Tuesday, May 28, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

​ሁለት ሥራ ተቋራጮች ከ750 ሚሊዮን ብር በላይ የሚወጣበት መንገድ ለመገንባት ተፈራረሙ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የአዲስ አበባ ከተማ መንገደች ባለሥልጣን ለአዲሱ በጀት ዓመት የመጀመሪያ የሆነውን መንገድ ከ750 ሚሊዮን ብር በላይ ለማስገንባት፣ ከሁለት የአገር ውስጥ ሥራ ተቋራጮች ጋር የግንባታ ውል ተፈራረመ፡፡

ማክሰኞ ነሐሴ 23 ቀን 2009 .. የግንባታ ውል የተፈረመለት የመንገድ ፕሮጀክት በሁለት ቦታ ተከፍሎ የሚገነባ ነው፡፡ የመጀመሪያው ከቦሌ ቡልቡላ የግብዓት ማምረቻ መግቢያ ወረዳ 12 መስቀለኛ መንገድ፣ ቡልቡላ 40/60 ኮንዶሚኒየም ድረስ 3.8 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን መሆኑ ተገልጿል፡፡ ለዚህ መንገድ አሸናፊ ሆኖ ግንባታውን ለማካሄድ የተዋዋለው ፉል ጄኔራል ኮንትራክተር የተባለ አገር በቀል ኩባንያ ነው፡፡ ይህንን መንገድ ለመገንባት በጨረታ አሸናፊ የሆነበት ዋጋ 381.8 ሚሊዮን ብር እንደሆነ የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን ገልጿል፡፡ የእግረኛ መንገድን ጨምሮ 30 ሜትር ስፋት እንደሚኖረው፣ የወሰን ማስከበር ሥራውን ጨምሮ በ24 ወራት የጊዜ ገደብ ውስጥ እንደሚጠናቀቅ ተገልጿል፡፡

ሁለተኛው ደግሞ ከቦሌ ቡልቡላ ወረዳ 12 መስቀለኛ መንገድ መነሻ አድርጎ ቡልቡላ አደባባይ፣ ቡልቡላ 40/60 ኮንዶሚኒየም አቋርጦ ኖቫ ሪል ስቴት የሚዘልቅ ሲሆን፣ ሁለት አገናኝ መንገዶችን የሚያጠቃልል ነው፡፡ 4.1 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ይህ የግንባታ ክፍል እግረኛ መንገዱን ጨምሮ በ30 ሜትርና በ25 ሜትር ስፋት የሚገነባ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ይህንን መንገድ ለመገንባት አሸናፊ የሆነው ራማ የተባለው አገር በቀል ኮንትራክተር ነው፡፡ ራማ አሸናፊ የሆነበት ዋጋም 374.4 ሚሊዮን ብር እንደሆነ ተገልጿል፡፡

አጠቃላይ ርዝመታቸው ስምንት ኪሎ ሜትር የሚሸፍኑት ሁለቱ መንገዶች በአሁኑ ወቅት በጣም የተጎዱና ጠባብ በመሆናቸው፣ ለእግረኛም ሆነ ለአሽከርካሪዎች እንቅስቃሴ አዳጋች ሆነው እንደቆዩ ተገልጿል፡፡ በተጨማሪም የ40/60 እና የ20/80 የጋራ ቤቶች መገንባታቸውና አዳዲስ የመኖሪያ መንደሮች እየተስፋፋ በመምጣታቸው፣ ከዚህ ቀደም የነበረው መንገድ በበቂ ሁኔታ ተጠቃሚዎችን ሊያስተናግድ ባለመቻሉ ነው መንገዶቹ የሚገነቡት፡፡ የመንገዶቹ ግንባታ ሲጠናቀቅ የሚስተዋለው ችግር በከፍተኛ ደረጃ እንደሚቀረፍና የከተማዋን የመንገድ ሽፋን ለማሳደግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ባለሥልጣኑ ገልጿል፡፡

የግንባታ ስምምነቱን በባለሥልጣኑ በኩል የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሀብታሙ ተገኝ (ኢንጂነር) በፉል ኮንስትራከሽን በኩል የድርጅቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ልመነው ፈለቀ፣ በራማ ኮንስትራክሽን በኩል ደግሞ የድርጅቱ ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ፍሬው ተድላ (ኢንጂነር) ፈርመዋል፡፡

ከእነዚህ የመንገድ ግንባታዎች በተጨማሪ ባለሥልጣኑ በ2010 በጀት ዓመት ግንባታ የሚያስጀምርባቸውና በጨረታ ሒደት ላይ የሚገኙ መንገዶች እንዳሉም አስታውቋል፡፡ በቅርቡ የጨረታ ውጤታቸው ታውቆ የግንባታ ስምምነት ይደረግላቸዋል ተብለው ከሚጠበቁ መንገዶች መካከል ከፋፋ ምግብ ፋብሪካ፣ ዳማ ሆቴል፣ ብሔረ ጽጌ፣ ሰኔ ዘጠኝ ትምህርት ቤት፣ ደብረዘይት መንገድ፣ አያት መሪ ሳይት አራት ኮንዶሚኒየም፣ ቦሌ አያት፣ አያት ኮንዶሚኒየም፣ ኃይሌ ጋርመንት አደባባይ፣ ጀሞ አደባባይ፣ ከ22 ማዞሪያ እስከ እንግሊዝ ኤምባሲ ያሉት መንገዶች ይገኙባቸዋል፡፡ ከራስ ደስታ ሆስፒታል እስከ ቀጨኔ መድኃኔዓለም፣ ከሽሮሜዳ እስከ ቁስቋም፣ ከመገናኛ ውኃ ልማት እስከ ወረዳ 17 ጤና ማዕከል፣ ከሲኤምሲ እስከ አያት፣ ጉርድ ሾላ፣ ሰሚት፣ መሪ፣ ቄራ፣ ሳርቤት፣ ጎፋ መብራት ኃይል ኮንዶሚኒየም ያሉት የመንገድ ፕሮጀክቶችም በተመሳሳይ ይገነባሉ ተብለው ከሚጠበቁት ፕሮጀክቶች ውስጥ ተካተዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣንን ለ2010 በጀት ዓመት 6.3 ቢሊዮን ብር በጀት እንደተመደበለት ይታወቃል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች