Thursday, December 1, 2022
ሌሎች ዓምዶች

  የሕገ መንግሥቱ ቅቡልነትና ተፈጻሚነት አሁንም እያከራከረ ነው

  - Advertisement -spot_img

  በብዛት የተነበቡ

  ባለፉት 23 ዓመታት ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ሚዲያዎች፣ ሲቪል ማኅበራት፣ ሙያ ማኅበራትና ምሁራን በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ላይ ጥያቄዎች ማንሳታቸውና አሉታዊ ትንታኔዎች መስጠታቸው የተለመደ ነበር፡፡

  የአንዳንዶች ሕገ መንግሥታዊ ትንታኔ በሕገ መንግሥቱ ተቀባይነት ላይ የሚያጠነጥን ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱን ‹‹የኢሕአዴግ ሕገ መንግሥት›› ብለው የሚጠሩት በርካታ አካላት የመኖራቸውን ያህል ጥቂቶች ‹‹የአቶ መለስ ሕገ መንግሥት›› እስከ ማለት ደርሰዋል፡፡ ይህን ጥያቄ ለማንሳትና አቋም ለመያዝ የሚያቀርቧቸው መከራከሪያ ነጥቦች በሕገ መንግሥት ማርቀቅ ሒደት፣ በሕገ መንግሥቱ አፈጻጸምና በሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ ያለው የለውጥ ዝግጁነት ላይ ይሽከረከራሉ፡፡ በእርግጥም ኢሕአዴግ ሕገ መንግሥቱን በማርቀቅ፣ አፈጻጸሙ ላይ ተፅዕኖ በማሳረፍና የማሻሻያ ሐሳቦችን በመከላከል ጉልህ ሚና ተጫውቷል፡፡

  እነዚህ ትችት የሚያቀርቡ አካላት በሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ ላይ ለውጥ እንዲደረግ ሲጠይቁም ይስተዋላል፡፡ በተጨማሪም በሥርዓቱ ላይ ተፅዕኖ አላቸው ብለው የለዩዋቸው የመንግሥት ፖሊሲዎችም እንዲለወጡ ወይም እንዲከለሱ በተደጋጋሚ ይጠይቃሉ፡፡ የገዥው ፓርቲ የረዥም ጊዜ መሪና ቁልፍ ቀያሽ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ከአምስት ዓመታት በፊት በድንገት ሕይወታቸው ሲያልፍና አዲስ አመራር ወደ ሥልጣን ሲመጣ እነዚህ ጥያቄዎች ተጠናክረው ቀርበው ነበር፡፡

  በወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትርን ‹‹ሌጋሲ ሳይበረዝ ለመቀጠል›› እንደሚሠሩ በመግለጽ ሳይገደቡ፣ ፓርቲው ያለምንም የፖሊሲ ለውጥ ለመቀጠል መወሰኑን አውስተው ነበር፡፡  ይሁንና በመጀመርያው ይፋዊ ንግግራቸው ከምሁራን፣ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ ከጥናትና ምርምር ተቋማት፣ ከሚዲያ ተቋማት፣ ከሙያ ማኅበራት፣ ከሲቪል ማኅበራትና ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር ተባብረው ለመሥራት ቃል መግባታቸው ይታወሳል፡፡ በዚህም ሕገ መንግሥቱን ጨምሮ በተለያዩ አንገብጋቢ አገራዊ ጉዳዮች ላይ እነዚህ አካላት ያላቸውን ሐሳብ በነፃነት እንዲሰጡ በማድረግ፣ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ በተሻለ መልኩ አካታች እንደሚሆን ብዙዎች ጠብቀው ነበር፡፡ በተግባር ግን ድኅረ መለስ አመራሩ እንደ ቀደመው መቀጠል የተሳነው ይመስላል፡፡ በዚህም የሕገ መንግሥት ቅቡልነት ላይ የሚነሱ ጥያቄዎች ይበልጥ እየተጠናከሩ መጥተዋል፡፡ ባለፉት ሁለት ዓመታት በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ከተነሳው አመፅና ተቃውሞ ጋርም ይኼው ጥያቄ ተጠናክሮ አገርሽቷል፡፡

  በርካታ የጥናት ሥራዎች የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ሥልጣን ላይ ያለው የኢሕአዴግ በተለይ ሕወሓት ፕሮግራም ጋር ተመሳሳይ እንደሆነ ያመለክታሉ:: ይህም በሕገ መንግሥቱ ዋነኛ አንቀጾች ላይ ለምሳሌም የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ሉዓላዊነት ላይ፣ የመገንጠል መብት ላይ፣ የመሬት ባለቤትነት መብት ላይ እንደሚንፀባረቅ ይጠቅሳሉ:: የሕገ መንግሥት ትርጉም ላይ፣ የሕገ መንግሥት ማሻሻያ፣ የዴሞክራሲያዊና የሰብዓዊ መብት ልዩነት ላይ፣ የክልልና የፌዴራል መንግሥቱ የሥልጣን ክፍፍል ላይ ደግሞ ከዲዛይን አንፃር ተጨማሪ ጥያቄዎች ይቀርባሉ፡፡

  ኢሕአዴግ ሥልጣን ላይ እስካለ ድረስ ሕገ መንግሥቱ ምንም ዓይነት ለውጥ አያስተናግድም በማለት የሚከራከሩ አካላት፣ ኢሕአዴግ በሰላማዊ የመድበለ ፓርቲ የምርጫ ውድድር ሥልጣን ቢያጣ ሕገ መንግሥቱ የመቀጠል ዕድሉ ምን ያህል ነው? ሲሉም ይጠይቃሉ፡፡ ሕገ መንግሥቱ ላይ ከሚነሳው የተቀባይነት ጥያቄ አንፃር በበላይነት ካረቀቀው ኢሕአዴግ ባሻገር፣ ሁሉም የሚሠራበት ሕገ መንግሥት ለመሆን ሊስተካከሉ የሚገቡ ነጥቦችን ምሁራኑ ያስረዳሉ፡፡

  የሕገ መንግሥት ማርቀቅ ሒደቱ እንደ ማንኛውም ሌላ ሕገ መንግሥት ኮሚሽን ተዋቅሮ፣ የሌሎች አገሮች ተሞክሮ ተወስዶ፣ ሕዝብ እንዲወያይበት ተደርጎ፣ ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈውበት በክርክር፣ በውይይት፣ በአስተያየቶች ዳብሮና በአብላጫ ድምፅ መፅደቁን ሁሉም ይጠቅሳሉ፡፡ ይሁንና ከኢሕአዴግ የጎላ ተፅዕኖ ጋር መወዳደር የሚችሉ አማራጭ ሐሳቦች እንዳልነበሩ በተወካዮች ምክር ቤት፣ በሕገ መንግሥቱ አርቃቂ ኮሚሽንና በሕገ መንግሥታዊ ጉባዔው የተሳተፉ አካላት ይገልጻሉ፡፡

  በሽግግር መንግሥቱ ቻርተር አማካይነት የሕገ መንግሥት አርቃቂ ኮሚሽኑ በወቅቱ ሕግ አውጪ አካል እንዲዋቀርና ያረቀቀውን ሕገ መንግሥት በተወካዮች ምክር ቤትና በሕዝቡ ውይይት ተደርጎበት፣ አስተያየቶቹ ተካተውበት ለሕገ መንግሥታዊ ጉባዔ በመጨረሻ ቀርቦ እንዲፀድቅ ተደንግጓል፡፡

  አንድ ሕገ መንግሥት ተቀባይነቱ የሚለካው በሕጋዊነት፣ በሞራልና በማኅበራዊ መሥፈርት መሆኑን የሕገ መንግሥት ጥናት ምሁራን ይጠቅሳሉ፡፡ ይሁንና ተቀባይነት አንፃራዊ ቃል በመሆኑ አንድ ሕገ መንግሥት ተቀባይነት አለው ወይም የለውም ለማለት አስቸጋሪ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ አንድ ሕገ መንግሥት ከመነሻው ከማርቀቅ ሒደቱ ጋር በተያያዘ የተቀባይነት ጥያቄ የሚነሳበት ቢሆንም፣ በሒደት ቅሬታዎችን አሳታፊ በሆነ ሁኔታ በመቅረፍ ተቀባይነት ሊጎናጸፍ እንደሚችል የሚሞግቱ ምሁራንም አሉ፡፡ ከተቀባይነት በተጨማሪ ሕገ መንግሥታዊነትና አፈጻጸም የተሻለ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት ለመፍጠር አስፈላጊ መሆናቸውንም ይጠቁማሉ፡፡ ሕገ መንግሥቱ የሁሉንም ዜጋ የባለቤትነት ስሜት እንዲያገኝ ከሕገ መንግሥቱ ጋር የሚጋጩ ነገሮችን በማስወገድ ሕገ መንግሥታዊ የበላይነትን ማረጋገጥ፣ በባለሥልጣናትና በዜጎች በእኩል እንዲከበር ማድረግ፣ ሕገ መንግሥታዊ ተቋማት እንዲጠናከሩ፣ ነፃ እንዲሆኑና ራሳቸውን የቻሉ እንዲሆኑ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑንም ይመክራሉ፡፡

  የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ቤት ነሐሴ 1 እና 2 ቀን 2009 ዓ.ም. ለመጀመርያ ጊዜ ባዘጋጀው ዓመታዊ የጥናት ኮንፈረንስ ይኼው ጉዳይ የመወያያ ርዕስ ሆኖ ነበር፡፡ በተሳታፊዎች ንቁ ተሳትፎ በታጀበው ኮንፈረንስ ሕገ መንግሥት፣ ሰብዓዊ መብት፣ ዓለም አቀፍ ሕግና ቢዝነስ ሕግ የተካተቱ ቢሆንም ርዕሰ ጉዳዩ የተነሳው በመጀመርያው ቀን የሕገ መንግሥቱ ቅቡልነት ላይ ባተኮረው ፕሮግራም ነው፡፡ በጉዳዩ ላይ አራት ጥናታዊ ጽሑፎች የቀረቡ ቢሆንም፣ በርካታ ጥያቄዎችና አስተያየቶችን የሳቡት ግን በዶ/ር አበራ ደገፋና በዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ የቀረቡት ላይ ነው፡፡

  የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አንጋፋ መምህርና የሕገ መንግሥት ጥናት ኤክስፐርቱ ዶ/ር አበራ ደገፋ ‹‹State-building and Issues of Legitimacy in Ethiopia: Chronicling Achievements, Failures and Prospects›› በሚል ርዕስ ባቀረቡት ጥናት፣ የአገረ መንግሥት ግንባታ ታሪኮች ብዙዎቹ ዘመናዊ አገሮች የተመሠረቱት በኃይል እንደሆነና ወደ ፍላጎትን መሠረት ያደረገ አገዛዝ ለመለወጥ በርካታ ጊዜያት እንደወሰደባቸው አስታውሰዋል፡፡

  በኢትዮጵያ ግን አሁንም ፍላጎትን መሠረት ያደረገ አገዛዝ መመሥረት እንዳልተቻለ አመልክተዋል፡፡ ለረዥም ዘመናት በሥልጣን ላይ የቆዩት መንግሥታት ፍላጎትን መሠረት ያደረገ አገዛዝ ባለመተግበራቸው የቅቡልነት ችግር እንደነበረባቸውና አሁንም በሥልጣን ላይ የሚገኘው መንግሥት ይህን እንዳልቀረፈ ዶ/ር አበራ ገልጸዋል፡፡ ‹‹በአጠቃላይ የተረጋጋ የፖለቲካ ሥርዓት፣ ዘላቂ ሰላምና ልማት ከማምጣት አንፃር በጣም ትንሽ መሻሻል ነው የተመዘገበው፤›› ብለዋል፡፡

  ዶ/ር አበራ በመንግሥት ቅቡልነትና በአገር መረጋጋት መካከል ጥብቅ ግንኙነት እንዳለ አውስተው፣ የዜጎችን አዎንታ ያላገኘ መንግሥት ተረጋግቶ ለመቀጠል እንደማይችል አመልክተዋል፡፡ በተለይ የፖለቲካ ቀውስ በሚያጋጥምበት ወቅት የመንግሥት ቅቡልነት ይበልጥ አሳሳቢ ጉዳይ እንደሚሆን አስገንዝበዋል፡፡ የፖለቲካ ቀውስ ቅቡልነት የሌላቸው፣ ገና እየመሠረቱ ያሉና እያጠናከሩ ያሉ መንግሥታትን ይበልጥ ፈተና ላይ እንደሚጥል ጠቅሰዋል፡፡

  የመንግሥት ቅቡልነት ከሒደት፣ ከአፈጻጸምና ከጋራ እምነት አንፃር እንደሚታይ የጠቆሙት ዶ/ር አበራ፣ ከሒደት አንፃር የመንግሥት ቅቡልነት የሚለካው ዜጎች በተስማሙባቸው ሕጎችና ሥነ ሥርዓቶች መሠረት እየመራ በመሆኑና ባለመሆኑ እንደሆነም አመልክተዋል፡፡ ከአፈጻጸም አንፃር ደግሞ መንግሥት ለሕዝቡ በሚሰጠው አገልግሎት ጥራትና ብዛት እንደሚለካ ጠቅሰዋል፡፡ የጋራ እምነት ደግሞ ሕዝቦች በጋራ መንግሥት ስላለው የመግዛት ሥልጣን በሚሰማቸው ስሜት እንደሚለካ ገልጸዋል፡፡ 

  የመንግሥት ቅቡልነት በኃይል ከመምራት ይልቅ በዜጎች ፍላጎትና ይሁንታ ለመምራት እንደሚያገለግል የጠቆሙት ዶ/ር አበራ፣ ይህንንም በጣም ውስን የሆነ ኃይል በመጠቀም ለማሳካት እንደሚያስችል አስገንዝበዋል፡፡ ከዚህ በተቃራኒ የቅቡልነት ችግር ያለበት መንግሥት አገዛዙን በኃይል ለማስቀጠል ሰፊ ሀብት ለመጠቀም እንደሚገደድ አመልክተዋል፡፡ ይህም ድጋፍ ስለሚቀንስ መልሶ በኃይል እንዲወርድ መነሻ እንደሚሆን ጠቁመዋል፡፡

  ኢትዮጵያን የመሩና እየመሩ ያሉ ሦስት መንግሥታት በኃይል ወደ ሥልጣን እንደመጡ አስታውሰው፣ ሁለቱ በመጡበት መንገድ በኃይል ከሥልጣናቸው እንደተወገዱም አውስተዋል፡፡ ሦስቱም መንግሥታትና የመሠረቷቸው ተቋማት ከዜጎች ጋር መልካም የሚባል ግንኙነት እንዳልነበረባቸውም ገልጸዋል፡፡ የኃይለ ሥላሴና የደርግ መንግሥታት ፈላጭ ቆራጭ የሆነ የፖለቲካ ባህል በመመሥረታቸው የአገሪቱ የፖለቲካ ልሂቃን አስተሳሰብ በዚሁ እንዲቃኝ ማድረጉንም ተችተዋል፡፡ ‹‹ልሂቃኑ የፖለቲካ ሥልጣንን በብቸኝነት ለመጠቀም በተለይም እንደ መሬት ያለን ሀብትም በተማከለ ሁኔታ ለመጠቀም እንዲያልሙ ያደረጋቸው ይኼ የተወረሰ ባህል ነው፤›› ብለዋል፡፡ በዚህ የተነሳ ያለፉት ሁለት መንግሥታት የቀረጿቸው ሕገ መንግሥታትና ተቋማት ከመንግሥታቱ ጋር አብረው መጥፋታቸውንም አስታውሰዋል፡፡

  ዶ/ር አበራ የ1983 ዓ.ም. ሽግግር ኢትዮጵያን በአዲስ መልኩ ፍላጎት ላይ መሠረት ባደረገ አገዛዝ እንደገና ለማዋቀር ዕድል ፈጥሮ የነበረ ቢሆንም ጥቅም ላይ እንዳልዋለ አመልክተዋል፡፡ ‹‹ከአኃዳዊ አገዛዝ ወደ ኅብረ ብሔራዊ ፌዴሬሽን የተደረገው ሽግግር መሠረታዊ ለውጥ አምጥቷል፡፡ ከአፈጻጸምም አኳያ በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት አገልግሎት በመስጠትና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን በማረጋገጥ የሚታይ ስኬት አስመዝግቧል፡፡ ነገር ግን ሁሉን አካታች የሆነ የፖለቲካ ማኅበረሰብ በመፍጠር ረገድ አሁንም ክፍተቶች አሉ፤›› ብለዋል፡፡

  በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ቅቡልነት ላይ ጥያቄዎች እንደሚነሱ ጊዜ እየጠበቁ የሚነሱት አመጾችና ተቃውሞዎች የማያጠራጥሩ ማሳያ እንደሆኑም አመልክተዋል፡፡ ‹‹የእነዚህ አመጾችና ተቃውሞዎች ሥረ መሠረት በአግባቡ መጠናት አለበት፡፡ ኢትዮጵያ የተመሠረተችው በወረራና በኃይል ቢሆንም ዘላቂ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት ለመገንባት በፈቃድ ላይ የተመሠረተ አገዛዝ ሊመሠረት ይገባል፡፡ ያለፉት ሥርዓቶች መለያ ከሆኑት ልሂቃንን መሠረት ያደረገ አገዛዝና ፈላጭ ቆራጭ ከሆነ የፖለቲካ ባህል ተላቀን፣ ፍትሐዊ የሥልጣንና የሀብት ክፍፍል የሚያደርግ ሥርዓት ለመገንባት መጣር አለብን፤›› ሲሉ ደምድመዋል፡፡

  ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ በበኩላቸው ‹‹Constitutionalism without Liberals, Democracy without Democrats: The Ethiopian Case›› በሚል ርዕስ ባቀረቡት ጥናት፣ የኢትዮዽያ የዴሞክራሲ ባህል ሕገ መንግሥታዊ ዴሞክራሲን ለመገንባት ለሚደረገው ጥረት ትልቅ እንቅፋት እንደሆነ ተከራክረዋል፡፡ ዴሞክራቶችና ሊበራሎች ሳይኖሩ ዴሞክራሲንና ሕገ መንግሥታዊነትን ለማረጋገጥ የተደረገው ሙከራ ትልቅ ውድቀት እንደሆነም አመልክተዋል፡፡

  በዴሞክራሲ ላይ የሚመራመሩ እንደ ሳሙኤል ሃንቲንግተን፣ ማርቲን ሊፕሲትና ሮበርት ዳል ያሉ ምሁራን የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ዋነኛ መገለጫ ፍትሐዊ ውድድር የሚደረግበት ሥነ ሥርዓት መሆኑን እንደሚያሰምሩበት ጠቅሰዋል፡፡ ሒደቱ ዕድሜያቸው ለአቅመ አዳምና ሔዋን ለደረሱ ግለሰቦች በተወዳዳሪነት፣ በመራጭነት፣ በተንታኝነት፣ በተችነትና በመሳሰሉ እንቅስቃሴዎች እንዲሳተፉ ምኅዳር እንደሚያመቻችም አስገንዝበዋል፡፡ ይኽም በዋነኝነት የተሻለ ፖሊሲ ያለውንና የፖለቲካ ውሳኔ የሚሰጠውን ኃይል ለትልቁ የፖለቲካ ሥልጣን ዜጎች እንዲያበቁ ዕድል በመስጠት እንደሚገለጽ ገልጸዋል፡፡

  በአጠቃላይ በአንድ አገር ዴሞክራሲያዊ አገዛዝ እንዲሰፍን ለማድረግ ከሚያስፈልጉ ተቋማዊ ማስተማመኛዎች መካከል ፖለቲካ ፓርቲዎችንና ሲቪል ማኅበራትን ጨምሮ ማኅበራት የመፍጠር ነፃነት፣ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት፣ የመምረጥና የመመረጥ መብት፣ የፖለቲካ ድጋፍ የማሰባሰብ ነፃነት፣ ነፃና ፍትሐዊ ምርጫ ማድረግና የመንግሥት ፖሊሲዎችን የሚያወጡ ተቋማት ውሳኔዎች በመራጩ ሕዝብ ፍላጎትና ጥቅም እንዲቃኙ ማድረግ ተጠቃሽ እንደሆኑ አስረድተዋል፡፡

  ሕገ መንግሥታዊነትም በዋነኛነት የሚገለጸው በመንግሥት ሥልጣን ላይ ሕጋዊ ገደብ በማድረግ እንደሆነም አስታውሰዋል፡፡ ሕገ መንግሥቱም በዋነኛነት የመንግሥት ሥልጣን ላይ ገደብ ለማድረግ የተቀረፀ ከመሆኑ አኳያ፣ ሕገ መንግሥታዊነት ወይም ሕገ መንግሥቱን መሠረት ያደረገ አገዛዝ ተብሎ ይተረጎማል፡፡

  ይህ ገደብ መንግሥት የዜጎችን ሲቪል መብት እንዲያከብር፣ የሥልጣኑ ወሰን እንዲታወቅና ሥልጣኑን እንዴት እንደሚጠቀምበት በመደንገግ እንደሚገለጽም ጠቁመዋል፡፡ እነዚህን ሕገ መንግሥታዊ ገደቦችን ያላከበረ መንግሥት ቅቡልነት ያለውና የመግዛት ሥልጣኑ ሊከበርለት የሚገባ ተደርጎ እንደማይወሰድም አመልክተዋል፡፡

  በጽንሰ ሐሳብ ደረጃ ‹ሊበራሊዝም› እና ‹ኮንስቲቲውሽናሊዝም› የማይነጣጠሉ ናቸው፡፡ ሊበራሊዝም ለግለሰቦች ነፃነት ሲባል በመንግሥት ሥልጣን ላይ ገደብ እንዲደረግ ይጠይቃል፡፡ በዚህም ሊበራሊዝም ለኮንስቲቲውሽናሊዝም ርዕዮተ ዓለማዊ መሠረት ይጥላል፡፡ ዴሞክራሲና ‹ኮንስቲቲውሽናሊዝም› ሲቀላቀሉ ደግሞ ሕገ መንግሥታዊ ዴሞክራሲን ይፈጥራሉ፡፡

  አንድ ሕገ መንግሥት ለአንድ ማኅበረሰብ የተስማማና ረግቶ የሚቆይ መሆኑን የሚወስነው የፖለቲካ ባህሉ እንደሆነም አመልክተዋል፡፡ የፖለቲካ ባህል በዋነኛነት የሚገለጸው ዜጎች በፖለቲካ ተዋናዮች ላይ ባላቸው የአተያይ አዝማሚያ ስብጥር እንደሆነም ጠቅሰዋል፡፡ በተጨማሪም የፖለቲካ ሥርዓቱ ላይ ተፅዕኖ መፍጠር የሚችሉና በአብዛኛው ማኅበረሰብ ዘንድ የሚንሸራሸሩ እምነቶች፣ እሴቶችና አመለካከቶች የፖለቲካ ባህሉን እንደሚቀርፁ አስገንዝበዋል፡፡ የፖለቲካ ልሂቃኑ የፖለቲካ ባህልን በመቀየር ረገድ ቁልፍ ሚና እንደሚጫወቱም አክለዋል፡፡

  በ1987 ዓ.ም. ሕገ መንግሥት ላይ የመንግሥት ሥልጣን የተገደበ ቢሆንም፣ በተግባር ግን ይህ እንደማይስተዋል ይልቁንም በየቀኑ እንደሚጣስ ገልጸዋል፡፡ ሥልጣን በዘፈቀደ ጥቅም ላይ እንደሚውልም አመልክተዋል፡፡ አገሪቱ በአንድ ፓርቲ ሥር መሆኗም ይህንን እንዳጠናከረው ገልጸዋል፡፡ ሕገ መንግሥቱ በወረቀት ላይ ቢኖርም በተግባር አለመቀየሩ ‹‹አልሞትኩም ብዬ አልዋሽም›› የሚለውን አባባል እንደሚያስታውሳቸው አስረድተዋል፡፡

  በእውነታውና በዜጎች ፍላጎት መካከል ላለው አለመመጣጠን ዋነኛው ተጠያቂ የአገሪቱ የፖለቲካ ባህል መሆኑን ያመለከቱት ዶ/ር ጌድዮን፣ የ1966 ዓ.ም. አብዮት፣ የ1983 ዓ.ም. ሽግግርና የ1997 ዓ.ም. ምርጫ የኅብረተሰቡን የፖለቲካ ባህልና እምነት በመቅረጽ ጉልህ ሚና መጫወታቸውን አስገንዝበዋል፡፡ በተለይ ከ1966 ዓ.ም. አብዮትና ከ1960ዎቹ የተማሪዎች ንቅናቄ የተወረሰው በማርክሲስትና ሌኒኒስት ርዕዮተ ዓለም የተቃኘው የግራ ፖለቲካ በአገሪቱ የፖለቲካ ባህል ላይ ጠባሳ ትቶ እንዳለፈ ሞግተዋል፡፡

  ዶ/ር ጌድዮን ሲደመድሙ፣ ‹‹በአብዛኛው ዴሞክራሲያዊና ሊበራል የሆነ ሕገ መንግሥት ሠርተናል፡፡ አሁን ዴሞክራቶችንና ለሕገ መንግሥት መከበር የሚተጉ ወይም ሊበራሎችን የምንፈጥርበት ጊዜ ነው፤›› ብለዋል፡፡ በሕግና በተቋማት ላይ ከመጠን ያለፈ ትኩረት በማድረግ ለውጥ ሊደረግበት የሚገባው የሕገ መንግሥት ተግባራዊነትና ለሕገ መንግሥታዊነትና ለዴሞክራሲ የሚመች አዲስ የፖለቲካ ባህል ግንባታ በቂ ትኩረት እንዳልተሰጠው በማመልከትም እዚህ ላይ መረባረብ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

  ሁለቱ ምሁራን ጥናቶቻቸውን ካቀረቡ በኋላ ታዳሚዎች የተለያዩ ጥያቄዎችንና አስተያየቶችን ሰንዝረዋል፡፡ የሕግና ፍትሕ ሥርዓት ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው ረዳ፣ ‹‹ቅቡልነት የውይይት ውጤት ነው ወይስ ሁሉን አካታች የሆነ የልሂቃን የድርድር ውጤት ነው?›› ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

  አቶ ጌታቸው፣ ‹‹ዶ/ር ጌድዮን ምዕራብ አትላንቲክ ላይ ያመዘኑ ምሁራንን ነው የጠቀሱት፡፡ ከሞላ ጎደል የጠቀሱት የዴሞክራሲ ጽንሰ ሐሳብ ሊበርቶሪያን የሚባለው ነው፡፡ ማርቲን ሊፕሲት፣ ሳሙኤል ሃንቲንግተን፣ ሮበርት ዳል አንዳቸውም ቢያንስ የሰሜን አትላንቲክን አስተሳሰብ የሚወክሉ አይደሉም፡፡ ሁሉንም ወገን የሚወክሉ ምሁራን ሥራዎች ቢጠቀሱ ጥሩ ነው፤›› የሚል አስተያየትም አክለዋል፡፡

  ‹‹የፖለቲካ ባህል በጣም አስፈላጊ ነገር ነው፡፡ የሚስትን እኩል መሆን የማይቀበል አባወራና ሚስቱ ጥያቄ ባቀረበች ቁጥር ግልምጫና ዱላ የሚቀናው ሰው ድንገት የሥልጣን ኮሪደር ላይ ራሱን ቢያገኘው፣ ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብ ሊያራምድ አይችልም፡፡ ፓርቲዎቹም እንደዚሁ ናቸው፤›› ሲሉም አቶ ጌታቸው በፖለቲካ ባህል ግንባታ ላይ ከታች  ጀምሮ ሊሠራ እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡

  ሌላኛው አንጋፋ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር ዶ/ር መሓሪ ረዳኢ ለዶ/ር አበራ አንድ ወሳኝ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡ ‹‹የኢትዮዽያ መንግሥታት የቅቡልነት ዕጦት አለባቸው ብለው ደምድመዋል፡፡ ምናልባት መደምደሚያው ላይ ብዙም ችግር ላይኖር ይችላል፡፡ የእኔ ጥያቄ ድምዳሜው የተደረሰበት መንገድ ላይ ነው፡፡ የኃይለ ሥላሴና የደርግ መንግሥታት አሀዳዊ የመንግሥት መዋቅር ነበራቸው፡፡ አሁን የምንከተለው ደግሞ የፌደራል መዋቅር ነው፡፡ አሀዳዊ የመንግሥት መዋቅር ያለበትን የቅቡልነት ዕጦት ለመመርመር የምንጠቀመው መሣሪያ በተመሳሳይ የፌዴራል መዋቅርን ለመመርመር ጥቅም ላይ መዋል አለበት ወይ? ወይስ ተጨማሪ መሣሪያ ያስፈልጋል? የቅቡልነት ዕጦትስ አለ እያልን ያለነው በፌዴራል ደረጃ ነው ወይስ በክልል ደረጃ?›› ብለዋል፡፡

  የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕግ፣ ፍትሕና አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ጴጥሮስ ወልደ ሰንበት ፣ ‹‹የነባሮቹን መንግሥታት ቅቡልነት መጠየቅ ተገቢ ነው፡፡ የአሁኑ መንግሥት ላይ ግን ልዩነት አለኝ፡፡ አመጣጡ በኃይል መሆኑ አንድ ጉዳይ ነው፡፡ ግን የሕዝብ ተሳትፎን ከማረጋገጥ አኳያ፣ በምርጫ አሸንፎ ከመምራቱ አንፃር፣ ሕገ መንግሥቱ ላይም መጀመርያ ሕዝቡ እንዲወያይበት በኋላ ላይ ደግሞ በሕዝብ ተወካዮች እንዲፀዲቅ መደረጉ ከመጀመርያዎቹ አይለየውም ወይ?›› ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

  አቶ ጴጥሮስ፣ ‹‹የምርጫ 97 ቅድመ ምርጫ ዴሞክራሲያዊ ከሆነ ድኅረ ምርጫው እንዴት ኢዴሞክራሲያዊ ሊሆን ይችላል? የተወሰነ ኃይል የሚፈልገውና ያሸንፋል ተብሎ የተገመተው ክፍል ሲሸነፍ ዴሞክራሲ አይደለም ብሎ እንደ መደምደም አይወሰድም ወይ?›› ሲሉም ሌላ ጥያቄ አክለዋል፡፡ 

  ብሎገሩ አቶ በፍቃዱ ኃይሉ በበኩላቸው፣ ‹‹በሥራ ላይ ያለው ሕገ መንግሥት ላይ ተቃውሞ ያላቸው አካላት የመኖራቸውን ያህል ተጠብቆ እንዲቆይ የሚፈልጉም አካላት አሉ፡፡ አሁን ደግሞ እያደጉ የመጡ አመጾች ወይም ተቃውሞዎች አሉ፡፡ ባለፈው አንድ ክፍለ ዘመን ሕገ መንግሥቶችን እያፈረስንና እየገነባን ነው የመጣነው፡፡ አሁን በአገሪቱ ያሉ አመጾች ወይም ንቅናቄዎች አዲስ ሕገ መንግሥት እንዲረቀቅ ነው የሚፈልጉት? ወይስ እንዲጠበቅ ነው እየጠየቁ ያሉት? የትኛው ድምፅ ነው የሚያደላው?›› ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

  ሌላኛው አንጋፋ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር አቶ ዘካሪያስ ቀንአ፣ ‹‹ሕገ መንግሥትና ሕገ መንግሥታዊነት እንደ ሌላው ሕግ ከሌሎች አገሮች በመቅዳት የምንሞክረው ነው? ኢትዮጵያ ውስጥ ላለፉት 60 ዓመታት የውጭ ሕጎች አልሠሩም፡፡ ከሞላ ጎደል ዘይትና ውኃ ሆነው ነው የቆዩት፡፡ ዛሬም ባህላዊና ልማዳዊ ሕጎች በብዙ መልኩ የበላይነት አላቸው፡፡ ስለዚህ ስለባህል ስናወራ በሕዝቡ ዘንድ ያለውን ባህል ነው? ወይስ ዘመናዊ ሕጎችን በተመለከተ ስላለው ባህል ነው የምናነሳው? ብዙ ነገሮቻችን ዘመናዊ ሕጎቻችንን ጨምሮ ለዕይታና ለማስመሰል ብቻ የሚውሉ ናቸው፡፡ ጥሩ ሕገ መንግሥትና ሕጎች ቢኖሩም አንተገብራቸውም፤›› ሲሉ ጥያቄና አስተያየታቸውን አቅርበዋል፡፡

  የሕወሓት መሥራችና አንጋፋው ፖለቲከኛ አቶ ስብሐት ነጋ ደግሞ በአቶ በፍቃዱ ጥያቄ ላይ አስተያየት ሲሰጡ፣ ‹‹አሁን ያለው ተቃውሞ መነሻ በሕገ መንግሥቱ ቃል ገብቶ ያልፈጸማቸውና ያጎደላቸው መሠረታዊ ጉድለቶች አሉ መባሉ ነው እንጂ፣ ሕገ መንግሥቱ ይለወጥ አይደለም፡፡ ይኼ ማለት ሕገ መንግሥቱን የሚቃወም የለም ማለት አይደለም፤›› ብለዋል፡፡

  በጥያቄዎቹና በአስተያየቶቹ ላይ ጥናት አቅራቢዎቹ በድጋሚ ሐሳባቸውን አካፍለዋል፡፡ በዚህም ዶ/ር አበራ በአጠቃላይ አሁን በሥልጣን ላይ ያለውን መንግሥት ቅቡልነት አስመልክተው ሲናገሩ፣ ‹‹የአገር ግንባታ በተቋማት ግንባታ መታገዝ አለበት፡፡ ይኼ ዴሞክራሲያዊ ሕገ መንግሥትን ይጨምራል፡፡ ተቋማቱ ሁሉን አካታች መሆን አለባቸው፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥታት ግን አግላይ፣ በዝባዥና ጠቅላይ የሆኑ ተቋማትን ነው ሲፈጥሩ የኖሩት፡፡ የኢኮኖሚውም ሆነ የፖለቲካው ዘርፍ ለልሂቃኑ ብቻ የተመቸና የተማከለ ነው፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ የተከፋፈሉ ማኅበረሰቦች የሚኖሩባቸው አገሮች ተቋማቱ ሁሉን አካታች መሆን አለባቸው፡፡ በተለይ ጠንካራ ቡድኖችን ካገለሉ ቀውስ ውስጥ መግባታቸው አይቀርም፡፡ መንግሥትም ቅቡልነት የሚያገኘው በአግባቡ ከተካተተውና ጥቅሙ ከተከበረለት ቡድን በተለይም ከቡድኑ ልሂቃን ነው፡፡ ሌሎቹ የተገለሉት ቡድኖች ግን ቅቡልነቱን መገዳደራቸው አይቀርም፤›› ብለዋል፡፡

  ዶ/ር አበራ፣ ‹‹በሥራ ላይ ያለውን የፌዴራል መዋቅር ቅቡልነት እገዳደራለሁ፡፡ ኃይልን መሠረት ካደረገ አመራር ፈቃድን መሠረት ወዳደረገ አመራር አልመጣንም፡፡ የመንግሥት የመምራት መብት በሕዝቡ ተቃውሞ ጥያቄ ከቀረበበት የቅቡልነት ዕጦት መገለጫ ሊሆን ይችላል፡፡ በኢትዮጵያ ታሪክ በአግባቡ ሕዝቡ የመከረበት ሕገ መንግሥት አፅድቀን አናውቅም፡፡ ባህሉ እስካሁን ድረስ ልሂቃንን መሠረት ያደረገ ነው፡፡ ሕዝብን መሠረት ያደረገና ከታች ወደ ላይ የሚሄድ አገዛዝም ኖሮ አያውቅም፡፡ ጥሩ ሕገ መንግሥት መያዝና ምርጫ ማካሄድ ቅቡልነት አያስገኝም፡፡ ሕገ መንግሥቱ ተግባር ላይ ካልዋለ በእውነታው ያ አገር ሕገ መንግሥት የለውም ማለት ነው፡፡ በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት የተወሰኑ ስኬቶች አስመዝግቧል፡፡ ከአሀዳዊ የመንግሥት መዋቅር ወደ ፌዴራል መዋቅር መምጣት በኢትዮጵያ ላሉት መሠረታዊ ችግሮች በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ዕውቅና ለመሰጠቱ ማሳያ ነው፡፡ ነገር ግን በትክክል ለመተርጎም ብዙ አልተሄደበትም፡፡ ከዴሞክራሲያዊ አገር የሚጠበቀው ሁሉን አካታችነት በተግባር የለም፡፡ አንድ ፓርቲ ፓርላማው ላይ ፍፁም የበላይ መሆኑ የት እንደምንገኝ ግልጽ ማሳያ ነው፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡

  ዶ/ር ጌዲዮን በበኩላቸው፣ ‹‹መንግሥትና ተቃዋሚ ፓርቲዎች ብቻ የፖለቲካ ባህሉን ሊቀይሩት አይችሉም፡፡ አብዛኛው ሥራ ከመንግሥት ውጪ ባሉ አካላት የሚከናወን ነው፡፡ አመለካከታችንና አስተሳሰባችንን የሚቀርፁ እንደ ቤተሰብ፣ ትምህርት ቤት፣ ሲቪል ማኅበራት፣ የሃይማኖት ተቋማትና የመሳሰሉት አካላት ቁልፍ ሚና አላቸው፡፡ ነገር ግን ለዚያ የሚሆን ምኅዳር መንግሥት መፍጠር አለበት፡፡ የፖለቲካ ባህሉን ከግምት ውስጥ ካስገባን ሕገ መንግሥታዊ ዴሞክራሲን ለመገንባት የምናደርገው ጥረት ከባድ እንደሚሆን ግምት ውስጥ ማስገባት አለብን፡፡ የፖለቲካ ባህላችን ይበልጥ ፈላጭ ቆራጭ በሆነ ቁጥር ጉዞው ይበልጥ ይከብዳል፡፡ የፖለቲካ ባህል ባይኖረንም መፍጠር እንችላለን፡፡ ከራሳችን ልማድና ባህል ጋር የተያያዘ ሕገ መንግሥት ብናፀድቅ በተሻለ ተግባራዊ ልናደርገው እንችላለን የሚል ክርክር ይነሳል፡፡ እኔ በዚህ አልስማማም፡፡ ምክንያቱም በባህላችንና በታሪካችን ያልነበሩ እንደ ፖሊስና እስር ቤት ያሉ አዳዲስ ተቋማትንና የአገዛዝ ሥርዓትን ከውጭ ሕጎች ውስጥ ነው ያገኘናቸው፡፡ የግድ ከውጭ ሕጎች ማምጣት አለብን ብዬ አላምንም፡፡ ነገር ግን የነበረው የሚበቃን አልመሰለኝም፡፡ መጨመርና አዲስ ነገር መፍጠር ይኖርብናል፤›› ብለዋል፡፡ 

  ‹‹በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 14፣15 እና 17 በሕይወት ስለመኖር፣ ስለአካል ደህንነትና ነፃነት መብት የዛሬ 22 ዓመት ቃል የገባውንና አሁን ያለንበትን ሁኔታ ስናይ፣ ሕገ መንግሥቱ ሕያው ነው ብሎ በሙሉ አፍ ለመናገር የሚያስደፍር አይመስለኝም፤›› ሲሉም ደምድመዋል፡፡   

  spot_img
  - Advertisement -

  ትኩስ ጽሑፎች

  ተዛማጅ ጽሑፎች

  - Advertisement -
  - Advertisement -