Saturday, June 10, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርወገኖቻችንን ከጎዳና ላይ ለማንሳትም እናቅድ

ወገኖቻችንን ከጎዳና ላይ ለማንሳትም እናቅድ

ቀን:

በሮቤል ባልቻ

ኢትዮጵያ የራሷ የቀን አቆጣጠር ያላት አገር ናት፡፡ ይህም በመሆኑ የአዲስ ዓመት አቀባበላችን አብዛኛው የዓለም ሕዝብ ከሚጠቀምበት ዕለት ይለያል፡፡ የአሥራ ሁለቱም ወራት የቀን አቆጣጠራችን ወጥና የማይዛነፍ የሰላሳ ቀናት ሥሌት የተከተለ ነው፡፡ በዚሁ አቆጣጠር ላይ ተመሥርተን የምንቀበለው አዲስ ዓመት ከሌሎች አገሮች መለየቱን እንደ አንድ መለያና አገራዊ ቅርስ አድርጎ መመልከት በአብዛኛው ሕዝባችን ዘንድ የተለመደ ነው፡፡ ጥቂቶች የምዕራባውያኑን ጎርጎሮሳውያን ዘመን አቆጣጠር በ‹‹ይሻላል›› ማንነታቸው እንደተጠበቀ ሆኖ ማለቴ ነው፡፡

የነሐሴ ወር አልቆ ጳጉሜን 5 ቀን (በአራት ዓመት አንዴ ስድስት ቀን ይሆናል) ከተጠናቀቀ ዘመን ተለውጦ መስከረም አንድን እንደ አዲስ ዓመት ተቀበልነው ማለት ነው፡፡ ይህ ለዘመናት በኢትዮጵያውያን ዘንድ ተጠብቆ የቆየ ነው፡፡ ዛሬ ከኢትዮጵያ ተለይታ ራሷን ከቻለችው ኤርትራ ጋር ሁለቱ አገሮች ይህን አቆጣጠር ይጠቀማሉ ማለት ነው፡፡

አሮጌ ዓመት ሊያበቃና አዲሱ ዓመት ሊገባ ሲቃረብ፣ ሰዎች በግል ሕይወታቸው ብዙ ያቅዳሉ፡፡ ተማሪዎች ለሚቀጥለው ዓመት ከወትሮው የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ያቅዳሉ፡፡ በአንድ የንግድ ዘርፍ የተሰማራ ነጋዴ የነባር ንግዱን የመሥሪያ ቦታ ለማሻሻል ወይም ካፒታሉን አሳድጎ በዓይነትና በጥራት የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት ሊያቅድ ይችላል፡፡ ወይም ደግሞ ቅርንጫፎች ለመክፈትና ሌሎች ተጨማሪ የንግድ ዘርፎች ውስጥ ለመግባት ይወጥናል፡፡ ስፖርተኞች፣ የፖለቲካ ሰዎችና ሌሎችም በየሥራ ወይም በየሙያ መስካቸው ስህተቶቻቸውንና ድክመቶቻቸውን አርመው፣ በአዲሱ ዓመት ተሽለው ለመገኘት ለራሳቸው ቃል ይገባሉ፡፡ ዕቅዳቸውን ተግባራዊ የሚያደርጉበትን ሥልትና አቅጣጫም ይቀይሳሉ፡፡

ይኼ ሁሉ መልካም ነው፡፡ በመጪው አዲስ ዓመትም የተሻለ ሥራ ለመሥራት፣ የተሻለ ሆኖ ለመገኘት፣ የነበሩብንን ድክመቶች አርመን ውጤታማና ጠንካራ ሆኖ ለመገኘት አስቀድሞ ማቀድ ጠቃሚ ነው፡፡ በግል ሕይወታችን፣ በድርጅታችን፣ በቤተሰባችንና በዙሪያችን ያሉትን ከባቢያዊ ሁኔታዎች ማስተካከልና ማቀድ የስኬት አንዱ ዕርምጃ ነውና ይደገፋል፡፡    

አገር የሚመራ መንግሥት ደግሞ የረዥምና የአጭር ጊዜ ዕቅዶች በመንደፍ በማኅበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊና በፖለቲካ ዘርፎች የሚኖሩትን ክንዋኔዎች ያመላክታል፡፡ በአገራችን ባህል መንግሥት የአዲስ ዓመቱን ዕቅድ ይፋ በማድረግ በበጀቱ ሥራ የሚጀምረው፣ ዘመኑ ሳይቀየር ከሐምሌ 1 ቀን ጀምሮ ነው፡፡ በየዓመቱ ሐምሌ 1 ቀን የቀጣዩ ዓመት ክንዋኔዎች ተለይተው፣ የአዲሱ ዓመት አስፈላጊው በጀት በይፋ መጀመርያ ወቅት ነው፡፡ የክልል መስተዳድሮችና በፌዴራል መንግሥት ሥር የሚገኙ ሁለቱ አስተዳደሮች (አዲስ አበባና ድሬዳዋ) የየራሳቸውን የበጀት ቀመር አስቀድመው ይሠራሉ፡፡ በዚሁ ዕቅዳቸው የፌዴራል መንግሥትና ክልሎች ከበጀቶቻቸው ቀመር ለማኅበራዊ ዘርፍ የተወሰነ ሚሊዮን ብሮች ይመድባሉ፡፡ የማኀበራዊ ዘርፉ ብዙ ንዑሳን ክፍሎች ስለሚኖሩት፣ ማንሳት ለምንፈልገው አሳሳቢ ችግር ምን ያህል ትኩረት እንደተሰጠ ግን ለጊዜው ለመረዳት ያዳግታል፡፡ ቢሆንም ግን ለመጪው ዓመት የክንዋኔ ዕቅድ የተነደፈላቸው ማኅበራዊ ዘርፎች ይኖራሉ፡፡ በማኅበራዊ ዘርፎ የሚታዩ ችግሮቻችንም ዘርፈ ብዙ ናቸው፡፡

አዲስ አበባ ከተማን እንደ ማሳያ ብንወስዳት፣ የቆዩ ማኅበራዊ ችግሮች ሁሉ አመልካች ናት ለማለት ይቻላል፡፡ ታምሞ መታከሚያ ያጣ የከተማዋ ነዋሪ ወይም የክልል ሕመምተኛ ለመታከሚያ የሚለምነው በእግረኛ መንገዶችዋ ላይ ነጠላ አንጥፎ ነው፡፡ ሊታከም ከክልል መጥቶ የጊዜ ቀጠሮ የተሰጠው ሕመምተኛም እዚህ መጠጊያ ዘመድ ከሌለው መኖሪያውና ዕርዳታ መጠየቂያው እዚሁ አውራ ጎዳና ዳርቻ ላይ ነው፡፡ ዘላቂ የአካል ጉዳት ያለባቸው ሕፃናትና ታዳጊዎች፣ በወላጅ ወይም ወላጅ ባልሆኑ ግለሰቦች ጠዋት እዚሁ መንገድ ላይ ይተዋሉ፡፡ ዝናብና ፀሐይ ሲፈራረቅባቸው ውሎ ምሽት ላይ በልመና ካገኙት ምፅዋት ጋር አስቀማጮቹ በሸክም ወይም በእጅ በሚገፉ ጋሪ ይወስዱዋቸዋል፡፡

ሌሎች ማረፊያ ቤት እያላቸውና የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ሆነው ደጋፊና አቅም በማጣት ሕፃናት ልጆቻቸውን ይዘው የሕዝብ ዕርዳታ የሚጠይቁትም እዚሁ በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ላይ ነው፡፡ በበሽታ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸውን እናት ወይም አባት ደግፈው በመያዝ፣ የመታከሚያ ገንዘብ ዕርዳታ የሚጠይቁ ታዲጊዎችና ወጣቶችም እዚሁ አዲስ አበባ ጎዳናዎች ላይ መፍትሔ ፍለጋ ይውላሉ፡፡ በሁሉም የከተማዋ አቅጣጫዎች በርካታ የችግር ዓይነቶችንና የዕርዳታ ጥያቄዎችን ማስተዋል ይቻላል፡፡

እነዚህንና ሌሎች ያሉብንን ችግሮች አንስተን ብዙ ጊዜ ተነጋግረንባቸዋል፡፡ በተፈጥሮ አደጋ ክስተቶች፣ በሰው ሠራሽ ችግሮች፣ በተያያዥ ሁኔታዎችና ውጤቶች የተነሳ ድህነት በዚህች ምድር ተንሠራፍቶ መቆየቱንም ደጋግመን አንስተናል፡፡ ችግሮቹን ለመፍታትና ዘላቂ የመፍትሔ አቅጣጫዎች ለማስቀመጥ ግን አልተቻለም፡፡ በተለያዩ ጊዜያት በፌዴራል መንግሥትና በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተደረጉ ጥረቶች መኖራቸውን አስታውሳለሁ፡፡ ግን የተደረጉ ጥረቶች ምን ያህል በጥልቀት የታቀዱ፣ የተጠኑና የተቀናጁ ነበሩ? ለሚለው ጥያቄ ብዙ የማውቀው የለም፡፡ በተጨባጭ የሚታየው ግን በተለይም በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ላይ እነዚህ ችግሮች እየሰፉ መምጣታቸውን ነው፡፡

በመጪው ዓመት የተሻለ ዕቅድና ቅንጅት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና በክልል መስተዳድሮች መካከል ቢፈጠር ችግሮቹን ለመቀነስ እንደሚያግዝ እገምታሁ፡፡ ክልሎች ዘላቂ ጉዳት ላለባቸው ዜጎች በየአካባቢያቸው የማቋቋሚያ ፕሮጀክቶች ነድፈው ተግባራዊ ማድረግ ቢጀምሩ፣ ወደ አዲስ አበባ የሚደረገው ፍልሰት ይቀንሳል፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለዘላቂው የማቋቋሚያ ፕሮጀክቶች የሚሆኑ ጥናቶችን በጋራ በማጥናትና በማዘጋጀት፣ የባለሙያና የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ የሚሳተፍበት መንገድ መፈለግ ይኖርበታል፡፡ ይህ በአዲስ አበባ አስተዳደርና በክልሎች መካከል የሚደረግ መተጋገዝና መደጋገፍ ዘላቂ ጉዳት ያለባቸውን ሰዎች ወደ አዲስ አበባ ከመፍለስ ሊያቆማቸው ይችላል፡፡

በእርግጥ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሊያደርግ የሚችለው ድጋፍና ትብብር ሁሉንም ችግር የሚፈታ ሊሆን አይችልም፡፡ የእሱም አቅም የተመጠነ ስለሚሆን ማለት ነው፡፡ ግን በፌዴራል ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ባለቤትነት ጉዳዩን የመምራት፣ የማስተባበርና የማቀናጀት ኃላፊነት አለበት፡፡ ተጨባጭ ዕቅድና ሊያሠራ የሚችል ፕሮጀክት ከተነደፈ ደግሞ የዕርዳታ ምንጩ የሚቸግር አይመስለኝም፡፡ ከክልል ያልሆኑና የከተማዋ ነዋሪ ሆነው ዘላቂ ጉዳትና ጧሪ የማጣት ችግር ላለባቸው ወገኖች፣ አስተዳደሩ ዘላቂ የመንከባከቢያና መርጃ ሥፍራዎች የማመቻቸት ኃላፊነት አለበት፡፡ ቀደም ሲል በመንግሥታዊ አካል በትንሹ የተጀመሩና ዕድገት ያላሳዩ የእንክብካቤና የመጦሪያ ሥፍራዎች እንደገና ታይተው መሻሻልና ብዙዎችን ማስተናገድ በሚችል ደረጃ ሊደራጁ ይገባል፡፡ በጎ አመለካከት ያላቸው ዜጎች በግል ያቋቋሟቸው የመርጃ ድርጅቶችን ማበረታታትና መደገፍም እንደተጠበቀ ሆኖ ማለት ነው፡፡

መኖሪያና መጠለያ የሌላቸው ዜጎች በእነሱ አቅም ደረጃ ሊያርፉባቸው የሚገቡ አካባቢዎች ሊመቻቹላቸው ይገባል፡፡ ቤት በማኅበር መሥራት ለምንችል ወይም ኮንዶሚኒየም መግዛት ለምንችል የኅብረተሰብ ክፍሎች የሚታሰበው ዕቅድ መልካም ነው፡፡ ግን የከተማዋ ነዋሪዎች ሆነው ሁለቱንም መመዘኛዎች ማሟላት የማይችሉ ወገኖቻችን ከመንገድ ዳር ላስቲክ ዘርግተው እንዲኖሩ መተው የለብንም፡፡ የመጪው ዓመት አንዱ ዕቅዳችን ለእነሱም ችግር መፍትሔ የሚሰጥ ሊሆን ይገባል፡፡

እንደ አካባቢው ሁኔታ ማረፊያና መኖሪያ ኖሮዋቸው ምንም መተዳደሪያ ስለሌላቸው ሕፃናት ልጆቻቸውን ይዘው ጎዳና የወጡ ዜጎች አሉ፡፡ እነዚህም በአግባቡ ተመዝግበውና ተለይተው ባሉበት ዕርዳታ የሚያገኙበት አሠራር ቢዘረጋ፣ አሠራሩ ካለም ሁሉን በአግባቡ ተደራሽ ቢያደርግ ችግሩን መቀነስ ይቻላል፡፡    

ሌላው ከባድ የጤና ችግር እንዳለባቸው በግልጽ የሚታዩ ግለሰቦችን የዕርዳታ ጥያቄ በጎዳናዎች ላይ የሚያቀርቡ ግለሰቦች ጉዳይ ነው፡፡ ታማሚዎቹ ከክልል ወደ አዲስ አበባ በሪፈራል የመጡ ከሆነ ሆስፒታሎቹ ተቀብሎ የማስተናገድና ሕክምና የመስጠት ግዴታ አለባቸው፡፡ ከአዲስ አበባ ከተማም ከሆኑ አሠራሩ ተመሳሳይ ነው፡፡ የመታከሚያ ገንዘብ እጥረት ለተባለው ችግር አቅም ለሌላቸው ተብሎ በመንግሥት ሆስፒታሎች በነፃ የሚሰጥ የቆየ የሕክምና አገልግሎት እንዳለ አውቃለሁ፡፡ ምናልባት እዚያ አካባቢ ላይ የማይመች ሁኔታ ካለ፣ አገልግሎቱን መፈተሽና ችግሮቹን ማስተካከል ያስፈልጋል፡፡ እጅግ የተጎዳ ታማሚ በአውራ ጎዳና ዳር በሰው ተደግፎ መታከሚያ ዕርዳታ ሲለመንለት መመልከት ግን በጣም ያሳምማል፡፡ በመንገድ ሲያልፉ ይህንን ሁኔታ የሚመለከቱ የሕክምና ባለሙያዎች ደግሞ ከሌላው ተመልካች በበለጠ እንደሚያሳምማቸው እገምታለሁ፡፡   

በአጠቃላይ በጤና መጓደል ምክንያትም ሆነ የመሥራት አቅም በማጣት በአውራ ጎዳና ዳር በልመና ለተሰማሩ ዜጎቻችን መፍትሔ ለመስጠት በቂ ጥናት ሊኖረን ይገባል፡፡ መጪው ዓመት ሰብዓዊ ክብራቸውንና መብታቸው በተጠበቀ ሁኔታ ከጎዳና ላይ ተነስተው ዘላቂ ክብካቤና ዕርዳታ የሚያገኙበት እንዲሆን መሥራት ይኖርብናል፡፡ ሕዝቡም ከአስተዳደሩና ከፌዴራል መንግሥት ጎን ቆሞ በሙያውና በገንዘቡ የድርሻውን ያበረክታል ብዬ አስባለሁ፡፡ ሕዝቡ አሁንም ቢሆን በየመንገዱ ዳር ወድቀው ዕርዳታ ለሚጠይቁ ለእነዚህ ወገኖቻችን የአቅሙን እየሰጠ ነው፡፡

ከመንገድ ዳር ተነስተው የተሻለ ሕይወት የሚመሩበት ሁኔታ ከተመቻቸ ደግሞ የምፅዋት አሰጣጥ ሥርዓቱ ይቀየራል እንጂ፣ የሕዝቡ ዕርዳታ የሚቋረጥ አይሆንም፡፡ በፈቃደኝነት ለተቸገረ የሚረዳ ኅብረተሰብ ቀደም ብሎ የተፈጠረ ስለሆነ፣ የሚያስተባብር ማዕከል ሲደራጅ ግንዛቤ ለመፍጠር ብዙም አያደክምም፡፡ ጥሩና ዘላቂ ፕሮጀክት ተነድፎ ዕቅዱ ወደ ተግባር የሚቀየርበት ዓመት ማየትና በዕርዳታው በቋሚነት መሳተፍ የብዙዎች ፍላጎት እንደሚሆን አምናለሁ፡፡ ወገኖቻችን ከመንገድ ዳር ወድቀው መቅረት የለባቸውም፡፡ ድህነት ከምድራችን እስኪወገድ ልመና እንዲቀጥል መፍቀድ የለብንም፡፡ በዚህ ረገድ አረጋውያንና በተለያዩ ደዌ የተያዙ ዜጎችን ለመርዳት መልካም ራዕይ ይዘው የተነሱ ግለሰቦች ጥሩ አርዓያዎቻችን ናቸው፡፡ ዕውቀቱና ራዕዩ ያላቸው ሌሎች ግለሰቦችም ለዚህ ዓይነቱ መልካም ተግባር መነሳሳት አለባቸው፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከክልሎች ጋር በመቀናጀት ዘላቂ ጉዳት ያለባቸው ግለሰቦች በየክልሎቹ የሚረዱበትና የሚቋቋሙበት ሁኔታ ካመቻቸ፣ ግማሽ መንገድ ተጓዘ ለማለት ይቻላል፡፡ አስተዳደሩ ዕርዳታ የሚሹ ወገኖችን እንደየሁኔታቸው ከለየና ሕይወታቸውን መስመር ማስያዝ ከቻለ ደግሞ፣ ከከተማው ሕዝብ ድጋፍ ጋር ሙሉ መንገድ ተጓዘ ለማለት ያስችላል፡፡ ቀሪው ሥራ ጉዞውን ማሻሻል፣ ማጠናከር፣ ማስፋፋት፣ ደረጃውን ማሳደግና ማዘመን ብቻ ይሆናል፡፡ ይህ ከሆነ የከተማ አስተዳደሩ የአውራ መንገዶቹ ዳርቻዎች የእግረኛ መመላለሻ (መጓጓዣ) ብቻ ናቸው ብሎ ደፍሮ መናገርና ሌላውን ተግባር ማስቆም ይቻለዋል፡፡

ሌላው ለከተማዋ ጎዳና እንቅፋት ሆኖ የሚታየው የመንገድ ዳር ንግድ ነው፡፡ ይህ ንግድ ሕጋዊ አለመሆኑ ስለሚታወቅ ሻጮቹ የ‹‹ሌባና ፖሊስ›› ዓይነት ጨዋታ የሚያካሂዱበት ነው፡፡ የከተማ ሥነ ሥርዓት ወይም ደንብ አስከባሪዎቹን ከርቀት ሲመለከቱ በእግረኛ መንገድ ላይ የዘረጉትን ዕቃዎች ሰብስበው ለማምለጥ ሲሞክሩ፣ ለመኪና አደጋም ሆነ ለሌላ ጉዳት እየተዳረጉ ነው፡፡ ሕጋዊ ነጋዴዎችም ገበያቸው ላይ ተፅዕኖ እንዳሳደረ በመግለጽ ስሞታ ሲያቀርቡ ይደመጣሉ፡፡ በንግዱ ተሠማርተው የሚታዩ ግለሰቦችም ወጣቶችና ከአካል ጉዳት ነፃ ሆነው የሚታዩ ናቸው፡፡ በዚህ ዘርፍ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት በመጪው ዓመት አስተዳደሩ ጥሩ ዕቅድ ይኖረዋል የሚል ግምት አለኝ፡፡ ወጣት ሻጮቹን በእግርም ሆነ በመኪና በማባረር የተወሰነ ችግር መቀነስ ይቻል ይሆናል እንጂ ማስቆም ያዳግታል፡፡ ስለዚህ በመጪው ዓመት ሌሎች የተሻሉ አማራጮችን ማየት ሳይሻል አይቀርም፡፡ የሚካሄደው ቁጥጥር እንዳለ ሆኖ ዕቅዶች መሠረታዊ ችግሮቹ ላይ ቢያተኩሩ መልካም ነው፡፡

እንደሚባለው እነዚህ በየመንገዱ ዳር የሚሸጡ ዕቃዎች በከፊል ጉምሩክ ከኮንትሮባንድ ነጋዴዎች ወርሶዋቸው በጨረታ ሽያጭ ያስተላለፏቸው ናቸው፡፡ ቀሪዎቹ ደግሞ ራሳቸው የኮንትሮባንድ ነጋዴዎቹ ኬላዎችን አሳልፈው ለገበያ የሚያቀርቡዋቸው እንደሆኑ ይነገራል፡፡ ዕቃዎቹ በአንደኛው መንገድም ገቡ በሁለተኛው፣ የጨረታ ሥርዓቱን አካሄድ በመቀየርና የኬላዎችን ቁጥጥር እንደገና ፈትሾ በማስተካከል ለመግታት ወይም ለመቀነስ የሚቻል ይመስለኛል፡፡   

ወጣት ሻጮቹን በተመለከተ ደግሞ በየሙያ መስኩ ሥልጠና እየተሰጣቸው፣ ራሳቸውን ችለው ሕጋዊ ሥራ በሕጋዊ ሥፍራዎች የሚያካሂዱበት ዕቅድ ቢነደፍላቸው፣ የመንገድ ዳር ንግዱን ለመቀነስ ይረዳል፡፡ ወጣቶቹም በሥጋትና በመሯሯጥ የመንገድ ላይ ንግድ መቀጠላቸው የማይመች የሕይወት ጉዞ እንደሆነ ያውቁታል፡፡ ስለዚህ ንግዱን በሚያካሂዱባቸው ክፍላተ ከተሞች አካባቢዎች በማስተባበር በየሙያ መስኮች አሠልጥኖ የተሻለ የሕይወት ዕድል ቢሰጣቸው፣ ከመንገድ ዳር ንግድ ጋር የሚያቆራኛቸው ሌላ ምክንያት የሚኖር አይመስለኝም፡፡

ስለዚህ በመጪው ዓመት የፌዴራል መንግሥት፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና የክልል መስተዳድሮች ተግባራዊ የሚሆኑ ዕቅዶች በእነዚህ ዘርፎች ቢያሳዩን የሕዝቡም ተሳትፎ በስፋት ይኖራል ብዬ አስባለሁ፡፡ ዘላቂ የአካልና የጤና ጉዳት ያለባቸው ወገኖች ከየአውራ ጎዳናዎች ተነስተው ክብካቤ የሚያገኙበት ማዕከል የመኖር ዕድል ይመቻችላቸው፡፡ በሕመምና በጉዳት ላይ የሚገኙ ዜጎችን መንገድ ዳር ደግፎ በመያዝ ለሕክምና የሚውል ዕርዳታ ገንዘብ መጠየቅ በሁሉም መንገድ ከሰብዓዊነት ውጪ ስለሆነ ሲያጋጥም ቶሎ የሚረዱበት ሁኔታ ቢፈጠር፣ ካልተቻለም ወደ መኖሪያ ቤት ወይም ሕክምና ማዕከል ተወስደው ተገቢውን ድጋፍ የሚያገኙበት መንገድ ቢታቀድ መልካም ይሆናል፡፡

ማረፊያ ቤት ኖሯቸው አቅም ወይም ረዳት በማጣት ሕፃናት ልጆቻቸውን ይዘው ከጎዳና የወጡ ግለሰቦች በቂ ክትትልና ድጋፍ በቋሚነት በቤታቸው የሚያገኙበትን መንገድ ማቀዱና በተግባር መተርጎሙ፣ ሌላው መታሰብ የሚገባው ተግባር ነው፡፡ የከተማዋ ነዋሪዎች ሆነው መኖሪያ ቤት የሌላቸው ወገኖች ከላስቲክ ቤት ወጥተው፣ አቅማቸውን የሚመጥን ማረፊያ እንዲኖራቸው በዚህ ዓመት ጥረት ሊደረግ ይገባል፡፡ ይኼ ለግለሰቦቹ ከሚሰጠው ጥቅም ባሻገር ትልቅ ደስታን የሚሰጥና የዜጎችን ሕይወት መታደግ ነው፡፡

በሕመም፣ በችግርና በልዩ ልዩ ተያያዥ ምክንያቶች መንገድ ላይ ወጥተው ዕርዳታ የሚጠይቁ ወገኖችን እስከ ዛሬ የአቅማችንን በመለገስ ስንረዳ ቆይተናል፡፡ ነገ ደግሞ መልካም ነገር ታቅዶ ከመንገድ ላይ የሚነሱበት ሁኔታ ቢፈጠር፣ የምፅዋት አሰጣጥ ሥርዓታችን ይቀየራል እንጂ ዕርዳታን አያቋርጥም፡፡ ይኼ የብዙዎቻችን እምነት እንደሚሆን አስባለሁ፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

       

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አያሌ የውኃ “ጠርሙሶች”ን በጫንቃ

መሰንበቻውን በአይቮሪ ኮስት መዲና አቢጃን የምትኖር አንዲት ሴት፣ በሚደንቅ...

ወልቃይትን ማዕከል ያደረገው የምዕራባዊያን ጫና

በትግራይ ክልል የተከሰተው የዕርዳታ እህል ዘረፋ የዓለም አቀፍ ተቋማት...

ከቀጣዩ ዓመት በጀት ውስጥ 281 ቢሊዮን ብሩ የበጀት ጉደለት ነው ተባለ

ለቀጣዩ በጀት ዓመት ከቀረበው 801.65 ቢሊዮን ብር አጠቃላይ በጀት...