Tuesday, May 28, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

መድን ድርጅት አራት አዳዲስ የዋስትና አገልግሎቶችን ሊጀምር ነው

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

በተሽከርካሪ ዋስትና ላይ የዋጋ ክለሳ ሊደረግ ነው

የኢትዮጵያ መድን ድርጅት የሪል ስቴት የመድን ሽፋንን ጨምሮ፣ አራት አዳዲስ የዋስትና አገልግሎቶችን ቀርፆ ገበያ ላይ ለማዋል ዝግጅት ማጠናቀቁ ታወቀ፡፡ እንደ ተሽከርካሪ ያሉ ዋስትናዎች ላይ የዋጋ ክለሳ ሊያደርግ መሆኑ ተገለጸ፡፡

ከድርጅቱ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ ከሪል ስቴት ፖሊሲ ሌላ እጀምራቸዋለሁ ያላቸው ቀሪዎቹ ሦስት አዳዲስ ፖሊሲዎች ለቱሪስቶች አጠቃላይ ደኅንነት ዋስትና፣ በአመፆች ሳቢያ ለሚከሰቱ የንብረት ጉዳቶች ዋስትናና ከ30 ዓመታት በላይ ላገለገሉ ተሽከርካሪዎች ዋስትና ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ነፃነት ለሜሳ እንደገለጹት፣ የእነዚህ አዳዲስ አገልግሎቶች የመጨረሻው የዋስትና ቀረፃ ሥራ  በመጠናቀቁ በጥቂት ወራት ውስጥ ወደ ገበያ ይገባል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ በቀረፃ ሒደት ላይ ከነበሩ ሰባት አዳዲስ ዋስትናዎች ውስጥ ማክሮ ኢንሹራንስ ተጠናቆ ለገበያ እንደቀረበ ተነግሯል፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ የአየር አምቡላንስ ወጪ፣ ጠቅላላ የገጠር ኢንሹራንስ፣ የቱር ኦፕሬተሮች ኃላፊነት፣ የሕግ ባለሙያዎች፣ የሐኪሞችና የአካውንታንቶች የሙያ ጉዳት ካሳ ኢንሹራንስ ዋስትናዎች ደግሞ ተጠናቀው፣ ለጠለፋ ዋስትና ሰጪዎችና በድርጅቱ ለሚመለከታቸው የሥራ ክፍሎች ቀርቦ አስተያየት እየሰጠበት እንደሚገኝም ለማወቅ ተችሏል፡፡

ኩባንያው ወደ ገበያ ለማስገባት የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ ደርሻለሁ ብሎ ከቀረፃቸው አዳዲስ ዋስትናዎች በተጨማሪ፣ አንዳንድ ነባር ዋስትናዎቹን ለመከለስ እየሠራ ነው ተብሏል፡፡ በገበያ ላይ ከሚገኙ ነባር ዋስትናዎች ውስጥ የተሽከርካሪ ዋስትና አንዱ ነው፡፡ ይህ ዋስትና ጥናትና ክለሳ ሥራ እየተካሄደበት እንደሆነ ሥራ አስፈጻሚው ገልጸዋል፡፡ እንዲሁም በረዥም ጊዜ መድን ዘርፍ የትምህርት ዋስትና የፖሊሲው ዝርዝር ድንጋጌዎችና የኢንዶውመንት ዋስትናዎች ላይ፣ የደንበኞችን ወቅታዊ ፍላጎትና የገበያ ሁኔታ መሠረት በማድረግ የመገምገምና አስፈላጊውን የዋስትናና የተመን ማሻሻል ሥራ መጠናቀቁን መረጃው ያመለክታል፡፡ እነዚህ የማሻሻያ ሥራ የተሠራላቸው ነባር ዋስትናዎች አስፈላጊ ግብዓቶች ከተወሰደባቸው በኋላ፣ በአዲሱ ዓመት ተግባራዊ ይሆናሉ ተብለው ይጠበቃሉ፡፡

በ2009 በጀት ዓመት የኢትዮጵያ መድን ኢንዱስትሪ 7.5 ቢሊዮን ብር የአረቦን ገቢ ያስመዘገበ እንደሆነ ያመለከቱት አቶ ነፃነት፣ ይህም በ2008 ከነበረው በ16.6 በመቶ ዕድገት የተመዘገበበት እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡ ከዚህ የአረቦን ገቢ ውስጥ 95.2 በመቶ ከጠቅላላ መድን ዘርፍ የተገኘ ሲሆን፣ ቀሪው 4.8 በመቶ ከረጅም ጊዜ መድን ዘርፍ የተገኘ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ዋና ሥራ አስፈጻሚው በሪፖርታቸው ዓለም አቀፍ የመድን ኢንዱስትሪ ምን እንደሚመስልም አስገንዝበዋል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2016 በዓለም አቀፍ ደረጃ በመድን ዘርፉ አጠቃላይ የተመዘገበው አረቦን 4.732 ትሪሊዮን ዶላር ሲሆን፣ ዕድገቱም እ.ኤ.አ. በ2015 ከነበረው 4.3 በመቶ ወደ 3.1 በመቶ ቀንሷል፡፡ ለዚህ እንደ ዋና ምክንያት የተጠቀሰው በአደጉት አገሮች የመድን ዘርፍ ላይ የታየው ቅናሽ ነው፡፡

እ.ኤ.አ. በ2016 በረጅም ጊዜ መድን ዘርፍ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተመዘገበው ጠቅላላ አረቦን 2.617 ትሪሊዮን ዶላር ሲሆን፣ ዕድገቱም እ.ኤ.አ. በ2015 ከነበረው ከ4.4 በመቶ ወደ 2.5 በመቶ እንደቀነሰም ተገልጿል፡፡ በተመሳሳይ በጠቅላላ መድን ዘርፍ የተመዘገበው አጠቃላይ አረቦን 2.115 ትሪሊዮን ዶላር ሲሆን፣ እ.ኤ.አ. በ2015 ከነበረው ከ4.2 በመቶ ወደ 3.7 በመቶ መቀነሱንና ለዚህም እንደ ዋና ምክንያት የሚቀርበው በአደጉት አገሮች የታየው ቅናሽ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች