መንግሥት የዋጋ ንረቱን ከ30 በመቶ ወደ 16 በመቶ ዝቅ ማድረጉን በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አማካይነት በቅርቡ ማስታወቁ ይታወሳል፡፡ ገበያው ውስጥ ያለው የምርቶችና አገልግሎቶች ዋጋ የሚያሳየው ተቃራኒውን ነው፡፡ የምግብና ምግብ ነክ፣ የተለያዩ ሸቀጦች፣ የትራንስፖርት፣ የኤሌክትሪክ፣ የውኃ፣ የቴሌኮምና ሌሎች ዋጋ በየጊዜው ጭማሪ እያሳየ ነው፡፡ በበርካታ መንግሥታዊ አገልግሎቶች ላይ የሚስተዋለው ጭማሪም ይታወቃል፡፡ እነዚህና መሰል ምርቶችና አገልግሎቶች ዋጋቸው እያሻቀበ እያለ፣ እያሰለሰ የሚደረገው የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እየሆነ ነው፡፡ ታኅሳስ 29 ቀን 2017 ዓ.ም. በነዳጅ ላይ የተደረገው የዋጋ ጭማሪ የዜጎችን ኑሮ ከድጡ ወደ ማጡ እንደሚያደርገው ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ በቤንዚን፣ በናፍጣና በአውሮፕላን ነዳጅ ላይ የተደረገው ጭማሪ የዋጋ ንረቱን የበለጠ የሚያባብስ እንጂ፣ መንግሥት እንዳለው የኑሮ ውድነቱን የሚያረግብ አይደለም፡፡ የነዳጅ ዋጋ ጭማሪውን ተከትሎ በሌሎች ምርቶችና አገልግሎቶች የሚከሰቱ ጭማሪዎች ከወዲሁ ብዙዎችን ሥጋት ውስጥ ከተዋል፡፡
በአሁኑ ጊዜ ለዋጋ ንረትም ሆነ ለዜጎች ኑሮ ተግዳሮት ከሆኑ ችግሮች መካከል በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሰው የሰላም ዕጦት ነው፡፡ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ከሚካሄዱ ግጭቶች በተጨማሪ እንደ ዕገታና ዘረፋ የመሳሰሉ አደገኛ ድርጊቶች፣ ኢኮኖሚው በሚፈለገው መጠን እንዳይንቀሳቀስ እግር ተወርች አስረውታል፡፡ ትርፍ አምራች የነበሩ አካባቢዎች ራሳቸው የምግብ እጥረት ተጠቂ ሲሆኑ፣ ከታረሰባቸው አካባቢዎች ምርት በአግባቡ ወደ ገበያ መውጣት ሲያቅተው፣ ፋብሪካዎች ወትሮም በጣም ዝቅተኛ ከነበረው አቅማቸው ወርደው ማምረት ሲሳናቸው፣ የውጭ ምርቶችን በአገር ውስጥ ለመተካት የሚደረገው ጥረት በበርካታ መሰናክሎች ሲከበብ፣ በአጠቃላይ ምርትና ምርታማነት እያሽቆለቆለ ኢኮኖሚው ችግሩ ሲባባስ ነው የሚታየው፡፡ በዚህ ዓይነቱ ግራ የተጋባ ሁኔታ መቀጠል ስለማይቻል ለሰላም መስፈን ሲባል ተገቢ የፖሊሲ ውሳኔ ያስፈልጋል፡፡ ሰላም የሁሉም ነገር መሠረት ስለሆነ ተገቢው ዋጋ ይከፈል፡፡
መንግሥት የራሱን ገቢ በከፍተኛ መጠን ለመጨመር የተለያዩ ዕርምጃዎችን ሲወስድ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ዜጎች ከአነስተኛና ጥቃቅን ጀምሮ እስከ ከፍተኛው አምራችነት ድረስ ተሰማርተው እንዲሠሩ መሰናክሎችን ያስወግድ፡፡ የመንግሥት ገቢ ማደግ የሚችለው የመሥራት አቅም ያላቸው ዜጎች መብታቸው ተከብሮ ግዴታቸውን በኃላፊነት ስሜት ሲወጡ ነው፡፡ ሁሉም መንግሥታዊ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት በሠለጠነና ሥነ ምግባር ያለው የሰው ኃይል፣ በዘመናዊ አደረጃጀት፣ ዘመን አፈራሽ በሆኑ ቴክኖሎጂዎችና ዘመኑን በሚመጥኑ ዕሳቤዎች በሕግ የተሰጣቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ግብር ለመክፈል፣ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ለማግኘት፣ ለማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎቶች ተደራሽ ለመሆንና ለመሳሰሉት ተገልጋዮች መሰቃየት የለባቸውም፡፡ እነዚህና ሌሎች ተደራራቢ ችግሮች ምርታማነትን በማዳከም የራሳቸውን ሚና እየተጫወቱ ነው፡፡ ድምር ውጤታቸውም የኑሮ ውድነት በማባባስ የዜጎችን ሕይወት ያመሰቃቅላል፡፡
በተለያዩ ምክንያቶች በሚፈጠሩ እጥረቶች ሳቢያ የምርቶች አቅርቦት ሰንሰለት እየታነቀ፣ የግብይት ሥርዓቱ ለሰው ሠራሽ የዋጋ ንረት መጋለጥ ከጀመረ በጣም ቆይቷል፡፡ ኋላቀሩ የግብይት ሥርዓት በሚገባ በተደራጁ ኃይሎች ቁጥጥር ሥር ሆኖ በአደገኛ ደላሎች አስተናባሪነት ሕገወጥ ዋጋ ይወሰንበታል፡፡ ይህንን ድርጊት መቆጣጠር ያለባቸው የሚመለከታቸው መንግሥታዊ ተቌማት ያላቸው አቅም ደካማ በመሆኑ፣ እንዲሁም የግብይት ሥርዓቱን ከላይ እስከ ታች አንቀው የያዙ ኃይሎች ከበስተጀርባቸው በሙስና የተበከሉ ባለሥልጣናትን ተገን በማድረጋቸውና የሌብነት ሥልቱ የረቀቀ በመሆኑ ሸማቹ ሕዝብ ለሰው ሠራሽ የዋጋ ጭማሪ ተጋልጦ የሚታደገው ማግኘት አልቻለም፡፡ እነዚህ ሁሉ ጫናዎች ተበራክተው ጭምር ነው በላይ በላዩ ጭማሪዎች እየተደረጉ የሕዝቡ ኑሮ አዘቅት ውስጥ እየገባ ያለው፡፡ በዚህም ምክንያት መካከለኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ይገኙ የነበሩ ወደ ድህነት፣ ድህነት ውስጥ የነበሩ ደግሞ ወደ ከፋ ድህነት ተሸጋግረዋል፡፡
በቅርቡ ከሪፖርተር ጋር ቆይታ የነበረው የኦሊምፒክ ጀግናውና የዓለም ሻምፒዮኑ ሻለቃ ኃይሌ ገብረ ሥላሴ፣ ‹‹እየተፋርን ስለሆነ ነው እንጂ ሁላችንም ኑሮን መቋቋም አቅቶናል›› ያለው እንደ ዋዛ የሚታይ አይደለም፡፡ በአሁኑ ጊዜ 130 ሚሊዮን ይሆናል ተብሎ ከሚታሰበው የኢትዮጵያ ሕዝብ ውስጥ፣ በከፍተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙት በጣም ሳይጋነን ከአንድ በመቶ አይበልጡም፡፡ በመካከለኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ ተብለው የሚታሰቡት ቁጥራቸው እጅግ በጣም ትንሽ ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ ከኢትዮጵያ አጠቃላይ ሕዝብ ውስጥ በጣም ትልቁን ቁጥር የሚይዙት ከድህነት ወለል በታች የሚኖሩት ናቸው፡፡ ለምክንያታዊም ሆነ ለሰው ሠራሽ የዋጋ ጭማሪ የሚጋለጡትም በጣም በከፋ ድህነት ውስጥ የሚኖሩ ሁሉም ኢትዮጵያውያን ናቸው ማለት ይቻላል፡፡ በመንግሥት በስፋት እየተነገረለት ያለው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ የዜጎችን ኑሮ ካላሻሻለ ፋይዳው ምንድነው መባል አለበት፡፡
በሌላ በኩል መንግሥት ቀስ በቀስ የነዳጅ ድጎማውን ሲያስቀር በተለይ በዝቀተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ያሉ ዜጎች ጉዳይ ሊያሳስበው ይገባል፡፡ የነዳጅ ዋጋ ሲጨምር የሁሉም ምርቶች ዋጋ በተነፃፃሪ እንደሚጨምር የታወቀ ነው፡፡ ነዳጅ ስትራቴጂካዊ ምርት ስለሆነ በከፍተኛ ጥንቃቄ ሊመራ ይገባል፡፡ የኢትዮጵያ የነዳጅ ዋጋ ከሌሎች አገሮች ጋር ሲነፃፀርም የሕዝቡ ገቢና የመግዛት አቅም አብሮ መታየት ይኖርበታል፡፡ በኢትዮጵያ በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ከውጭ ተገዝቶ የሚገባ ነዳጅ ሥርጭቱና አጠቃቀሙ ጥብቅ ቁጥጥር ሊደረግበት የሚገባ ሲሆን፣ እጃቸውን አስረዝመው ያስገቡ ሕገወጥ ተዋንያንና ድጋፍ ሰጪ ሙሰኛ የመንግሥት ሹማምንትም ጉዳይ አብሮ መታየት አለበት፡፡ ከዚህ ውጪ የፖለቲካ እንካ ሰላንቲያውን በመተው፣ የሕዝቡን ኑሮ እያናጉ ያሉ ችግሮች ላይ ትኩረት ተደርጎ አዋጭ መፍትሔ ይፈለግ፡፡ የኑሮ ውድነቱን እያባባሱ ያሉ ዕርምጃዎች ፋታ ስለማይሰጡም ይታሰብባቸው!