Friday, June 2, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በአፍላቶክሲን ጉዳይ መጠየቅ የሚገባው የአውሮፓ ኅብረት ነው ተባለ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኅብረቱ ልዑክ ስለጉዳዩ የማውቀው ነገር የለም ብሏል

የተለያዩ ቅመማ ቅመሞችን ወደ አውሮፓ የሚልኩ ነጋዴዎች፣ በመንግሥት አሠራር ሳቢያ ምርታቸውን መላክ እንዳልቻሉ በመጥቀስ በቀረበው ዘገባ ላይ ምላሽ የሰጠው የምግብ፣ መድኃኒትና ጤና ክብካቤ አስዳደርና ቁጥጥር ባለሥልጣን ተገቢውን እየሠራ እንደሚገኝ በማስታወቅ ይልቁንም በአፍላቶክሲን ጉዳይ መጠየቅ የሚገባው የአውሮፓ ኅበረት ነው በማለት ወቀሳውን አሰምቷል፡፡

‹‹የአውሮፓ ኅብረትን ዝቅተኛ የአፍላቶክሲን ደረጃ ያሟሉ በርበሬ ላኪዎች ከገበያ ውጭ የመሆን ሥጋት ገብቷቸዋል፡፡ ለሥጋታቸው መነሻው የመንግሥት አሠራር ነው፤›› በሚል ርዕስ ሪፖርተር በነሐሴ 7 ቀን 2009 ዓ.ም. ዕትሙ ያስነበበውን ዜና መነሻ በማድረግ በባለሥልጣኑ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ዳይሬክተር አቶ አያልሰው መለሰ ለሪፖርተር ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ በዘገባው ውስጥ ሪፖርተር ያነጋገራቸው በርበሬ ላኪዎች የአውሮፓ ኅብረት በቅርቡ ባሻሻለው ሕግ መሠረት፣ ወደ አባል አገሮች የሚገባው በርበሬ በውስጡ እንዲኖረው የሚፈቀደው የአፍላቶክሲን ይዘት በኪሎ ግራም ከአሥር ማይክሮ ግራም መብለጥ እንደሌለበት መጥቀሳቸው ተመልክቷል፡፡ ይሁንና ይህንን በመመልከት የኤክስፖርት ማረጋገጫ መስጠት የሚጠበቅባቸው መንግሥታዊ ተቋማት ለላኪዎቹ ማረጋገጫ ለመስጠት እያቅማሙ በመሆናቸው፣ የበርበሬ የወጪ ንግድ ከአውሮፓ ገበያ ውጭ የመሆን ዕድሉ ከፍተኛ መሆኑ እንዳሰጋቸውም ተዘግቦ ነበር፡፡

አቶ አያልሰው እንዳብራሩት ከሆነ፣ በአፍላቶክሲን ጉዳይ ላይ የአውሮፓ ኅብረት ያስቀመጠውን መመርያ መሠረት በማድረግ ወደ አውሮፓ የሚልኩ ነጋዴዎች የገጠማቸውን ችግር ለመፍታት ጥረት ሲደረግ ቆይቷል፡፡ ቅሬታ ያቀረቡት ነጋዴዎችን በመጥቀስ ጭምር ምን ያህል ድጋፍና ክትትል ሲደረግላቸው እንደነበርም አብራርተዋል፡፡

ነገሩ የጀመረው የአውሮፓ ኅብረት በጥር ወር ያወጣው የአፍላቶክሲን አዲስ መመርያ መነሻነት እንደሆነ ከሥር መሠረቱ ያብራሩት አቶ አያልሰው፣ ኅብረቱ ከኢትዮጵያ ወደ አባል አገሮች የሚላከው የምግብ ምርት በተለይም በርበሬ ውስጥ የአፍላቶክሲን ይዘት እየተገኘ ነው በማለት መግባት የሚችለው በርበሬም ሆነ ሌላው ምግብ ነክ ምርት ዝቅተኛ ደረጃውን ማሟላት እንደሚጠበቅበት ይፋ አድርጓል ብለዋል፡፡ የአውሮፓ ኅብረት የምግብ ደኅንነት ባለሥልጣን አወጣ የተባለው መመርያ በሚላከው የምግብ ምርት ውስጥ መገኘት የሚገባውን ዝቅተኛ የአፍላቶክሲን ይዘት ብቻም ሳይሆን፣ ይህንን በማረጋገጥ የምስክር ወረቀት አያይዞ መላክ የሚገባውን መንግሥታዊ መሥሪያ ቤት ጭምር በማስቀመጡ የተፈጠረ ችግር እንደሆነም አቶ አያልሰው አብራርተዋል፡፡

ይኸውም ኅብረቱ የጥራት ደረጃው ዕውቅና በተሰጣቸው ላቦራቶዎች ተረጋግጦ ወደ አባል አገሮች የሚላከው ምርት፣ የጥራት ደረጃውን አሟልቷል በማለት የምስክር ወረቀት እንዲሰጥ የፈለገው አካል የግብርናና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴርን በመሆኑ ምክንያት የተፈጠረ ችግር እንጂ ባለሥልጣኑ አገልግሎቱን ባለመስጠቱ ሳቢያ ላኪዎቹ የገጠማቸው የአሠራር ችግር እንደሌለ ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል፡፡

‹‹የላቦራቶሪ ውጤትን የፍተሻ ቁጥር ጠቅሰን ተመርምሮ ደረጃውን አሟልቷል ብለን እንልካን፡፡ ችግር የገጠመን ግን የአውሮፓ ኅብረት እንደ አገር የጤና ሰርቲፊኬት መስጠት አለበት ብሎ ያሰበው ባለሥልጣኑን ሳይሆን ሚስቴሩን ነው በማለቱ ነው፡፡ እንዲህ ብለው በመደምደማቸው የተፈጠረ ችግር ነው፤›› ያሉት አቶ አያልሰው፣ የባለሥልጣኑ ኃላፊዎች የፈረሙበትን ማረጋገጫ ኅብረቱ አልቀበልም በማለቱ ምክንያት ላኪዎች ምርቶቻቸውን ወደ አውሮፓ ለመላክ ሲቸገሩ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

ይህ ከተፈጠረ በኋላ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርም ጉዳዩን እንዲያወቀው በማድረግ ለመፍታት መሞከሩን ጠቅሰዋል፡፡ በአዲስ አበባ የሚገኘው የኅብረቱ ልዑክ ስለጉዳዩ ደብዳቤ በመጻፍ፣ የምግብ ጤንነት ማረጋገጫውን የሚሰጠው መንግሥታዊ አካል ማን እንደሆነና  ሕጋዊ ሰውነቱ እስከምን ድረስ እንደሆነ መጠየቁን አቶ አያልሰው አስታውሰው፣ ባለሥልጣኑን በመወከል በጻፉት ደብባቤም በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ መሠረት ይህ ለባለሥልጣኑ የተሰጠው ኃላፊነት መሆኑን አብራረተው በመጥቀስ ምላሽ እንደሰጡ ገልጸዋል፡፡

ምርቶች በአውሮፓ ኅብረት ያልተገባ ጥያቄ ምክንያት እንጂ በባለሥልጣኑ ችግር እንዳልሆነ፣ ይልቁንም ባለሥልጣኑ ቀድሞ በመሄድ ኅብረቱ ያወጣቸውን ግዴታዎች በመንተራስ ለሚላኩ ምርቶች ማረጋገጫ በመስጠት አገልግሎት ሲሰጥ እንደቆየ አብራርተዋል፡፡ ማረጋገጫ የሚሰጠውም በሚቀርብ ጥያቄ መሠረት በፍላጎት ላይ ተመሥርቶ እንጂ በባለሥልጣኑ አስገዳጅነት የሚሰጥ እንዳልሆነም መገንዘብ እንደሚገባ ጠቅሰዋል፡፡

ከዚህም ባሻገር የአውሮፓ ኅብረት መንግሥታዊ አካል ማረጋገጫ የሰጠበት ስለመሆኑ ማረጋገጥ እንጂ፣ የትኛው መሥሪያ ቤት ማረጋገጫ መስጠት እንዳለበት መወሰኑ አግባብ እንደልሆነ አስታወቀዋል፡፡ ባለሥልጣኑ ኅብረቱ የሚጠይቃቸው መሥፈርቶች መሟላታቸውን በማረጋገጥ ምርቶች እንዲላኩ እያገዘ ቢሆንም፣ ኅብረቱ ይህን ችላ በማለት ምርቶች እንዳይገቡ የሚያደርግበት ክልከላ ካለ ግን ጉዳዩ የጤና ማረጋገጫ ሰርቲፊኬት ሳይሆን፣ የኢትዮጵያ ምርቶች ሆን ተብሎ ወደ አባል አገሮቹ እንዳይገቡ የሚደረግ ሴራ ሊሆን እንደሚችል ሥጋታቸውን ገልጸዋል፡፡

ስለጉዳዩ ሪፖርተር በስልክ ያነጋገራቸው የአውሮፓ ኅብረት ልዑክ፣ የፖለቲካ፣ የፕሬስና የኢንፎርሜሽን ክፍል ኃላፊ ሚስተር ሮበርት ዋዴ፣ ስለጉዳዩ የሚያውቁት ነገር እንደሌለና አዲስ አበባ በሚገኘው የልዑኩ የሥራ ምድቦች ውስጥም ይህንን ጉዳይ የሚያውቅና የሚያብራራ ኃላፊ በአሁኑ ወቅት እንደሌለ ተናግረዋል፡፡

ከበርበሬ ባሻገር የለውዝ ምርትን ጨምሮ ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ ምርቶች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአፍላቶክሲን ሳቢያ ችግር ሲገጥማቸው እየታየ ነው፡፡ አፍላቶክሲን ‹‹ኤስፐርጊለስ ፍሌቨስ›› እና ‹‹ኤስፐርጊለስ ፓራሲተከስ›› በተባሉ የፈንገስ ዝርያዎች የሚከሰት አደገኛ ኬሚካል ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች