የሰሜን ኢትዮጵያ ከተሞች መቐለ፣ ዓቢ ኣዲ፣ አክሱም፣ ዓዲግራት፣ ማይጨው፣ ሰቆጣ፣ ላሊበላ፣ ቆቦ ወዘተ በነሐሴ መንፈቅ፣ ልዩ ድባብ የሚያለብሳቸው ከተሜውም ሆነ ከዚያም ውጪ ያለውን ኅብረተሰብ ቀልብ የሚገዙበት አጋጣሚን ያገኛሉ፡፡ ዓመት ሄዶ ዓመት ሲመጣ 12ኛው ወር ላይ ከምትመጣው እንደየአካባቢው አጠራር አሸንዳ፣ ዓይኒ ዋሪ፣ ማሪያ፣ ሻደይ፣ አሸንድዬ፣ ሶለል ጋር ይገናኛሉ፡፡ ልጃገረዶችና ሴቶችም በልዕልና የሚታዩበት፣ በነፃነት ነግሠው የሚጫወቱበት በዓል ነው፡፡ በዓሉ በደቡብ ኤርትራ ጭምር ይከበራል፡፡
በተለይ ጠንካራው የክረምት ወቅት ቀዝቀዝ የሚልበት ወደ ብራ ወደ ጥቢ ለማምራት የሚንደረደርበት ሰሙን ነው፡፡ ነሐሴ 13 ቀን ከተከበረው የቡሔ በዓል በኋላ በሰሜን ኢትዮጵያ ከመንፈቀ ነሐሴ ጀምሮ የሚከበረው አሸንዳ/ ሻደይ በተለይ በልጃገረዶችና በሴቶች ይዘወተራል፡፡
ከሕፃን እስከ አዋቂ የበዓሉ መገለጫ በሆኑ አልባሳትና ማጋጊያጫዎች የሚታዩት ከነሐሴ አጋማሽ ጀምሮ ነው፡፡ የፀጉር አሠራሩ ከአልባሶ እስከ ግልብጭ፣ ከጋመ እስከ ድርብ፣ ከደቃቅ እስከ ጉልህ ከሕፃን እስከ አዋቂ ተቆናጅተው የታዩበትም ጭምር ነው፡፡ ቆነጃጅቱ ዓይናቸው ላይ የተኳሉት ኩል በቤት ተወቅጦ የተዘጋጀ ነው፡፡ ከቱባው ባህል ልብስ አንሥቶ ከዘመናዊው ስፌት ከተገኙት ጃርሲ፣ ሽፎን ቀሚስ ጋር ተውበው ይታዩበታል፡፡ ጌጣ ጌጣቸውም ልዩ ልዩ ዓይነት አንገት ላይ ከሚንጠለጠለው ሕንቆ፣ እግር ላይ እስከሚጠለቀው አልቦ፣ ድሪ፣ ድኮት፣ ጉትቻ፣ ማርዳ፣ መስቀል ሲሆን፣ አለባበሳቸውም በመልጉም /ጥልፍ ቀሚስ/ ፣ ሹፎን፣ ጃርሲ የታጀበ ነበር፡፡
የበዓሉ ኩነት ለከተማው ባዳ፣ ለአካባቢው እንግዳ ለሆነው ብቻ ሳይሆን በዚያው ከተማ የሚኖሩትን ሁሉ ማስደነቁ፣ ማስደመሙ ቀልብ መግዛቱ አይሳትም፡፡
የአሸንዳ መንፈስ፣ በፀጉር አሠራርና በአልባሳት፣ በመዋቢያ ቁሶችና በመጋጋጪያዎች ብቻ አይደለም የሚገለጠው፣ ርሱን የሚያገዝፉ የሚያጎሉ የተለያዩ ዘፈኖች ይገኙበታል፡፡
በክረምት ወቅት ከሚበቅለው የአሸንዳ ተክል ስሙን የወረሰውና ልጃገረዶችና ሴቶች በየአካባቢያቸው አሸርጠው የሚጫወቱበት የአሸንዳ/ሻደይ በዓል አከባበር ሁሉም በዕድሜ ደረጃቸው ተቧድነው ያከብሩታል፡፡ በዓሉ በኦርቶዶክሳውያኑ ምዕመናን ከሁለት ሳምንት ጾም በኋላ ከሚያከብሩት ከቅድስት ድንግል ማርያም ስም ጋር የተያያዘ ነው፡፡
አሸንዳ ሴቶች ነፃነታቸውን የሚያውጁበት የሚነግሡበት፣ ጥብቅ የሆኑ ወላጆችና ባሎች ልጆቻቸውንና ሚስቶቻቸውን በበዓሉ እንዲታደሙ የሚፈቅዱበት ዕለት ነው፡፡ በፀጋይ ሓድሽ ጽሑፍም ተንፀባርቋል፡፡ ሴቶች ነፃነታቸውን የሚያውጁበት ብቻ ሳይሆን፣ ነፃነታቸውን በተሟላ መልኩ እንዲሰፋ የሚያግዝ ነው፡፡ በያዛቸው ቁም ነገሮችም እንደ ባሕር ነው፡፡ ብዙዎች የዕደ ጥበብ ውጤቶች የሚቀርቡበት፣ ለትምህርት ዕድገትና ለፈጠራ ጽሑፍ የሚሆን ሀብት የተከማቸበት፣ ለቱሪስት መስህብነትም የሚውል ነው፡፡
ነሐሴ 16 ቀን ከሚከበረው የቅድስት ማርያም በዓል ጋር የተያያዘው ክብረ በዓል ከዋዜማው እስከ ማግሥት ልጃገረዶች የአሸንዳ ቅጠልን አሸርጠው አደባባይ በመውጣትና በየቤቱ በመዞር እየጨፈሩና እያዜሙ የሚያከብሩት በዓል ዘንድሮም በተለያዩ ከተሞች ተከብሯል፡፡ ከሕፃን እስከ አዋቂ የበዓሉ መገለጫ በሆኑ አልባሳትና መጋጊያጫዎች ተውበው ታይተዋል፡፡
በክረምት ወቅት ከሚበቅለው የአሸንዳ ተክል ስሙን የወረሰው በዓሉ በኦርቶዶክሳውያኑ ምዕመናን ከሁለት ሳምንት ጾም በኋላ ከሚያከብሩት ከቅድስት ድንግል ማርያም ስም ጋር የተያያዘ ነው፡፡ በተለይ ዓይኒ ዋሪ በአክሱም ከነሐሴ 24 ዋዜማ ጀምሮ እስከ መስከረም 17 (መስቀል) ድረስ እየተከበረ ይዘልቃል፡፡
በየዓመቱ ነሐሴ 16 የሚከበረው አሸንዳ የ15ቷን ቀን የፍልሰታ ጾምም የሚፈሰክበትም ቀን ነው፡፡ የበዓሉ ሥረ መሠረት ወይም አጀማመር ከዮፍታሔ ሴት ልጅ ለአምላክ መስዋዕት ከመደረጓ ጋር የሚያይዙት አሉ፡፡ የኦሪት መጽሐፍ እንደሚያትተው ሁልጊዜም ዮፍታሔን ይቀበለው የነበረ ነጭ በግ የነበረ ሲሆን፣ ዮፍታሔም መጀመሪያ ለአምላኩ የሚቀበለኝን እሰዋለሁ ብሎ ቃል ገባ፡፡ ግን ቤቱ ሲደርስ የተቀበለችው ሴት ልጁ ነበረች፡፡ እናም ቃል በገባው መሠረት መስዋዕት ሊያደርግ ወሰነ፡፡ ከዚያም የተለያዩ ታሪክ አዋቂዎች እንደሚናገሩት እሷም ስለ ድንግልናዬ ትንሽ ጊዜ ስጠኝ በማለት ከልጃገረዶች ጋር እንደጨፈረች፣ ይኼም ቀንን ያንን ለማስታወስ እንደሚከበር ይነገራል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ይኼንን በዓል ከማርያም ሞት መነሳትም ጋር ያያይዙታል፡፡
እንደ የትግራይ ባህል ማኅበር ዋና ዳይሬክተር አቶ ብርሃኑ ወልደሚካኤል አገላለጽ፣ የአሸንዳ አከባበር መነሻው አክሱም አካባቢ ነው፡፡ ምክንያቱም ከክርስትና ጋር የተያያዘ በመሆኑ ነው፡፡ የኦርቶዶክስ ክርስትና መስፋፋት የጀመረውም በ3ኛውና በ4ኛው ክፍለ ዘመን በአክሱም ነው፡፡ አሸንዳውም ከአክሱም ተነሥቶ ወደ ኤርትራና ወደ ደቡብ እስከ ላስታና ሰቆጣ ዋግ ድረስ ሊሄድ ችሏል፡፡
ቀኑ በተለያዩ አካባቢዎች የሚከበረው በደመቀ ሁኔታ ነው፡፡ በዓሉ ለሳምንት እንዲሁም አንዳንድ አካባቢዎች ለሳምንታት ቢቆይም መከበሩ የሚጀምረው ከዋዜማው ጀምሮ ነው፡፡ እንኳን አደረሰንም መባባልም ይጀምራሉ፡፡
በዕለቱም በአገር ባህል ልብስ ደምቀውና አጊጠው ወደ ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን ጉዟቸውን ያደርጋሉ፡፡ የአሸንዳ ልጃገረዶች ወደ መንገዶች ወጥተው ጭፈራቸውን በጥዋቱ የሚጀምሩት ቤተ ክርስቲያን ከተሳለሙ በኋላ ነው፡፡ ሴቶቹ የተጠለፈ ቀሚስ፣ ነጠላ፣ ሽፌን ቀሚስ፣ ሦስት የተለያዩ መጠን ያላቸው መስቀሎች፣ ድሪ፣ አምባር፣ ድኮት፣ ትልቅ ቀለበትና ጉትቻ፣ ኩል በመሳሰሉት አጊጠው ነው የበዓሉን አከባበር እንደሚጀምሩ ይወሳል፡፡ እንደ አባባሉም ‹‹በአሸንዳ ጊዜ እጮኛ መምረጥ የለብህም›› የሚባለውም አሸብርቀውና ደምቀው ስለሚወጡና በአዘቦት ቀን ያንን ስለማይመስሉ ነው፡፡
በዓሉን በተለይ ለቱሪስት መስህብነት ማዋል እንደሚገባ አስተያየት እየተሰጠበት ነው፡፡ ከቱሪስት መስህብነት ባለፈም በዩኔስኮ በማይዳሰሱ ባህላዊ ቅርሶች (ኢንታንጀብል ካልቸራል ሄሪቴጅ) መዝገብ ውስጥ እንዲገባ ከ2008 ዓ.ም. ጀምሮ በክልሎቹና በፌደራል ሥራ ተጀምሯል፡፡ የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን በየአካባቢዎቹ ያለውን ያከባበር ገጽታ መሰነዱንና በመጽሐፍ ማሳተሙን እንዲሁም ቀጣይ ሥራዎችን እየሠራ መሆኑን የባለሥልጣኑ የዘርፍ ዳይሬክተር አቶ ኤፍሬም አማረ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
ሃቻምና በክብረ በዓሉ ላይ ተገኝተው የነበሩት የዩኔስኮ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ኢትዮጵያዊው አቶ ጌታቸው እንግዳ ባደረጉት ንግግር፣ ዩኔስኮ ለአሸንዳ በዓል ልዩ ትርጉም እንደሚኖረው በምክንያትነት ያብራሩት፣ ‹‹የጾታ እኩልነትን ማረጋገጥና የአፍሪካ አህጉርን መደገፍ ድርጅቱ ቅድሚያ የሚሰጣቸው የትኩረት አቅጣጫ በመሆናቸው ነው፤›› በማለት ነበር፡፡ የአሸንዳ በዓል በዩኔስኮ የሰው ልጆችን ድንቅ የባህል ቅርስ በሚወክል የምዝገባ ሰነድ ውስጥ ተመዝግቦ ለማየት የየበኩላችንን ጥረት ማድረግ ይኖርብናል ማለታቸውን ሪፖርተር መዘገቡ ይታወሳል፡፡