በዳዊት እንደሻው
ከዚህ ቀደም በፓስታ አስመጪና ላኪነት ብቻ ተሰማርቶ የነበረው አልቪማ አስመጭና ላኪ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር፣ በአገር ውስጥ ፓስታ ለማምረት የሚያስችለውን ፋብሪካ በአዳማ ከተማ ገነባ፡፡
በዋናነት ከጂቡቲ በመጡ ባለሀብቶች የተቋቋመው ይህ ኩባንያ፣ ፋብሪካውን ለመገንባት ግማሽ ቢሊዮን ብር ወጪ ማድረጉ ተገልጿል፡፡
በመስከረም ወር 2009 ዓ.ም. የመጀመርያ ሳምንታት ሥራውን ይጀምራል የተባለው ፋብሪካ፣ በቀን 66 ቶን ፓስታ የማምረት አቅም እንዳለው ተነግሯል፡፡
በአብዛኛው የፓስታ ምርት ከውጭ የምታስመጣው ኢትዮጵያ፣ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ብቻ አርባ ሚሊዮን ዶላር የሚያወጡ የፓስታ ምርቶች ወደ አገር ውስጥ እንደገቡ የኩባንያው ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ድሬ አሊ ተናግረዋል፡፡
ኩባንያቸው ላለፉት አሥር ዓመታት በዋናነት የመዋል ፓስታ አስመጪና አከፋፋይ ሆኖ ሠርቷል፡፡ በቀጣይ ዓመት ሥራውን የሚጀምረው ፋብሪካ ከፓስታ በተጨማሪ በቀን 120 ቶን ዱቄት የማምረት አቅም አለው፡፡
ድርጅቱ ፋብሪካውን ለማቋቋም የሚያስችሉትን ማሽኖች ከጀርመን ያስመጣ ሲሆን፣ የፋብሪካው ላብራቶሪ ለመገንባት የሚያስችሉ ምርቶችን በ15 ሚሊዮን ብር ወጪ በተመሳሳይ ከአውሮፓ አስመጥቷል፡፡
ፋብሪካው በአጠቃላይ በ11 ሔክታር መሬት ላይ አርፏል፡፡ ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ ሲገባ ለ120 ሰዎች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥርም ተገልጿል፡፡ ዋና ሥራ አስኪያጁ፣ ‹‹በዋናነት ዓላማችን በአገር ውስጥ ገበያ ላይ የሚስተዋለውን ፍላጎት ማሟላት ነው፤›› ብለዋል፡፡
በተያያዘ ዜና ኩባንያው ለምርቱ የሚያስፈልገውን የስንዴ አቅርቦት ለማሟላት በኦሮሚያ ክልል ከሚገኙ በሥራቸው 1,000 ገበሬዎች ከያዙ የኅብረት ሥራ ማኅበራት ጋር ስምምነት ላይ ደርሷል፡፡
በስምምነቱም የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲን ጨምሮ የግብርናና የተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር ተካተዋል፡፡ ‹‹አሁን ትልቁ ጉዳይ የስንዴ አቅርቦት ክፍተትን መሙላት ነው፤›› ያሉት አቶ ድሬ፣ ስምምነቱ ችግሩን በመጠኑም ቢሆን እንደሚቀርፈው ገልጸዋል፡፡
አቶ ድሬ በአገር ውስጥ የስንዴ አቅርቦት ፋብሪካው የሚፈልገው የጥራትና የመጠን ፍላጎት እስካልተሟላ ድረስ፣ የፓስታ ዱቄት ከውጭ እንደሚያስመጡ ተናግረዋል፡፡
አልቪማ በጂቡቲ የሚገኘው መዋል ግሩፕ አንድ አካል ሲሆን፣ ግሩፑ ሥራ ከጀመረ 60 ዓመታት አስቆጥሯል፡፡