Friday, April 19, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ኢትዮጵያና ጃፓን ከሰሜን ኮሪያ ኑክሌር እስከ አፍሪካ ቀንድ ባሉ ሥጋቶች ተመሳሳይ አቋም እንዳላቸው ተገለጸ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ጃፓን ለመንገድ ግንባታ ከ100 ሚሊዮን ዶላር በላይ ብድር ማቅረብ ትፈልጋለች

እሑድ ነሐሴ 21 ቀን 2009 .. ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ከአገሪቱና ከአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ባለሥልጣናት ጋር የተወያዩት የጃፓን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ታሮ ኮኖ፣ ከሰሜን ኮሪያ የኑክሌርና የሚሳይል ጥቃት ጀምሮ በአፍሪካ ቀንድ ቀጣና በሚታዩት የፀጥታ ሥጋቶች ላይ አገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር የሚስማማ አቋም እንዳላት አስታወቁ፡፡

የጃፓን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ፣ እንዲሁም በሚኒስቴሩ የፕሬስና ፐብሊክ ዲፕሎማሲ ዳይሬክተር ጄኔራል ረዳት ሚኒስትር ኖሪዮ ማሩያማ፣ ከአገር ውስጥና ከውጭ መገናኛ ብዙኃን አባላት ጋር ባደረጉት ቆይታ እንዳስታወቁት፣ ጃፓን ከሰሜን ኮሪያ ተስፋፊ የኑክሌር፣ የሚሳይልና የጃፓን ዜጎችን ጠልፎ የመውሰድና የማገት ከፍተኛ ሥጋት እንደተጋረጠባት አስታውቀዋል፡፡ ለዚህም የተመድ የፀጥታው ምክር ቤት የማያወላዳ ማዕቀብ እንዲጥል የጃፓን ፍላጎት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የሰሜን ኮሪያ ጉዳይ ከቁጥጥር ውጪ ከመውጣቱ በፊት ሊገታ ይገባዋል ያሉት ቃል አቀባዩ ማሩያማ፣ በተመድ የፀጥታው ምክር ቤትም ከባድ ማዕቀብ እንዲጣል ዝግጅት እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡ የፀጥታው ምክር ቤት ተለዋጭ አባል የሆነችው ኢትዮጵያም በሰሜን ኮሪያ ላይ ተመሳሳይ አቋም እንደሚኖራት ተናግረዋል፡፡ ይሁንና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ የድጋፍ ድምፅ እንድትሰጥ ጠይቀዋል ወይ ለሚለው የጋዜጠኞች ጥያቄ ቀጥተኛ ምላሽ ከመስጠት ተቆጥበዋል፡፡ ምንም እንኳ ጃፓንና አጋሮቿ የፀጥታው ምክር ቤት ከረረ ያለ ዕርምጃ እንደሚወስድ ይናገሩ እንጂ፣ ሩስያና ቻይና ከሰሜን ኮሪያ ጋር ያላቸው የንግድ ግንኙነት እንዲገታ ለማድረግ ከአባል አገሮች ከፍተኛ ግፊት ማድረግ ይጠበቃል ተብሏል፡፡ ሰሜን ኮሪያ ከ90 በመቶ በላይ የወጪ ንግዷ ከቻይና ጋር እንደሚከናወን ቃል አቀባዩ ጠቁመዋል፡፡

በደቡብ ሱዳን ላለፉት አምስት ዓመታት ሲንቀሳቀስ የቆየው የጃፓን ራስ ተከላካይ ጦር ተልዕኮ በማብቃቱ እንደወጣ ያብራሩት ማሩያማ፣ በእነዚህ ዓመታት 5,000 ያህል የጃፓን ራስ ተከላካይ ጦር አባላት ልዩ ልዩ የመሠረተ ልማትና የምህንድስና ሥራዎችን ሲያከናውኑ ይቆዩ እንጂ በመደበኛ ውጊያ የመሠማራት ዓላማ እንዳልነበራቸውም አብራርተዋል፡፡ ከደቡብ ሱዳን በተጨማሪ ጃፓን በጂቡቲ ስላላት ወታደራዊ ተልዕኮም ጥያቄ ቀርቦላቸው ማብራሪያ የሰጡት ማሩያማ፣ የመርከቦችን ህልውና ከባህር ወንበዴዎች ለመከላከልና በሰላይ አውሮፕላኖች የታገዘ የመረጃ ማሰባሰብ ሥራ እንደሚከናወን አብራርተዋል፡፡ የሚሰበሰበው መረጃም አጋር ለሆኑ አገሮች ጭምር እንደሚሠራጭ አስረድተዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ማንሰራራት ከጀመረው የባህር ላይ ውንድብና እስከ አሸባሪዎች ጥቃት መንግሥታቸው ከአፍሪካ አገሮች ጋር አብሮ የመሥራት ፍላጎት እንዳለው አስታውቀዋል፡፡ በፀረ አክራሪነት ዘመቻ ጃፓን ኢትዮጵያ የምታከናውናቸውን ተግባራት እንደምትደግፍ ጠቁመዋል፡፡ ከዚህም በላይ የአክራሪነትና የአሸባሪነት መነሻው የልማት መጓደል ስለሆነ፣ ኢትዮጵያን ጨምሮ ለአፍሪካ አገሮች የሚሰጠው ድጋፍ እንደሚጠናከር ማያማ ሲገልጹ፣ በአፍሪካና በጃፓን መካከል እ... 1993 ጀምሮ ሲካሄድ የቆየውን የአፍሪካ ልማት ላይ ያነጣጠረ ጉባዔ አስታውሰዋል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በቅርቡ በሞዛምቢክ የተካሄደውን የ‹‹ቶኪዮ ዓለም አቀፍ ጉባዔ ለአፍሪካ ልማት (ቲካድ)›› የሚኒስትሮች ስብሰባ መርተዋል፡፡ እግረ መንገዳቸውን ወደ አዲስ አበባ የመጡት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፣ ባለፈው ዓመት በናይሮቢ በተካሄደው ስድስተኛው የቲካድ ዓለም አቀፍ ጉባዔ ወቅት ስምምነት የተደረሰባቸው ጉዳዮችና የድርጊት መርሐ ግብሮች አተገባበር ላይ መወያየታቸውም ተገልጿል፡፡

በናይሮቢው የቲካድ ስድስት ጉባዔ የጃፓን ጠቅላይ ሚኒስትር ሺንዞ አቤ ለአፍሪካ ልማት አገራቸው 30 ቢሊዮን ዶላር መመደቧን ይፋ አድርገው ነበር፡፡ ይህ ገንዘብ እ... እስከ 2018 ከጃፓን መንግሥትና ከግል ኩባንያዎች በመመንጨት ለአፍሪካ ልዩ ልዩ የልማት ሥራዎች እንደሚውል መገለጹም ይታወሳል፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ቃል አቀባይ ማሩያማ፣ ከተጠቀሰው ገንዘብ ውስጥ አምስት ቢሊዮን ዶላር መለቀቁን አውስተዋል፡፡ ከዚህ ገንዘብ ውስጥም 3.8 ቢሊዮን ዶላር ለመሠረተ ልማት ሥራዎች መዋሉን አስታውቀዋል፡፡

በኢትዮጵያ በኩል ኦፊሴላዊ የዕርዳታ ድጋፍ ከመስጠት ባሻገር፣ የጃፓን መንግሥት በአገሪቱ መገበያያ ገንዘብ (የን) ላይ የተመሠረተ ብድር ከ43 ዓመታት በኋላ ለኢትዮጵያ መስጠት መጀመሩ ይታወሳል፡፡ ከጥቂት ወራት በፊት ከተፈደቀው የ50 ሚሊዮን ዶላር ብድር በተጨማሪ፣ በቅርቡ ከ100 ሚሊዮን ዶላር በላይ የሚገመት ብድር ለመስጠት መንግሥታቸው ፍላጎት እንዳለው ማሩያማ ይፋ አድርገዋል፡፡

ከጅማ ከተማ እስከ ጭዳ ላለው የመንገድ ዕድሳት የሚውል 100 ሚሊዮን ዶላር ዕርዳታ እንደምትሰጥ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ በኩል ያስታወቀችው ጃፓን፣ ከዚህ ገንዘብ በላይ እንደሚሆን የሚጠበቅ የብድር ስምምነትም በዚሁ አካባቢ ለሚገነባ የመንገድ ፕሮጀክት ለማበደር የሚያስችሉ ሥራዎች መጀመራቸውንና የሰነድ ስምምነት ለማድረግ የሚረዱ ዝግጅቶች እየተከናወኑ እንደሚገኙ ማሩያማ አስታውቀዋል፡፡

በሞዛምቢኳ ማፑቶ ከተማ የተካሄደው የሚኒስትሮች ስብሰባ አምና በኬንያ የተደረገውን ጉባዔና ውጤቶቹን ከመገምገም ባሻገር፣ ለመጪው ጉባዔ የዝግጅት አጀንዳዎችም የሚደረጉበት እንደሆነ ታውቋል፡፡ የቲካድ ጉባዔ መላው የአፍሪካ አገሮች በከፍተኛ ባለሥልጣኖቻቸው የሚታደሙበት ሲሆን፣ ካለፈው ዓመት ጀምሮ በየሦስት ዓመቱ መካሄድ ጀምሯል፡፡ ከዚህ ቀደም በየአምስት ዓመቱ በጃፓን ይካሄድ የነበረው የቲካድ ጉባዔ ከእንግዲህ በአፍሪካና በጃፓን ከተሞች መካከል ይዘዋወራል፡፡

የጃፓን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እሑድ ዕለት ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ወርቅነህ ገበየሁ (/) ጋር ውይይት ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች