Sunday, June 16, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ለ8.5 ሚሊዮን የድርቅ ተጎጂዎች ከ480 ሚሊዮን ዶላር በላይ ያስፈልጋል

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

በሁለት ወራት ከ1.7 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን በላይ የዕርዳታ እህል ተከፋፍሏል
በዚህ ዓመት በተካሄደው የበልግ ወቅት ጥናት መሠረት፣ በአሁኑ ወቅት ከ8.5 ሚሊዮን በላይ የድርቅ ተጎጂዎች ከሐምሌ 2009 ዓ.ም. እስከ ታኅሳስ 2010 ዓ.ም. የሚያቆይ የምግብና ሌሎች የዕለት ደራሽ ዕርዳታዎችን ለማቅረብ 487.7 ሚሊዮን ዶላር ያስፈልጋል ተባለ፡፡

ብሔራዊ የአደጋና የሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ለሪፖርተር እንዳስታወቀው ከሆነ፣ በቆላማና አርብቶ አደር አካባቢዎች በተደረገ ጥናት መሠረት ይፋ የተደረገው የድርቅ ተጎጂዎች ቁጥር 7.8 ሚሊዮን ነበር፡፡ የዕለት ደራሽ የምግብ ዕርዳታን ጨምሮ የትምህርት፣ የሰውና የእንስሳት ጤና፣ የእርሻና የውኃ አቅርቦቶችን ከግምት ባስገባው አዲሱ የበልግ ጥናት መሠረት፣ 8.5 ሚሊዮን የድርቅ ተጎጂዎች በአገሪቱ እንደሚገኙ የኮሚሽኑ ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ደበበ ዘውዴ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡

በጥናቱ የተሳተፉ 200 ባለሙያዎች በአገሪቱ 177 ወረዳዎች ውስጥ ለ21 ቀናት ተዘዋውረው ባደረጉት የመስክ ጥናት መሠረት፣ ቁጥራቸው ከ8.5 ሚሊዮን በላይ መድረሱ ለተረጋገጠው ተጎጂዎች የሚያስፈልገውን የምግብ፣ የምግብ ነክና ሌሎች አቅርቦቶች ለማሟላት 487.7 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ መረጋገጡን አቶ ደበበ አስታውቀዋል፡፡ በዚህም መሠረት ባለፈው ሐምሌ 1.2 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን እህል ሲቀርብ፣ በዚህ በነሐሴ ወር ደግሞ 550,000 ሜትሪክ ቶን የዕርዳታ እህል መከፋፈሉ ተጠቅሷል፡፡

መንግሥት 63 በመቶውን የ487.7 ሚሊዮን ዶላር እንደሚሸፍን ሲገለጽ፣ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዓለም የምግብ ፕሮግራም 20 በመቶውን፣ እንዲሁም 17 በመቶውን ደግሞ ዓለም አቀፍ የተራድኦ ድርጅቶች እንደሚሸፍኑት አቶ ደበበ ገልጸዋል፡፡ በዚህ ዓመት መንግሥት 170 ሚሊዮን ዶላር ያህል ለዕርዳታ ማዋሉ ሲጠቀስ፣ የአሜሪካ መንግሥት በቅርቡ 137 ሚሊዮን ዶላር እንደለገሰ ማስታወቁ ይታወሳል፡፡

በ2008 ዓ.ም. በተከሰተው ድርቅ ሳቢያ 10.2 ሚሊዮን ሕዝብ ለአስቸኳይ የዕለት ደራሽ ዕርዳታ ተዳርጎ ቆይቷል፡፡ በወቅቱ ያስፈልጋል ከተባለው የዕርዳታ ገንዘብ ውስጥ መንግሥት 16.5 ቢሊዮን ዶላር ወጪ ማድረጉን አቶ ደበበ አስታውሰዋል፡፡ የተመድ የሰብዓዊ ዕርዳታ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት በሳምንታዊ መግለጫው ባለፈው ሳምንት እንዳረጋገጠው፣ በጥር ወር ከነበረው የ5.6 ሚሊዮን ተረጂዎች ቁጥር ይልቅ በአሁኑ ወቅት ለተመዘገበው የ8.5 ሚሊዮን ተረጂዎች 487.7 ሚሊዮን ዶላር ያስፈልጋል፡፡

ከተረጂዎቹ ውስጥ 3.6 ሚሊዮን ሕፃናት፣ ነፍሰ ጡሮችና የሚያጠቡ ሴቶች የተመጣጠነ የምግብ እጥረት ስለሚታይባቸው የአልሚ ምግብ አቅርቦት ይፈልጋሉ፡፡ 10.5 ሚሊዮን ዜጎች በቋሚነት የንፁህ ውኃ አቅርቦት እንደሚያስፈልጋቸው ተመድ አስታውቆ፣ 2.2 ሚሊዮን አባወራዎችም የቁም እንስሳት ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው ይፋ አድርጓል፡፡ ይህን ያህል አባወራዎች የቁም እንስሳት ድጋፍ ይሻሉ ያለው የተመድ ሪፖርት፣ የሞቱ እንስሳት ቁጥር ምን ያህል እንደሆነ በግልጽ አልጠቀሰም፡፡

ድርቅ እንደ ቀድሞው በአሥርና በአምስት ዓመታት ውስጥ የሚከሰትበትን ዑደት በመቀየር በአሁኑ ጊዜ በየዓመቱ ደጋግሞ መምጣቱ የአየር ንብረት ለውጥ ያመጣው ተፅዕኖ እንደሆነ የሚገልጹት አቶ ደበበ፣ ከድርቅ በተጨማሪ ከዚህ ቀደም በጎርፍ ምክንያት ይከሰት የነበረው አደጋ ግን መቀነሱን አስረድተዋል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ክልሎች ለጎርፍ መከላከል የሚጠበቅባቸውን ሥራ በማከናወናቸው ነው ብለዋል፡፡ በአንፃሩ በአዲስ አበባ ከተማ ለጎርፍ አደጋ ተጋላጭ እንደሆኑ በከተማው አስተዳደርና በኮሚሽኑ የጎርፍ ግብረ ኃይል የተለዩ 25 አካባቢዎች እንዳሉ ጠቁመዋል፡፡ ይሁንና በክረምቱ በረዶ ቀላቅሎ በሚጥለው ዝናብ ሳቢያ፣ በከተማዋ ዋና ዋና መንገዶች ከፍተኛ የጎርፍ ውኃ እየተከሰተ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች