Thursday, June 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

እስከዚያስ?

እነሆ መንገድ። ያጠበቁት እየላላ፣ ያላሉት እየጠበቀ፣ በፍየል ወዲህ ቅዝምዝም ወዲያ ግራ መጋባት የሄድንበትን መንገድ ደግመን ልንሄድበት ታክሲ  ተሳፍረናል። ከኮልፌ ወደ ቀራንዮ። ቁጭት፣ ሰቀቀን፣ ተስፋ ማጣት፣ ማግኘት፣ ጉትትና ጉጉት የለሽነት ውስጥ ሆነው ብዙ ተሳፋሪዎች ተደራርበው ቆመዋል። አንዱ አቀርቅሮ ስልኩን ይጎረጉራል። አንዱ ውልብታውን በመስኮት አነጣጥሮ እንደ ፊልም እያየ፣ ያለበትን ረስቶ አፍንጫው እስኪደማ ይጎረጉረዋል። በዚህ ቀልበ ቢስ የሚጠቋቆሙ ወጣቶች የማያስቀው ሁሉ አሳቀን እያሉ ይንከተከታሉ። ባለተራ ሆኖ ያሳቃቸው ቀስት ወደ እሱ እንዳይነጣጠር የሰጋ ርብትብት ደግሞ ምንም ሳይገባው ያጅባቸዋል። ታክሲያችን ጥቂት ሳብ ጥቂት ቆም እያለ ይወዛወዛል፡፡ ወሬ የተከለከለ ይመስል ተሳፋሪዎች እርስ በርሳቸው እየተፋጠጡ ቆይተው አንገታቸውን የደፉት ያቃናሉ። በአንፍጫ ጎርጓሪው ቀልበ ቢስነት ተመስጠው ፌሽታ ከፈጠሩት ወጣቶች ፊት ለፊት የተቀመጡ ወይዘሮ አንዴ ጆሯቸውን እየነካከኩ፣ አንዴ ወደ መንጋጋቸው የእርቅ ጣታቸውን ሰደው ስንቅር አኞ እየፈለጉ ነገረ ሥራቸው አልጥም ያላቸውን ወጣቶች ይታዘባሉ። 

ወያላው በተደጋጋሚ ብቅ እያለ፣ ‹‹ይኼ ፀረ ሲጋራ በረራ ነው። ማንም ሰው እሳት መለኮስ፣ ነገር ማቡነን አይችልም፤›› እያለን ይሄዳል። የመረረው፣ “አቦ ይኼ ነገር ምንድነው? ሐበሾች እኮ ነን። እንኳን ነገር ተደጋግሞብን እንዲሁም ጠርጥረን ዱር የምንመነጥር፤” ይላል አንድ አጭር ደንዳና። አዛውንቷ ፈገግ ብለው እያዩት፣ “አንተስ ብትሆን ስለነገር አዋቂነታችን ለማውራት ምን ይኼን ያህል ጉልበት ያስጨርስሃል? ‘ምሳር ባወቀበት ደን ይመነጥራል፣ አትቀደም ያለው በዓይን ‘ይጠረጥራል› ብለህ ዝም አትልም?›› አሉት። ‹‹ይቅር ይበሉኝ እማማ። ጨዋታው የመቀደምና ያለመቀደም መሆኑ አልገባኝም ነበር፤›› ብሎ እንደ ሽርኩ በዓይኑ ሲጠቅሳቸው እንዳላዩ አለፉት። ሳይገባው የገባው መስሎ የሚታየው በዝቶም ይሆናል እኮ ክልከላና ማስጠንቀቂያው የሚያጨናንቀን!

 ወያላው፣ “እስኪሞላ ስለመሠረተ ልማት ምናምን አውሩ እስኪ፣ እኔ ላይ አታፍጥጡ፤” ይላቸዋል ከሾፌሩ ጀርባ የተሰየሙ ወጣት ሴቶችን እየገላመጠ። አንደኛዋ ቆንጅት አልዋጥላት ብሎ፣ “ትንሽ ቆይተህ ጠጋ በይ ለማለት ነው ነቅቼብሃለሁ። አልሰማህም፤” ትለዋለች። ወያላው ወዲያው በስጨት ብሎ፣ “ምን ስለሆንሽ ነው የማትጠጊው? ዘለዓለም ከአንቺ ጋር ድብድብ? ቆይ ለምን የእኔን ታክሲ መርጠሽ ትሳፈሪያለሽ?” ብሎ ጮኸባት። የወያላውና የለግላጋዋ ትውውቅ የዛሬ ብቻ አይመስልም። “ማንነትን ትርፍ መሀል ምን አመጣው? ትርፍ መጫን ወንጀል ነው! ወንጀል ነው!” ብላ በስምንት ነጥብ ዘነጋችው። “አንተ በቃ ተዋት። የራስህ ጥፋት ነው። ገና በሩቁ ስታያት አልጭንሽም አትላትም፤” ብሎ ሾፌሩ መዓት ከወረደበት በኋላ ጋቢና ወደተሰየሙት ሹክክ ብሎ፣ ‹‹ይኼ ሁሉ ሰው ቆሞ በፀሐይ ሲቀቀል እያየች ምንም አይመስላትም። እሷም እንዲችው ስትቀቀል ትውላታለች እንጂ ትርፍ ልጫንሽ ብትላት እሺ አትልም፤” ይላል።

ይኼኔ ሰምታው፣ “ፀሐይ ብርቅ ነው ታዲያ? እንኳን የክረምቱን ፀሐይ ለበጋውም አልተበገርን፤” ቱግ አለች። “ተረፋችኋ! እናንተ ስትተርፉ እኛ ምን እናድርግ?” ወያላው የሚያቆም አይመስልም። አዛውንቷ ይኼኔ፣ ‹‹እባካችሁ ይብቃችሁ። አንቺም አንዴ አቋምሽ ታውቋል ዝም በይ። አንተም ገና ለገና በአገሩ አንድ ሰው ዘራፍ አለብኝ ብለህ ግስላ አትሁን። መብቷ ነው። መደራረብ እኮ ለእኛም ቢሆን የውዴታ ግዴታ ሆኖብን እንጂ ፍላጎታችንም መብታችንም አይደለም። ዱላውን እስኪያቀብሉን ድረስ ማራቶኑን መቻል ነው፤” ብለው ውኃ ሲቸልሱበት ነገሩ በረደ። መትረፋችን ሳያንስ ትርፍ የምንነጋገረው ነገር ባሰን!

         ጉዞው ከተጀመረ ቆይቷል። ማንም እንዳይደረብብኝ ካለችው ሞጋች በስተቀር ሁሉም ወንበር ላይ ትርፍ ተገጥግጧል። ወያላው በዚህ መሀል እያንዳንዱን ሒሳብ ካላመጣችሁ ብሎ ይተናነቀናል። “እባክህ ፋታ ስጠን? ገና ለገና ወደ ቀራንዮ ጫንኳቸው ብለህ መስቀል ታሸክመናለህ?” ይለዋል አንዱ። ወያላው ዝም። ይኼኔ ሦስተኛው ረድፍ ከጎልማሳው አጠገብ የተየመች ወይዘሮ፣ ‹‹የራሱን መስቀል ያልተሸከመ ሰው ማን አለ? ይኼ እኮ በመፈጠር ዕጣ የሚታደልህ እንጂ ታክሲ ስትሳፈርና ስትወርድ የሚጫንብህ አይደለም፤” አለችው። እንዲያ ስትለው ቀራኒዮን በመስቀል አዋዝቶ ያነሳው ተሳፋሪ ዝም ብሎ አያት። ዝም አለኝ ብላ ቀጠለች። ‹‹ይህቺ ዓለም እኮ ሰጥቶ በመቀበል ሒሳብ ብቻ ሳይሆን የምታምነው ሒሳብ በማወራረድም ነው። እያንዳንዳችን ሒሳብ ሳናወራርድ ከዚህች ሕይወት ውልፍት ማለት የለ፤” ትላለች። ‹‹እሱንማ እየያነው ነው። ብቻ ሒሳቡ አልቋል ብለው በሕዝብ ንብረት የቀለዱትን ማወራረድ እንዳያቆሙ እንጂ፤›› አለ ጎልማሳው ፈገግ ብሎ።

      ወይዘሮዋ፣ ‹‹ገና ምኑን ዓይተህ። ገና ብዙ እንወራርዳለን። ገና ብዙ እንመራመራለን፡፡ ያልተመረመረ ሕይወት ደግሞ ሕይወት ነው እንዴ?” ስትለው፣ “ግን ኑሮንስ? ራሷ ሕይወትን እንዴት እናወራርዳት? እሱም አለ እኮ፤” ብሎ ሥጋት ያዘው። ‹‹ኑሮ ማለት እኮ ምላስ ነው የእኔ ልጅ። ንግግርህን ሳትመረምርና ሳታወራርድ በረከትህን ከመርገምህ መለየት አትችልም። ዘረኝነት፣ ስድብ፣ ጥላቻ፣ በቀል የሚያጭሩና የሚበረታቱ ያልታረሙ ንግግሮችን፣ ያልተገሩ አስተሳሰቦችን፣ እያራመድን መስሎኝ ደህና ተስፋ የሰጠን እንቅስቃሴ ሁሉ እንዲህ ውርጭ የወረሰው፤›› አሉት ወይዘሮዋ። ፖለቲካ ሊናገሩት መስሎት በጥርጣሬ ዓይን አያቸውና ዝም አለ።

ወያላው ሒሳብ ስብስቦ መልስ ይበትናል። ሆላንድ ኤምባሲን እንደጨረስን አንጠጋጋም ያለችው ተሳፋሪ ከእነ ጓደኛዋ ወረደች። ወያላው፣ ‹‹ሁለተኛ እንዳላያችሁ እያለ፤›› ይዝታል። ‹‹እንዴ ምን ሊላቸው ነው ይኼ ልጅ? በገዛ አገራቸው? በገዛ መሬታቸው?” ትላለች ወይዘሮዋ። ‹‹ኧረ እባክሽ ሴትዮ ዝም በይ። ዝም ብለሽ መብቷ ብቻ አትይም? አገር፣ መሬት፣ ቅብጥርስ ምን ያስብልሻል? ልታስወነጭፊብን ነው እንዴ?” ብሎ መጨረሻ ወንበር የተሰየመ ወጣት ደነፋ። “በገዛ አፌ ምን አገባህ? አስቸኳይ ግዜ አዋጁን እንደሆነ አርግዘን ተገላግለነዋል፤” ብላ ዞራ ልትገጥም ስትል አዛውንቱ፣ “እናንተ ሰዎች እርቧችሁ ነው? ሆዳችሁ ባዶ ነው? ከሆነ ንገሩንና ምግብ እንዘዝላችሁ። በተረፈ ሆዳችሁ ካልጎደለ ምንድነው በትንሽ ትልቁ ሽቅብ ሽቅብ የሚላችሁ? እኛም እኮ ያለመለከፍ መብት አለን፤” ሲቆጡ ጫጫታው ረጭ አለ። አጠገቤ እናትና ልጅ ተሰይመዋል። ሚሚ ቀልባችንን መሳብ ጀምራለች። 

ከታክሲው ንጭንጭ ያለያየን ቢመስለንም መልሶ ስለታክሲ መሆኑ አልቀረም። “ማሚ ለምንድነው ሁሌ ብር መኪና ውስጥ ለሌላ ሰው የምትሰጭው?” ጠየቀች ሚጡ። “እየሰጠሁ ሳይሆን እየከፈልኩ ነው እናትዬ። ካልከፈልን እኮ አይወስዱንም፤” እናት አባብላ ታስረዳለች። “ለምንድነው ሁሉም ነገር የሚከፈልበት?” ብላ መልሳ ስትጠይቃት ተሳፋሪው እየተሳሳቀ ማደግን ይረግማል። እናት፣ “ይኼ ለእነሱ ሥራ ነው፣ እኔ ሥራ ሠርቼ ለአንቺ ከረሜላ፣ ብስኩት፣ ልብስ፣ እንደምገዛልሽ እነሱም ሰው በመኪና እየወሰዱ ለልጆቻቸው ልብስ፣ ከረሜላ ይገዛሉ። ገባሽ?” ገባት ብለን ስንጠብቅ ሌላ ጥያቄ መጣ። “ግን ከረሜላም፣ ብስኩትም፣ ልብስም፣ ምግብም፣ ታክሲም፣ ሁሉም ነገር ለምን ይከፈልበታል? ለምን ሁሉም በነፃ የፈለገውን እየበላ ደግሞ እየሰጠ አይኖርም?” ብላ ብትጠይቅ ጥያቄና መልሱን መቋጫው የጨነቃት እናት፣ ‹‹እሱ ስታድጊ ይገባሻል . . . ›› ብላ አለፈቻት። ከገባን የተምታታብን እንደማይብስ ሁሉ!

ወደ መዳረሻችን ተቃርበናል። አንዱ፣ “አሁን ይኼ ሁሉ ትዝታ ከመፈንቀል በአጭሩ ኮንዶሚኒየም ተመዝግቤያለሁ ዕጣ አልወጣልኝም አይልም? እኔን ጨምሮ እስኪ አሁን ጎል መክተት፤” እያለ ስልኩን ይነካካል። “ማንነው?” አለችው ከጎኑ የተሰየመች። “አንድ ወዳጄ ነው እንጂ። ሥራ ላስቀጥረው አንድ መሥሪያ ቤት ልኬው ጥያቄና መልሱን ሁሉ የሚያገኘው ከሙስናና በሥልጣን ከመባለግ ጋር ነው ብለውኝ እኮ . . . ፤” ሲል፣ “የመንገዱ ፀባይ ነው። ምንም ማድረግ አይቻለም። ይኼ መንገድ እንደሆነ ገና ብዙ ብዙ ያነጋግራል። እንዲያውም እኛ እኮ አንነጋገርም ያልነው፤” ብላ ጣል አረገችበት። “ኤድያ። ተነጋገርን አልተነጋገር ደግሞ እኛ። ገና ሀ ብለን ሁ ሳንል በየፊናችን ዱላና እብሪት ሲቀድመን ነው የኖረው። ተጨነቁ ብሏችሁ፤” አለች ሌላዋ። “የለም። እንደዚያማ አይባልም። በአሥር ሚሊኒየም አንዴም ቢሆን መነጋገር ጥሩ ነው። ይህቺን ታህል ያኖረን ምን ሆነና? ደህና ዋልክ፣ ደህና አደርሽ መባባላችን አይደለም እንዴ?” ሲላት ከጀርባዋ የሚወዛወዝ ጎልማሳ፣ “እሱማ የእግዜር ሰላምታ ነው። ደግሞ በእሱም በአዋጅ እስኪከለከል እንታዘብ እንዴ? እንዴት ያለ ነገር ነው፤” ብላ መለሰችለት።

“ታዲያ የምን ንግግር ነው እሱ የናፈቃችሁ?” ጠየቀ ጎልማሳው ግራ ገብቶት። “የአንተ ትብስ የአንቺ ትብስ ነዋ። ‘ይኼው ጥፋትህ እንዲህ ያደረግከው፣ እንደዚህ ቢሆን ነበር መልካም’ ሲባል ‘ነው? ልክ ነው ተቀብያለሁ! ተሳስቻለሁ’ የምንባባልበት ንግግር ነው ያልንህ? አይደለም? ነው?” ብላ ዙሪያ ገባዋን ስትቃኝ አዛውንቱ፣ ‘”እሱማ ዱላውን መቀባበል ስንጀምር መሆኑ አይቀርም። ነፍሳቸውን ይማረውና የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር የማይተካ ነገር የለም። ሩጫው ዱላ ቅብብል እንጂ ማራቶን አይደለም ብለው አልነበር። አይዟችሁ ዱላውን አንዴ መቀበል ከጀመርን ከዚያ እንኳን ንግግር ዝምታውም ወርቅ ይሆናል፤” ሲሉ ተሳፋሪው በኅብረት በአንድ ድምፅ “እስከዚያስ?” ብሎ በጥያቄ ጮኸ። “መጨረሻ” ብሎ ወያላው በሩን ሲከፍት ከእነ ጥያቄያችን ወርደን ማዝገም ጀመርን። እውነት እኮ ነው እስከዚያስ? መልካም ጉዞ!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት