ኢትዮጵያ በሥልጣኔ ፋና ወጊነት፣ በቀደምት ምድርነት፣ በሚዳሰሱና በማይዳሰሱ ቅርሶች ባለቤትነት፣ በአስደማሚ ታሪኮችና በበርካታ ጉዳዮች የምትታወቅ ድንቅ አገር ናት፡፡ ይህች ታሪካዊት አገር የበርካታ ብሔር ብሔረሰቦች፣ ቋንቋዎች፣ ባህሎችና እምነቶች ባለቤት ከመሆኗም በላይ፣ በተለያዩ ዘመናት ደማቸውን አፍስሰው አጥንታቸውን ከስክሰው የጠበቋት ልጆቿ እናት ናት፡፡ በየዘመኑ በተነሱ ገዥዎች ሥር በጭቆና ብትተዳደርም፣ አንድም ጊዜ ለውጭ ወረራ ያልተንበረከከች የጀግኖች አገር ናት፡፡ በተፈጥሮ በታደለችው መልክዓ ምድሯ ውስጥ የሚመነጩ በርካታ ወንዞች ያሏት፣ ተዝቀው የማያልቁ የተለያዩ ማዕድናት የታቀፈች፣ መጠነ ሰፊ ለም መሬት፣ ለኑሮና ለግብርና የሚመቹ የተለያዩ የአየር ፀባዮች፣ ብርቅዬ የዱር እንስሳትና አዕዋፍ፣ እንዲሁም ልዩ ልዩ የተፈጥሮ ስጦታዎችን የታደለች አገር ናት፡፡ ከምንም ነገር በላይ ግን እናት አገሩን ወደር በሌለው ፍቅርና ጀግንነት ከትውልድ ትውልድ እየተቀባበለ የጠበቀ ኩሩ ሕዝብ እናት አገር ናት፡፡ ይህ ኩሩ ሕዝብ ከእናት አገሩ አልፎ ለዓለም ጥቁር ሕዝቦች መመኪያ የሆነውን ታላቁን ፀረ ኮሎኒያሊስት የዓደዋ ጦርነት በድል የደመደመ ነው፡፡ በዓለም ታሪክም ህያው ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ የታላቅነት መገለጫም ነው፡፡
ኢትዮጵያ ታላቅ አገር ነበረች፡፡ ታላቅነቷን እየተጋፉ ሕዝቧን ለእርስ በርስ ግጭት የዳረጉና ወደ ድህነት አዘቅት የወረወሩ የታሪክ አጋጣሚዎችም ነበሩ፡፡ የእነዚህ የታሪክ ጠባሳዎች እስካሁን ድረስ በቀጠለው ድህነትና ኋላቀርነትም ይጠቀሳሉ፡፡ በአክሱም ዘመን የነበረው ሥልጣኔ ለምን አልቀጠለም? የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ዓይነት ኪነ ሕንፃዎች በስፋት ለምን አልተሠሩም? የአክሱም ሐውልቶችን የቀረፁ እጆች ዓይነት ለምን አልተፈጠሩም? ወዘተ. የመሳሰሉ ጥያቄዎች ሲነሱ በርካታ ምክንያቶች ይቀርባሉ፡፡ ከሁሉም በላይ ግን በተለይ በዘመነ መሳፍንት የነበረው የእርስ በርስ ሽኩቻና በየቦታው ግዛት መመሥረት ብዙ ኪሳራ አድርሷል፡፡ አፄ ቴዎድሮስ ተነስተው የማዕከላዊ መንግሥት ምሥረታ ሐሳብ እስኪመጣ ድረስ በርካታ ዕድሎች አምልጠዋል፡፡ ከዚያም በኋላ ባሉት ጊዜያት በመነሳትና በመውደቅ ውስጥ የማንሰራራት ምልክቶች ቢታዩም አጥጋቢ አልነበሩም፡፡ ይህ ሁሉ ውጣ ውረድ በበዛበት ጎዳና ውስጥ ግን ኢትዮጵያዊነት ተከብሮ የቀጠለው፣ የመጣውን መከራ ሁሉ ችሎ ባሳለፈው አስተዋዩና ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው፡፡
ይህ ታላቅ ሕዝብ በየዘመኑ የተነሱበት ገዥዎች ያደረሱበትን መከራና ስቃይ ችሎ አገሩን ሳያስደፍር ኖሯል፡፡ በገዛ አገሩ ገባርና ባይተዋር ሆኖ የኖረ ሕዝብ እንደ ገዥዎቹ ሳይሆን እርስ በርስ ተከባብሮና ተስማምቶ ከመኖር በላይ፣ ተጋብቶና ተዋልዶ ዘመናትን ተሻግሯል፡፡ በደጉም ሆነ በክፉ ጊዜ ከልዩነቶቹ ይልቅ አንድነቱን አጉልቶ ይህችን ኅብረ ብሔራዊት አገር ታድጓል፡፡ በታጋሽነቱ፣ በአርቆ አሳቢነቱና በአስተዋይነቱ ዘር፣ ቋንቋ፣ እምነት፣ ባህልና የተለያዩ ልዩነቶች አንድነቱን አልሸረሸሩትም፡፡ የእናት አገሩን ሰንደቅ ዓላማ ከፊት አስቀድሞ በደሙ መስዋዕትነት ሲከፍል ኖሯል፡፡ ይህችን ታላቅ አገር እያስከበረ የኖረ ታላቅ ሕዝብ አደራ ምንጊዜም ሊዘነጋ አይገባም፡፡ በተለይ አገራቸውን በተለያዩ ዘርፎች እንቅልፍ አጥተው አገልግለው ያለፉ ወገኖችም ሆኑ፣ በዓለም አደባባይ ስሟን ያስጠሩ ታዋቂዎች አገራቸው ታላቅ ትሆን ዘንድ ብርቱ ተጋድሎ አድርገዋል፡፡ ይህንን ተጋድሎ የበለጠ ማድመቅና ህያው ማድረግ የእዚህ ትውልድ ኃላፊነት ነው፡፡ አገርን ታላቅ ከማድረግ በላይ የሚያኮራ ተግባር የለምና፡፡
ይህ በዚህ እያለ ግን በዚህ ዘመን ይህችን ኅብረ ብሔራዊት አገር ከመቼውም በበለጠ ታላቅ ለማድረግ ጥረቶች ቢኖሩም፣ እነዚህን ጥረቶች የሚፈታተኑ ችግሮች ይታያሉ፡፡ የአገሪቱ ሕዝብ አሁንም ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምዕራብ እስከ ምሥራቅ ባለው ሰፊ መልክዓ ምድር ውስጥ እየኖረ ሥነ ልቦናው ተመሳሳይ ቢሆንም፣ ከሕዝብ ፈቃድና ፍላጎት ውጪ ልዩነት የሚያጦዙና አንድነትን የሚሸረሽሩ ወጣ ገባ እያሉ ነው፡፡ ልዩነቱን ውበት አድርጎ የሚኖር ሕዝብ ውስጥ የተፈጠሩ ወገኖች፣ የፖለቲካ ልዩነታቸውን ማቻቻል አቅቷቸው የግጭት ቅስቀሳ ያካሂዳሉ፡፡ ዴሞክራሲ የተለያዩ ሐሳቦች የሚንሸራሸርበት ዓውድ መሆኑ እየታወቀ፣ ልዩነትን ላለመቀበል ብቻ ዘርንና እምነትን የጥቃት ዒላማ ለማድረግ ይዳዳሉ፡፡ አገርን የሚበትን አጀንዳ በመያዝ ግለሰቦችን በሐሳባቸው ከመሞገት ይልቅ ዘር ላይ ያነጣጠረ ፕሮፓጋንዳ ላይ ይጣዳሉ፡፡ በተለይ በማኅበራዊ ሚዲያ ተምረናል የሚሉ ወገኖች እንዲህ ዓይነት ዝቅጠት ውስጥ ተዘፍቀው ለማመን የሚያዳግቱ ቅስቀሳዎች ያካሂዳሉ፡፡ ይህ ድርጊት ለዚህች ታላቅ አገርና ለዚህ ኩሩ ሕዝብ አይመጥንም፡፡
ቤተሰብ የኅብረተሰብ መሠረት ነው፡፡ አንድ ቤተሰብ ሰላሙ ከደፈረሰ ባልና ሚስት ይፋታሉ፡፡ ልጆች ይበተናሉ፡፡ ከፍተኛ የሆነ ሥነ ልቦናዊ ቀውስ ይፈጠርባቸዋል፡፡ ይህንን ወደ አገር አስፍተን ስናይ ማኅበረሰቡ ጤናማት ከጎደለው ችግር ይኖራል፡፡ ወደ ማኅበራዊ ቀውስ ይሸጋገራል፡፡ ነገር ግን ችግሮችን በአገር ወግ መሠረት ማስተናገድ ከተቻለ ሰላም ይፈጠራል፡፡ ቤተሰብ እንደሚበተነው ሁሉ አገርን ለብተና የሚዳርጉ፣ ሕዝብን ለስደስት ብሎም ለዕልቂት የሚያዘጋጁ ድርጊቶች የሚፈጠሩት ከአገር በላይ ሥልጣን ሲቀድም ነው፡፡ የሥልጣኑ ባለቤት ግን ሕዝብ ነው፡፡ እሱ ነው ዋነኛውና ወሳኙ፡፡ ዓለም በቴክኖሎጂ እየገሰገሰና ያለ ፓስፖርትና ቪዛ ከአንዱ ወደ ሌላው የመጓዝ ደረጃ ላይ በተደረሰበት በዚህ ዘመን፣ መራራቅንና መለያየትን መስበክ ዕብደት ነው፡፡ ‹እኔ ካልበላሁት እበትነዋለሁ› እንዳለችው ዶሮ ራስ ወዳድ ከመሆን በመውጣት ለአገር ዘላቂ ሰላም፣ ዴሞክራሲ፣ ብልፅግና፣ እንዲሁም ህልውና ማሰብ ሲገባ በብሔር ተቧድኖ አገር ለማፍረስ መሞከር በታሪክ ያስጠይቃል፡፡ የገዛ ወገንን እንደ ጠላት እያዩ ለባዕድ ጠላት አገርን ማመቻቸት ወንጀል ነው፡፡ በታላቁ የዓደዋ ፀረ ኮሎኒያሊስት ድል ምክንያት የአፍሪካውያን መሰባሰቢያ ለመሆን የቻለች ድንቅና ታሪካዊት አገር ይዞ፣ ይህንን ክብር ለሌሎች እንደ ዋዛ አሳልፎ መስጠት ከጤናማ አዕምሮ የሚመነጭ አይደለም፡፡ በአፍሪካ ኅብረት መቀመጫነት ምክንያት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የተለያዩ አካላት መናኸሪያ የሆነችን ኅብረ ብሔራዊት አገር የበለጠ ታላቅ ማድረግ ሲገባ፣ ክፍልፋዮች ለማድረግ ማሰብ የክህደቶች ሁሉ ታላቅ ክህደት ነው፡፡ አፍሪካውያን ተስፋ የጣሉባትን አገር ተስፋ ማሳጣት ተገቢ አይደለም፡፡ ለዚህች ታላቅ አገር አይገባም፡፡
እዚህ ላይ ልብ ሊባል የሚገባው ከእያንዳንዱ ዜጋ ጀምሮ የቡድኖች መብት መከበር አለበት፡፡ በተለይ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ተከብረው ማኅበራዊ ፍትሕ እንዲሰፍን መታገል ተገቢ ነው፡፡ መብትም ነው፡፡ ነገር ግን የትግሉ መነሻና መድረሻ ሕዝብ መሆን አለበት፡፡ የሥልጣኑ ባለቤት የሆነው ሰፊው ሕዝብ የማያምንበትንና ለዘመናት ሲፀየፍው የኖረውን ዘረኝነት ማቀንቀንና አገርን ለማተራመስ መሞከር ሊታሰብ አይገባም፡፡ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በዚህ መንገድ ተገንብቶም አያውቅም፡፡ በሕዝብ ስም እየማሉ ከሕዝብ ፍላጎት ማፈንገጥ ለአገር አይበጅም፡፡ ይህች ታላቅ አገር የምትሻው ወደነበረችበት ታላቅነቷ ከፍ ማለት ነው፡፡ ከድህነት አዘቅት ውስጥ እንድትወጣና ዜጎቿን በእኩልነት የምታስተናግድ እንድትሆን፣ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ያሉ ልጆቿ የሚፈለግባቸውን አስተዋጽኦ የማድረግ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ ኢትዮጵያ ዳግም ወደ ጦርነት መመለስ የለባትም፡፡ አስመራሪ ከሆነው ድህነት መገላገል አለባት፡፡ ፍትሕ ሊነግሥባት ይገባል፡፡ ዴሞክራሲ ሰፍኖ ልጆቿ በነፃነት ኮርተው መኖር አለባቸው፡፡ የጀመረቻቸው የመሠረተ ልማት ግንባታዎች ከግብ ደርሰው በፍትሐዊነት የሚዳረሱባት አገር መሆን አለባት፡፡ እውነተኛው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ዕውን እንዲሆን፣ ልጆቿ ልዩነቶቻቸውን በሠለጠነ መንገድ አስታርቀው እጅ ለእጅ ሊያያዙ ይገባል፡፡ ያኔ ኅብረ ብሔራዊት አገር ዕውን ትሆናለች! ወደ ታላቅነትም ትገሰግሳለች! ይህንን ማሳካትም አያቅትም!