ለአምስተኛ ጊዜ የሚካሄደውና ለአገራቸውና ለወገናቸው ላቅ ያለ አገልግሎት የሰጡ ዜጎች የሚከብሩበት የዓመቱ በጎ ሰው ሽልማት መርሐ ግብር ነሐሴ 28 ቀን 2009 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴል ይካሄዳል፡፡ ተቋሙ በድረ ገጹ እንደገለጸው፣ በ10 ዘርፎች ሽልማት ተዘጋጅቷል፡፡ እነርሱም መንግሥታዊ የሥራ ኃላፊነትን በብቃት መወጣት ዘርፍ፣ ሚዲያና ጋዜጠኛነት፣ ማኅበራዊ ጥናት፣ ለኢትዮጵያ መልካም የሠሩ የውጭ ሀገር ዜጎች፣ ቅርስ ባህልና ቱሪዝም፣ ሳይንስ፣ ኪነ ጥበብ (በቴአትር ዘርፍ)፣ መምህርነት፣ በጎ አድራጎት ዘርፎች ናቸው፡፡ ለዚህ ክብር መብቃት አለባቸው የተባሉ ዜጎች በሕዝቡ የተጠቆሙ ሲሆን፣ በየዘርፉ ከተጠቆሙት ዜጎች መካከልም ሥራዎቻቸው ተመዝነው በሽልማት ኮሚቴው አማካይነት ሦስት ሦስት ዕጩዎች መለየታቸው ታውቋል፡፡
***
ኢትዮ ዞዲያክ ሽልማት በመስከረም ይካሄዳል
በኪነ ጥበብ ሦስት ዘርፎች በፊልም፣ በሙዚቃና በተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማዎች የዓመቱን ሽልማት ማዘጋጀቱን ዞዲያክ መልቲ ሚዲያ አስታውቋል፡፡ ተቋሙ ለሪፖርተር በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው፣ መስከረም 8 ቀን 2010 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር የሚካሄደው ኢትዮ ዞዲያክ ሽልማት 11 የመወዳደሪያ ምድቦች አሉት፡፡ እነሱም በፊልም ዘርፍ የዓመቱ ምርጥ ዳይሬክተር፣ ምርጥ ፊልም፣ ምርጥ መሪ ወንድ ተዋናይ፣ ምርጥ መሪ ሴት ተዋናይት፣ ምርጥ ተስፋ የተጣለበት ተዋናይ/ ተዋናይት፤ በሙዚቃ ዘርፍ የዓመቱ ምርጥ ነጠላ ዜማ፣ ምርጥ ቪዲዮ ክሊፕ፣ ምርጥ አቀናባሪ፣ ምርጥ አዲስ ዘፋኝ፣ ምርጥ አልበም፤ በተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማዎች ዘርፍ የዓመቱ ምርጥ ተከታታይ የቴሌቭዥን ድራማ ናቸው፡፡