Friday, June 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበኦሮሚያ የሥራ ማቆም አድማ በ29 ወረዳዎች የትራንስፖርትና የንግድ አገልግሎቶች ተቋርጠው ነበር

በኦሮሚያ የሥራ ማቆም አድማ በ29 ወረዳዎች የትራንስፖርትና የንግድ አገልግሎቶች ተቋርጠው ነበር

ቀን:

በጅማ የቦምብ ጥቃት 13 ሰዎች ተጎድተዋል
በኦሮሚያ ክልል በማኅበራዊ ሚዲያ ከረቡዕ ነሐሴ 17 እስከ እሑድ ነሐሴ 21 ቀን 2009 ዓ.ም. በተጠራው የሥራ ማቆም አድማ፣ በ29 ወረዳዎች የትራንስፖርትና የንግድ አገልግሎቶች ተቋርጠው መሰንበታቸውን የክልሉ መንግሥት አስታወቀ፡፡

የክልሉ የመንግሥት የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ አዲሱ አረጋ ዓርብ ነሐሴ 19 ቀን 2009 ዓ.ም. ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ በክልሉ ውስጥ ካሉ 315 ወረዳዎች መካከል በ29 ወረዳዎችና በአራት ዋና ዋና ከተሞች ለሦስት ቀናት የሥራ ማቆም አድማ ተደርጓል፡፡

ለዚህ ሥራ ማቆም አድማ መሠረታዊ ተደርጎ በማኅበራዊ ሚዲያ ሲዘዋወሩ ከነበሩ ጉዳዮች መካከል በኦሮሚያ ክልል ከአዋሳኝ አካባቢዎች ጋር ያለው ድንበር በአግባቡ ባለመካለሉ ተደጋጋሚ የሆነ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እንዳሉ፣ የቀን ገቢ ግምቱ ትክክል አለመሆኑን፣ የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) አመራሮች ይፈቱ የሚሉ መሆናቸውን አቶ አዲሱ አስረድተዋል፡፡

በዚህም ሳቢያ በተጠራው የተቃውሞ ጥሪ በስድስት ዞኖች ውስጥ በሚገኙ ወረዳዎችና ከተሞች የትራንስፖርትና የንግድ እንቅስቃሴዎች ተቋርጠው ነበር፡፡ ለአብነትም ሆሮ ወረዳ፣ አምቦ ከተማ፣ ግንደበረት፣ ጀልዱ፣ ሚዳቀኝ፣ ጮኬ፣ ጮቢ፣ አቡናና፣ ሜጀሬ፣ አሰቦ፣ መኢሶ፣ አወዳይ፣ ሀረማያ፣ ኮምቦልቻ፣ ነቀምቴ፣ ሆለታ፣ ቄለም፣ ደንቢዶሎ ወዘተ እንደሚገኙበት ጠቁመዋል፡፡

በእነዚህ ወረዳዎች ውስጥ ሕገወጥ እንቅስቃሴ ሲፈጽሙ የነበሩ ግለሰቦች እንደነበሩም አቶ አዲሱ ጠቁመዋል፡፡ የንግዱ ማኅበረሰብም በእነዚህ ወረዳዎችና ከተሞች በተነሳው ተቃውሞ እንደተሳተፈ ገልጸው፣ የተደራጁ ቡድኖች በማኅበራዊ ሚዲያ በሚያስተላልፉት መልዕክት ሐሳባቸውን በግድ የመጫን አዝማሚያ እንደነበር አስረድተዋል፡፡

‹‹ሐሳብን በተለያየ መንገድ መግለጽ ሕገ መንግሥታዊ መብት እንደመሆኑ መጠን የሌላውንም ፍላጎት ማክበር ያስፈልጋል፤›› ብለዋል፡፡ መደብሮቻቸውን የዘጉ ነጋዴዎች በዚህ ሕገወጥ ድርጊት ሙሉ በሙሉ እንደማያምኑበትም አቶ አዲሱ ተናግረዋል፡፡

መደብሮቻቸውን በሚከፍቱ ነጋዴዎች ላይም በማኅበራዊ ድረ ገጾች በመታገዝና ዕርምጃ ይወሰድባቸው ብሎ በማስፈራራት፣ አስገድዶ የማዘጋት እንቅስቃሴዎች እንደነበሩ አቶ አዲሱ አስታውቀዋል፡፡

ከዚህ ባለፈም ቀን ከፍተው በነበሩ ነጋዴዎች ላይ በሌሊት በመደብሮቻቸው ላይ ዕርምጃ ሲወስዱ እንደነበረ ጠቁመዋል፡፡ በአወዳይ ከተማ የዚህ ዓይነት ችግር መከሰቱን አቶ አዲሱ ለአብነት አንስተዋል፡፡

በተለይም በመጀመሪያዎቹ ሦስት ተከታታይ ቀናት ውስጥ በሰው አካልና በንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን ገልጸዋል፡፡ ሆለታ አካባቢ የሁለት አውቶብሶች መስታወት እንደተሰበረ ጠቁመው፣ የክልሉ መንግሥት የሠራተኞች ሰርቪስ ላይም ተመሳሳይ ጥቃት መድረሱን አስረድተዋል፡፡

ሐሙስ ነሐሴ 18 ቀን 2009 ዓ.ም. ደግሞ በጅማ ከተማ ቦምብ በማፈንዳት በ13 ሰዎች ላይ የአካል ጉዳት መድረሱንም አስታውቀዋል፡፡ ጉዳት የደረሰባቸው በጅማ ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል የሕክምና ዕርዳታ እንደተደረገላቸው፣ ከተጎጂዎቹ ውስጥም የአሥር ዓመት ታዳጊና ሁለት ሴቶች እንደሚገኙበት ተገልጿል፡፡

አቶ አዲሱ ‹‹መንግሥት ቤት ውስጥ በመዋል አድማ የማድረግ ፍላጎት ያላቸውን ዜጎች መብት እንደሚያከብር ሁሉ፣ ሱቃቸውን ከፍተው መሸጥ የሚፈልጉና ሰላማዊ ሕይወት መምራት ለሚፈልጉ ሰዎች ከለላ የመስጠት ግዴታ አለበት፤›› ብለዋል፡፡

የአድማ ጥሪው ከተላለፈ በኋላ ጫት ከኦሮሚያ ክልል ወደ ድሬዳዋ፣ ሐረርና ሶማሌ ክልሎች እንዳይሄድ ሰፊ ቅስቀሳ ሲደረግ እንደነበር አቶ አዲሱ ገልጸዋል፡፡

የክልሉ መንግሥት በዚህ ድርጊት የተሳተፉ ዜጎችን በመለየት እየያዘና ለሕግ ተጠያቂ እያደረገ መሆኑን የገለጹት ኃላፊው፣ ምን ያህል ዜጎች ከዚህ ጋር በተያያዘ እንደታሰሩ ከሪፖርተር ለቀረበላቸው ጥያቄ እስካሁን ቁጥሩ በውል እንደማይታወቅ ተናግረዋል፡፡

የክልሉ መንግሥት ይህ የተቃውሞ ጥሪ መሠረት እንደሌለው ቢገለጽም፣ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች ግን ይህን ሐሳብ ተቃውመዋል፡፡ የሰማያዊ ፓርቲ የወቅቱ ፕሬዚዳንት አቶ የሺዋስ አሰፋ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ ‹‹ይህ ተቃውሞ ቀድሞ የተተነበየ ነው፤›› ብለዋል፡፡ አቶ የሺዋስ ከ2007 ዓ.ም. ምርጫ በኋላ ሕዝቡ መንግሥትን አልመረጥኩም እያለ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

 አቶ የሺዋስ ይህን ጉዳይ ሲያብራሩ፣ ‹‹መንግሥት በርካታ የፖለቲካ ጥያቄዎች እየተጠየቀ የወጣቶች ፈንድ አቋቋምኩ በማለት ለራሱ ነው መልስ የሰጠው፡፡ ይህ ደግሞ መንግሥት እያጭበረበረ መቀጠሉን ያሳያል፤›› ብለዋል፡፡ 

በኦሮሚያ ክልል የተከሰተውን ተቃውሞ ተከትሎ የአሜሪካ መንግሥት ወደ ኦሮሚያ፣ ጎንደርና ባህር ዳር የጉዞ ዕገዳ በዜጎቿ የጣለ ሲሆን፣ ይህን ጉዳይ በተመለከተ ሪፖርተር ለውጭ ጉዳዩ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ መለስ ዓለም ጥያቄ አቅርቧል፡፡

አቶ መለስ በምላሻቸውም፣ ‹‹ኤምባሲዎች ዋነኛ ሥራቸው እንደዚህ ዓይነት ትንንሽ ጉዳዮች ሲፈጠሩ ይህንን መሰል ማስጠንቀቂያ ማውጣት ነው፡፡ ለምሳሌ የአሜሪካ ኤምባሲ ባለፈው ጊዜ አውጥቶት የነበረውን የጉዞ ክልከላ ስህተት ሆኖ ስላገኘው ይቅርታ ጠይቋል፤›› ብለዋል፡፡

በኦሮሚያ ክልል ከሦስት ሳምንት በፊት ከቀን ገቢ ግምት ጋር በተያያዘ ተነስቶ በነበረው ተቃውሞ በንብረት ላይ ጉዳት መድረሱ ይታወሳል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በአዲስ አበባ በድምቀት ተከበረ

የአዛርባጃን ኤምባሲ  የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በትላንትናው ዕለት አከበረ። ሰኞ...

የመንግሥትና የሃይማኖት ልዩነት መርህ በኢትዮጵያ

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች የሃይማኖት ተቋማት አዎንታዊ ሚና የጎላ...

ሐበሻ ቢራ ባለፈው በጀት ዓመት 310 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ

የአንድ አክሲዮን ሽያጭ ዋጋ 2,900 ብር እንዲሆን ተወስኗል የሐበሻ ቢራ...