ተከታትለው የሚከንፉት መኪኖች የሚጓዙበት የአስፓልት መንገድ የላቸውም፡፡ ለጥ ባለው አሸዋማ ሜዳ ላይ ባሻቸው አቅጣጫ እየቀደዱ ይከንፉበታል፡፡ መኪኖቹ ባለፉ ቁጥር መንገዱ ሙሉ ለሙሉ ዕይታን በሚጋርድ አቧራ ይዋጣል፡፡ አካባቢውን የአቧራ ጋቢ ያለብሱታል፡፡ በመሆኑም ሊፈጠሩ የሚችሉ አደጋዎችን ለማስቀረት ይመስላል ከኋላ የሚከተሏቸው ተሽከርካሪዎች ፍጥነታቸውን በመቀነስ የመንገዱ ዕይታ እስኪጠራ ይጠባበቃሉ፡፡ ወይም የተሻለ አቅጣጫ ይዘው በረሃማውን የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ያቋርጣሉ፡፡
በአቧራ በተዋጠው መንገድ ጓዛቸውን በግመል የጫኑ የአካባቢው ተወላጆች፣ ወደ ሩቅ አቅጣጫ ሲጓዙ ይታያሉ፡፡ አልፎ አልፎም በአጥንታቸው የቀሩ ከብቶቻቸውን እየነዱ የሚያልፉም አሉ፡፡ በየመንገዱ ሞተው የወዳደቁ ከብቶችም ለቁጥር የበዙ ናቸው፡፡ በድናቸው ከአፈር የተቀላቀለ፣ ሥጋቸው ገና ያልፈረሰ በርካቶች ናቸው፡፡ እነዚህ በክልሉ በተፈጠረው ድርቅ እንደ ቅጠል ከረገፉት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ከብቶች መካከል የሚታዩት ናቸው፡፡ እንደ ጢስ ከሚጎነው አቧራ ውስጥ የሞቱትን ከብቶች በቅርብ ርቀት መመልከቱ የሚደብት ስሜት ይፈጥራል፡፡ ከአንድ የሆሊውድ ፊልም ላይ የተቀነጨበ ትዕይንት በዘመናዊ መንገድ በተቀናበረ ምስል እንደመመልከት ያለ እንጂ ክስተቱ በዕውን የሚታይ፣ እውነተኛ ትዕይንት፣ ያውም በዚህ ዘመን የተከሰተ፣ በረሃብ ጦስ የተፈጠረ የእንስሳት እልቂት አይመስልም፡፡
ከምድር ወገብ በዜሮና በ23 ዲግሪዎች መካከል የምትገኘው ኢትዮጵያ ሞቃት የአየር ንብረት ካላቸው አገሮች ተርታ ትመደበለች፡፡ ዓመታዊ የዝናብ መጠኗም በአማካይ ከ1,000 እስከ 2,200 ሚሊ ሜትር ይደርሳል፡፡ ለአየር ንብረት ለውጥ ተጋላጭነቷም በገሃድ የሚታይ ነው፡፡ ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተቆራኝተው ከሚከሰቱ ችግሮች መካከል የሙቀት መጠን መጨመር፣ የግግር በረዶ መቅለጥ፣ በተለይም በኢትዮጵያ ደግሞ የዝናብ እጥረት፣ በወቅቱ አለመዝነብ፣ በዚህም ሳቢያ የሚከሰት ድርቅ ከሚጠቀሱ የአየር ንብረት ለውጥ ጉዳቶች ውስጥ ጥቂቶቹ ናቸው፡፡
በተለያየ ጊዜ የተከሰቱ የድርቅ አደጋዎችም አገሪቱ በድህነትና በረሃብ እንድትታወቅ አድርገዋል፡፡ እያደረጉም ይገኛሉ፡፡ በታሪክ ከማይዘነጉ የረሃብ ወቅቶች መካከል፣ በንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ አፄ ምኒሊክ ዘመን የተከሰተውና ‹‹ክፉ ቀን›› የሚል መጠሪያ ያተረፈው ረሃብ፣ በ1960ዎቹ የተከሰተውና በንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ ላይ ሕዝብ እንዲቆጣ ያስገደደው የወሎ ድርቅ፣ በ1977 ዓ.ም. ሚሊዮኖችን ለዕልቂት የዳረገው የደርግ ዘመን ድርቅ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
ለ50 ዓመታት ታይቶ የማይታወቀውና ከአሥር ሚሊዮን በላይ ዜጎችን ለአስቸኳይ ጊዜ የምግብ ዕርዳታ የዳረገው የአምናው ድርቅም የሚጠቀስ ነው፡፡ በሰዎች ላይ የሞት አደጋ ባያስከትልም፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ከብቶችና ሌሎች የቤት እንስሳት እንዲያልቁ አድርጓል፡፡ የዱር እንስሳትም የድርቁ ሰለባ መሆናቸው እርግጥ ነው፡፡ ዘንድሮም በተከሰተው ድርቅ ከ8.5 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ለምግብ ዕርዳታ መዳረጋቸው ተረጋግጧል፡፡
በአሁኑ ወቅት በሶማሌ ክልል ብቻ ከአምስት ሚሊዮን በላይ ተረጂዎች ለዕለት ደራሽ ዕርዳታ ተዳርገዋል፡፡ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ከብቶች፣ ፍየሎችና በጎች እንዲያልቁም ምክንያት ሆኗል፡፡ በሁለቱ የድርቅ ወቅቶች ከሌላው ጊዜ በተለየ ‹‹አንድም ሰው በረሃብ አልሞተም፤›› ተብሎ እየተገለጸ ነው፡፡ በድርቁ ሳቢያ ግጦሽና ውኃ እያጡ እንደቅጠል የሚረግፉትን ከብቶች መታደግ አሳሳቢ ከመሆን አልፏል፡፡
በአገሪቱ 82 በመቶ የሚሆነው አርብቶ አደር በአፋርና በሶማሌ ክልሎች እንደሚገኝ፣ ከዚህም ውስጥ 53 በመቶው የሚሆነው በሶማሌ ክልል እንደሚኖር በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የቴክኖሎጂ ሥርፀትና ኮሜርሻላይዜሽን ዳይሬክተር አቶ ደረሰ ተሾመ ይናገራሉ፡፡ ከክልሉ ነዋሪዎች የአብዛኛዎቹ ህልውና መሠረት አርብቶ አደርነት ነው፡፡ ይሁንና እንስሳቱ ዘመናዊ የከብት እርባታ ዘዴን ከሚከተል ርቢ ይልቅ በተፈጥሮ ላይ ብቻ በተመሠረተ ዘዴ የሚተዳደሩ በመሆናቸው፣ ከእንስሳቱ ተገቢውን ጥቅም ለማግኘት እንዳላስቻለ አቶ ደረሰ ይናገራሉ፡፡
ለዚህም የሚጠቀሰው ዋናው ችግር የመኖ እጥረት ነው፡፡ በመኖ ማልማትና አቅርቦት ዙሪያ ከፍተኛ ችግር በመኖሩ ምክንያት በተለይም በድርቅ ወቅት ከፍተኛ የእንስሳት ዕልቂት እንዲከሰት ሰበብ ሆኖ እንደሚገኝ አቶ ደረሰ ይናገራሉ፡፡ ‹‹እዚህ ያሉ እንስሳት ተፈጥሮ በለገሰችው ግጦሽ ላይ በተመሠረተ የርቢ ሥርዓት የቆዩ ናቸው፡፡ ለዚህም ነው ድርቅ በመጣ ቁጥር ከፍተኛ ዕልቂት የሚከሰተው፤›› ያሉት አቶ ደረሰ፣ ለዚህ ምላሽ መስጠት የሚችሉ የምርምር ሥራዎች ትግበራ መጀመሩን ይናገራሉ፡፡
ከ20 ዓመታት በፊት በወረር፣ በቢሾፍቱ፣ በመልካሳና በሆለታ የግብርና ምርምር ተቋማት የአገሪቱን ቆላማ አካባቢዎች ታሳቢ ያደረጉ ቴክኖሎጂዎች መበልጸጋቸው ይጠቀሳል፡፡ እነዚህን ቴክኖሎጂዎች የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ማዕከል ከአፋር ክልል የምርምር ማዕከል ጋር በመተባበር ወደ ማኅበረሰቡ ለማድረስ ደፋ ቀና ማለት ከጀመሩ ሰነባብተዋል፡፡
በምርምር ከዳበሩት መካከል ዘጠኝ የመኖ ዓይነቶችን በመምረጥ በክልሉ ለሚገኙ እንስሳት ማቅረብ ተጀምሯል፡፡ እነዚህ የመኖ ዓይነቶች ሮደስ፣ ፓኒከም፣ ሲንክረስ የተባሉ የሳር መኖዎች፣ የሌጊዎም ዝርያዎች ይገኙበታል፡፡ የፕሮቲን ምንጭ በመሆን ለእንስሳቱ ዕድገት ሚናቸውን የሚጫወቱ አልፋ አልፋ፣ ዴስሞዲየስ፣ ዴሊቾ ሰለብለም የተባሉትም ይጠቀሳሉ፡፡ ለግመሎች የሚውሉ የዛፍ ዝርያ የሆኑ እንደ ሰስባኒያ፣ ሉሲኒያ የተሰኙ የመኖ ዓይነቶችም በክልሉ ለሙከራ እየዋሉ ይገኛሉ፡፡
እነዚህ የመኖ ዝርያዎች በተወሰነ ቦታ ተዘርተው በአጭር ጊዜ ውስጥ ከፍተኛ ምርት ማስገኘት እንደሚችሉ በተግባር ማረጋገጣቸውን ባለሙያዎቹ ይናገራሉ፡፡ ይህንን በማስመልከትም ሪፖርተርን ጨምሮ ሌሎች የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች በአፋር ክልል፣ ምዕራብ ጎዴ ተገኝተው እንዲጎበኙ ተደርጓል፡፡
በ250 ሔክታር መሬት ላይ የለሙት የእንስሳት መኖዎችና ጥራ ጥሬዎች በከፍተኛ ድርቅ በተመታው የክልሉ መሬት ላይ የበቀሉ አይመስሉም፡፡ ልምላሜያቸው ወቅቱን ጠብቆ የሚመጣ፣ በቂ የዝናብ መጠን በሚያገኝ አካባቢ የለሙ እንጂ፣ በበረሃማው የሶማሌ ክልል የበቀሉ አይመስሉም፡፡ ‹‹ማምረት ብቻ በቂ አይደለም፡፡ ዓመቱን ሙሉ ማምረት ስለማይቻል፣ አምርቶ ማከማቸትም ያስፈልጋል፡፡ በስፋት አምርቶ ለማከማቸት ደግሞ ብዙም የሚከብድ አይደለም፡፡ እነዚህ መኖዎች አንዴ ከተላመዱ በኋላ በየወሩ የሚታጨዱበት ሰፊ ዕድል አለ፤›› የሚሉት አቶ ደረሰ፣ በማሳው የለሙት መኖዎች በሦስት ወራትና ከዚያም ባነሰ ጊዜ እንደሚደርሱ አብራርተዋል፡፡
ከውጤት አኳያም በተፈጥሮ ከሚገኘው ግጦሽ ጋር ሲወዳደረሩ ከፍተኛ ልዩነት እንዳላቸው ይገለጻል፡፡ በተፈጥሮ ግጦሽ በሔክታር ከሁለት ቶን በላይ መኖ ማግኘት አይቻልም፡፡ ይሁንና በምርምር ከተገኙት የመኖ ዝርያዎች በሔክታር እስከ 65 ቶን መኖ ማግኘት እንደሚቻል ባለሙያዎቹ ይገልጻሉ፡፡ እንዲህ ባለ ከፍተኛ ልዩነት የሚገኘውን ውጤት ወደ ኅብረተሰቡ ማድረስ ዋናው ግዳጅ ነው፡፡
ይህንን ለማድረግም የማላማድ ሥራዎችን ማከናወን፣ በሰፋፊ ማሳዎች ሠርቶ ማሳያ ማካሄድና የዘር ብዜት ሥርዓቱን ማጠናከር የሚጠበቁ አስፈላጊ ሥራዎች ናቸው፡፡ እንደ አልፋ አልፋ ያሉ ከፍተኛ ጥቅም የሚያስገኙ የመኖ ዝርያዎችን የዘር አቅርቦት ለማስፋፋት ከፍተኛ ሥራ እንደሚጠይቃቸው የግብርና ባለሙያዎቹ ያውቃሉ፡፡ በእንስሳት የዕድገት ዑደት ከሌሎቹ መኖዎች የተሻለ ውጤት የሚያስገኘው የአልፋ አልፋ መኖ የዘር ሥርጭት ግን በጣም ደካማ መሆኑ አሳሳቢ ነው፡፡
እንደ አቶ ደረሰ ገለጻ፣ የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት በዚህ ተሳትፎ ለሚያደርጉ የተወሰኑ ባለሀብቶች መነሻ የዘር ቴክኖሎጂ በመስጠት አባዝተው እንዲያቀርቡ ይፈልጋል፤ ያደርጋል፡፡ ነገር ግን ለማቅረብ አቅሙና ፍላጎቱ ያላቸው በጣም አነስተኛ መሆናቸው ላይ ነው ችግሩ፡፡ ‹‹አልፋ አልፋ የእንስሳት ኢንዱስትሪውን ለማዘመን የሚረዳ ትልቅ ግብዓት ነው፤›› የሚሉት አቶ ደረሰ፣ እርግጥ ዋጋው በጣም ውድ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ የአልፋ አልፋ ዘር ባለፉት አሥር ዓመታት ውስጥ በኪሎ ከ400 ብር ተነስቶ 900 ብር መግባቱን በዋቢነት ይጠቅሳሉ፡፡ አንድ ሔክታር ለማልማትም አምስት ኪሎ ግራም ዘር እንደሚያስፈልግ አክለዋል፡፡
ይህ በመሆኑም ከአርብቶ አደሩ የመግዛት አቅም ጋር ሲነፃፀር ትልቅ የተደራሽነት ችግር እንደሚፈጥር መገመቱ ከባድ ባይሆንም፣ አልፋ አልፋ የመሰሉትን የመኖ ዝርያዎችን በስፋት አምርቶ ለአርሶ አደሩ ማቅረብ ግን የግድ እንደሆነ ባለሙያዎቹ ይገልጻሉ፡፡ በምዕራብ ጎዴ በ250 ሔክታር መሬት ላይ የለማው የመኖ እርሻም ይህንን ችግር ለመፍታት ያለመ ነው፡፡ ሌሎችም በዚህ ዓመት የተለቀቁ የመኖ ዝርያዎች ለችግሩ መፍትሔ ይሆኑ ዘንድ ተስፋ ይጣልባቸዋል፡፡ በቅርብ ጊዜ ከስፔን የመጣ የመኖ ዝርያም በምርምር ተቋሟቱ የማላመድ ሥራ እየተካሄደበት ይገኛል፡፡
አገሪቱ መኖ ማልማት የምትችልበትን አቅም እንደገነባች አቶ ደረሰ ጠቅሰዋል፡፡ ችግሩ በስፋት በሚታይበት በሶማሌ ክልል 27,000 ሔክታር መሬት ማልማት የሚችል የመስኖ መሠረተ ልማት ዝርጋታ ሥራ ተሠርቷል፡፡ ፋፋና ጀራር የሚባሉና በክልሉ የሚገኙ ወንዞችን መነሻ ያደረጉ አራት የመስኖ ግድቦች ተሠርተዋል፡፡ ግድቦቹ ተጨማሪ 25,000 ሔክታር መሬት የማልማት አቅም አላቸው፡፡ ይሁንና የዘር ብዜቱ ላይ የቤት ሥራው ካልተሠራ ትርጉም እንደማይኖረውም ከወዲሁ ታምኖበታል፡፡ ይህንን ኃላፊነት በመቀበል የተቋቋመ የሶማሌ ክልል ምርጥ ዘር ኢንተርፕራይዝ የሚባል ድርጅትም አለ፡፡
ድርጅቱ ከተቋቋመ ብዙ ጊዜ ቢሆንም እስካሁን ግን ወደ ሥራ መግባት አለመቻሉ ታውቋል፡፡ ‹‹የሶማሌ ክልል ምርጥ ዘር ኢንተርፕራይዝ ወደ ሥራ መግባት ያለበት፣ የመኖ ዘር በማባዛት ነው፡፡ ለክልሉም ለአገርም የሚኖረው ፋይዳ የጎላ ነው፡፡ በምርምር የመጡ ቴክኖሎጂዎችም መነሻ ዘር ይሆኑታል፤›› በማለት ድርጅቱ ኃላፊነቱን መወጣት ቢችል፣ በአርብቶ አደሩ ዘንድ በመኖ ዙሪያ ለሚታዩ ችግሮች ምላሽ መስጠት እንደሚቻል አቶ ደረሰ ይናገራሉ፡፡
በሶማሌ ክልል ግብርና ምርምር ሥር የሰብል ዳይሬክተርና በጎዴ የግብርና ምርምር ማዕከል ሥራ አስኪያጅ አቶ አብዲ ከድር በበኩላቸው፣ ‹‹በክልሉ በተከሰተው ድርቅ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ እንስሳት እየሞቱ ነው፡፡ ስለዚህም የመኖ ችግርን መቅረፍ አንደኛው ስትራቴጂ ነው፤›› ብለዋል፡፡ ከዚህ ቀደም በክልሉ የሚገኘው የግብርና ምርምር ማዕከል ችግሩን ለመፍታት የተለያዩ ጥረቶች ቢያደርግም፣ ከሙከራ ባለፈ በስፋት መሥራት አለመቻሉን ጠቅሰዋል፡፡
የዘር ማባዣ ኢንዱስትሪው የተቋቋመ ሰሞን የተወሰኑ ሥራዎችን መሥራት ቢችልም፣ በጉዞው ሒደት ግን መዳከሙን ይናገራሉ፡፡ ‹‹ክልሉ በሁለት ወቅቶች ነው ዝናብ የሚያገኘው፡፡ አንደኛውና ትልቁ የዝናብ ወቅት ዝናብ ሳይጥል አልፎናል፡፡ መጠነኛ ዝናብ ብቻ ነው ያገኘነው፡፡ በዚህ የዝናብ ወቅት በመጠኑም ቢሆን ሳር በመብቀሉ ከብቶች እሱን እየጋጡ ከርመዋል፤›› ብለዋል፡፡ ከብቶቹ ከዚህ በኋላ እስከ ጥቅምት ባለው ጊዜ ድረስ ዝናብ አያገኙም፡፡
በዚህ መሀል ተጨማሪ ከብቶች እንዳይሞቱ በማሳ የለሙት የመኖ ዝርያዎች የህልውናቸው ዋስትና ሊሆኗቸው እንደሚችሉ ይገመታል፡፡ ነገር ግን በጉዳዩ የሚሳተፉ ባለድርሻዎች ኃላፊነታቸውን መወጣት ካልቻሉ፣ ትርጉም ያለው ለውጥ ማምጣትም መሥራትም እንደማይቻል ኃላፊዎቹ የሚናገሩት ነው፡፡