በመንግሥት አምራች ተብለው ከተለዩት ውስጥ የግብርና ዘርፍ ዋናው ነው፡፡ ሰሞኑን ከንግዱ ማኅበረሰብ ጋር የመከሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ እንደገለጹት ይህ አምራች ዘርፍ በሦስት ይከፈላል፡፡ በግብርናው ዘርፍ ስትራቴጂያዊ የምግብ ሰብሎች የተባሉ ምርቶችን ጨምሮ አትክልት፣ ፍራፍሬና አበባ በዚህ ዘርፍ ተካተዋል፡፡ ዘመናዊ የእንስሳት ሀብት ልማትም የዚሁ ዘርፍ አካል ነው፡፡
ይሁንና ከሰፋፊ እርሻዎች አንፃር በርካታ ችግሮች እንዳሉ ሲገለጽ፣ ዘርፉን በተመለከተ የተጠኑ ጥናቶችም ይህንኑ አመላክተዋል፡፡ ልዩ ትኩረት ያሻቸዋል ከሚባሉ የኢንቨስትመንት መስኮች መካከል የሰፋፊ እርሻዎች ይካተታል፡፡ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤትም በአማካሪዎች አስጠንቶ በዓብይ አጀንዳነት ከያዛቸው ጉዳዮች ውስጥ በሰፋፊ እርሻዎች የተሰማሩ ባለሀብቶች ገጥሟቸዋል ያላቸውን ችግሮች ለመንግሥት አቅርቧል፡፡ የአገሪቱን የሰፋፊ እርሻዎች የተመለከተው የንግድ ምክር ቤቱ ጥናት፣ በዘርፉ የሚታዩ ችግሮችን በሰፊው ዳሷል ማለት ይቻላል፡፡
ለሰፊ የሥራ ዕድል ፈጠራ፣ ለኢንዱስትሪ ግብዓት ምንጭነት፣ ለቴክኖሎጂ ሽግግር፣ ለወጪ ንግድ ገቢ መጨመርና በጠቅላላው ለኢኮኖሚው ዕድገት አስተዋጽኦው የጎላ ቢሆንም፣ የሰፋፊ እርሻዎች ልማት በሚፈለገው ደረጃ አለማደጉ ከዘርፉ ሊገኝ የሚችለውን ጥቅም መንገድ እንዳስቀረው ያመለክታል፡፡ ለዚህ ተጠቃሽ ከሚሆኑት ምክንያቶች ውስጥ ዘርፉን የሚገዛ ፖሊሲና ስትራቴጂ ባለመኖሩ የተነሳ በቂ ማበረታቻና ድጋፍ ሥርዓት ሊዘረጋ አለመቻሉን ጥናቱ ይጠቁማል፡፡ ደካማ የክክትል ድጋፍና ቁጥጥር ሥርዓት፣ ሰፋፊ መሬቶችን ለልማት የሚያስፈልገው የመሬት ገንዘብ አቅርቦት ችግር፣ የዘርፉ ማነቆዎች ሆነው የገንዘብ አቅርቦት ችግር፣ የቴክኒክ ክህሎት ደካማነት፣ የዕውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር ክፍተቶች፣ የዘርፉ ማነቆዎች ሆነው ቀርበዋል፡፡ የመሠረተ ልማት አለመሟላት፣ የዘርፉ የሥጋት ተጋላጭነትና ከአካባቢ እንክብካቤና ቁጥጥር ጋር የተያያዙ ችግሮች ይታዩበታል፡፡
የእነዚህን ችግሮች ስፋትና ጥልቀት በመገንዘብ በመንግሥት በኩል ለዘርፉ ልማት ጥረቶች እንደተደረጉ ምክር ቤቱ ጠቅሶ፣ ቀሪ ሥራዎች በመኖራቸው ግን በቅርቡ የፀደቀውን የመንግሥት መመርያ በመንተራስ ለዘርፉ ፖሊሲና ስትራቴጂ በመቅረፅ የሰፋፊ እርሻዎችን ልዩ ባህሪ ያገናዘቡ ማበረታቻዎችን ማቅረብ እንደሚገባ ይጠቅሳል፡፡ ንግድ ምክር ቤቱ በመንግሥት ሊፈጸሙ ይገባቸዋል በማለት በጥያቄ ካቀረባቸው ውስጥ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ልምድ የሰፋፊ እርሻዎች ፓርክ እንዲቋቋም በማድረግ በየቦታው የተበታተኑ እርሻዎችን በማሰባሰብ የመሠረተ ልማት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ የሚለው ይገኝበታል፡፡
ለሰፋፊ እርሻዎች መሬት የማዘጋጀት ሥራን በእሽሙር ሽርክና እንዲሁም በመንግሥትና በግሉ ዘርፍ ሽርክና ማዕቀፍ ማልማት፣ ማካሄድ፣ በልማት ባንክ ለአልሚዎች የሊዝ ማሽነሪ ግዥ ሥርዓት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማመቻቸት ያስፈልጋል የሚል ጥያቄም ቀርቧል፡፡ ሰፋፊ እርሻዎች የግብርና ኤክስቴንሽን አገልግሎት ተጠቃሚ የሚሆኑበትን መንገድ መዘርጋትም ዘርፉን እንደሚያግዘው ምክር ቤቱ አመልክቷል፡፡
ሰፋፊ የእርሻ ልማት በሚካሄድባቸው አካባቢዎች የሚገኙ ማኅበረሰቦችን ጥቅም በማይጋፋ መልኩ የካሳ ክፍያ አመቻችቶ የአልሚዎችን የንብረት ጥበቃና የይዞታ መብት ማረጋገጥ አስፈላጊ እንደሆነና የግብርና ኢንሹራንስ አገልግሎቶች እንዲስፋፋ በማድረግም አልሚዎች የመድን ሽፋን ተጠቃሚ ማድረግም ለዘርፉ መንግሥት ማከናወን የሚጠቅበት ሥራዎች ውስጥ ይደመራል፡፡ የአካባቢ ፀጥታና ደኅንነትን ማረጋገጥም የመንግሥት ኃላፊነት ይሆናል፡፡ መሬት የማዘጋጃ ወጪንና የዘርፉ የአደጋ ተጋላጭነት ሥጋትን ለመቀነስ በመንግሥትም ሆነ በግል ባንኮች በኩል የረዥም ጊዜ ልዩ የእርሻ ሥራ ብድር ማመቻቸት ለሰፋፊ እርሻዎች ስለሚያስፈልጉ፣ ይህንንም ጉዳይ እንዲያየው መንግሥት ተጠይቋል፡፡
መሬት ለማግኘት የሚወስደውን ረዥም ጊዜና የተንዛዛ አሠራር በማሻሻል የአልሚዎችን አቅም ያገናዘበ የመሬት አቅርቦት ሥርዓት በመዘርጋትና እውነተኛ አልሚዎችን መለያ መሥፈርት በማዘጋጀት አቅርቦቱን ቀላልና ቀልጣፋ ማድረግ እንደሚገባም ተጠይቋል፡፡ እንዲህ ያሉ በርካታ ጥያቄዎችን ላቀረበው ንግድ ምክር ቤቱ፣ ባለፈው ቅዳሜ በተካሄደው የመንግሥትና የግሉ ዘርፍ የምክክር መድረክ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
የአገሪቱ ግብርና በተለይም የአርሶ አደር ግብርናና የጓሮ ግብርና ሰፊ ድርሻ እንደያዙ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የግሉ ዘርፍ በግብርናው መስክ ያለው ተሳትፎ ግን እምብዛም እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ሙከራዎች ስለመኖራቸው በማስታወስ፣ በአበባ በተወሰነ ደረጃም በአትልክልት ዘርፍ የተሻሉ ሥራዎች በአንድ ወቅት ቢታዩም ሥራዎቹ እንዳልቀጠሉ ገልጸዋል፡፡
የግሉ ዘርፍ ያለበትን ደረጃ ለማመላከት መንግሥት በራሱ በኩል ያስጠናውን ጥናት ዋቢ በማድረግ አሁን ያሉ አነስተኛና መካከለኛ ደረጃ ያላቸው 1,280 እርሻዎች እንደሚገኙ የገለጹት አቶ ኃይለ ማርያም፣ ‹‹እነዚህ እርሻዎች ምን ደረጃ ላይ ይገኛሉ? ተብሎ ጥናት ሲደረግ፣ ከእነዚህ ውስጥ ባይገርማችሁ 48 በመቶ የሚሆኑት በበሬ የሚያርሱ ናቸው፡፡ እነዚህ እርሻዎች የያዙት ግን 3.6 ሚሊዮን ሔክታር መሬት ነው፡፡ ይህ ማለት በትግራይና በደቡብ ክልል የሚታረሰውን መሬት የሚያህል ነው፤›› በማለት ገልጸዋል፡፡
ከሦስት እስከ ስድስት ሚሊዮን ሔክታር መሬት አነስተኛና መካከለኛ ባለሀብቶች ለእርሻ ሥራ መያዛቸው ተገልጿል፡፡ ይህ የቡና እርሻን የሚያጠቃልል እንደሆነ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በባለሀብቶች በተያዙ የእርሻ መሬቶች የሚመረተው ምርትም ቢሆን ዝቅተኛ እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡ እንደ ምሳሌ ያነሱትም ባለሀብቶቹ በያዙት መሬት አካባቢ ተመሳሳይ ምርት በሚያመርቱ አርሶ አደሮች ከሚመረተው ጋር በማነፃፀር ነበር፡፡
ከባለሀብቶቹ መሬት አጠገብ ሞዴል አርሶ አደር በሔክታር 32 ኩንታል ቡና ሲያመርት፣ ባለሀብቶቹ ግን በሔክታር በአማካይ ስምንት ኩንታል ያመርታሉ ብለዋል፡፡ አንዳንዱ ባለሀብት በሔክታር 13 እና የ14 ኩንታል ያመርት ይሆናል፡፡ በአብዛኛው ሦስትና አራት ኩንታል የሚያመርት ባለሀብት ተይዞ ሰፋፊ እርሻ አለ ለማለት እንደሚያስቸግራቸው አስታውቀዋል፡፡ ‹‹ከሦስት እስከ ስድስት ሚሊዮን ሔክታር የሚሆነውን መሬት በቴክኖሎጂ ታግዞ መልማት ቢችል ኖሮ ይህች አገር የት በደረሰች?›› ያሉት አቶ ኃይለ ማርያም፣ ባለሀብቶች ችግር እንዳለባቸው ጠቅሰዋል፡፡
በአትክልትና ፍራፍሬ ስለቀረቡት ችግሮች ማሻሻያ እንደሚደረግ ቃል ሲገቡ፣ ይኸው ዘርፍ ግን ወደ ኋላ ከቀሩት የኢንቨስትመንት ዘርፎች አንዱ እንደሆነም አስታውቀዋል፡፡ ይሁንና ምርጥ የሚባሉ ኢትዮጵያውያን ባለሀብቶች እየተሰታፉበት እንደሚገኙ በማመላከት በጥሩ ምሳሌነት የተጠቀሱት ራያ አካባቢ የኢንጆሪ ምርት በከፍተኛ ደረጃ ይልካሉ የተባሉ ባለሀብትን ዋቢ ባደረጉበት ወቅት፣ ‹‹እንዴት አድርገን ነው እንዲህ ያሉ ባለሀብቶችን መፍጠር የምንችለው?›› የሚል ጥያቄ ሰንዝረዋል፡፡
ለአነስተኛው አርሶ አደር የኤክስቴንሽን አገልግሎት እንደሚሰጠው ሁሉ ለሰፋፊ እርሻ ባለሀብቶች ይህ አገልግሎት ይቅረብ የሚለው ጥያቄ ተገቢ እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡ ‹‹እናንተ ሙያተኛ መቅጠር አትችሉም ማለት ነው? ይህ ካልሆነ በመጀመርያ ሰፋፊ እርሻ እንዴት ሆነ? መሬት ተለክቶ ስለተሰጣችሁ ነው ሰፋፊ እርሻ የተባለው?›› በሚሉ አፋጣጭ ጥያቄዎች አስታከው ውድቅ አድርገውታል፡፡
‹‹በእኔ እምነት ሰፋፊ እርሻ የሚባለው የአዋጭነት ጥናት ተካሂዶበት፣ ከባንክ ጋር የሚሠራ፣ ባንክም አዋጭ ነው ብሎ የያዘው በገንዘብ ብቻ ሳይሆን ባለሙያዎች ያስፈልጋል ተብሎ የተለየለት እርሻ ነው፤›› ብለዋል፡፡ ሜዳውን በሙሉ አጥሮ ያስቀመጠ ሁሉ ሰፋፊ እርሻ ሊባል እንደማይችልም ተናግረዋል፡፡
የንግድ ምክር ቤቱ ጥናት፣ የግል ባለሀብቱ የተሰማራበት ደረጃ በሚጠቀበው ደረጃ ያለመሆኑ አንዱ ምክንያት የመሬት አቅርቦትና የተረከቡትን መሬት በአግባቡ ያለመሥራት ነው ይላል፡፡ በአንዳንድ አካባቢዎች ሦስትና አራት ሺሕ ሔክታር መሬት ቦታ የተሰጣቸው ግለሰቦችና ድርጅቶች ትንሽ ጎጆ ከመቀለስ ውጭ እዚህ ግባ የሚባል ሥራ ሳይሠሩ መገኘታቸው ነው፡፡
ጥሩ እንደሚሠሩ የሚታመንባቸውም ቦታ ለማግኘት ቢሮክራሲው ፈተና እንደሆነባቸው ምክር ቤቱ አሳይቷል፡፡ መሬት ለማግኘት ከቢሮክራሲ ባሻገር የፀጥታ ችግርም ተጠቅሷል፡፡ ስለዚህም በተረከቡት መሬት ማምረት ያልቻሉ ሲሆን፣ በበርካታ ቦታዎችም ምርታቸውን ለገበያ ለማቅረብ የሚያስችል መሠረተ ልማት ማጣታቸው ዘርፉን እንደጎዳው ምክር ቤቱ ይጠቅሳል፡፡ በዘርፉ ለተሰማራ ባለሀብት መሬት ሲሰጥ መመዘኛ አለመኖሩ፣ አቅሙ አለመታየቱና የመሳሰሉት ከሚጠቀሱ ችግሮች ውስጥ ይገኙባቸዋል፡፡ ሌላው በጥናቱ የተካተተው በዘርፉ ለመሰማራት ፈቃድ ከወሰዱ ባለሀብቶች ውስጥ አብዛኞቹ ወደ ሥራ አለመግባታቸው ነው፡፡
ጥናቱ እንደሚያመለክተው፣ ባለፉት 24 ዓመታት (ከ1992 እስከ 2015) ውስጥ ለግብርና ሥራ ፈቃድ ያወጡ የውጭና የአገር ውስጥ ባለሀብቶችና ኩባንያዎች ቁጥር 10,634 ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት በተለያየ ደረጃ በዘርፉ የሚገኙት ከተጠቀሰው ቁጥር ከ25 በመቶ በታች ናቸው፡፡ በሥራ ላይ እንዳሉ ከሚነገርላቸው 1,385 ባለሀብቶች ውስጥ የ829ቱ ፕሮጀክቶች ብቻ በተግባር ላይ ይገኛሉ፡፡ ከዚህ ውስጥም 1,042 የአገር ውስጥ 343 የውጭ መሆናቸው ታውቋል፡፡
በግብርና ዘርፍ ትራንስፎርሜሽን ማረጋገጥ የሞት ሽረት ጉዳይ እንደሆነ የገለጹት አቶ ኃይለ ማርያም፣ ለግብርና ትልቁ ማነቆ የሆነው የመሬት አቅርቦት እንደሆነ አልሸሸጉም፡፡ ችግሩን ለመቅረፍ ሲሞከር እንደነበር፣ ነገር ግን ሙከራዎቹ የተፈለገውን ውጤት ማምጣት እንዳላስቻሉ ተናግረዋል፡፡ አንደኛው ለግብርና የሚስማሙ መሬቶች የሚገኙባቸው አካባቢዎች ከመሀል አገር መራቃቸው ለታየው ክፍተት አንዱ ምክንያት ነው፡፡ በደጋው አካባቢ የሚኖረው ሕዝብ ቁጥር ከፍተኛ በሆኑ፣ የመሬት ድርሻው በአነስተኛ አርሶ አደር ማሳያ የተያዘ በመሆኑ ያለው አማራጭ ወጣ ብሎ መሥራት እንዲሆን አስገድዷል ብለዋል፡፡
በግብርና ዘርፍ ላይ መሬት የማቅረብ ችግርን ለመፍታት እንደ ኢንዱስትሪ ፓርኮች የግብርና ልማት ኮሪደር ወይም የልማት ዞን ተከልሎ በዚያ ዙሪያ መሥራት ይገባል ለሚለው ጥያቄም ምላሽ ተሰጥቷል፡፡
የመሬት ባንክ አሠራር ላይ ስለነበረው ችግር ሲገልጹም፣ የተካለለው መሬት ለልማት የሚውልና እርሻ ሊታረስበት የሚችል ስለመሆኑ ሳይረጋገጥ መሆኑ በመንግሥት በኩል የታየ ክፍተት እንደሆነ በመጥቀስ ነበር፡፡
ይህንን ለመቅረፍ የመሠረተ ልማት ኮሪደሮችን በመለየትና በማልማት በኩል ጥሩ ውጤት ተገኝቷል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በኮሪደሮቹ አካባቢ የአስፋልት መንገዶች ግንባታ መከናወኑን ጠቅሰዋል፡፡ ይሁንና መሬት ለግል ባለሀብት መስጠት ጋብ መደረጉን አስታውሰዋል፡፡ መሬት መስጠት የቆመው መሠረተ ልማት ባልተሟላበት አኳኋን እምብዛም ውጤታማ ስለማያደርግና ሄዶ ሄዶ መቆሙ አይቀርም ከሚል መነሻ ነው ብለዋል፡፡ የመሠረተ ልማት ችግሮችን ለመቅረፍ የሚሠራ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤት መቋቋሙንም ጠቅሰዋል፡፡ ባለሥልጣኑ ቀለል ካለው እንዲጀምር ታስቦ፣ በአበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ ዘርፍ ለተሰማሩ የሚሆን መሬት የማዘጋጀት ሥራ እንደተሠራ ተብራርቷል፡፡ በመሆኑም በራያ፣ በሻሸመኔ፣ በባህር ዳርና በሐዋሳ ትልልቅ አውሮፕላን ማረፊያዎች በሚገኙባቸው ከተሞች ዙሪያ 3,500 ሔክታር መሬት እንዲዘጋጅ ተደርጓል ብለዋል፡፡
በአትክልትና ፍራፍሬ ልማት መሰማራት የሚሹ ባለሀብቶች የተዘጋጀውን ቦታ እንዲጠቀሙበት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ይህንን ለማድረግም በአትክልትና ፍራፍሬ መስክ የሚሰማሩትን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን እየመዘገበ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል፡፡