[ክቡር ሚኒስትሩ ለወዳጃቸው ባለሀብት ስልክ ይደውላሉ]
ሄሎ ወዳጄ፡፡
ሄሎ ክቡር ሚኒስትር፡፡
ሰሞኑን ምነው ጠፋህ?
ፆም ስለነበር ነዋ፡፡
ዛሬ እኮ ስልክህን በጣም ጠብቄ ነበር፡፡
ቁርጥ እንድንቆርጥ ብለው ነው?
እህሳ ወዳጄ፡፡
ቁርጥ ተውኩ እኮ ክቡር ሚኒስትር፡፡
እንዴት ሆኖ?
ሐኪም ከለከለኝ፡፡
በፊትስ ሐኪም ይከለክልህ አልነበር እንዴ?
ክቡር ሚኒስትር አሁን እኮ በየቀኑ እየጨመረብኝ ነው፡፡
ግብሩ ነው?
ኧረ ስኳርና ደም ግፊቱ፡፡
ምን ሆነህ?
ሰሞኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያሉትን አልሰሙም እንዴ?
ምን አሉ?
ፊታችንን ወደ ባለሀብቱ እናዞራለን ብለዋል እኮ?
ለምን?
በሙስና በግብር ማጭበርበር ነዋ፡፡
ታዲያ አንተ ምን አገባህ?
እንዴት አያገባኝ?
ተነካክተሃል እንዴ?
ክቡር ሚኒስትር ከሰው ስህተት ከብረት ዝገት አይታጣም ሲባል አልሰሙም?
ስለዚህ ተሳስቻለሁ እያልከኝ ነው?
ፍፁም ነኝ ማለት ይከብደኛል፡፡
እሱን እንግዲህ ጊዜ ይፈታዋል፡፡
ክቡር ሚኒስትር አሁንስ ተጨንቄ ልሞት ነው፡፡
ምን ሆነህ?
ካሁን ካሁን ያዙኝ እያልኩ ነዋ፡፡
ኧረ ይኼን ያህል አትጨነቅ፡፡
ክቡር ሚኒስትር ከሁሉ በላይ የልጆቼ ጉዳይ ነው የሚያሳስበኝ፡፡
ምን እንዳይሆኑ ነው?
ምን አላቸው ያለ እኔ?
ሦስት ሕንፃዎችና ሦስት ፋብሪካዎች ነዋ፡፡
እኔን ካስገቡኝ እነሱስ ቢሆኑ መታገዳቸው መቼ ይቀራል?
አንተ እኮ በአካል ነው እንጂ በሐሳብ ገብተሃል፡፡
የት ክቡር ሚኒስትር?
ቂሊንጦ፡፡
እውነትዎትን ነው አንደኛዬን ገብቼ ባርፈው ይሻለኛል፡፡
ለማንኛውም ዛሬ የደወልኩልህ የልምዳችንን እንድናደርስ ነው፡፡
ስነግርዎት ክቡር ሚኒስትር አልበላም፡፡
ስማ እዛ ደንበኛችን ጋ ለምሳ ቦታ ይያዝልን ብያለሁ እኮ፡፡
እኔ እኮ ፆም ላይ ነኝ፡፡
ተፈታ አይደል እንዴ?
በዚህኛው ፆም እኮ እስከ 21 ነው የምፆመው፡፡
እንዴ ለምን?
አሁን የመጣው የሙስና ጎርፍ እንዳይወስደኝ ነዋ፡፡
እና ፆሙን ቀጥለኸዋል?
እስካሁን እግዚአብሔር ይቅር እንዲለኝ ነበር የፆምኩት፣ ከዚህ በኋላ ያለውን ደግሞ መንግሥት ይቅር እንዲለኝ ነው፡፡
መንግሥት ምንድነው ይቅር የሚልህ?
በማወቅ በድፍረት. . .
እ. . .
ሳላውቅ በስህተት ለሠራሁት!
ለሠራኸው ምን?
ሙስና!
[አንድ ሀቀኛ ባለሀብት ለክቡር ሚኒስትሩ ደወለላቸው]
ሰላም ክቡር ሚኒስትር፡፡
ሰላም ወዳጄ፡፡
በጣም ጠፉ እኮ ክቡር ሚኒስትር?
የሥራችንን ፀባይ እያወከው?
እሱማ ይገባኛል፡፡ ሰሞኑን እንደውም ሳስብዎት ነበር፡፡
በምን ጉዳይ?
አይ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት በሙስና ተጠርጥረው መታሰራቸውን ስሰማ ትዝ ብለውኝ ነበር፡፡
በሙስና እጠረጥርሃለሁ እያልከኝ ነው?
ኧረ እንደዛ ማለቴ አይደለም፡፡
ታዲያ ምን እያልክ ነው?
በጉዳዩ ዙሪያ እንድንጨዋወት ብዬ ነው፡፡
እእእ. . .
እርስዎማ በዚህ እንዴት ይጠረጠራሉ?
ሁሉም ሰው መቼ እንዳንተ ያውቀኛል ብለህ ነው?
እርስዎን ሙሰኛ ናቸው ብሎ የሚያስብ አለ እንዴ?
አየህ አንዳንድ ፀረ ልማቶች እንደዚያ ሊያስቡ ይችላሉ ብዬ ነው፡፡
ለማንኛውም የሰሞኑ ጉዳይ እኔንም አሳስቦኛል፡፡
ይህማ ሊሆን አይችልም፡፡
ሀቀኛ ነው ብለው ነው አይደል?
እንዴ አንተ እኮ እኔ ራሱ ከምመሰክርላቸው ሀቀኛ ባለሀብቶች መካከል አንዱ ነህ፡፡
ልክ ነው፣ በእሱስ እኔም አላሳፍርዎትም፡፡
ታዲያ ምኑ ነው ያሳሰበህ?
ክቡር ሚኒስትር ሰሞኑን የማላውቃቸው ሰዎች ስልክ እየደወሉልኝ ነው፡፡
ምን ብለው?
በስልክ ማስፈራሪያ ቢጤ ነው የነገሩኝ፡፡
የምን ማስፈራሪያ?
ሰሞኑን የበርካታ ባለሀብቶች ንብረት መታገዱን አልሰማህም ወይ ምናምን እያሉ ሊያስፈራሩኝ ይሞክራሉ፡፡
ምን?
ከስልክም ባለፈ ለአንዳንድ ወዳጆቼ ጠንቀቅ እንድል ምክር አዘል ማስፈራሪያ አስልከውብኛል፡፡
አንተ የሠራኸው ነገር አለ እንዴ?
ኧረ በፍፁም ክቡር ሚኒስትር፡፡
ታዲያ ለምንድነው የሚያስፈራሩህ?
እኔም ሊገባኝ አልቻለም፡፡
ለመሆኑ ምን እያሉ ነው የሚያስፈራሩህ?
በቀጣይ በሰፊ ዕርምጃ የሚወሰደው የግል ባለሀብቱ ላይ ስለሆነ ተጠንቀቅ ይሉኛል፡፡
አንተ ግብር ምናምን በአግባቡ ነው አይደል የምትከፍለው?
የመንግሥት አንዲት ስባሪ ሳንቲም የለችብኝም፡፡
ታዲያ ምን ፈልገው ነው?
ጉቦ ፈልገው ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
የምን ጉቦ?
ከሊስት ውስጥ እናሰርዝሃለን ነው የሚሉት፡፡
የምን ሊስት ነው?
በሙስና የሚጠረጠሩ ሰዎች ሊስት ነዋ፡፡
ታዲያ ምኑን ነው የሚሰርዙልህ?
ስሜን!
[ለክቡር ሚኒስትሩ የውጭ ስልክ ተደወለላቸው]
ሄሎ ክቡር ሚኒስትር፡፡
ማን ልበል?
ባለፈው የመሥሪያ ቤትዎን የፈርኒቸር ጨረታ የሰጡኝ ነኝ፡፡
ሰላም ነው ወዳጄ?
ምን ሰላም አለ ክቡር ሚኒስትር?
ምን ሆንክ ደግሞ?
ስልክ በተደወለልኝ ቁጥር መደንበር ነው ሥራዬ፡፡
እንዴ ለምን?
ይኸው እንቅልፍ በዓይኔ ከዞረ ራሱ ስንት ጊዜው?
ሥራ ቀየርክ እንዴ?
ወደ ምን?
ወደ ጥበቃ ነዋ፡፡
አይ ክቡር ሚኒስትር አሁንም ይቀልዳሉ?
ይህ ኑሮ ካልቀለድክበት አትገፋውም ብዬ ነው፡፡
ለነገሩ እውነትዎትን ነው፡፡
ለመሆኑ የት ሆነህ ነው የምትደውልልኝ?
ከአገር ወጣ ብያለሁ፡፡
እንዴ ለምን ወጣህ?
የሰሞኑ ማዕበል እስኪረጋጋ ነዋ፡፡
የምን ማዕበል ነው?
የሙስናው ማዕበል ነዋ፡፡
ምነው ፈራህ እንዴ?
እኔ ካልፈራሁ ማን ሊፈራ?
ምን ያስፈራሃል?
ክቡር ሚኒስትር ጥያቄው የተገላቢጦሽ ነው መሆን ያለበት፡፡
ማለት ይኼን ጥያቄ መጠየቅ ያለብዎት እርስዎ ነዎት እያልከኝ ነው?
አይደለም አይደለም፣ የማያስፈራህ ነገር ምን አለ ብለው ቢጠይቁኝ ይሻላል ልልዎት ፈልጌ ነው፡፡
ይህን ያህል ፈርተሃል ማለት ነው?
ክቡር ሚኒስትር ሰዎች ስሜን ሊስት ውስጥ ማየታቸውን ነግረውኝ ነበር፡፡
ታዲያ ሊስቱ ውስጥ ከነበርክ እንዴት ከአገር ወጣህ?
የወጣሁት በቦሌ አይደለማ፡፡
ታዲያ በየት ነው የወጣኸው?
በባሌ!
[የክቡር ሚኒስትሩ ቢሮ የፋይናንስ ኃላፊው ገባ]
ፈልጌዎት ነበር ክቡር ሚኒስትር፡፡
ለምን ጉዳይ?
በወጪ ቅነሳው ላይ እንድንወያይ፡፡
የምን ወጪ ቅነሳ ነው?
ለሚቀጥለው ዓመት መሥሪያ ቤታችን ወጪ መቀነስ እንዳለበት መንግሥት አሳስቧል፡፡
ታዲያ መቀነስ ነዋ፡፡
ስለእሱ ጉዳይ እንድንመካከር ብዬ ነው፡፡
ምኑ ላይ የምንመካከረው?
የሚቀነሱት ነገሮች እርስዎን ይመለከታሉ፡፡
እንዴት ሆኖ?
ለምሳሌ ለልጅዎ የተሰጠው መኪና መመለስ አለበት፡፡
ምን?
እሱ ብቻ ሳይሆን የባለቤትዎትም መኪና መመለስ አለበት፡፡
እንዴት ነው የተናናቅነው እባክህ?
ይህ እኮ ንቀት አይደለም፡፡ መመርያን የማስፈጸም ጉዳይ ነው፡፡
አንተን ማን ነው አስፈጻሚ ያደረገህ?
ክቡር ሚኒስትር እኔንም እኮ ያስጠይቀኛል፡፡
ሰውዬ በጣም የደፈርከኝ አልመሰለህም?
ክቡር ሚኒስትር ለምን ፐርሰናል ያደርጉታል?
ይህማ ፐርሰናል ጉዳይ ነው፡፡
እንዴት ሆኖ?
ይኸው ልጅህና ሚስትህ መኪና ይቀሙ እያልከኝ ነዋ?
ታዲያ እነሱ የመሥሪያ ቤታችን አባል እኮ አይደሉም፡፡
እኔ ሚኒስትር መሆኔን ረሳኸው?
ኧረ በፍፁም ክቡር ሚኒስትር፡፡
ታዲያ ምን ፈልገህ ነው?
ወጪ መቀነስ!
[የክቡር ሚኒስትሩ ሚስት ስልክ ደወሉ]
ለመሆኑ በሕይወት አለህ?
ምነው ታሰረ አሉሽ እንዴ?
ብትታሰር ይሻልሃል፡፡
ምንድነው የምትቀባጥሪው?
ምን እየተደረገ ነው ለመሆኑ?
ምን ተደረገ?
መኪናዬን እኮ ሊቀሙኝ ነው?
እ. . .
አንተ ነህ እንዴ የላካቸው?
ወጪ ቆጥቡ ተብለን እኮ ነው፡፡
ታዲያ እኔን መኪና በመቀማት ነው ወጪ የምትቆጥቡት?
መመርያ ተላልፎ እኮ ነው፡፡
እና በዜሮ ልታስቀሩኝ ነው እንዴ?
በዜሮማ አትቀሪም፡፡
ይኸው ሁሉን ነገር ተከለከልን አይደል እንዴ?
ያልተከለከልነው አንድ ነገር አለ፡፡
ምንድነው እሱ?
ድጋፍ የምናደርግለት ማኅበር ማቋቋም እንችላለን፡፡
የምን ማኅበር ነው የምናቋቁመው?
የአካል ጉዳተኞች ማኅበር!