Friday, December 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊበአዲስ ቪው ሆቴል ባለቤት ላይ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ተፈቀደ

በአዲስ ቪው ሆቴል ባለቤት ላይ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ተፈቀደ

ቀን:

አራጣ በማበደር ወንጀል ተጠርጥረው በእስር ላይ በሚገኙት የአዲስ ቪው ሆቴል ባለቤት አቶ ዓብይ አበራ ላይ፣ የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቡድን የጠየቀው ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ተፈቀደለት፡፡

መርማሪ ቡድኑ ተጠርጣሪውን በፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ወንጀል ችሎት ለአራተኛ ጊዜ ነሐሴ 17 ቀን 2009 ዓ.ም. አቅርቧቸዋል፡፡ ምንም እንኳን ተጠርጣሪውን በቁጥጥር ሥር ያዋላቸው አራጣ በማበደር ወንጀል ቢሆንም፣ ምርመራ በሚያደርጉበት ወቅት በሕገወጥ የሰዎችና የገንዘብ ዝውውር ወንጀልም መሰማራታቸውን መረዳቱን አመልክቷል፡፡ ተጠርጣሪው በሌሎች የፌዴራል ፍርድ ቤቶችም ክስ ቀርቦባቸው ዋስትና መከልከላቸውንም መርማሪ ቡድኑ ገልጿል፡፡

ከመንግሥት ኃላፊዎች ጋር በመመሳጠር ሰነዶችን ማጥፋታቸውን፣ የመንግሥት ኃላፊዎችን ስም በመጥራት ምርመራ እንዳያደርጉ እንቅፋት እየፈጠሩና የምርመራ ሒደቱንም ውስብስብ እያደረጉባቸው መሆኑን መርማሪ ቡድኑ ለፍርድ ቤቱ ገልጿል፡፡ በመሆኑም ሕገወጥ የሰዎች ዝውውርና ሕገወጥ የገንዘብ  ዝውውር ወንጀሎችን ለመመርመርና ለማጣራት፣ ተጨማሪ 14 የምርመራ ቀናት እንዲፈቀድለት ጠይቋል፡፡

በተደጋጋሚና ተመሳሳይ ሥራዎችን በማንሳት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ሲጠይቅ ለአራተኛ ጊዜ መሆኑን ያስታወሱት የተጠርጣሪ አቶ ዓብይ አበራ ጠበቃ አቶ ደስታ በርሄ፣ መርማሪ ቡድኑ ምርመራውን እንደጨረሰ ለፍርድ ቤቱ ማስረዳቱን አስታውሰዋል፡፡ ደንበኛቸው ተጠርጥረው የታሰሩት አራጣ በማበደር ወንጀል መሆኑንና በዚህ ላይም ምርመራ መጨረሱን ጠበቃው ተናግረው፣ ደንበኛቸውን አስረው ለማቆየት ሌላ ወንጀል እየተፈለገባቸው መሆኑን አመልክተዋል፡፡

በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ አንድ ተጠርጣሪ ከመያዙ በፊት መረጃና ማስረጃዎች ተሰብስበው ማለቅ እንዳለባቸው መደንገጉን ጠቁመው፣ አቶ ዓብይ ግን በእስር ላይ ሆነው ማስረጃ እየተፈለገባቸው መሆኑ ተገቢ አለመሆኑንና ሕጉን የሚቃረን እንደሆነም አመልክተዋል፡፡ በአራጣ ወንጀል በተከፈተ ምርመራ ላይ ሌሎችን ፈልጎ ማካተት ተገቢ አለመሆኑንና ሊዘጋ እንደሚገባም አክለዋል፡፡

መርማሪ ቡድኑ ከመንገድና ትራንስፖርት ባለሥልጣንና ከገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ያልሰበሰባቸው ሰነዶች እንዳሉ የተናገረ ቢሆንም፣ ሰነዶቹ በመንግሥት ተቋማት ውስጥ ያሉ በመሆናቸው ከደንበኛቸው ጋር እንደማይገናኙም አስረድተዋል፡፡ ሕገወጥ የገንዘብ ዝውውርን በሚመለከትም መንግሥት ከውጭ አገር መንግሥታት ጋር ባለው ግንኙነት መሠረት ማስረጃዎችን መሰብሰብ እንደሚችል ጠበቃው ጠቁመው፣ የአቶ ዓብይ በዋስ መፈታት የሚያደርሰው ተፅዕኖ እንደሌለ አስረድተዋል፡፡

የአቶ ዓብይ የባንክ ሒሳቦች በሙሉ መዘጋታቸውን የገለጹት አቶ ደስታ፣ በሌላ ፍርድ ቤት በተመሳሳይ ወንጀል ተከሰው ዋስትና በመከልከላቸው እዚህም ፍርድ ቤት ሊፈቀድላቸው እንደማይገባ መናገር ስህተትና አንድ ሰው በተመሳሳይ ክስ በተለያየ ቦታ ሊከሰስ እንደማይገባ ጠቁመዋል፡፡

መርማሪ ቡድኑ እንደገለጸው አቶ ዓብይ በፌዴራል ፖሊስ ላይ ተፅዕኖ ይፈጥራሉ ሊባል እንደማይገባ ጠበቃው ተናግረው፣ ‹‹ይኼ ትልቅ ተቋም እንኳን ራሱን እኛንም ይጠብቃል፤›› ብለዋል፡፡ አንድ ግለሰብ ተፅዕኖ ያሳድራል ማለት ተቋሙን ዝቅ ማድረግ ነው ብለዋል፡፡ ከመቶ በላይ ሠራተኞች እንዳሏቸው በመግለጽና ፍርድ ቤቱም ይኼንኑ አቤቱታ በማረጋገጥ ቼክ እንዲፈርሙ ትዕዛዝ ቢሰጥም፣ በፖሊሲ እንቢተኛነት የፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ተግባራዊ ሊሆን አለመቻሉንም አስረድተዋል፡፡ ለሠራተኞች ደመወዝ መክፈል ባለመቻሉም ተቋሙ ሊዘጋ መሆኑንም አክለዋል፡፡

ተጠርጣሪው አቶ ዓብይ እንዲናገሩ ዕድል እንዲሰጣቸው ጠይቀው ሲፈቀድላቸው እንደተናገሩት፣ አሁን የታሰሩት ከሦስት ዓመታት በፊት ከአንድ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣን ጋር በመካሰሳቸው፣ ያንን ለመበቀል ሆን ተብሎ በተቀናበረ ወንጀል መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የተጠረጠሩት አራጣ ከማበደር ወንጀል ጋር የተገናኘ ቢሆንም፣ እሳቸው ግን አራጣ አበድረው ሳይሆን ዮሐንስ ኃይለየሱስ ከሚባሉ ግለሰብ ጋር በጋራ የገዙት ፋብሪካ አላዋጣ ሲላቸው በመሸጣቸው ምክንያት፣ በእሱ ላይ የተቀነባበረ ነገር መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ታስረው ባሉበትም ከባድ ተፅዕኖ እየደረሰባቸው መሆኑን፣ ከፍተኛ ሕክምና የሚያስፈልገው ሕመም እንዳለባቸው፣ የቤተሰብ አስተዳዳሪና በቂ ሀብት ያላቸው መሆኑን ተናግረው ዋስትና እንዲፈቀድላቸው ጠይቀዋል፡፡

መርማሪ ቡድኑ ደግሞ ባቀረበው ክርክር ለፍርድ ቤቱ እንዳስረዳው፣ ምርመራው የተጀመረው እንደተገለጸው በአራጣ ወንጀል ተጠርጥረው ነው፡፡ ነገር ግን አራጣውን ሲያጣራ ሕገወጥ የሰውና የገንዘብ ዝውውር እንደሚያከናውኑ መረጃዎች ማግኘቱን ገልጿል፡፡ ሌሎች ተጎጂዎችም እየቀረቡ ነው ብሏል፡፡ ሀብት ያፈሩም ቢሆን፣ በሕገወጥ መንገድ የተገኘ መሆኑንና አንዳንድ ጥገኛ ባለሥልጣናትም ሊኖሩ ስለሚችሉ፣ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ እንደሚያስፈልገው አመልክቷል፡፡

ፍርድ ቤቱ በመሀል፣ ‹‹መዝገቡን የከፈታችሁት ከአራጣ ጋር በተገናኘ ነው፡፡ በተፈቀደላችሁ ጊዜ ምን ሠራችሁ?›› የሚል ጥያቄ ለመርማሪ ቡድኑ አቅርቧል፡፡ መርማሪ ቡድኑ በሰጠው ምላሽ እንዳስረዳው የባንክ ሒሳብ መግለጫ ማሰባሰቡን፣ ከገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ተሽከርካሪ በዝቅተኛ ቀረጥ ያስገቡበትን ሰነድ ማግኘቱን፣ ነገር ግን በዚያው ተቋም ከመሀል ተገንጥሎ የጠፋ ሰነድ መኖሩ ስለታወቀ፣ እሱን በሚመለከት እየሠራ መሆኑን፣ ለተለያዩ ባንኮች ደብዳቤ መበተኑንና ሌሎች በርካታ ሥራዎችን ማከናወኑን ገልጿል፡፡ በዋስ ቢወጡም ተፅዕኖ ስለሚፈጥሩ የምርመራ ሒደቱን እንደሚያበላሹበት በማስረዳት፣ ዋስትናው ውድቅ ተደርጎ የጠየቀው ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ እንዲፈቀድለት ጠይቋል፡፡

ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማ በኋላ በሰጠው ትዕዛዝ ተጠርጣሪው የጠየቁትን የዋስትና መብት እንዳልተቀበለ ገልጾ፣ ለተጨማሪ ምርመራ አሥር ቀናት መፍቀዱንና ለነሐሴ 27 ቀን 2009 ዓ.ም. ቀጠሮ መስጠቱን አስታውቋል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...