የፊንጫ አመርቲነሼ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ በብልሽት ምክንያት አገልግሎት መስጠት አቆመ፡፡ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ወለጋ ዞን በ237.8 ሚሊዮን ዶላር ያስገነባው የፊንጫ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ፣ 97 ሜጋ ዋት ኃይል የማመንጨት አቅም ነበረው፡፡
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኃይል ማመንጫ ኦፕሬሽን ሥራ አስፈጻሚ አቶ አንዳርጌ እሸቴ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የፊንጫ አመርቲነሼ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ባጋጠመው የቴክኒክ ብልሽት በአሁኑ ወቅት ኃይል እያመነጨ አይደለም፡፡
‹‹ችግሩን በመፍታት ጣቢያው ኃይል እንዲያመነጭ ማድረግ የሚያስችሉ መሣሪያዎች ግዥ ተፈጽሞ ወደ አገር እየገቡ ነው፡፡ ዕቃዎቹን የሚያቀርበውም ቀደም ሲል ግንባታውን ያካሄደው ሲጂጂሲ ኦሲ ኩባንያ ነው፤›› ሲሉ አቶ አንዳርጌ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
የፊንጫ አመርቲነሼ ፕሮጀክት ግንባታ ያካሄደው የቻይናው ሲጂጂሲ ኦሲ ኩባንያ ሲሆን፣ ግንባታውን ካጠናቀቀ በኋላ ለተፈጠሩ ችግሮች ማረሚያዎችን አካሂዶ ፕሮጀክቱን እንዲያስረከብ ማሳሰቢያ እንደተሰጠው ሪፖርተር መዘገቡ ይታወሳል፡፡
ኩባንያው ይህንን ሥራ አጠናቆ ካስረከበ በኋላ የገናሌ ዳዋ ቁጥር ሦስት ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክትን ተረክቦ ግንባታውን በማካሄድ ላይ ይገኛል፡፡
የቻይናው ኩባንያ ሲጂጂሲ ኦሲ ፕሮጀክቱን ካስረከበ በኋላ የኦፕሬሽንና የጥገና ሥራዎችን የሚያካሂደው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ቢሆንም፣ የኃይል ማመንጫ ጣቢያው ያጋጠመውን ችግር ፈትቶ ወደ ሥርጭት ማስገባት አለመቻሉን ምንጮች ገልጸዋል፡፡
ፊንጫ በቴክኒክ በኩል ካጋጠመው ችግር በተጨማሪ ወደ ግድቡ የሚገባው ውኃ መጠንም አጥጋቢ እንዳልሆነ እየተገለጸ ነው፡፡
አቶ አንዳርጌ እንደሚሉት፣ እስካሁን ከተወሰኑ ግድቦች በስተቀር በአጠቃላይ በክረምቱ ወራት የጣለው ዝናብ በቂ ባለመሆኑ የውኃ አገባቡ አጥጋቢ አይለም፡፡
ነገር ግን አጠቃላይ ግድቦቹ የያዙት ውኃ የሚታወቀው በመስከረምና በጥቅምት ወራት ነው፡፡ በሚቀጥሉት ወራት የክረምቱ የዝናብ መጠን የተሻለ ይሆናል ተብሎ ስለሚጠበቅ፣ በተፈጠሩ የቴክኒክ ችግሮች ምክንያት ግን በኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት በኩል ችግር እንዳልተፈጠረ አቶ አንዳርጌ ገልጸዋል፡፡
ነገር ግን በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥም ሆነ የአቅርቦት ችግር እየተስተዋለ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡