Friday, June 9, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ሥራችን ‹‹ና ብሎ ዕዳ›› እንዳያሰኘን ጥንቃቄ እናብዛ

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ከንግዱ ማኅበረሰብ ጋር ባለፈው ቅዳሜ  ውይይት አካሂደዋል፡፡ ውይይቱ በርካታ ጉዳዮችን አስተናግዷል፡፡ በኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክክር ቤት ፕሬዚዳንት በኩል በጽሑፍ የቀረቡ ጥያቄዎችን ጨምሮ በስብሰባው ከተገኙት ተሳታፊዎችም የቀረቡት ጥያቄዎችና ምላሻቸው በጥቅሉ ከሁለት ሰዓታት በላይ ፈጅተዋል፡፡

በመንግሥትና በኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት መካከል ከሚደረጉ ምክክሮች በኋላ በዓመቱ መጨረሻ፣ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር የሚደረገው ውይይት እንደማጠቃለያ ይቆጠራል፡፡ እንዲህ ዓይነቱን ውይይት ለማካሄድ የመግባቢያ ሰነድ ከተፈረመ ሰባት ዓመታት ተቆጥሯል፡፡ የቅዳሜውን ጨምሮ ሦስት ጊዜ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ውይይት ሲካሄድ፣ ባለፈው ዓመት በአገሪቱ ከተከሰተው አለመረጋጋት ሳቢያ መቋረጡ ይታወቃል፡፡

ባለፈው ሳምንት በተደረገው ስብሰባ ዓምና በይደር ተይዘው የነበሩና ዘንድሮ ይመከርባቸዋል የተባሉትን ጨምሮ አዳዲስ አጀንዳዎችም ተካተው በቅዳሜው መድረክ  መቅረባቸው የመወያያ አጀንዳዎቹ እንዲለጠጡ አድርጓል ማለት ይቻላል፡፡

በንግድ ምክር ቤቱ በኩል ብቻ ጥናት ተደርጎባቸዋል የተባሉ 13 አጀንዳዎች ቀርበዋል፡፡ ከምክር ቤቱም ሆነ ከተሳታፊዎች ለቀረቡ ጥያቄዎች የጠቅላይ ሚኒስትሩ ምላሽ ከሁለት ሰዓት ከ20 ደቂቃ በላይ የፈጀ ነበር፡፡ መንግሥታቸው እንደማይቀበላቸው በመግለጽ ተግሳጽ የታከለበት ምላሽ የሰጡበት ጥያቄም ቀርቦላቸዋል፡፡ አዎንታዊ ምላሽ የሰጡባቸው ጥያቄዎችም ነበሩ፡፡ መንግሥት ሊያስተካከል ይገባዋል በማለት ስህተት መሥራቱን ያመኑባቸው ነጥቦች ላይም በምክክር እንፈታቸዋለን ብለዋል፡፡

የባንኮች 27 በመቶ የቦንድ ግዥ ይሻሻል ለሚለው ጥያቄ ዳግመኛ ይህንን ጥያቄ እንዳታነሱ የሚል ምላሽ ሲሰጡ፣ በቀን ገቢ ግምት ላይ ያለውን ችግር መንግሥት የተረዳው በመሆኑ እንደሚስተካከል ቃል ገብተዋል ማለት ይቻላል፡፡ እንዲህ ያለው መድረክ በሕግ እንዲደገፍ አዋጅ ይውጣለት በማለት ንግድ ምክር ቤቱ ላቀረበው ጥያቄ፣ ያን ያህል ጠቃሚ እንደሆነ ባያምኑበትም አስፈላጊ ከሆነ ይፈጸማል ብለዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰፋ ያለ ማብራሪያ ከሰጡባቸው ጉዳዮች አንዱ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦትን የተመለከተው ነው፡፡ ሥራ ለመጀመር የኤሌክትሪክ ኃይል እስኪለቀቅላቸው የሚጠባበቁ ማምረቻዎች ኃይል ስለማጣታቸው ላቀረቡላቸው ጥያቄ ላይ አቶ ኃይለ ማርያም የሰጡት ምላሽ ግን ግር ሳያሰኝ አልቀረም፡፡

የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት በሁሉም ዘርፍ ውስጥ የሚታይ ችግር መሆኑን የሚያምኑት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ተበታትነው ለተተከሉ ኢንዱስትሪዎች ኃይል ማቅረብ መንግሥታቸው እንደቸገረው አመልክተዋል፡፡ ፈታኝ ሆኗል ያሉትን የአቅርቦት ችግር ለመፍታት የአገር ውስጥ ባለሀብቶችም ሆኑ የውጭ ኩባንያዎች፣ በኢንዱስትሪ መስክ  ሲሰማሩ፣ ወደ ኢንዱስትሪ ፓርኮች መግባት ግድ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ፓርኮቹ እንደ ኤሌክትሪክ ኃይል ያሉ መሠረተ ልማቶችን በተደራጀ መንገድ ለማቅረብ እንዲያስችሉ ታስበው የተቋቋሙ ናቸው፡፡ አቋማቸው ምክንያታዊ ነው፡፡ ይሁንና በየቦታው የተገነቡ ኢንዱስትሪዎች ጉዳይስ ምን ሊሆን ነው? በሚለው መሠረታዊ ጥያቄ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቁርጥ ያለ መልስ ሰጥተዋል ለማለት ስለሚቸገር ጉዳዩ ማሳሰቡ አልቀረም፡፡

በየቦታው ማምረቻዎችን የገነቡ ባለሀብቶች ጉዳይ ግን ወደፊት በምክክር እንፈታዋለን በሚል መልስ ብቻ በቀላሉ የሚታለፍ አይመስልም፡፡ ምክንያቱም በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የተነገቡ ማምረቻዎች አብዛኞቹ በቂ ኃይል ስላልተለቀቀላቸው በሙሉ አቅማቸው ወደ ሥራ ሊገቡ አልቻሉም፡፡ ይህ የሚፈጥረው ተፅዕኖ ቀላል አይሆንም፡፡ የኤሌክትሪክ ኃይል አጣን የሚሉት አምራቾች ኃይል ማግኘት ካልቻሉ፣ ቀድሞውኑ ወደ ግንባታ እንዲገቡ መንግሥት ለምን ይፈቅዳል የሚል ጥያቄም ያስነሳል፡፡ ለምሳሌ በዱከም በመቶ የሚቆጠሩ ማምረቻዎች ለሥራቸው የሚበቃ ኃይል ባለማግኘታቸው ሥራ መጀመር እንዳልቻሉ በቅርቡ በተደረገ ማጣራት መረጋገጡ ተሰምቷል፡፡

ማምረቻዎቹ ኃይል ያገኙ ዘንድ የክልሉ መንግሥት በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት ደጅ እየጠና ቢሆንም፣ አዎንታዊ መልስ አለማግኘቱን በአንድ የውይይት መድረክ ይፋ አድርጓል፡፡ በቅዳሜው የምክክር መድረክም የኤሌክትሪክ ኃይል ሥራ ላይ ያሉትንም እያወከ ለመሆኑ መረዳት ይቻላል፡፡

የኤሌክትሪክ ኃይል ፍላጎት በከፍተኛ መጠን መጨመሩ ባያጠራጥርም፣ ከፍተኛ ገንዘብ ፈሶባቸው የተገነቡና እየተገነቡ የሚገኙ ድርጅቶች ኃይል ስላላገኙ ብቻ ወደ ሥራ ሊገቡ አልቻሉም መባሉ ግን ለኢኮኖሚው ያውም እንዲጎለብት ለሚፈለገው አምራች ዘርፍ አስጊ ነው፡፡

የኃይል አቅርቦት እጥረት ካለም ቀድሞውኑ ግንባታዎች እንይካሄዱ ማድረግ ሲቻል የአገር ሀብት መባከኑ ለምን ያሰኛል፡፡ ከዚህ በኋላ በኢንዱስትሪው ዘርፍ መግባት የሚፈለግ ወደ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ይግባ መባሉ አንድ ነገር ሆኖ፣ እስካሁን በየቦታው ለተገነቡ ኢንዱስትሪዎች አፋጣኝ ምላሽ መስጠትም ይገባል፡፡ ምክንያቱም ኢንዱስትሪዎች እንዲገነቡ የፈቀደው መንግሥት ራሱ ስለሆነ፣ ለውድቀታቸው የተወሰነ ኃላፊነት ስለሚኖርበት ነው፡፡ ለችግሩ መፍትሔ ማፈላለግም ይጠበቅበታል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከዚህ በኋላ የሚመጣው አምራች ወደ ፓርኮች ይግባ ማለታቸው ትኩረቱ ሁሉ ወደዚያ ብቻ እንደሚሆን ያሳያል፡፡ የንግድ ኅብረተሰቡ መሪዎችም የግል ባለሀብቱ በተበታተነ አካባቢ ማምረቻ እንዳይገነባ ምከሩ ተብለዋል፡፡ ወደፊት ለሚመጣው የሚታሰበውን ያህል አሁን ላለውም ትኩረት መስጠት ይገባል፡፡

ኢትዮጵያ ራሷን ለመሸጥ ወይም ኢንቨስትመንትን ለመሳብ በሚካሄዱ የማስተዋወቂያ ሥራዎች ከፌዴራል እስከ ክልል ድረስ ያሉ የኢንቨስትመንት ቢሮዎች በኢትዮጵያ ኢንቨስት ማድረግ ውጤታማ ከሚያደርጉ እውነታዎች መካከል አንዱ ብለው የሚጠቅሱት ለኤሌክትሪክ ኃይል የምታስከፍለው ገንዘብ ዝቅተኛ መሆኑን በመጥቀስ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ለኤሌክትሪክ ኃይል ፍጆታ የተጣለው ታሪፍ ከዓለም ዝቅተኛ መሆኑ የዘመቻ መቀስቀሻ በሆነበት ወቅት፣ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦቱ ቀድመው ለተገነቡ ማምረቻዎች የማይደረስበት፣ የማይቧጠጥ ሰማይ መሆን የለበትም፡፡

የኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ፍጆታ ታሪፍ ዝቅተኛ እንደሆነ ገልጾ፣ ኢንቨስተሮች መሳብ ጥሩ ብልኃት ነው፡፡ እንዲህ ተብሎ ተወትውቶ የመጣ ኢንቨስተር ግን ፋብሪካ ገንብቶ ማሽኖች ተክሎ ኃይል ካልቀረበለት፣ በአንዱ እጅ ውኃ እየቀዱ በሌላው እጅ እንደማፍሰስ ይሆናል፡፡

ከዕድገት ጋር የተቆራኙ የመሠረተ ልማት ፍላጎቶቻችንን ለማሟላት የጠራ ሥራ መሠራት ብቻ ሳይሆን፣ ፈቃድ ሲሰጥም አቅም ተመዝኖ ቢሆን መልካም ነው፡፡ ኃይል የሌለበት ማምረቻ መገንባት ትርጉም አይሰጥም፡፡ በሌላ በኩል የራሳቸውን ኃይል በማልማት መጠቀም የሚችሉ ኢንዱስትሪዎችን የሚያበረታታ አሠራር ቢኖር ዛሬ የሚደመጡ ሮሮዎች ሊቀንሱ በቻሉ ነበር፡፡ በዚህ ረገድ ብዙ ለመሥራት አማራጮች መታየት ይኖርባቸዋል፡፡ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦትን ለማሳደግ አሁን እየተደረገ ያለው እንቅስቃሴ ነገ እየተፈጠረ ከሚመጣው ፍላጎት ጋር ላይጣጣም ስለሚችል  በዚህ ዘርፍ ብዙ መሠራት አለበት፡፡

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት