- ከ330 በላይ ሕፃናት በምግብ እጥረት ሞተዋል ተብሏል
በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት ውስጥ ከወሊድ ጋር በተያያዘ 620 እናቶች መሞታቸውን፣ የኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ለፓርላማ አስታወቀ፡፡
ተቋሙ ይህንን ያስታወቀው የ2017 ዓ.ም. የግማሽ ዓመት የሥራ ክንውን ሪፖርቱን ጥር 28 ቀን 2017 ዓ.ም. ለጤና፣ ማኅበራዊ ልማት፣ ባህልና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሲያቀርብ ነው፡፡
የጤና ሚኒስትር ደኤታ ደረጀ ድጉማ (ዶ/ር) በኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ላለፉት ስድስት ወራት በእናቶችና ሕፃናት ላይ የተደረገ ክትትል፣ ወባን ጨምሮ ሌሎች ተላላፊና ተላላፊ ባልሆኑ ወረርሽኞች ላይ የተደረገውን ቁጥጥርና ክትትል ለቋሚ ኮሚቴው አቅርበዋል፡፡
በቀረበው ሪፖርት 620 እናቶች ከወሊድ ጋር በተያያዘ ሕይወታቸው ማለፉ የተገለጸ ሲሆን፣ ነገር ግን የሞታቸው ምክንያት በዝርዝር አልተብራራም፡፡ ይህም በቋሚ ኮሚቴው ጥያቄ በማስነሳት የሪፖርቱን ተዓማኒነት አጠራጣሪ እንደሚያደርገው ተመላክቷል፡፡
አቶ ተስፋሁን ቦጋለ የተባሉ የቋሚ ኮሚቴው አባል ከቀረበው ሪፖርት በመነሳት ጥያቄዎችን ያቀረቡ ሲሆን፣ ከወሊድ ጋር በተያያዘ ሕይወታቸውን ያጡ እናቶች የሞት ምክንያት ለምን በዝርዝር ማቅረብ እንዳልተቻለ ጠይቀዋል፡፡
በሌላ በኩል ባለፉት ስድስት ወራት በአገር ደረጃ ከፍተኛ የምግብ እጥረት መከሰቱ በሪፖርቱ የተመለከተ ሲሆን፣ በዚህም ምክንያት 352 ሕፃናት ሲሞቱ 232‚389 ሕፃናት ደግሞ ለሕመም መዳረጋቸው ተገልጿል፡፡
በግምገማው በስፋት ከተነሱ ጉዳዮች መካከል የወባ ሥርጭትን በተመለከተ በስፋት የቀረበው ነው፡፡ የወባ ወረርሽኝ ከ2016 ዓ.ም. ተመሳሳይ ዕቅድ አፈጻጸም ጋር ሲነፃፀር፣ በሁለት እጥፍ በመጨመሩ ለበርካታ ዜጎች ሕመምና ሞት ምክንያት ነው ተብሏል፡፡
እ.ኤ.አ. እስከ 2030 የወባ በሽታን ከኢትዮጵያ ለማጥፋት ሥራ መጀመሩን የተናገሩት ደረጀ (ዶ/ር)፣ ይሁን እንጂ ከ2013 ዓ.ም. ጀምሮ ባሉት ተከታታይ ዓመታት የወባ በሽታ ባልተጠበቀ ሁኔታ እየጨመረ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
የኮቪድ-19 መከሰት፣ የአየር ንብረት ለውጥ፣ የተለያዩ ሰው ሠራሽና ተፈጥሮአዊ ችግሮች ለወባ ወረርሽኝ መጨመር ምክንያቶች እንደሆኑ የተናገሩት ሚኒስትር ደኤታው፣ ለወባ መጨመር 50 በመቶ መንስዔው የአየር ንብረት ለውጥ ነው ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል ግጭቶች ባሉባቸው አካባቢዎች መድኃኒት ለማድረስ አስቸጋሪ መሆኑን፣ እንዲሁም ወባ ጠፍቷል የሚል የተሳሳተ ግንዛቤ በማኅበረሰቡና በአመራሩም ጭምር መፈጠሩ፣ የአልጋ አጎበር በትክክል አለመጠቀም፣ በበርካታ የጤና ኬላዎች በቂ አገልግሎት አለመኖርን ሚኒስትር ደኤታው ለወባ ወረርሽኝ ምክንያት ናቸው ሲሉ የዘረዘሯቸው ምክንያቶች ናቸው፡፡
ለበሽታው መጨመር የተለያዩ ምክንያቶችን የጠቀሱት ደረጀ (ዶ/ር)፣ ይሁን እንጂ የሞት ምጣኔው ዓምና ከነበረው ጋር ሲነፃፀር በእጅጉ መቀነሱን ተናግረዋል፡፡
ባለፉት ስድስት ወራት 13.9 ሚሊዮን የወባ ተጠርጣሪ ሕሙማን ምርመራ ማድረጋቸውን የተናገሩት ደረጀ (ዶ/ር)፣ ከእነዚህ ውስጥ 5.9 ሚሊዮን ሕሙማን ተለይተው ሕክምና ተሰጥ~ቸዋል ብለዋል፡፡
ነገር ግን ባለፉት ስድስት ወራት በወባ በሽታ ስንት ሰዎች ሕይወታቸውን እንዳጡ በሪፖርቱ አልተገለጸም፡፡
በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች ከፍተኛ የወባ ሥርጭት መኖሩን የተናገሩት ሚኒስትር ደኤታው፣ ግጭቶች ባሉባቸው ቦታዎች መድኃኒት ለማቅረብ መቸገራቸውን ጠቅሰው በዚህም የጤና ባለሙያዎች መስዋዕትነት እየከፈሉ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
ከወባ ጋር ተያይዞ ያጋጠሙ ችግሮችን በሪፖርታቸው ያቀረቡት ደረጀ (ዶ/ር)፣ ከበጀት እጥረት ጋር ተያይዞ ችግሮች እንዳሉ ተናግረዋል፡፡
በተለይ በቅርቡ በተቋቋሙ አዳዲስ ክልሎች ከፍተኛ የሆነ የበጀት እጥረት መኖሩን የተናገሩት ሚኒስትር ደኤታው፣ ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የበጀት እጥረት ስለሚያጋጥመው ለጤና ባለሙያዎች በወቅቱ ደመወዝ አለመክፈልና ጥቅማ ጥቅሞችን አለማስጠበቅ ለወባ ወረርሽኝ መጨመር እንደ አንድ መንስዔ ሊወሰድ እንደሚችል ተናግረዋል፡፡
የኮሌራ ወረርሽኝን በተመለከተ ሰፊ ሥራ መከናወኑን፣ እንዲሁም በ463 ወረዳዎች የኩፍኝ በሽታ እንዳለ ጠቅሰው በ443 ወረዳዎች መቆጣጠር መቻሉን አስረድተዋል፡፡
በግማሽ ዓመቱ 370 አምቡላንሶች በመግዛት በተለይ በግጭት ለተጎዱ አካባቢዎች መተላለፋቸውን የተናገሩት ደረጀ (ዶ/ር)፣ ከዚህ ባሻገር በ40 ሚሊዮን ብር ወጪ ጥገና መደረጉን አክለዋል፡፡
የመድኃኒትና የሕክምና መሣሪያዎች አቅርቦት ችግርን በተመለከተ በሪፖርታቸው ያቀረቡት ሚኒስትር ደኤታው፣ የመድኃኒት መግዣ ብድር መከልከልና ጤና ተቋማት በቂ የሆነ የመድኃኒት በጀት አለመኖርን እንደ ችግር ጠቅሰዋል፡፡
kሚ ኮሚቴው በተለያዩ ክልሎች ባደረጋቸው የመስክ ምልከታዎች የወባ ወረርሽኝ መከላከልና መቆጣጠር የሚያስችሉ የግብዓት አቅርቦቶች ኢፍትሐዊ ክፍፍል እንዳለባቸው ማየታቸውን፣ የቋሚ ኮሚቴው አባል አቶ ተስፋሁን ተናግረዋል፡፡
የተለመዱ የወባ መከላከያ መንገዶች እንዲዛቡ መደረጋቸውና በዚህም በአንዳንድ ቦታዎች ባልተለመደ ሁኔታ ወባ እንዲከሰት ምክንያት መሆናቸውን የጠቀሱት አቶ ተስፋሁን፣ ለምሳሌ በአዲስ አበባ ከ17 ሺሕ በላይ ሰዎችን በማጥቃት ከፍተኛ ሕመምና ሞት እያደረሰ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡
በሌላ በኩል ቋሚ ኮሚቴው በቅርቡ በደቡብ በኢትዮጵያ ክልልና በኦሮሚያ ክልል ቦረና ዞን አደረግኩት ባለው ምልከታ፣ የኤችአይቪ/ኤድስ የሥርጭት መጠን በእጅጉ መጨመሩን አስታውቋል፡፡