Friday, June 2, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኃይል አቅርቦት እንዲዘረጋለት ለሚጠይቀው ባለሀብት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ‹‹የተደራጀ አምራች ሁን›› ይላሉ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

የንግድ ማኅበረሰቡ ከመንግሥት አካላት ጋር በሚያደርጋቸው ስብሰባዎች ወቅት ሳይጠየቅና ምሬት ሳይሰማበት የማያልፍ ጉዳይ ቢኖር፣ የመሠረተ ልማት አቅርቦት በተለይ የኤሌክትረክ አቅርቦት እጥረት ብሎም ጭራሽኑ የኃይል ሥርጭት ያለማግኘት ችግር ነው፡፡ ይኸው ችግር ቀውስ እየፈጠረ እንደሚገኝ የሚያመለክቱ ጥያቄዎች እየተነሱ ይገኛሉ፡፡

ሰሞኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ፣ የንግድ ማኅበረሰቡን ባወያዩበት ወቅት፣ ‹‹የኤሌክትሪክ ኃይል ያለህ›› የሚለው ጥያቄ ተነስቷል፡፡ በኤሌክትሪክ ኃይል ዕጦት ሳቢያ እየደረሰበት ያለውን ጉዳት በተለያየ መንገድ ጥያቄውን ያቀረበው ነጋዴውና አምራቹ ክፍል እንዲሁም የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት ችግሩን በማስመልከት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አስታውቀዋል፡፡ በኤሌክትሪክ ኃይልና በመሰል የመሠረተ ልማት ጥያቄዎች ዙሪያ ምላሻቸውን ያቀረቡት አቶ ኃይለ ማርያም፣ ‹‹መሠረተ ልማትን በተበታተነ ሁኔታ ማቅረብ እጅግ አስቸጋሪ ነው፤›› በሚል መንደርደሪያ የመንግሥታቸውን አቋም አስታውቀው ነበር፡፡

መንግሥት የኢንዱስትሪ ፓርኮችንና ክላስተሮች የመገንባት አስፈላጊነትን መሠረተ ልማትን በአሃዳዊ መንገድ ለማቅረብ እንዲያመቸው በማሰብ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡ ኢንዱስትሪዎች በተበታተነ ሁኔታ የሚገነቡ ከሆነ፣ መሠረተ ልማት ለማቅረብ አንችልም የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

‹‹ምንም ያህል ብንጠራራ መብራት በየቦታው ማቅረብ አንችልም፤›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ‹‹አሁን ባለን አቅም ምንም የፍሳሽ ማስወገጃ አገልግሎትንም በየቦታው መገንባት የማይቻል ሆኗል፡፡ ስለዚህ በየሠፈሩ መሬት ስላገኘን ፋብሪካ አቋቁመናልና መብራት አምጡ ከተባለ፣ የመንግሥት ምላሽ አንችልም ይሆናል፤›› በማለት፣ መሠረተ ልማት በማቅረብ ረገድ የመንግሥት አካሄድ መቀየሩን የሚያመላክት መከራከሪያ አቅርበዋል፡፡

ይህን አባባላቸውን ሲያብራሩም፣ ‹‹በፍጥነት እያደገ ያለ ኢኮኖሚ በየሠፈሩ መብራት ጎትቶ ማስገባት ይችላል ማለት አይደለም፡፡ እንዲህ የሚያደርግ መንግሥትም ዓለም ላይ አልተፈጠረም፣ ሊኖርም አይችልም፡፡ ስለዚህ በየሠፈሩ ለሚገኘው ቀርቶ ለኢንዱስትሪ ዞኖቻችንና ክላስተሮቻችን ሳይቆራረጥ መብራት ቢያገኙ ትልቅ ድል ነው፤›› ካሉ በኋላ፣ መንግሥት ለኢንዱስትሪ ፓርኮች የሚሰጠው ተመሳሳይ ማትጊያ በሌላው አካባቢ ለለማውና ወደፊትም ለሚለማው ይሰጥ ተብሎ በንግድ ምክር ቤቱ ለቀረበው ጥያቄ ‹‹መልሱ ተመሳሳይ ማትጊያ አይሰጥም ነው፡፡ ምክንያቱም አቅም የለንም፡፡ በየቦታው ለተበታተነው ኢንዱስትሪ መብራት ለመዘርጋት፣ የአንድ መስኮት አገልግሎት ለመስጠት፣ የፍሳሽ አገልግሎት ለማቅረብ አቅሙ የለንም፡፡ ያለን አማራጭ ወደ ኢንዱስትሪ ፓርኮችና ክላስተር የሚመጣ ከሆነ መቀበል ነው፤›› በማለት ወደ ፓርኮቹ ለሚመጡ የሚሰጠው የኢንቨስትመንት ማበረታቻም ‹‹ሌላ ቦታ እንዳይመኝ መሳቢያ ነው፤›› ብለውታል፡፡

በመሆኑም በሌሎች በሚመቻቸው ቦታ ኢንቨስት ለሚያደርጉ ባለሀብቶች ተመሳሳይ ማትጊያ መንግሥት እንደማይሰጥ አረጋግጠዋል፡፡ ይህ ሲባል ግን በኢንቨስትመንት ሕጉ ውስጥ የተቀመጡትን ማበረታቻዎችን ወይም ማትጊያዎችን ከማግኘት እንደማይገታም አስታውሰዋል፡፡ ከዚህ ባሻገር ኢንዱስትሪው ባለበት አካባቢ በቂ የኤሌክትሪክ ኃይል ያለበት ከሆነ፣ በተለይ ማሰራጫዎች የሚገኙበት አካባቢ ከሆነ በተበታተነ ሁኔታ ለሚገኙ ኢንዱስትሪዎች የሚውል መፍትሔ እንደሚሰጥ ጠቅሰዋል፡፡ ‹‹ነገር ግን ለሁለትና ለሦስት ኢንዱስትሪዎች ተብሎ በሰብስቴሽን ማቋቋም በጣም ከባድ ነው፤›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በዚህ አኳኋን ለሚገነቡ ኢንዱስትሪዎች የኃይል አቅርቦቱን ከባድ የሚያደርገው ለአንድ ሰብስቴሽን የሚወጣው ዋጋ 200 ሚሊዮን ዶላር በመሆኑ ነው ብለዋል፡፡

ከዚህ ባሻገር በየሠፈሩ የተቋቋሙት ኢንዱስትሪዎች አዋኪ እየሆኑ መምጣታቸውንም ሳይናገሩ አላለፉም፡፡ ‹‹በየሠፈሩ የሚቋቋሙ ኢንዱስትሪዎች እየበጠበጡ ነው፡፡ ምክንያቱም በአካባቢው ያለው ኃይል ለኢንዱስትሪ ተብሎ የተሠራ ባለመሆኑ፣ ሶኬት በሰኩ ቁጥር ሠፈሩ በሙሉ ይናጋል፤››

 የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ችግሮችን ለመቅረፍ የተጀመሩ ፕሮጀክቶችንም ጠቁመዋል፡፡ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ስለሚገኘው የኃይል አቅርቦት ሥራም በዝርዝር አቅርበዋል፡፡ ከዚህ በኋላ እንዲህ ያሉ የመሠረተ ልማት ችግሮችን ለመፍታት ከሚያስችሉ ዕርምጃዎች አንዱ የንግዱ ኅብረተሰብ በክላስተር ሲታቀፍ እንደሆነና ይህንን ማድረጉን ማጤን እንደሚኖርበትም አሳስበዋል፡፡

በየአካባቢው የተቋቋሙትንና ወደ ሥራ የገቡትን ወይም እሳቸው የተበታተኑ ስለሚሏቸው ኢንዱስትሪዎች ‹‹ምን እናድርግ?›› ለሚለው ጉዳይም በጋራ መሥራት ያስፈልጋል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ለወደፊቱ ግን የንግድ ምክር ቤቶች ኃላፊዎችም በክላስተር የሚሠሩትን እንዲያበረታቱ ጠይቀዋል፡፡ በእስካሁኑ አካሄድ የሚከሰቱ የመሠረተ ልማት ችግሮችን ከእንግዲህ ‹‹በእኛ ይብቃ በሉ›› ሲሉም ተደምጠዋል፡፡ 

ስለ ኢንዱስትሪ ፓርኮች አካሄድ ማብራሪያ ሲሰጡም በፌዴራልም ሆነ በአዲስ አበባ ከተማ ደረጃ በሚለሙት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ መካከለኛና አነስተኛ ባለሀብቶች መግባት እንደሚችሉ አስታውሰዋል፡፡ ይሁንና እስካሁን ለመግባት የሚፈልጉ ባለሀብቶች የመግባት ፍላጎት እንደሌላቸው፣ የመግባት ጥያቄ እንዳላቀረቡ አቶ ኃይለ ማርያም አልሸሸጉም፡፡ የአገር ውስጥ ባለሀብቶች ወደ ኢንዱስትሪ ፓርኮቹ እንዲገቡ እስከ የ85/15 በመቶ ብድር አቅርቦትን ጨምሮ የተለያዩ ማበረታቻዎችን መንግሥት ቢያቀርብም ፍላጎት ያሳየ ወገን አልተገኘም፡፡

አገራዊ ባለሀብት ያልተሳተፈበት ዘላቂ ልማት መፍጠር አስቸጋሪ እንደሆነ በመግለጽም፣ ‹‹ላስተላልፍ የምፈልገው ጥሪ ይህች አገር፣ አገራዊ አምራች ዘርፍ ሳይኖራት በውጭ ባለሀብት ብቻ ተደግፋ መሄድ አትችልም፤›› ብለዋል፡፡ አክለውም ‹‹እናንተ በዘገያችሁ መጠን ግን መንግሥት እጅና እግሩን አጣጥፎ አይቀመጥም፡፡ መግባት የሚችል፣ የተመረጠ የውጭ ባለሀብት እያስገባ ይቀጥላል፤›› ብለዋል፡፡ አገር በቀል ኩባንያዎች ወደ ኢንዱስትሪ ፓርኮች እንዲገቡ መንግሥት ቀድሞውንም አይፈልግም ነበር የሚለውን የግሉን ዘርፍ ቅሬታም ውድቅ ለማድረግ ሞክረዋል፡፡

አገሮች ኢንዱስትሪዎቻቸውን ማስፋፋት ሲጀምሩ አብዛኛው የውጭ ባለሀብቶችን በመያዝና ድጋፋቸውን በመስጠት እንደሆነም አስታውሰዋል፡፡ የውጭ ባለሀብቶች መግባትም በርካታ ጠቀሜታዎች እንዳሉት በመጥቀስ፣ በጨርቃ ጨርቅ መስክ የተሰማራና የአገር ውስጥ ባለሀብት፣ ከውጭ አገር ገዥዎች ጋር ካልተጣመረ በቀር ዓለም አቀፍ ገበያ ውስጥ ሊገባ እንደማይችል አመልክተዋል፡፡

በመሆኑም የንግዱ ማኅበረሰብ ለአገሪቱ አምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ዋጋና መስዕዋትነት በመክፈል የአገሪቱን የወደፊት የኢንዱስትሪ ባለቤትነት እንዲያረጋግጥ ጥሪ ያቀረቡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ለአገር ውስጥ ባለሀብቱ የቀረቡት ማበረታቻዎችና ድጋፎችን በመቀጠም ሳይረፍድበት ውጤታማ እንዲሆንም አሳስበዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች