሹራን ዘርፍ ከጠቅላላው የኢንሹራንስ ሽፋን ከፍተኛውን ድርሻ የሚወስድ ሲሆን በኢትዮጵያ በተቃራኒው የሆነበት ምክንያት ምንድነው?

/ መሠረት፡- በሌላው አገር በእርግጥም የሕይወት ኢንሹራንስ ዘርፉ ብልጫ ይያዛል፡፡ በአንዳንድ አገሮች የጡረታ ገንዘብ (የፔንሽን) ከሕይወት ኢንሹራንስ ጋር አብሮ የሚሠራ ነው፡፡ የጡረታ (ፔንሽን) ገንዘብ ደግሞ በጣም ከፍተኛ ነው፡፡ የጡረታውን ገንዘብ በሕይወት ኢንሹራንስ እንዲያስተዳድረው ካልተደረገ ገንዘቡ ሰው ለመጦር ብቻ የምትጠቀምበት ይሆናል፡፡ ይህ ደግሞ ትክክል አይደለም። ምክንያቱም የጡረታ ገንዘብ (ፈንድ) ብዙ ኢንቨስትመንት የምታደርግበትን ዕድል የሚሰጥ ነው። ጡረተኛው ወር ጠብቆ ክፍያ እንዲያገኝ ከማድረግ በዘለለ ሲቸገርም ገንዘብ ማበደር የሚቻልበት አሠራር መዘርጋት ይቻላል፡፡ በሌላው አገር የሕይወት ኢንሹራንስ ፈንድን በመጠቀም ትልልቅ ኢንቨስትመንቶችን ያካሂዳሉ፡፡ በዚህም ጡረተኛውን ጨምሮ አጠቃላይ ማኅበረሰቡን የሚያግዙ ተግባራትን ያከናውናሉ፡፡ በእኛ አገር ግን የጡረታ ገንዘብ የመንግሥት እንደሆነ ነው የሚቆጣጠረው፡፡ የሕይወት ኢንሹራንስ የሚቆጣጠረው አይደለም፡፡ የጡረታ ገንዘብ በሕይወት ኢንሹራንስ  ሥር መተዳደር ቢችል ብዙ ኢንቨስትመንቶችን በማካሄድ ከኢንቨስትመንቶቹ የሚገኘውን ትርፍ እንደገና ለሌሎች ተጠቃሚዎች ማዋል ይችላል፡፡ ስለዚህ የሕይወት ኢንሹራንስ በሌላው አገር ብዙ ሥራ የሚሠራበት ሲሆን በእኛ አገር ግን ይህ ሁሉ የለም፡፡ ስለዚህ የሕይወት መድን ሥራ ሽፋን ዝቅተኛ የሆነበት አንዱ ምክንያት ይህ ነው፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ የጡረታ ገንዘብ በመንግሥት ቁጥጥር ሥር ነው ያለው፡፡ የሜዲካል ኢንሹራንስን በተመለከተም በየገጠሩ የጤና መድን ተብሎ የሚሠራው በመንግሥት ነው። ነገር ግን ትክክለኛውን አሠራር ወይም የሌሎች አገሮችን ልምድ ብንመለከት አንድ ሰው አሥር ሺሕ ብር አውጥቶ የሕይወት ኢንሹራንስ ሲገዛ ይህ ወጪ እንደ ጥቅም ተቆጥሮ ከታክስ ነፃ ያደርጋል፡፡ በኢትዮጵያ ግን እንዲህ ዓይነት አሠራር የለም፡፡ ስለዚህ የሕይወት ኢንሹራንስን ለማሳደግ እንደ ሌሎች አገሮች ዘርፈ ብዙ ጥቅም እንዲኖረው ለማድረግ አጋዥ የሆኑ የፖሊሲ ውሳኔዎች ያስፈልጋል፡፡  

ሪፖርተርየኢትዮጵያ የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ እንደ ሌሎች የፋይናንስ ዘርፎች ለአገራዊ  ኢኮኖሚው ያለው አስተዋጽኦው የጎላ ያለመሆኑም ይነገራል፡፡ እንደውም ኢንዱስትሪው ለአገራዊ ኢኮኖሚ ዕድገት (ጂዲፒ) ያለው አስተዋጽኦ አንድ በመቶ ብቻ ነው ይባላል፡፡ ይህ ለምን ሆነ?

/ መሠረት፡- ብዙ ጊዜ ይህ ይነገራል፡፡ የኢትዮጵያ ኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ አገራዊ ኢኮኖሚው ላይ ያለው ድርሻ ትንሽ ነው ይባላል፡፡ ይህንን ያህል በመቶ ነው ሲባልም እንሰማለን፡፡ ይህ በመንግሥት ጭምር በተደጋጋሚ ይገለጻል፡፡ ይህ አገላለጽ ግን ተገቢ አይደለም፡፡ ለምሳሌ ፈሳሽ ነገር ስትመዝን በሌትር ነው፡፡ ጠጣር ነገሮችን ደግሞ በሌላ የልኬት መሣሪያ ትመዝናለህ፡፡ ኢንሹራንስ ግን የሚመዘነው እንዲህ ባለው ሁኔታ አይደለም፡፡ ለአገራዊ ኢኮኖሚው ዕድገት (GDP) ምን ያህል አስተዋጽኦ አደረገ? ሲባል የሚያመጣው ዓረቦን (ፕሪሚየም) በማሰብ ብቻ መሆን የለበትም፡፡ የኢትዮጵያ ኢንሹራንስ ዘርፍ ለኢኮኖሚው የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ከሚገለጸው በላይ ከፍተኛ ነው፡፡ ለምሳሌ እንደ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ያሉ ትልልቅ ፕሮጀክቶች የኢንሹራንስ ሽፋን ማግኘች ካልቻሉ ተግባራዊ መሆን አይችሉም። ኢትዮጵያውያን የምንኮራበትና ትልቅ ደረጃ ላይ ያለው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ኢንሹራንስ ከሌለው አንድ ማይል አይንቀሳቀስም፡፡ ባንኮች ይህንን ያህል ትርፍ አገኙ ሲባል የኢንሹራንስ ኩባንያዎች አስተዋጽኦ አይነገርም፡፡ ነገር ግን ባንኩ ኢንሹራንስ ሽፋን ከሌለው አንድ ብር ከካዝና አውጥቶ ወደ ብሔራዊ ባንክ አይልክም፡፡ ባንክ አምስት ሳንቲም ለማንቀሳቀስ ኢንሹራን ያስፈልገዋል፡፡ ስለዚህ የኢንሹራንስ ዘርፉ ከአጠቃላይ አገራዊ ኢኮኖሚው ውስጥ ያለው ድርሻ አነስተኛ ነው የሚባለው እንዲህ ያሉ መሠረታዊ ጉዳዮችን በመዘንጋት በመሆኑ አመለካከቱ መለወጥ አለበት፡፡ አጠቃላይ ኢኮኖማውን ተሸክሞ ያለው የኢንሹራንስ ዘርፉ ነው፡፡ ሌላም ምሳሌ ልስጥህ፡፡ ሚሊዮኖችንና ቢሊዮኖችን ያፈሰስክበት ኢንቨስትመንት ወይም ፋብሪካ ቢቃጠልብህ ተስፋ የምታደርገው ኢንሹራንስ ይከፍለኛል ብለህ ነው፡፡ መንግሥት መንገድ ሲሠራ መንገዶቹ ሁሉ የኢንሹራንስ ሽፋን አላቸው፡፡ ነገ ጎርፍ ቢያጥለቀልቃቸው ኢንሹራንስ ይከፍላል ተብሎ ይታሰባል፡፡ ስለዚህ ይህንን ሁሉ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ እየደገፈ የሚገኘውን የኢንሹራንስ ዘርፍ ለኢኮኖሚው የሚያበረክተው አስተዋጽኦ በጣም ዝቅተኛ ነው ማለት አይቻልም፡፡ የኢንሸራንስ ዘርፉ ኢኮኖሚውን በዚህ መልክ እየደገፈ ነው የሚለው ነገር ስለማይነሳ እንጂ አስተዋጽኦው እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡ ምናልባት እንዲህ ያለው አመለካከት ተደጋግሞ እየተነሳ ያለው እኛም በደንብ አስተዋጽኦውን በሚገባ ባለመግለጻችን ይሆናል፡፡  

ሪፖርተርሌላም የሚነሳ ነገር አለ፡፡ የኢትዮጵያ የኢንሹራን ኢንዱስትሪ ጠቅላላ ሽፋን ውስጥ 60 እስከ 70 በመቶ የሚሆነው የሞተር ወይም የተሽከርካሪ ኢንሹራንስ ነው፡፡ ይህ ማለት ደግሞ ሌላው የኢኮኖሚ ዘርፍ በቂ ሽፋን እንዳላገኘ ያመለክታል። ይህ በሆነበት ሁኔታ እርስዎ አሁን የገለጹልኝ አስተዋጽኦ ሚዛናዊ ነው ማለት ይቻላል?

/ መሠረት፡- ኢትዮጵያ ውስጥ አስገዳጅ ኢንሹራንስ ካልሆነ በስተቀር ብዙ ሰው ኢንሹራንስ አይገባም፡፡ ከባንክ ብድር ስትወስድ ባንኩ ኢንሹራንስ እንድትገባ ያስገድዳል፡፡ ኢንሹራንስ ከባንክ ብድር ስትወስድ ባንኩ ኢንሹራንስ ግባ ይላል፡፡ ቤት ብትገዛ ለቤቱ ማስያዣ ባንክ ኢንሹራንስ እንድትገዛ ያደርግሃል እንጂ አስቦ ኢንሺራንስ የመግዛት ልምድ የለም፡፡ ኢንሹራንስ ግባ ተብሎ እንደ አስገዳጅ ካልተነገረ በቀር በውዴታ ኢንሹራንስ የሚገዛ ሰው የለም፡፡ የሌላው አገር ልምድ ከዚህ የተለየ ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ በቅኝ ግዛት  የቆዩ አገሮች ሳይቀር እያንዳንዱ ሕይወታቸው ኢንሹራንስ ውስጥ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ኢንሹራንስ የሌለው ሰው እንዳለ አይቆጠርም፡፡ ይህንን ልምድ አዳብረዋል፡፡ እኛ ደግሞ እግዚአብሔር ያውቃል ብለን እንተዋለን፡፡ በሌላው አገር አንድ ሱፐር ማርኬት ገብተህ ወድቀህ ብትሰበር ሱፐር ማርኬቱ ኃላፊነት (ሊያቢሊቲ) አለበት፡፡ ሕጉ ዓለም አቀፍ በመሆኑ ይታወቃል፡፡ እዚህም አገር መሠራት ነበረበት፡፡ ነገር ግን ይህንን ማንም አይጠይቅም፡፡ ነገሩን ሁሉ ለፈጣሪ ይሰጣል፡፡ 

ሪፖርተርየፋይናንስ ዘርፍ ሲባል ኢንሹራንስ ኢንዱስትሪውን ያካትታል፡፡ ነገር ግን በኢትዮጵያ የፋይናንስ ዘርፍ ስም ሲነሳ ቀድሞ የሚጠቀሰው ባንክ ነው፡፡ ሰሞኑን እንኳን በተከታታይ ከብሔራዊ ባንክ የወጡ የተሻሻሉ መመርያዎች ትኩረታቸው ሁሉ የባንክ ሥራን የተመለከቱ ናቸው፡፡ በኢንሹራንስ ዘርፍ እንዲህ ያሉ ማሻሻያዎች የማይደረጉበት ምክንያት ምንድነው?

/ መሠረት፡- ሰሞኑን የውጭ ባንኮች ወደ ኢትዮጵያ እንዲገቡ የሚፈቅድ ረቂቅ ሕግ ቀርቧል፡፡ የውጭ ኢንሹራንሶች ወደ ኢትዮጵያ ይገባሉ የሚለው ነገር አይነሳም፡፡ የታሰበም አይመስለኝም፡፡ ነገር ግን የኢንሹራንስ ዘርፉ ራሱን ችሎ ኮሚሽን ተቋቁሞለት እንደሚወጣ ይጠበቃል፡፡ ይህ ከተተገበረ በኋላ ኢንሹራንስ ዘርፉን የተመለከቱ ድንጋጌዎች ይወጣሉ ከሚል መነሻ ይመስለኛል፡፡ በብዛት ማሻሻያዎች እየተደረጉ ያሉት ባንኮችን የሚመለከት መሆናቸውን ግን አንዱ ምክንያት በባንክ ኢንደስትሪው ውስጥ መጠነኛ ችግሮች ስላሉ እነዚህን ለመቅረፍና ዘርፉን ለማረጋጋት ያለመ ነው፡፡ የወጡት ማሻሻያዎች ዓለም አቀፍ ደረጃን በጠበቀ መልኩ የተዘጋጁ ናቸው፣ በአንድ ጊዜ አምስት የሚሆኑ የተሻሻሉ መመርያዎች የወጡት ባንኮቹን ከውድቀት ያድናል ከሚል ነው።

ሪፖርተርየውጭ ባንኮች እንዲገቡ ለመፍቀድ እየተሰናዳ ነው። በተመሳሳይ ሁኔታ መንግሥት በኢንሹራንስ ዘርፉም የውጭ ኩባንያዎች እንዲገቡ ቢፈቅድ በኢትዮጵያ ኢንሹራንስ ኢንዲስትሪ ውስጥ ሊኖረው የሚችለው አዎንታዊና አሉታዊ ተፅዕኖው እንዴት ሊገለጽ ይችላል?

/ መሠረት፡- የውጭ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ቢገቡ ጥሩ ነው፡፡ መግባታቸው ይጠቅማል፡፡ ምክንያቱም ኢንሹራንስ በባህሪው ኢንተርናሽናል ነው፡፡ እኛም የምንሠራው ኢንተርናሽናል ቢዝነስ ነው፡፡ ለምሳሌ የአፍሪካ ኅብረት ሕንፃ የመድን ሽፋን የሰጠነው እኛ ነን (ኅብረት ኢንሹራንስ)። የሰጠነው የመድን ሽፋን በቢሊዮኖች የሚቆጠር ነው፡፡ ይህንን የመድን ሽፋን ግን ብቻችንን አይደለም የያዝነው፡፡ የተወሰነውን የሪስክ መጠን እኛ ይዘን ሌላውን ለሌሎች የወጭ የጠለፋ መድን ኩባንያዎች ነው የሰጠነው፡፡ ስለዚህ አሁንም ቢሆን ሥራችን ከውጭ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ነገር ግን የውጭ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ቢገቡ የተሻለ ቴክኖሎጂ፣ የተሻለ ዕውቀትና የተሻለ ክህሎት በማምጣት ኢንዱስትሪውን ሊያሳድጉ ይችላልና በእኛ በኩል ቢገቡ ይጠቅማል ብለን ነው የምናምነው፡፡ 

ሪፖርተርየውጭ ኩባንያዎች መግባት የአገር ውስጥ ኢንሹራን ኩባንያዎች ላይ ተፅዕኖ አያሳርፍም?

/ መሠረት፡- እንግዲህ ይለይልን፡፡ አሁን እኮ እኛ ጋር ትልቁ ችግር በአገር ውስጥ እርስ በራሳችን በደንብ እየተወዳደርን አይደለም፡፡ ችግሮች አሉ፡፡ 

ሪፖርተርከምን አንፃር?

/ መሠረት፡- እርስ በርስ እንኳን እየተወዳደርን አይደለም ለሚለው ብዙ ማሳያ ማቅረብ ይቻላል፡፡ እንደ ምሳሌ አንዱን ላንሳልህ፡፡ እዚህ ክልል ላይ እንዲህ የሚባለው የኢንሹራንስ ኩባንያ ነው የሚሠራው ይባላል፡፡ ያኛው ወደ ሌላ ይሄዳል፡፡ ይኼኛው ተቋም የመንግሥት ስለሆነ ኢንሹራንስ ሽፋን የሚገዛው ከመንግሥት የኢንሹራንስ ኩባንያ እንጂ ከግል ኢንሹራንስ ኩባንያ መግዛት አይቻልም ይባላል፡፡ እንዲህ ያሉ ነገሮችን እንኳን አላስተካከልንም፡፡ እርስ በርሳችን በአግባቡ መወዳደር አልቻልንም። ስለዚህ ዓለም አቀፍ ውድድር ሲመጣ የወደቀ ወድቆ አቅም ያለው ይነሳ እንጂ መቼም ዘለዓለም ፈርተን አንኖርም፡፡ እኔ ይህ ነው የሚታየኝ፡፡ ውድድር ፈርተን ቀጭጨን መቅረት የለብንም፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ፡፡ ምንም ከፍ አላልንም፡፡ ስለዚህ የውጭ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ይግቡና አቅም ያለው ይቀጥል፣ የሌለው ደግሞ እንደሚሆን ይሆናል፡፡ ስለዚህ በምንም መልኩ የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪው እንዲያድግ መደረግ አለበት፡፡ ሰዎች ጥቅሙን እንዲያውቁ በእኛ በኩል ትምህርት መሰጠት አለበት፡፡ በዚህ ረገድ ብዙ መሥራት ይኖርብናል፡፡ ከሁሉም በላይ ግን የፖሊሲ ድጋፍ በጣም ይፈልጋል፡፡ 

ሪፖርተርደጋግመው ዘርፉ የፖሊሲ ድጋፍ ያስፈልገዋል እያሉ ነው፡፡ የፖሊሲው ድጋፍ ምን ዓይነት ይዘት እንዲኖረው ነው የሚፈለገው፡፡ ይጥቀሱልኝ? 

/ መሠረት፡- አሁን ለምሳሌ የሊያቢሊቲ ኢንሹራንስ ግዴታ መኖር አለበት፡፡ በሌላው ዓለም ብትሄድ ግዴታ ነው። ኬንያ ብትሄድ ተመሳሳይ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕግ ላይ ለሠራተኛ አምስት ዓመት ክፈል ይላል፡፡ የአምስት ዓመት ደመወዙን እንድትከፍለው ያስገድድሃል፡፡ ለዚህ ግን የመድን ሽፋን ልትገባለት ይገባል፡፡ የዚህን የኢንሹራንስ ሠርተፊኬት ልክ እንደ ንግድ ፈቃድ ፊት ለፊት ታስቀምጣለህ፡፡ እንዲህ ያሉ አስገዳጅ የኢንሹራን ሽፋን የሚያስፈልጋቸውን በመለየት መንግሥት በሕግ ማስቀመጥ አለበት፡፡ አሁን በኢትዮጵያ አስገዳጅ የኢንሹራንስ ሽፋን ያለው የሦስተኛ ወገን ኢንሹራንስ ብቻ ነው፡፡ ነገር ግን በኮንስትራክሽን ዘርፍ አስገዳጅ ተብሎ የተቀመጠ ነገር የለም፡፡ ግን አስገዳጅ ሁኔታዎች መቀመጥ ነበረበት፡፡ ለሠራተኞችህ ኢንሹራንስ ካልገባህ ሰዎች ተጎድተው የትም የሚወድቁበት ሁኔታ ይፈጠራል፡፡ አስገዳጅ የመድን ሽፋን ያስፈልጋል የሚባልበት ብዙ ምክንያቶች አሉ፡፡ አሁን ለምሳሌ ቤት በብድር ስትገዛ የሞርጌጅ ቤት ገዥ አስገዳጅ የኢንሹራንስ ሽፋን እንዲኖረው ማድረግ አለብህ፡፡ በኢትዮጵያ በቶሎ ሊተገበሩ ከሚገባቸው አስገዳጅ የኢንሹራንስ ዓይነቶች አንዱ ይህ ነው፡፡ አለበለዚያ ቤት ገዥው ሲሞት በብድር የተገዛውን ቤት ባንክ ይወርሰዋል፡፡ በዚህ ጊዜ የሟች ቤተሰብ ሜዳ ላይ ይወድቃል፡፡ ኢንሹራንስ ቢገባለት ግን እንዲህ ያለው ማኅበራዊ ቀውስ አይኖርም፡፡ ስለዚህ አንዳንድ የመድን ሽፋኖች አስገዳጅ ሊሆኑ የሚገባቸው በኋላ ሊያስከትሉ የሚችሉት ቀውስ ከፍተኛ ስለሚሆን ነው፡፡ እንዲህ ያሉ የመድን ሽፋኖች የመንግሥት የማኅበራዊ ኃላፊነት በመሆናቸው መንግሥት ራሱ ነበር ሕጉን ማውጣት ያለበት፡፡ ስለዚህ የማኅበረሰቡ ደኅንነት እንዲጠበቅ የሚረዱ የመድን ሽፋኖች በአስገዳጅነት ማስቀመጥ በብርቱ ሊታሰብበት የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች