Thursday, June 1, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በግሉ ዘርፍና በመንግሥት ጎራ የጠቅላይ ሚኒስትሩና የነጋዴው አሠላለፍ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከታክስ ግርግር እስከ መንግሥት ጣልቃገብነት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች አቶ ኃይለ ማርያም የሰጧቸው ምላሾች
የመንግሥትና የግሉ ዘርፍ የምክክር መድረክ ከተቋቋመ ሰባት ዓመታት አስቆጥሯል፡፡ በመንግሥትና በግሉ ዘርፍ መካከል በተደረሰ ስምምነት መሠረት፣ በሚኒስትሮች የተመሩ 15 ያህል የምክክር መድረኮች በልዩ ልዩ ጉዳዮች ላይ ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡ በዓመት አንድ ጊዜም በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰብሳቢነት ምክክር ይደረጋል፡፡ በዚህ መሠረት ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ሁለት ስብሰባዎች ከዚህ ቀደም ተካሂደዋል፡፡ በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም የተመራው ሦስተኛው የምክክር መድረክ ቅዳሜ፣ ነሐሴ 13 ቀን 2009 ዓ.ም. ተካሂዷል፡፡

የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ሰለሞን አፈወርቅ፣ ከዚህ ቀደም በተደረጉ ስብሰበዎች ስለታዩ ለውጦች ጠቅሰው፣ በአሁኑ ወቅት ሊሻሻሉ ይገባቸዋል ያላቸው እንደ ታክስ ኦዲት ሥራዎች ያሉት በተገቢ ባለሙያዎች እንዲሠሩ፣ ግልጽ መመርያ እንዲኖራቸውና በኦዲት ውጤት ላይ የሚነሱ ያለመግባባቶች በገለልተኛ አካላት የሚፈቱበት አሠራር እንዲዘረጋ ማድረግ አሁንም መፍትሔ የሚሹ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

የግሉን ዘርፍ የፋይናንስ አቅርቦት ችግር መቅረፍ በከፍተኛ ፍጥነት በማደግ ላይ ላለው የአገራችን ኢኮኖሚ የተስተካከለ የገንዘብ አቅርቦት ወሳኝነቱ የሚያጠያይቅ እንዳልሆነ የገለጹት ፕሬዚዳንቱ፣ የግሉ ዘርፍ አባላት በአገሪቱ ዕድገት የሚጠበቅባቸውን ሚና እንዳይወጡ ከተጋረጡባቸው ችግሮች ዋነኛው የገንዘብ አቅርቦት ችግር ነው ብለዋል፡፡ የኢትዮጵያ የገንዘብ አቅርቦት የፖሊሲ፣ የሕጎችና የአሠራር ችግሮች ያሉበት ሲሆን፣ የአበዳሪ ተቋማት የማበደር አቅም መመናመን፣ ብድር ለማግኘት አላስፈላጊ ወጪ መብዛት፣ ዘመናዊና የተቀላጠፈ አሠራርን አለመከተል፣ አድሏዊና ሙስና የሰፈነበት የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት፣ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞችን ያገለለ የብድር አቅርቦት፣ ከብድር ውጭ ያሉ የፋይናንስ ምንጮች አለመዳበራቸውና ባሉት ሕጎችና መመርያዎች መሠረት በቅጡ አለመሥራት እንደሚታይ አስረድተዋል፡፡ የግሉ ዘርፍ የገንዘብ አቅርቦት ችግሮችን ለመፍታት በብድር አገልግሎት መመርያ ለአጭር ጊዜ ብድር የተሰጠው የአንድ ዓመት ገደብ ወደ ሁለት ዓመት ከፍ እንዲደረግ በማለት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡ የመጀመርያው ዓመት የብድር ተመላሽ የ40 በመቶ ምጣኔ ዝቅ እንዲረግና ባንኮች ለወጪ ንግድ ቅድመ ዕቃ መላኪያና የሸቀጥ ብድር ለመሳሰሉት የሚሰጡት ብድር ከአጠቃላይ የብድር አቅርቦታቸው ከአሥር በመቶ እንዳይበልጥ የሚገድበው ጣሪያ ሙሉ በሙሉ ባይነሳ እንኳ፣ የባንኮችን ወቅታዊ አቅም ባገናዘበ መልኩ ከፍ እንዲደረግ ፕሬዚዳንቱ ጠይቀዋል፡፡

ባንኮች በብድር ከሰጡት ገንዘብ ውስጥ ከአምስት በመቶ በላይ የተበላሸ ብድር እንዳያስተናግዱ፣ ካስተናገዱ ግን ተበዳሪዎቹንና ባንኮቹን የሚቀጣ መመርያ እየተተገበረ ይገኛል፡፡ መመርያው የተበዳሪዎችን የማገገም ዕድል የሚገድብ፣ ባንኮችም እንዲህ ያለውን ገንዘብ ለማስመለስ ሲሉ አዋጪነት እንደሌለው በሚገለጸው ሐራጅ አሠራር መሠረት ያልተከለፈ ብድራቸውን ለማግኘት ይገደዳሉ፡፡ ይህም ከደንበኞቻቸው ጋር ያላቸውን ግንኙነት የሚያሻክር በመሆኑ፣ ወቅታዊ ሁኔታዎችን ያገናዘበ አሠራር በጥናት መዘርጋት እንደሚገባ ጠይቀዋል፡፡

የባንኮች የማበደር አቅምን ለማጠናከር ሲባል፣ ከየብድሩ እየተቀነሰ ለቦንድ ግዥ የሚውለው የ27 በመቶ ምጣኔ እንዲቀነስ፣ የሚከለፈላቸው የሦስት በመቶ የወለድ ምጣኔም ወጪያቸውን ስለማይሸፍን ይሻሻል ብለዋል፡፡ የባንኮችን አሠራር የሚገዙ መመርያዎች ተለዋዋጭነትና ወቅታዊ ችግሮችን ለመፍታት የሚረዱ የውሳኔ አሰጣጥ ሥርዓት አለመዘርጋቱንም አቶ ሰሎሞን አንስተዋል፡፡ ለአብነትም በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኩል ሲሰጥ የነበረው የፕሮጀክት ብድር አገልግሎት በቅርቡ ወደ ኢትዮጵያ ልማት ባንክ እንዲዛወር የተደረገበት አሠራር ከፋይናንስ አቅርቦት ቅልጥፍናና ተደራሽነት አንፃር ይፈተሽልን የሚለው የንግድ ምክር ቤቱ ጥያቄ ነበር፡፡

የኢንዱስትሪ ፓርኮች እየተገነቡ ለአገር ውስጥና ለውጭ ባለሀብቶች እየቀረቡ ይገኛሉ፡፡ ወደ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ለሚገቡ የአገር ውስጥ ባለሀብቶች የሚሰጡ ማበረታቻዎችን ጭምሮ ሌሎችንም የተመለከቱ ከ15 በላይ ጥያቄዎች ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ቀርበዋል፡፡ ከንግድ ምክር ቤቱ ባሻገር ተሳታፊዎችም ጥያቄዎቻቸውን አሰምተዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ምላሽ ከሰጡባቸው ውስጥ የተወሰኑት እንደሚከተለው ቀርበዋል፡፡

የፋይናንስ እጥረት

የፋይናንስ ተቋማትን አስተዳደር የተመለከቱ ጥያቄዎች ምላሻቸውን የሰጡት አብዛኛዎቹ የፋይናንስ ፖሊሲና ሌሎች መመርያዎች በጥናት ላይ ተመሥርተው የተዋቀሩ መሆናቸውን በመግለጽ ነበር፡፡

መንግሥት አይሞክረውም ካሉባቸው ጉዳዮች መካከል የተበላሸ የብድር መጠን ከፍ ይደረግ መባሉን ነው፡፡ የተበላሸ ብድር መጠን አምስት በመቶ በላይ መሆን የለበትም ተብሎ የተቀመጠው በምክንያት እንደሆነ የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ‹‹በፋይናንስ ተቋማት እጅ የሚገኘው ገንዘብ የሕዝብ ነው፡፡ የመንግሥትም ሆነ የግል ባንኮች ገንዘብ የሕዝብ ነው፡፡ አንዴ ሸርተት ካለ አገሪቱ የማትወጣው ማጥ ውስጥ ትገባለች፤›› በማለት ለውጥ እንደማይደረግ ገልጸዋል፡፡

የተበላሸ የብድር መጠን ወደ አሥር በመቶ ቢደረግ ይጠቅመናል የሚል ሐሳብ ካለ ስህተት ነው ያሉት አቶ ኃይለ ማርያም፣ የተበላሸ የብድር ገደብ ከፍ ቢደረግ የንግዱ ኅብረተሰብ መሥራት የማይችልበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል ብለዋል፡፡

ባንኮች የሕዝብን ገንዘብ በአግባቡ አላስተናገዱም የሚል ትንሽ ምልክት ቢመጣ አስቀማጮች ሻንጣ ይዘው ገንዘቡን አምጣ ይላሉ፡፡ ይህ በብዙ አገሮች ታይቷል፡፡

ንግድ ምክር ቤቱ በጠየቀው መሠረት ቢፈጸም፣ ብድር ላይኖር እንደሚችል ገልጸው፣ የሕዝቡን አመኔታ ለማሳደግ የተበላሸ ብድር ገደብ መኖሩ ወሳኝ ነው ብለዋል፡፡ ‹‹እንደ አገርም እየተበደርንና እየከፈልን የምናድገው፣ ባንኮች በሥርዓት ሲሄዱ ነው፡፡ ይህም ሆኖ ባንኮች እያተረፉ ነው፡፡ ምክንያቱም ጠንካራ ቁጥጥር ስላለ ነው፤›› ብለዋል፡፡ ማሻሻያ እንደማይደረግ ሲናገሩም፣ ‹‹በምንም ዓይነት መንገድ ማሻሻያ አናደርግም፡፡ ይህ ግልጽ መሆን አለበት፡፡ ይኼ ከግለሰብ ነጋዴዎችና ከቡድን ነጋዴዎች በላይ ነው፤›› በማለት አስረግጠዋል፡፡

ስለ27 በመቶ የቦንድ ግዥ

በምክክር መድረኩ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩን የጎረበጣቸው ጥያቄና በተግሳጽ ጭምር ጠንካራ ምላሽ የሰጡበት፣ ባንኮች ከሚያበድሩት ገንዘብ ውስጥ 27 በመቶ ለቦንድ ግዥ የሚያውሉበት አሠራር ይስተካከል የሚለው ነበር፡፡ መንግሥታቸው እንዲነሱበት አጥብቆ ከማይፈልጋቸው መካከል አንዱ ይኸው እንደሆነም ያስገነዘቡበት ነበር፡፡

የግል ባንኮች ለቦንድ ግዥ የሚያውሉት የገንዘብ መጠን ይሻሻል የሚለው ጥያቄ በተደጋጋሚ ሲቀርብ ቆይቷል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ሆኑ ሌሎች ባለሥልጣናት ይህንን የመቀየር ሐሳብ እንደሌላቸው አመልክተዋል፡፡ በዘንድሮው መድረክም እንደገና መቅረቡ ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለጥያቄው ምላሽ የሰጡበት አግባብ ‹‹ከዚህ ቀደም ምላሽ መስጠታችን እየታወቀ ለምን ተመላሶ ይመጣል? በሚል አኳኋን ንግድ ምክር ቤቱ የተገሰፀበት ሆኗል፡፡ የጥያቄው መላልሶ መምጣት ከጀርባው ሌሎች ወገኖች ስላሉ ነው በማለት አቶ ኃይለ ማርያም ተናግረዋል፡፡ ከጥያቄው ጀርባ የዓለም ባንክና የዓለም የገንዘብ ድርጅት እንዳሉ በግልጽ ተናግረው፣ ‹‹ጥያቄው የእሱ በመሆኑ እናንተ አርፋችሁ ተቀመጡ፤›› በማለት የመንግሥት አቋም ፅኑ እንደሆነና በጉዳዩም እንደማይደራደር አስረግጠዋል፡፡

‹‹የአይኤምኤፍ ሰዎች ሰሞኑን መጥተው ስለሚወየያዩበት ይህንኑ ጥያቄ ካነሱ ሄዳችሁ [ፕሬዚዳንት] ትራምፕን ጠይቁ እንላቸዋለን፡፡ ምክንያቱም አዛዡ እሱ ስለሆነ፡፡ አይኤምኤፍና የዓለም ባንክ የዓለም ተቋማት ናቸው የሚባለው ውሸት ነው፡፡ የዓለም  አይደሉም፡፡ እነሱም ደጋግመው ጥያቄውን አንስተው አልተሳካላቸውም፡፡››

ስለፋይናንስ አቅርቦት እጥረት

የፋይናንስ አቅርቦት ችግርን ለመቅረፍ ጥናት ሲደረግ እንደቆየ በማስታወቅ፣ ወደ ልማት ባንክ ስለተዛወረው የፕሮጀክት ብድርም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰፊ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ከፋይናንስ አቅርቦት አኳያ የልማት ባንክን አቅም ማሳደግ ትክክለኛው አማራጭ መሆኑ እንደተረጋገጠ ገልጸዋል፡፡ አንድ ዓመት ሙሉ ጥናት መደረጉን በመጥቀስም፣ ‹‹ንግድ ባንኮች የረዥም ጊዜ ብድር ሊሰጡ አይችሉም፡፡ መስጠትም አይገባቸውም፡፡ ይኼ የሆነበት ዋናው ምክንያት፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በአንድ ወቅት በአፍጢሙ ተደፍቶ ወድሞ በነበረበት ወቅት መንግሥት ብዙውን ዕዳውን በማንሳት  ነፍስ እንዲዘራ ካደረገው ብዙ አልቆየም፡፡ ምናልባት አሥር ዓመት ቢሆነው ነው፡፡ ወደነበረበት እንዳይመለስ ግን እንደ ንግድ ባንክነቱ  የንግድ ሥራዎችን ይሠራል እንጂ አነስተኛ ወለድ በማመቻቸት የፖሊሲ ባንክ ሥራዎችን መሥራት ስለማይችል ከዚህ አኳያ የልማት ባንክ ኃላፊነቱን እንዲወጣ የማጠናከር ሥራ ተሠርቷል፤ በማለት የፖሊሲ ብድር ከንግድ ባንክ ስለመውጣቱ አስረድተዋል፡፡ ‹‹ከሥራ ማስኬጃ አኳያ ልማት ባንክ ለሰጣቸው ብድሮች የሥራ ማስኬጃውን ንግድ ባንክ ይስጥ የሚል የተወሰነ ማለሳለሻ ለማድረግ ተሞክሮ ነበር፡፡ ሊያስኬድ የማይችል መሆኑ ስለታወቀ ግን የልማት ባንክ ፕሮጀክቶችንም ሥራ ማስኬጃዎችንም በመስጠት ከጫፍ እስከ ጫፍ እንዲያስተዳድረው ተደርጓል፡፡ ስለዚህ ብድሩን የሰጠው ማን ነው የሚለው የእናንተ ጉዳይ ሊሆን አይገባም በማለት ጥያቄውን ውድቅ አድርገዋል፡፡  

‹‹የእናንተ ጥያቄ መሆን ያለበት ብድር አግኝተናል ወይ የሚለው ነው፡፡ መንግሥት ፖሊሲዬ ይህ ነው ብሎ የማስቀመጥ መብት አለው፡፡ ስለዚህ የንግድ ሥራዎቻችሁ፣ ለሌሎች የአጭርና የመካከለኛ ጊዜ ብድሮቻችሁ እንደ ማንኛውም አገር ውስጥ እንዳለ የንግድ ባንክ እዚያ ልትሳተፉ ትችላላችሁ፡፡ የመንግሥት የፖሊሲ ባንክ አንድና አንድ ብቻ ነው፡፡ ይህ የፖሊሲ ባንክም የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ነው፡፡ ንግድ ባንክ በንግድ ሥርዓቱ መሠረት መሥራት አለበት፡፡  ይኼ መታወቅ አለበት፡፡ ከሌሎች ባንኮች ጋር ተወዳድሮ መሥራት አለበት፤›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡

 አነስተኛና መካከለኛ ባለሀብቶች የሚያጋጥማቸውን የፋይናንስ አቅርቦት ችግር በተመለከተ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ከፕሮጀክት ትልመ ሐሳብ (ፕሮፖዛል) ጀምሮ እስከ ክትትልና ድጋፍ ድረስ ያሉ እገዛዎችን በመስጠት ማብቃት እንዳለበት ታምኖ፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከ70 ያላነሱ ቅርንጫፎች እንዲከፍት መደረጉን አስታውቀዋል፡፡  

ስለቀን ገቢ ግምት

በቅዳሜው የምክክር መድረክ ከንግድ ምክር ቤቱም ሆነ ከተሳታፊዎች ጥያቄዎች መካከል የግብር ጉዳይ ዓበይት ነበር፡፡ በተለይ የቀን ገቢ ግምት ላይ ስለተፈጠረው ችግር በተለያየ አቀራረብ ተጠይቋል፡፡

በንግዱ ማኅበረሰብ በኩል ከፍተኛ ቅሬታ ያስነሳ በመሆኑም ምክር ቤቱ የንግዱን ማኅበረሰብ አቋም በመንተራስ ጥያቄ ያረቀቡት አቶ ሰለሞን፣ የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን እንደሚገባው መጠን ባለማከናወኑ  ምክንያት ከተፈጠረው ግርታ ባሻገር፣ በአብዛኛው ግብር ከፋይ ላይ በግምት የተጣለው የቀን ገቢ እውነታን መሠረት ያላደረገና ወጥነት የጎደለው በመሆኑ ለዕሮሮ ምክንያት ሆኗል ብለዋል፡፡ በታክስ ሕጉ መሻሻል ሳቢያ በቀድሞው አዋጅ ደረጃ ‹‹ለ›› የነበሩ ግብር ከፋዮች፣ ወደ ደረጃ ‹‹ሐ›› እንዲገቡ ቢደረግም፣ አብዛኞቹ በቀድሞው አሠራር የሒሳብ መዝገብ ይይዙ የነበሩና ከአዋጁ መሻሻልም በኋላ በዚሁ የቀጠሉ እንደመሆናቸው የሒሳብ መዝገብ ማቅረብ እየቻሉ እንኳ በቀን ገቢ ግምት መስተናገዳቸው አጠያያቂ ነው ብለዋል፡፡ የጉዳዩን አንገብጋቢነት በመረዳት ለቀረበው አቤቱታ አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጡበት ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጠይቀዋል፡፡

የቀን ገቢ ግምት ችግር ከአሳታፊነት መጓደል ጀምሯል ያሉት ደግሞ የአዲስ አበባ ነጋዴዎች ፎረም ፕሬዚዳንት አቶ ገብረ ሊባኖስ ገብረ መድህን፣ ‹‹ሳያሳትፉ አሳትፈናል እያሉን ነው፡፡ አድሏዊ አሠራር ታይቷል፡፡ በተመሳሳይ ሥራ ላይ ላሉትና ተመሳሳይ የካፒታል ላላቸው የተለያየ የቀን ገቢ ግምት ተገምቷል፡፡ ለመስማት የሚዘገንን የቀን ገቢ ግምት የተተመነበት አለ፡፡ አንዳንዱ ግምት የማይታመንና የተለጠጠ ሆኗል፡፡ ጥቂቶችን ወደ ንግድ ሥርዓት እናስገባለን በሚል ሰበብ ብዙዎች ከንግድ ሥርዓት ውጭ እየተደረጉ ነው፤›› ያሉት አቶ ገብረ ሊባኖስ፣ እውነታው ምን ያህል ትክክለኛ እንደሆነ የንግድ ፈቃድ ዕድሳት ጊዜ ሲደርስ ሊታወቅ እንደሚችል ጠቅሰዋል፡፡

ጥያቄያቸውን ሲቀጥሉም ‹‹ንግድ ፈቃዱን መመለስ የፈለገ እንኳ መመለስ አልቻለም፡፡ አንድ ቁልፍ ቀራጭ 3,500 ብር ተገምቶበታል፡፡ ይህ በጣም ብዙ ገንዘብ ነው፡፡ አንዳንዱ 3,500 ብር ተብሎ በቅሬታ አፈታት 700 እስከ 800 ብር የሆነለት አለ፡፡ ይህ ደግሞ ግምቱ ምን ያህል እንደተጋነነ ያሳያል፤›› ብለዋል፡፡ ዝቅተኛው ነጋዴ በከተማ ልማት ተነሽነት፣ በከፍተኛ የመብራትና የውኃ አቅርቦት መቆራረጥ እንዲሁም በሕገወጥ ንግድ ወከባ፣ በኔትወርክና በድለላ የተያዘውን የንግድ ሥርዓት ተቋቁሞ ራሱን ለማስተዳደር በሚፍጨረጨርበት ወቅት፣ እንዲህ ያለ ዱብዳ ሲወርድበት ከፍተኛ ምሬትና ቅሬታ ላይ እንዲወድቅ እንዳደረገው አቶ ደብረ ሊባኖስ ተናግረዋል፡፡

በቀን ገቢ ግምቱ ላይ ስለነበሩ ችግሮችና ከዚህ በኋላ ስለታሰበውም አቶ ኃይለ ማርያም ምላሻቸውን በዝርዝር አቅርበዋል፡፡ ‹‹ለእኔ የደረጃ ‹‹ሐ›› ነጋዴዎች መረጃ በአግባቡ መረጃ አቅርበው መረጃህን አልቀበልም የሚል የግብር ሠራተኛ ካለ አጥፊ ነው፡፡ ገዳይ ነው፡፡ አብዛኛው አነስተኛ ገቢ ያለው የኅብረተሰብ ክፍላችን ወደ ግብር ማዕቀፍ ውስጥ እንዲገባ እንጂ ቆዳውን መላጨት አይደለም የምንፈልገው፡፡ ትንሹም ትልቁም ታክስ እየከፈለ እንዲያድግ እንጂ ብዙ ማስከፈል ዓላማ የለንም፡፡ የግብር ዓላማ ፍትሐዊነትን ማስፈን ነው፡፡ እኛ ብዙ ኪሳራ እንድንከፍል ያደረገው ዋናው ችግር ከንግዱ ኅብረተሰብ ጋር አሳታፊ በሆነ መንገድ ውይይት አለመካሄዱ የችግሩን 50 በመቶ ይይዛል፡፡ እሳት የሚቀሰቅሱ ቢኖሩም፣ የእኛ ሰዎች ትልቁ ስህተታቸው አጠቃላይ የገቢ መጠንን እንደ ግብር መለጠፋቸው ነው፡፡ ይህ ያስደነግጣል፡፡ ተመንዝሮ ሲመጣ ሁትለትና ሦስት ሺሕ ብር የሚሆን ግብር ሚሊዮን ብር ተብሎ መለጠፉ ስህተት ነው፤›› ብለዋል አቶ ኃይለ ማርያም፡፡

ሌላው ስህተት ብለው የጠቀሱት ነጥብ በቀን ገቢ ግምቱ ዙሪያ ሰብስበናል አወያይተናል እየተባለ ሲቀርብ የነበረው ‹‹የውሸት ሪፖርት›› እንደነበረ አምነዋል፡፡ ይህን በተናገሩ ጊዜም ከተሰብሳቢው የሞቀ ጭብጨባ ተችሯቸዋል፡፡ ‹‹ባለቤቱ በአግባቡ ሳይወያይ የታለፉ ጉዳዮች ናቸው ዋጋ ያስከፈሉን፤›› በማለት በቀን ገቢ ግምቱ ላይ በቂ ግንዛቤ የሚፈጥር ሥራ አለመሠራቱ ለቀረበው ዕሮሮ ትልቅ ድርሻ እንደነበረው የሰጡት ምላሽ ያስገነዝባል፡፡

‹‹ስለዚህ የመረጃና የግንዛቤ እጥረት፣ ሌብነትም ተደምሮበት የፈጠራቸው ችግሮች በርከት ይላሉ፡፡ ባደረግነው ግምገማ ወደ 40 በመቶ የሚሆነው የቀን ገቢ ትመና ችግር እንዳለበት አውቀናል፤›› ብለዋል፡፡

ይህንን ለማስተካከል የአዲስ አበባ አስተዳደር ካቢኔ በአጠቃላይ እንዲጣራ ተደርጎ የተቻለውን ያህል ከንግድ ኅብረተሰብ ጋር በመወያየት በተቀመጠው አቅጣጫ መሠረት ለመሥራት ሞክሯል ብለዋል፡፡ ቅሬታ ካቀረቡ ግብር ከፋዮች ውስጥ ለ51 በመቶው ምላሽ እንደተሰጠ፣ ሆኖም ምላሹ አልረካንም ያሉ በመኖራቸው እንደሚታይላቸው ገልጸዋል፡፡ አገሪቱ ከምታመነጨው ሀብት አኳያ የሚፈለገውን ያህል ግብር እየተሰበሰበ እንዳልሆነም ጠቅሰዋል፡፡

ለግብር ነክ ጉዮዳዮች በአዲስ አበባ አዲስ አሠራር እንደሚዘረጋ፣ በገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን አዲስ አበባ ላይ ሲያካሂድ የቆየው ሥራ ታይቶ፣ የፖለቲካ አመራርም እንደተሰጠበት ገልጸዋል፡፡ ‹‹የፖለቲካ አመራሩ ከላይ ተሰቅሏል፡፡ ግብር የሚሰበስበው ታች ነው ያለው፡፡ አልተጣጣመም፤›› በማለት የገቢ መሰብሰብ ሥራ እንደሌሎች አካባቢዎች ሁሉ አዲስ አበባ ከተማም ራሱን ችሎ በከንቲባው በተደራጀ ሥርዓት እንዲመራ በመወሰን፣ በባለሥልጣኑ ሥር የነበረው የሥራ ድርሻ ወደ አዲስ አበባ እንዲመለስ መደረጉን አስታውቀዋል፡፡ ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮም የአዲስ አበባ ታክስ ግብር በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እንደሚሰበሰብ ይፋ አድርገዋል፡፡

የኦዲት ሥራን በሚመለከት

ከታክስ አስተዳደርና ኦዲት ጋር በተገናኘ እየተሠራ ስላለው ሥራ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰጡት ማብራሪያ፣ እየተሠራበት ያለውን የኦዲት አሠራር ለመቀየር አማካሪ ተቀጥሮ እየተጠና እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡ አማካሪዎቹ አዳዲስ የመፍትሔ ሐሳብ በሁለት ሳምንት ውስጥ እንዳቀረቡ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ እንዲህ ኦዲት አድርጋችሁ ብዙ ነገር አታገኙም በማለት አማካሪዎቹ እንደገለጹላቸው ተናግረዋል፡፡

በዚህ ጉዳይ ከንግዱ ማኅበረሰብ ጋር ውይይት እንደሚደረግ የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የኦዲት ሥርዓቱን ዳግም የማዋቀር ሥራ እንዲጀመር አስታውቀዋል፡፡ በሠለጠነ መንገድ ኦዲት እንዴት ማድረግ እንደሚቻል፣ እንዴት የተሳሳተ ሒሳብ መለየት እንደሚቻልና መመዘኛዎች እንዴት መቀመጥ እንዳለባቸው አማካሪዎቹ አዳዲስ አሠራሮችን ስላመነጩ በዚያ ላይ ውይይት ተደርጎ አዲሱ አሠራር ይተገበራል ብለዋል፡፡

‹‹የመንግሥት ጣልቃ ገብነት መቼ ያበቃል?››

‹‹በእኔ እምነት ይህ ጥያቄ ትክክለኛ አይደለም፡፡ የጸሐፊዎች ጥያቄ ነው፡፡ መንግሥት መቼም ቢሆን እጁን አይሰበስብም፡፡ ለ200 ዓመት የሊብራሊዝም፣ የኒዮ ሊብራሊዝም ሰባኪዎች የነበሩ ሁሉ አሁን ልክ እንደ እኔና እንደ እናንተ ምክር ቤት እንመሥርት ብለው የባለሀብቱና የፕሬዚዳንቱ ምክር ቤት ብለው መከራቸውን እየበሉ ነው፡፡ ከዚህ በፊት ግን [የኢኮኖሚውን ችግሮች] ገበያው ይፈታል፡፡ መንግሥትና የግል ባለሀብት ግንኙነት የላቸውም ብለው ሲሰብኩን የኖሩ ሰዎች፣ አሁን ሲጨንቃቸው ምክር ቤት እንመሥርት በማለት የመሠረቱት ምክር ቤትም ተበትኖባቸዋል፤›› በማለት መንግሥት ጣልቃ ገብነቱን እንደማይገታ በአሜሪካ መንግሥት ተምሳሌነት ምላሻቸውን አሰምተዋል፡፡

‹‹መንግሥት ክፍተት ባለበት ውስጥ እየገባ ድርሻውን ይጫወታል፡፡ በሆነ ባልሆነው እጁን አይከትም፡፡ አሁንም፣ ነገም፣ ከነገ ወዲያም የኢኮኖሚው ሞተር ግን የግል ባለሀብቱ ነው፡፡ ይኼ ምንም ጥርጥር የሌለው ነው፡፡ እንዲሁ ለማለት ሳይሆን ከልብ የምንለው ነው፡፡ የአገራችን ኢኮኖሚ ሞተር እናንተ ናችሁ፤›› በማለት አሳርገዋል፡፡  

በሦስተኛው የምክክር መድረክ ወቅት እንደተለገጸው በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰብሳቢነት በተደረጉ ስብሰባዎች በርካታ የግሉ ዘርፍ ችግሮች ተነስተው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡ 54 በመቶ የሚሆኑት ችግሮችም መፍትሔ እንዳገኙም የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ሰለሞን ጠቅሰዋል፡፡ ለአብነትም የብቃት ማረጋገጫ ችግሮችን በዝርዝር በመፈተሽ እንደገና እንዲታዩ ከተደረጉት ውስጥ ይጠቀሳል፡፡ የንግድ ፈቃድና ምዝገባ አዋጁ ተሻሽሎ ለችግሮች ምላሽ እንዲሰጥ በሚያስችል መልኩ ትግበራው ተጀምሯል፡፡ በተሻሻለው የታክስ አስተዳደር አዋጅ ነጋዴው የግብር ይግባኝ ለማቅረብ ይጠየቅ በነበረው የ50 በመቶ ቅድመ ማስያዣ ግብር ላይ ይደመር የነበረው ወለድና መቀጮ ቀርቶ፣ 50 በመቶው በፍሬ ግብሩ ብቻ እንዲወሰን መደረጉ፣ የኢንቨስትመንት ምቹነትን በየወቅቱ ለመገምገም የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን እንዲሠራ መደረጉና ሌሎችም ጅምሮችን በመጠቅስ እንዲህ ያሉት ሥራዎች እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል፡፡

በአምራች ዘርፍ ምርታማነትና ተወዳዳሪነት ችግሮች ላይ ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ጋር በተደረገ ምክክር፣ አምራቾች ከሚገጥሟቸው ቁልፍ ችግሮች ውስጥ የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት ችግር አንዱ በመሆኑ፣ ይህንን ለመቅረፍ በብሔራዊ ባንክ የተወሰደው የኤል.ሲ. ብድር አገልግሎት የክፍያ መጠን ከ3.5 በመቶ ወደ 0.5 በመቶ እንዲቀነስ የተደረገበት ዕርምጃ ተገቢ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ ይህ በግርድፉ ሲሰላ በአምራቾች ላይ ይደርስ የነበረን የ2.89 ሚለዮን ዶላር ወጭ መቀነስ እንዳስቻለ የንግድ ምክር ቤቱ ዳሰሳ ያሳያል ብለዋል፡፡  

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች