በጌታሁን አስማማው
ፍራንክ ቲስትልዌይት የተባሉ አሜሪካዊ ጸሐፊ ‹‹The Great Experiment – an Introduction to the History of America People›› በሚለው አነስ ያለ መጽሐፋቸው መግቢያ ላይ ያሠፈሩትን ሐሳብ ለዚህ ጽሑፍ መንደርደሪያ ማድረግ ፈልጌያለሁ፡፡
ጸሐፊው እንዲህ ይላሉ፡፡ ‹‹ስለአሜሪካ የተሳሳተ ሥዕል እየታየ ያለው አገሪቱን በአንድ ዕይታ ብቻ ለመግለጽ እየተሞከረ በመሆኑ ነው፡፡ ለአብነት አሜሪካንን ከሕገ መንግሥቷ አንፃር ብቻ የሚመለከቱ አሉ፡፡ ከምጣኔ ሀብቷ፣ ከፖለቲካ አወቃቀሯም ሆነ ከአውሮፓ ከተወረሱ በርካታ ዕሳቤዎቿ አንፃር ነጣጥለው የሚመለከቷትም አሉ፡፡ እንዲህ ያሉ ዕይታዎች ግን ስለአሜሪካ አሁናዊ እውነት ሊያሳዩ አይችሉም፡፡ ትክክል የሚሆነው ከታሪኳ አንስቶ የተራመደችበትን መንገድ መቃኘትና ዘርፈ ብዙ ገጽታዋን መቃኘት ነው፡፡ በአንድ ጉዳይ ላይ አተኩሮ በሚቀርብ ሀተታም ትናትን፣ ከዛሬና ከነገ ጋር አስተሳስሮ መፈተሽ ነው ጠቃሚ የሚሆነው፤››
እኔም በእዚሁ መነሻ ላይ ተመሥርቼ የአገራችንን ወቅታዊ ሁኔታና አሳሳቢውን የምጣኔ ሀብት መንገራገጭ ገባ ወጣ እያልኩ ለመዳሰስ እሞክራለሁ፣ እስቲ እንወያይበት፡፡
ኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ሥርዓት መከተል ከጀመረች 32 ዓመታት ገደማ ዕድሜ ብታስቆጥርም፣ ተስፋና ሥጋት የተሞላበት ጉዞ ነው ስታሳልፍ የቆየችው፡፡ ቀደም ባሉት ዘመናት እንደ አገር ሥር ሰዶ ከቆየው አሃዳዊ ሥርዓት በመላቀቅ የብሔር ብሔረሰቦች ራስን በራስ የማስተዳደር መብት መከበር መጀመሩና ብዝኃነት ያላቸው ሕዝቦች ቋንቋቸው፣ ባህልና ታሪካቸው እየጎለበተ መምጣቱ መልካሙ የዚህ ዘመን ተግባር ተደርጎ ቢወሰድም፣ ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን መገንባት ከፍተኛ ፈተና እየሆነ መጥቷል፣ አሁንም ጭምር፡፡
ፌዴራላዊው ሥርዓት ወደ ፖለቲካ ሥልጣን ከወጣበት ጊዜ አንስቶ መለስ ቀለስ የሚል የትርክት መዛባት፣ ፍጥጫና መካረር፣ የፖለቲከኞች መፈላቀቅ፣ ግጭትና አልፎ ተርፎም የእርስ በርስ ጦርነት ከማስቀጠል አለመውጣታችን አንድ ማሳያ ነው፡፡ አሁን ለሚታየው የሰላም ዕጦትና የደኅንነት መጓደል፣ ብሎም የተረጋጋ የፖለቲካ ሥርዓት አለመኖር መንስዔው እሱ ነው ማለት ይቻል ይመስለኛል፡፡
በኢሕአዴግ 27 የአመራር ዓመታት በተለይም በኋላዎቹ 14 ዓመታት ገደማ በተወሰነ ደረጃ የፍትሐዊነትና የሙስና ተግዳሮት ቢታይበትም፣ ከቀደሙት ሥርዓቶች በተሻለ ልማትና ያልተማከለ ዕድገት የተመዘገበ ነበር፡፡ ዘላቂነቱ ላይ ጥያቄ ለመነሳቱ ግን የምንገኝበት ወቅት ጭምር አንድ ማሳያ ነው፡፡ አልፎ ተርፎ ችግሮች አንዱ በአንዱ ላይ መደራረባቸው ሰብዓዊና ማኅበራዊ ቀውስ እየወለዱ ይገኛሉ፡፡
በአገራችን ባለፉት አምስት ዓመታት አዲስ ዓይነት የሥርዓት ለውጥ ሲመጣ፣ ከዓለም አቀፍ ፈተናዎች ጋር ተደማምሮ የተጀመረ የምጣኔ ሀብት ዕድገት ለመገደቡና የኑሮ ውድነት ጫና ለመባባሱ ዋናው እንቅፋት የግጭትና የጦርነት ፖለቲካው ጋብ አለማለቱ ነው፡፡ ገና ከመነሻው የታየውን ተስፋ የሚያደፈርስ የግጭትና ያለመግባባት ፖለቲካ አገሩን አውኮት መቆየቱ፣ በአንድ በኩል የደሀዋ አገራችንን ኢኮኖሚ ጦርነት እዲበላው እያደረገ ሲሆን፣ በሌላ በኩል አገራዊ እንቅስቃሴውን በመገደብና አምራቹን ኃይል መስመር በማሳት ዕድገቱን በማደናቀፉ ነው፡፡ የአገር ገጽታ እየጠለሸ ዓለም አቀፍ የኢንቨስትመንትና የብድር ዕድሎችም እየጠበቡ በመምጣታቸውም ነው፡፡
እነዚህ ሁኔታዎች ምጣኔ ሀብትን ለማቀወስ ብቻ ሳይሆን፣ የአገር ህልውናን የሚያናጉ እንደመሆናቸው አደገኛና የሚያስፈራ ወቅት እንዳይመጣብን መጠንቀቅ ይገባል፡፡ በተለይ አለመተማመንና ሥጋትን በሰከነ የፖለቲካ ትግል ለማስተካከል አለመሞከር ደግሞ የመጪው ጊዜ የምጣኔ ሀብት ድቀት ምክንያት መሆኑ አይቀሬ በመሆኑ፣ ሁሉም ይመለከተኛል የሚሉ ኃይሎች ሁሉ ሊያስቡበት የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡
ባለፉት አምስት ዓመታት በኢትዮጵያ ሰማይ ሥር ምንም ያህል ስለመደመር፣ ዕርቅና አንድነት እየተሰበከ ቢሆንም ከራሩ የዘውግ ፖለቲካችን፣ በፖለቲካ ነጋዴዎችና በአንዳንድ የማኅበራዊ ትስስሮች አቀጣጣዮች በጥላቻ ትርክት እየተለወሰ ከዕለት ወደ ዕለት አገርን ወደ ከፋ አቅጣጫ እየጎተታት ነው፡፡
ለውይይትና ለድርድር እንዲሁም ለዴሞክራሲ ምኅዳር መስፋት ጅምር ዕድል ቢኖርም፣ ፅንፍ የረገጠው ትርክትና ተከታዩ አዲሱ ትውልድ ባለመገራቱ፣ ነጣጣይ የሕገ መንግሥት አናቅጽቱም መታረም ባለመጀመራችውና የፖለቲካ ባህሉም ድክመት ተጨምሮበት፣ ንፁኃንን ለዕልቂት እየዳረገ ከፍተኛ የአገር ሀብት እያወደመ ይገኛል፡፡ መንግሥትም ከኃይል አማራጭ ውጪ ሌላ አማራጭ አለማማተሩም ችግሩን እያባባሰው ነው፡፡
እውነት ለመናገር እንደ አገር ሕዝቡ ተደማምጦና ተግባብቶ የመኖር ችግር የለበትም፣ ለዘመናትም ኖሮበታል፡፡ ትልቁ ችግር ቆስቋሽ ግን የፖለቲካ ልሂቁና ኋላቀር ባህላችን ሳይሆን አይቀርም፡፡ በተለይ በማይታረቁ ህልሞች የሚባዝን የቡድን ፍላጎት ከአገር ጥቅም የበለጠባቸው ግለሰቦች አገራዊ መንግሥቱን ክፉኛ እየፈተኑት መሆኑን መጠራጠር የማይቻልበት ደረጃ ላይ ተደርሷል፡፡ በዚያም በዚህም ጎራ የተሠለፈ ኃይል አገርና ሕዝብን ወደ መቀመቅ ይዞ ሳይወርድ ከወዲሁ መገሰፅ ነው ያለበት የሚሉ ሚዛናዊና መሀል ላይ ያሉ ዜጎች ቁጥራቸው ትንሽ አይደለም፡፡
እናም ግጭትና ትርምስን አስወግዶ ሰላምና ልማትን ለመተካት በሰከነ መንገድና በሠለጠነ ሁኔታ መነጋገርና ማሻሻያዎችን ማድረግ፣ የለውጥ ዕርምጃውም የወሰደውን ጊዜ ያህል ቢወስድም በሕዝብ ይሁንታ መፈጸም ይበጃል፡፡ በሒደት ዴሞክራሲንም እየገነቡ በኃይል ሳይሆን በሠለጠነ ምርጫ ሥልጣን ለሚረከብ ወገን ዕድል ማመቻቸትም ተገቢ ይሆናል፡፡ የትውልዱ ታሪካዊ ኃላፊነት ብቻ ሳይሆን ከቀውስ ወጥቶ ወደ ተቃና የዕድገት ጉዞ ማምራት የሚቻለው በዚሁ መንገድ ብቻ ነው፡፡
አነሰም በዛም በአገራችን የቅርቦቹ አሥርት ዓመታት መነጋገሪያችን የዕድገት አጀንዳዎች ነበሩ፡፡ ከ1998 ዓ.ም. አንስቶ በየዓመቱ የተጀመረውን ባለሁት አኃዙ ዕድገት፣ ከ2002 እስከ 2007 ዓ.ም. በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ማስቀጠል ተችሎ ነበር፡፡ በተለይ በሥራ ዕድል ፈጠራ፣ በማኅበረ ኢኮኖሚያዊ ልማት ሥራዎች፣ በመሠረተ ልማት ግንባታዎችና በሜጋ ፕሮጀክቶች መጠናከር ብቻ ሳይሆን፣ በወጪ ምርት ዕድገትና በምንዛሪ መሻሻልም የሚታይ ነበር፡፡ በአሁኑ ሁኔታ የሚገለጽ የዋጋ ግሽበት ከዚህ ቀደም ስለመኖሩም የሚቀርብ መረጃ የለም፡፡
ይህንን አስመልክቶ ያነጋገርኩት የምጣኔ ሀብት ዘገባ ኤዲተር አገራችንን ለ21 ዓመታት (ከ1983 እስከ 2004 ዓ.ም.) የመሯት ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን በአካል ማግኘት ብቻ ሳይሆን፣ ሦስት አራት ጊዜ ያህል ቃለ ምልልስ የማድረግ ዕድል አጋጥሞኛል ይላል፡፡ ሰውየው በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ አወዛጋቢ ማንነት ያላቸው ቢሆኑም በአገራችን ሰላም፣ ፈጣን ልማትና ሰፋፊ የመሠረተ ልማት ግንባታዎችን በማቀድና በማስፈጸም ከፍተኛ አክብሮት የሚሰጣቸው እንደነበሩና ቅቡልነቱ የተሟላ እንኳን ባይሆን ጠንካራ አገረ መንግሥትም መሥርተው ነበር ሲልም ምስክርነቱን ይሰጣል፡፡
አገራችን በሰላም ማስከበር፣ የውጭ ስደተኞችን ተቀብሎ በማስተናገድና በዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲ ተቀባይነቷ ከፍ ያለ ደረጃ ላይ እንዲደርስ በማድረግ ረገድም የመለስ አመራር ከፍተኛ ምሥጋና የሚቸረው ነበር ያለው ባለሙያው፣ አሁን እየሆነ ካለው አገራዊ መወናበድና ኪሳራ አንፃር ያኔ የነበረው የመልካም አስተዳደር ጥረትም ሆነ ጅምር ዴሞክራሲ የሚጣጣል እንዳልሆነ ብቻ ሳይሆን፣ ለሁሉም ሰላምና ደኅንነት መሠረት ለመጣል የተሞከረ ነበር ብሎ መናገር ኃጥያት እንዳልሆነ በአጽንኦት ተናግሯል፡፡
በእዚህ ላይ የቀድሞው ሥርዓት ድክመትና ዝቅጠት (ሙስናው፣ መንደርተኝነቱ፣ ኢፍትሐዊነቱና ሥርዓት አልበኝነቱ) እንዲሁም በኢሕአዴግ ስም ይፈጸም የነበረው ፀረ ዴሞክራሲያዊነትና የተደራጀ የቡድን ጥቅም የማስከበር ጥድፊያ የተባባሰው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ካረፉ በኋላ በተቀፈቀፈው ጥገኛ ነበር የሚሉ ወገኖችም ሐሳብ ሲታይ፣ መንሸራተቱ ያኔ ጀምሮ ሳይቆም የቀጠለ እየመሰለ ነው፡፡
በእርግጥ ኢትዮጵያን ጨምሮ በብዙዎቹ አፍሪካ አገሮች ልማት በማፋጠን ረገድ ችግሩ ያለው የሰከነና አሳታፊ ዴሞክራሲ፣ ብሎም መልካም አስተዳደር በፍትሐዊነት ዕውን ባለማድረጉ ምክንያት በሚፈጠር አለመግባባት፣ ግጭትና ጦርነት መባባስ ብቻ አይደለም የሚሉ አሉ፡፡ ይልቁንም ገና ከመነሻው ኢኮኖሚያዊ መዋቅራዊ ለውጥ (Economical Structural Transformation) ደካማ በመሆኑም ነው የሚሉት፡፡
የምሥራቅ እስያ አገሮች በፍጥነት ማደግ የቻሉት፣ ዛሬ አድገዋል ከሚባሉት ምዕራባውያን አገሮች ከኢንዱስትሪ አብዮት በኋላ የሠሩትን ሥራ በአጭር ጊዜ ገልብጠው (ኮርጀው) በመሥራታቸው ብቻ አይደለም፡፡ ይልቁንም ዴሞክራሲን ዕውን ማድረግ እንኳን ባይችሉ (ቻይናን ልብ ይሏል) በተቻለ መጠን ጠንካራ አገራዊ አንድነትና ግጭት አልባ የአገረ መንግሥት ግንባታን ፈለግ፣ ከኢኮኖሚያዊ መዋቅራዊ ለውጥ ትግበራ ጋር አስተሳስረው በመተግበራቸው ነው፡፡ ለፈጠራ፣ ለቴክኖሎጂና ለምርምር ዕድል የሚሰጥ አስተማማኝ ሰላምና መረጋጋት በማግኘታቸውም እንደሆነ መካድ አይቻልም፡፡
ኢትዮጵያን ጨምሮ በአፍሪካ ውስጥ ግን ከዚህ ዓይነቱ መልካም እሴት ልምድ የወሰዱት እዚህ ግባ የሚባሉ አይደሉም፡፡ በአፍሪካ አኅጉር የምንኖር ሕዝቦች መጥፎ ዕድል አድርጎብን ከጎሰኝነትና ከአክራሪ ብሔርተኝነት እስር ቤት መውጣት አልቻልንም፡፡ ሥልጣንን ለጥቂቶች መጠቀሚያና ዘረፋ የማዋል ልክፍታችንም ያዋጋናል እንጂ ሊያደማምጠን አልቻለም፡፡ እውነት ለመናገር አሁን ኢትዮጵያውያን እንዲህ በመሰለው የእርስ በርስ መበላላትና ውድመት ውስጥ መገኘት ነበረብን? በተለይ ለውጥ ሲጀመር ከነበረው ተስፋና መቀራረብ አንፃር ይህ ወቅት ይጠበቅ ነበር?
በአሁኑ ወቅት በስንዴ ምርት ከፍተኛ እመርታ ያሳዩ አንዳንድ የአገራችን አካባቢዎች ቢኖሩም፣ በርከት ባሉ ሥፍራዎች ደግሞ መደበኛ የእርሻ ሥራዎችንም ማካሄድ እየተቻለ አይደለም፡፡ ለእርሻ ሥራ እንደ ማዳበሪያ፣ ምርጥ ዘርና ሌሎች ግብዓቶች ማግኘት ሲያስቸግር ነበር፡፡ ማንኛውንም ምርትና ግብዓት አንቀሳቅሶ መሸጥም ሆነ በገበያው ውስጥ አምራችና ሸማች በቀላሉ ማገናኘትም ሲከብድ ደጋግሞ ታይቷል፡፡
በትግራይ፣ በአማራና በአፋር ክልሎች ቀላል ቁጥር የሌላቸው አምራች ኢንዱስትሪዎች ከሥራ ውጪ ሆነዋል፡፡ በግጭትና በድርቅ ምክንያት ለተረጂነት የተዳረጉ ዜጎች ቁጥር እጅግ ጨምሯል፡፡ በርካታ የአማራና የኦሮሚያ አካባቢዎች ለእንቅስቃሴ ዝግ ናቸው፡፡ መንግሥት ሰላምና ደኅንነትን ለማረጋገጥ በየዕለቱ ከፍተኛ ሀብት ያባክናል፡፡ ታዲያ በዚህ ሁኔታ እንዴት ያለ የምጣኔ ሀብት ዕድገት ሊገኝ ይችላል ነው ጥያቄው፡፡
በተጨማሪም ምዕራባውያንን ለጋሽ ድርጅቶችና አበዳሪ ተቋማት በተለመደው ቅድመ ሁኔታና በአገር መረጋጋት ላይ የተመሠረተውን መሥፈርታቸውን በማጥበቃቸው፣ ለአገር ግንባታ የሚፈለገውን ያህል ፋይናንስ እያቀረቡልን አይደለም፡፡ በአገር ደረጃ በተፈጠረው የውጭ ምንዛሪ እጥረት ደግሞ በየዘርፉ የግብዓት እጥረት መፈጠሩ ብቻ ሳይሆን፣ መድኃኒትና መሠረታዊ ፍላጎቶች ላይ ጭምር ከፍተኛ የዋጋ ንረት መከሰቱ ችግሮችን ሲያባብስ እየታየ ነው፡፡
በምጣኔ ሀብት ችግር እየተፈተንን ያለነው እኛ ብቻ ሳንሆን፣ በሌሎች የአፍሪካ አገሮች ያለው ሁኔታም አስደንጋጭ እየሆነ ነው የሚሉ ተንታኞች አሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት በአኅጉር ደረጃ የፋብሪካ ሥራ የሚያገኙት አሥር በመቶ ያህሉ አፍሪካውያን ሠራተኞች ብቻ መሆናቸውን በመግለጽም ያስረዳሉ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ ዘመናዊና መደበኛ በሆኑና በቂ ቴክኖሎጂ ባላቸው ኢንዱስትሪዎች ውስጥ የመቀጠር ዕድል የሚያገኙት ከአንድ በመቶ ያነሱ ናቸው፡፡
በግብርናው መስክም ቢሆን እንደ ሁሉም በማደግ ላይ ያሉ የአፍሪካ አገሮች የእኛም ገበሬዎች ወደ ከተሞች በብዛት ይፈልሳሉ፡፡ ከተማ ከገቡ በኋላ ግን መዳረሻቸው እንደ ምሥራቅ እስያዎቹ ገበሬዎች በዘመናዊ የማምረቻ ኢንዱስትሪዎች ውስጥ አልሆነም፡፡ የሚሰማሩት በሸቀጣ ሸቀጥ ችርቻሮ ሚዛን ቅሸባና በማከፋፈል ሥራዎች ውስጥ ነው፡፡ አለፍ ሲልም አነስተኛ አገልግሎትና ዝቅተኛ ተቀጣሪነት ላይ ነው፡፡ ከምጣኔ ሀብት ተፈጥሯዊ ሽግሽግ ባሻገር በግጭትና በክልሎች/ገጠሮች ዋስትና በማጣት ወደ ከተማ እየገባ ያለው ሥራ አጥ ደግሞ የባሰ ማኅበራዊ ቀውስ የሚያባብስ ነው፡፡
እስካሁን በታየው አካሄድ ሁሉም (እየተመረቁ የሚወጡት ጭምር) በስፋት ማምረቻ ፋብሪካዎች/ኢንዱስትሪ ሴክተር ውስጥ አይቀጠሩም፡፡ ወይም የመቀጠር ዕድል አያገኙም፡፡ ኢኮኖሚያዊ መዋቅራዊ ለውጥ ለማምጣት ደግሞ ከግብርናው ዘርፍ የሚፈልሰው የጉልበት ኃይል የማምረቻ ኢንዱስትሪዎችን የምርታማነት መጠን ለማሳደግ መዋል ነበር ያለበት፡፡
ከተማ የገቡት ገበሬዎች የሚሰማሩባቸው የችርቻሮና የማከፋፈል፣ የትራንስፖርት (በአብዛኛው ባጃጅ ሥራ)፣ የጉልበትና የመዋተት ሥራዎች ከግብርናው የተሻለ ጥቅም የሚያስገኙላቸው ቢሆኑ እንኳን ቴክኖሎጂያዊና የፈጠራ ዕድገት ባህሪ የሌላቸው በመሆናቸው፣ አገራችንን ከዓለም ወደኋላ ከሚያስቀሩት በቀር መዋቅራዊ ለውጥ የሚያስገኙላት አይደሉም፡፡
በእርግጥ ግጭቱና ንትርኩ ቢቀርልንም በፍጥነት በማደግ ላይ ያሉ የአፍሪካ አገሮች ያለባቸው ተግዳሮትም በቀላሉ እንደማይለቀን መረዳት ተገቢ ነው፡፡ ይኼውም ዕምቅ ሀብትን ወደ እውነታ ለመቀየርና ምርታማነትን ለማሳደግ እንደ ውስጣዊ ሞተር የሚያገለግሉ ዘመናዊና ቴክኖሎጂ ነክ የሆኑ ኢንዱስትሪዎች እጥረት ነው፡፡ እናም መንግሥት፣ ምሁራንና ባለሀብቶች ሁሉ የትኩረት ቅኝታቸውን ፈጥነው ማስተካከል፣ ቢያንስ ሞዴል ሥራዎችን መጀመር ይኖርባቸዋል፡፡ የሥራ ዕድል ዕጦትና ድህነት የመጪው የቀውስ መንስዔ እንዳይሆኑ መጠንቀቅም ይገባል፡፡
የቅርብ መረጃዎች እንደሚያሳዩት ከሰሃራ በታች ያሉ አገሮች ሕዝብ ግማሽ ያህሉ ከ26 ዓመት ዕድሜ በታች ነው፡፡ በዓለም ባንክ ዘገባ መሠረት በየዓመቱ ሰባት ሚሊዮን ያህል ሕዝብ ከ15 ዓመት በላይ እየሆነ ይሄዳል፡፡ ከልጅነት ጊዜ ወደ አካለ መጠን ይሸጋገራል ማለት ነው፡፡ አሁን ባለው ዘገምተኛ አዎንታዊ መዋቅራዊ ትራንስፎርሜሽን ዕርምጃ ከቀጠለ፣ በሚቀጥሉት አሥር ዓመታት መደበኛ ቅጥር አግኝቶ ደመወዝ ተከፋይ ሠራተኛ የሚሆነው የአፍሪካ ወጣት ከአራት ሰዎች አንዱ ብቻ ነው፡፡
ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ በዘመናዊ ኢንዱስትሪዎች ውስጥ የሚገቡት በጣም ጥቂቶች ናቸው፡፡ ስለዚህ የአፍሪካ መሪዎች ‹‹እዬዬም ሲደላ ነው›› እንዲሉ፣ በትንሽ በትልቁ እየተባሉ ሰብዓዊና ቁሳዊ ሀብትን ከማውደም ወጥተው፣ በመነጋገር ለሰላምና ለልማት ትኩረት ከመስጠት ባሻገር የኢኮኖሚያዊ መዋቅራዊ ለውጥን (Economical Structural Transformation) የዕድገት ፍጥነት መጨመር ይኖርባቸዋል ነው እየተባለ ያለው፡፡ ለእኛ አገር ይህንኑ መመኘትና ዕውን እንዲሆንልን ከመትጋት ውጪ አማራጭ የለንም፡፡
በእርግጥ ከብዙ የአፍሪካ አገሮች አንፃር ሲታይ መቀጠል አልተቻለም እንጂ፣ የእኛ አገር ኢኮኖሚያዊ መዋቅራዊ ለውጥ የተሻለ ጅምር አሳይቶ ነበር፡፡ ‹‹ኢኮኖሚያዊ መዋቅራዊ ለውጥ›› የሚባለው ጽንሰ ሐሳብ የያዛቸውን አራት ዋና ዋና ጉዳዮች መሠረት አድርገን ማየት እንችላለን፡፡ የኢኮኖሚያዊ መዋቅራዊ ለውጥ የሚባለው በዋነኛነት ግብርና በኢኮኖሚ ምርታማነቱም ሆነ በሰው ኃይል አሳታፊነቱ (ሥምሪቱ) ያለው ዓመታዊ ድርሻ እንዲቀንስ ማድረግ ነው፡፡ የአገሪቱ ኢኮኖሚ ግብርና መር ከመሆን እንዲላቀቅ ማስቻል ማለት ነው፡፡
ሁለተኛው ዓብይ የመዋቅራዊ ለውጥ ጉዳይ በኢንዱስትሪ ረገድ ያሉት የከተማ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎችና ዘመናዊ አገልግሎቶች ዓመታዊ ድርሻ እንዲጨምር ማድረግ ነው፡፡ በሒደትም ግብርና ይዞት የነበረውን የመሪነት ሚና ለኢንዱስትሪው እንዲያስረክብ ማስቻል ነው፡፡ የግብርናው አቅም መዋቅራዊ ለውጡን ለመሸከም እስከቻለ ድረስ ብቻ ይቆይና ቦታውን፣ ዓመታዊ ድርሻውንና የሰው ኃይሉን ለኢንዱስትሪው እንዲያስረክብ ማድረግ ነው፡፡
ሦስተኛው የመዋቅራዊ ለውጥ ጽንሰ ሐሳብ ይዘት በገጠር ያለው የሥራ ኃይል ወደ ከተሞች እንዲመጣና በማኑፋክቸሪንግና በዘመናዊ ኢንዱስትሪዎች ውስጥ እንዲሳተፍ ማድረግ ነው፡፡ በዚያን ጊዜ ጉልበት ጠያቂ (Labour Intensive) ከሆነው ግብርና ወደ ኢንዱስትሪው የሚመጣው ኃይል መብዛት አለበት (በእኛ አገር ያለው ፈተና ግን ብሔር ተኮር በሆነው አከላለልና የጥላቻ ፖለቲካ ምክንያት ዜጎች በነፃነት የትም ተንቀሳቅሰው መሥራት አለመቻላቸው መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል)፡፡
አራተኛው ይዘት የሕዝብ ቁጥር ዕድገት በልደትና በሞት መካከል ያለው ምጣኔ ሽግግር ማድረግ ነው፡፡ ከሚሞተው ሕፃን የሚወለደው በዝቶ የሞትና የልደት መጠኑ እኩል ከመሆኑ (Equilibrium) ከመድረሱ በፊት፣ ለመዋቅራዊ ለውጡ ሽግግር የሚበጅ የሰው ኃይል ዕድገት እንዲኖር ማድረግ ነው፡፡ በአጭሩ በጨቅላነት የሚሞቱትን የሕፃናት ቁጥር መቀነስና የሚወለዱት ልጆች ቁጥር በዝቶ የሕዝብ ዕድገትና ትውልድ እንዲቀጥል የማድረግ ሥራ ነው፡፡
በአጠቃላይ አገራችንን በአንድ ዕይታ ብቻ ተመልክቶ መግለጽ በመግቢያው እንዳነሳሁት ወደ ስህተት ያመራል፡፡ ከታሪክና ካለንበት ሁኔታ አልፎ ነገን አመላክቶ ሥጋትና ተስፋዋን መመርመሩ ነው የሚጠቅመው፡፡ እየተባባሰ ያለው ግጭትና ውዝግብ መፍትሔ ካላገኘ ግን ተስፋውን ሁሉ የሚያጠወልግ፣ ቡቃያውን የሚያደርቅ፣ የአገር ህልውናንም ለአደጋ የሚያጋልጥ ስለሆነ ስለመፍትሔው መጨነቅ የሁሉም ግዴታ ሊሆን ይገባል፣ ፈጣሪም ይርዳን፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡