ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሽቆለቆለ የመጣውን የወርቅ ኤክስፖርት ገቢ ለማሻሻል የማዕድን፣ ነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስቴር የሥራ መርሐ ግብር ነደፈ፡፡
የማዕድን፣ ነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስትር አቶ ሞቱማ መቃሳ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ ከ2004 በጀት ዓመት ጀምሮ ለብሔራዊ ባንክ የሚቀርበው የወርቅ ምርት መጠን እየቀነሰ መጥቷል፡፡ በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱና በባለድርሻ አካላት በተደረጉ ውይይቶች የችግሩ ምንጮች ምን እንደሆኑ መለየታቸውን የገለጹት አቶ ሞቱማ፣ ሕገወጥ የወርቅ ንግድ (ኮንትሮባንድ) ዋነኛው ምክንያት እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
‹‹ዋናውና ትልቁ የኮንትሮባንድ ችግር ነው፡፡ የኮንትሮባንድ ችግር በአንድ ደረጃ የሚፈታ አይደለም፡፡ ሁለገብ ወርቅ ከሚመረትበት ቀበሌ ጀምሮ ጥረት መደረግ አለበት፡፡ ወርቅ ከሚመረትበት አካባቢ በኪስ በቀላሉ ተይዞ ሊወጣ የሚችል በመሆኑ፣ ባሉን ረዥም ድንበሮች በሙሉ የፀጥታ ኃይል አቁመን ለማስጠበቅ አንችልም፤›› ያሉት አቶ ሞቱማ፣ በኅብረተሰቡ ዘንድ የአስተሳሰብ ለውጥ የማምጣት ሥራ በስፋት መከናወን አለበት ብለዋል፡፡
ኅብረተሰቡ የኮንትሮባንድ ንግድ በአገር ኢኮኖሚ ላይ የሚፈጥረውን ከፍተኛ ጉዳት እንዲረዳ በማድረግ የአመለካከት ለውጥ እንዲያመጣ ሰፊ የቅስቀሳ ሥራ እንደሚከናወን ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡ ‹‹ወርቁ በሕገወጥ መንገድ ከአገር ሲወጣ ስለሚያስከትለው ጉዳት ማስገንዘብና ለማዕከላዊ ገበያ ቢቀርብ ግን እኔም በተወሰነ ደረጃ ልጠቀም እችላለሁ የሚል እምነት በኅብረተሰቡ ዘንድ ማስረፅ ያስፈልጋል፤›› ብለዋል፡፡
ይህን ለማድረግ ከተለያዩ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ጋር ሚኒስቴሩ እየሠራ እንደሚገኝ ገልጸው፣ አንድ ኮሚቴ መዋቀሩን ተናግረዋል፡፡ ኮሚቴው በ2010 ዓ.ም. የተለያዩ ሥራዎችን እንደሚሠራ ተገልጿል፡፡ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ እያሽቆለቆለ የመጣውን ከማዕድን ዘርፍ የሚገኘውን ገቢ ለመታደግ የነደፈው መርሐ ግብር የሕገወጥ ወርቅ ዝውውርን መቀነስ ሲሆን፣ ሁለተኛው የመርሐ ግብሩ ክፍል ደግሞ ከብሔራዊ ባንክ ጋር በጉዳዩ ላይ በቅርበት መሥራት ነው፡፡
አቶ ሞቱማ እንዳሉት፣ የኮንትሮባንድ ንግድን የሚያባብሰው አንዱ ምክንያት በባንክና በጥቁር ገበያ መካከል ያለው የውጭ ምንዛሪ ልዩነት መስፋት ነው፡፡ ‹‹በባንክ ያለው የዶላር ምንዛሪና በጥቁር ገበያ ያለው ምንዛሪ ልዩነት እየሰፋ በመጣ ቁጥር፣ በድንበር ወደ ጎረቤት አገሮች የሚሄደው የወርቅ መጠን እየጨመረ ይመጣል፤›› ያሉት አቶ ሞቱማ፣ ብሔራዊ ባንክ በዓለም ካለው የወርቅ ገበያ ዋጋ አምስት በመቶ በመጨመር ከአገር ውስጥ ወርቅ አምራቾችና አቅራቢዎች እንደሚገዛ አስረድተዋል፡፡ የምንዛሪ ልዩነት በሚሰፋበት ወቅት አምራቾቹ ከኮንትሮባንድ ገበያው የበለጠ ገንዘብ የሚያገኙ በመሆኑ ወደ ኮንትሮባንድ ንግዱ እንደሚያዘነብሉ አስረድተዋል፡፡ ይህን ችግር ለመፍታት በገንዘብ ፖሊሲው ላይ ሥራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ጠቁመዋል፡፡
‹‹በገንዘብ ፖሊሲ አካባቢ የሚሠሩ በርካታ ሥራዎች አሉ፡፡ ችግሮቹ ተለይተዋል፡፡ በችግሮቹ ላይ ሁላችንም ተስማምተናል፡፡ ቀጥሎ ያሉትን ችግሮች በጋራ ሆነን እንፈታለን፤›› ብለዋል፡፡
ሌላው ለኮንትሮባንድ ንግዱ መስፋፋት በምክንያትነት የተጠቀሰው የብሔራዊ ባንክ የወርቅ ግዢ ክፍያ ሥርዓት ለውጥ ነው፡፡ የወርቅ ዋጋ በዓለም አቀፍ ገበያ ውስጥ በየዕለቱ የሚለዋወጥ ነው፡፡ ብሔራዊ ባንክ ወርቅ አምራቾችና ነጋዴዎችን ለማበረታታት ከዓለም አቀፍ ገበያ ዋጋ አምስት በመቶ ጨምሮ የሚገዛ ከመሆኑም በላይ፣ የየዕለቱን የወርቅ ገበያ ዋጋ በመከታተል ትልቁን ዋጋ ተመልክቶ በዚያ ዋጋ ሲገዛ እንደነበር ተገልጿል፡፡
አቶ ሞቱማ እንዳሉት፣ በወር ውስጥ ከተመዘገበው ትልቁን ዋጋ በመውሰድ በዚያ ዋጋ ቆርጦ ተመን በማውጣት ወርቁን ከአቅራቢዎች ሲገዛ ቆይቷል፡፡ ይሁን እንጂ ይህ አሠራር በባንኩ ላይ ከፍተኛ ኪሳራ በማስከተሉ እንዲቀር በመንግሥት ተወስኗል፡፡
‹‹በማይሸጥበት ዋጋ እየገዛ ባንኩን ለኪሳራ የዳረገው በመሆኑ እንዲቀር ተደርጓል፡፡ ይህ ግን በወርቅ አቅራቢዎች ላይ ቅሬታ ፈጥሮ ወደ ኮንትሮባንድ ንግዱ እንዲሳቡ የበኩሉን አስተዋጽኦ አድርጓል፤›› ያሉት አቶ ሞቱማ፣ በወርቅ ንግድ ውስጥ በርካታ ችግሮች መታየታቸውን መሥሪያ ቤታቸው ከብሔራዊ ባንክና ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር የተለያዩ ሥራዎች በማከናወን ላይ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡
በአንደኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን የማዕድን ሚኒስቴር ከማዕድን ኤክስፖርት በየዓመቱ 800 ሚሊዮን ዶላር ለመሰብሰብ አቅዶ፣ በመጀመርያው ዓመት 600 ሚሊዮን ዶላር ለመሰብሰብ ችሎ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ በዓለም አቀፍ ገበያ የወርቅ ዋጋ በመቀነሱና የኮንትሮባንድ ንግድ በመስፋፋቱ ምክንያት ከ2005 ዓ.ም. ጀምሮ ከማዕድን ወጪ ንግድ የሚገኘው የውጭ ምንዛሪ እያሽቆለቆለ መጥቶ፣ ባለፈው ዓመት የተገኘው 230 ሚሊዮን ዶላር ብቻ ነው፡፡
በአገሪቱ ውስጥ ከፍተኛ የማዕድን ማውጫዎች እንደለሙ ይታወቃል፡፡ ብቸኛ ከፍተኛ ደረጃ ወርቅ አምራች የሆነው ሚድሮክ ጎልድ በለገደንቢ ወርቅ ማውጫ በዓመት ከ3.5 እስከ አራት ቶን ወርቅ እያመረተ ለውጭ ገበያ ያቀርባል፡፡
ከለገደንቢ ተጨማሪ በሌሎች ቦታዎች የወርቅ ፍለጋ ሥራዎች ያካሄደው ሚድሮክ ጎልድ፣ በመተከል ወርቅ ለማምረት ከማዕድን ሚኒስቴር ጋር ስምምነት ተፈራርሟል፡፡
የባህላዊ ወርቅ አምራቾች ከፍተኛ ምርት በማምረት ለብሔራዊ ባንክ በማቅረብ ከዘርፉ ለሚገኘው የውጭ ምንዛሪ ትልቅ አስተዋጽኦ ያደርጋሉ፡፡ በኦሮሚያ፣ በትግራይ፣ በደቡብ፣ በቤኒሻንጉልና በጋምቤላ ክልሎች ከአንድ ሚሊዮን በላይ ባህላዊ የወርቅ አምራቾች እንዳሉ ይገመታል፡፡ በማኅበራት የተደራጁ ባህላዊ ወርቅ አምራቾች በየዓመቱ እስከ ዘጠኝ ቶን ወርቅ እያመረቱ ለብሔራዊ ባንክ እያቀረቡ እስከ 400 ሚሊዮን ዶላር ያስገኙ ነበር፡፡ በወርቅ ዋጋ መቀነስና በኮንትሮባንድ መስፋፋት ከባህላዊ ወርቅ አምራቾች የሚገኘው የወርቅ መጠንና የውጭ ምንዛሪ እያሽቆለቆለ መጥቷል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ሦስት ኩባንያዎች ከፍተኛ የወርቅ ማውጫዎች በመገንባት ሒደት ላይ እንደሆኑ ተገልጿል፡፡ አቶ ሞቱማ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ኒው ሞንት የተሰኘው ግዙፍ የአሜሪካ ኩባንያ በትግራይ ክልል ሰፊ ሥራ እያከናወነ ይገኛል፡፡ ከፊ ሚነራልስ የተሰኘ የእንግሊዝ ኩባንያ በምዕራብ ወለጋ ቱሉካፒ በተባለ አካባቢ የወርቅ ማምረቻ ለመገንባት በዝግጅት ላይ ነው፡፡ ሚድሮክ ጎልድ በበኩሉ በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል መተከል ዞን ከፍተኛ ወርቅ ማዕድን ልማት ስምምነት፣ ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ጋር ተፈራርሞ ምርት ለመጀመር በዝግጅት ላይ እንደሆነ ታውቋል፡፡
አቶ ሞቱማ እንዳሉት፣ እነዚህ ሦስት ኩባንያዎች ማምረት ሲጀምሩ አገሪቱ ለውጭ ገበያ የምታቀርበው ወርቅ በከፍተኛ መጠን ያድጋል፣ ከዘርፉ የሚገኘው የውጭ ምንዛሪ መጠንም ይጨምራል፡፡
በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ማብቂያ ከማዕድን ዘርፍ በዓመት ሁለት ቢሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት መታቀዱ ይታወሳል፡፡
የተለያዩ ኩባንያዎች በማዕድን ልማት ዘርፍ ለመሰማራት የሚስችላቸውን ስምምነት ከማዕድን ሚኒስቴር ጋር ቢፈራረሙም፣ በአብዛኛው ወደ ልማት ሲገቡ አይታዩም፡፡ አቶ ሞቱማ በሰጡት ማብራሪያ፣ የማዕድን ፍለጋና ልማት ሥራ በባህሪው ውስብስብና ረዥም ጊዜ የሚወስድ የሥራ መስክ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ‹‹ጥልቅ የሆኑ ጉድጓዶች በሚቆፈሩበት ወቅት የሚፈጠሩ ችግሮች አሉ፡፡ ሥራው ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ የሚጠይቅ፣ ውስብስብ የሆነና ረዥም ጊዜ የሚፈጅ ነው፤›› ያሉት አቶ ሞቱማ፣ ኩባንያዎች በማዕድን ዋጋ መውረድ ወይም በሌሎች የራሳቸው ምክንያት ዕቅዳቸውን እንደሚለውጡ ገልጸዋል፡፡
ለማዕድንና ነዳጅ ፍለጋ ሥራ ገብተው ብዙ ሚሊዮን ዶላር ከስረው የሚወጡ ኩባንያዎች እንዳሉም ገልጸዋል፡፡ ከካሳ ክፍያና ከአካባቢ ጥበቃ ሥራዎች ጋር በተያያዘ በሚፈጠሩ ችግሮች የሚዘገዩ ፕሮጀክቶች እንዳሉ የገለጹት ሚኒስትሩ፣ በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በኩል የሚታዩ ችግሮችም እንዳሉ ተናግረዋል፡፡ በመሥሪያ ቤቱ በኩል የክትትል ማነስ ችግር እንዳለ አምነዋል፡፡
‹‹የእኛም የክትትል ችግር አለ፡፡ በምርመራ ላይ ያሉትንና የምርት ፈቃድ የወሰዱትን እየተከታተልን መደገፍ የሚገባቸውን እየደገፍን፣ ያላግባብ የቆዩትን እያስወጣን መሄድ አለብን፡፡ በዚህ ላይ ጠንክረን የተሻለ ሥራ ማከናወን ይኖርብናል፤›› ብለዋል፡፡
አገሪቱ ወደ ኢንዱስትሪ የጀመረችውን የሽግግር ጉዞ ለማገዝ የማዕድን ዘርፍ ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚውሉ ማዕድናትን በማምረት፣ የአምራች ኢንዱስትሪውን ለመደገፍ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሠራም ሚኒስቴሩ አስታውቋል፡፡