Sunday, June 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልየሆሄ ምርጦች የከበሩበት መድረክ

የሆሄ ምርጦች የከበሩበት መድረክ

ቀን:

አዳራሹ ከዳር እስከ ዳር በሰዎች ተሞልቷል፡፡ ታዳሚያኑ ሕፃናት፣ ወጣት፣ አዛውንት ሳይል በሁሉም የዕድሜ ክልል የሚገኙ ናቸው፡፡ ደራስያን፣ የጥበብ አፍቃሪያንና ሌሎችም ባለሙያዎች ትኩረት የሳበ ፕሮግራም የተዘጋጀው በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ነበር፡፡ ቀጠሮ አክብሮ በተባለው ሰዓት መገኘት የብዙዎች ችግር ቢሆንም የዕለቱ የክብር እንግዶች ሳይቀሩ ቦታ ቦታቸውን የያዙት ቀደም ብለው ነበር፡፡

ፕሮግራሙ ይጀመራል በተባለው ሰዓት ሳይጀመር ደቂቃዎች ቢያልፉም ሞቅ ተደርገው የተለቀቁት ቆየት ያሉ ጥዑመ ዜማዎች ታዳሚውን ሲያዝናኑ ነበር፡፡ በተለይም በፌዴራል ፖሊስ የማርሽ ባንድ የቀረቡት ዜማዎች ሁሉንም ያነቃቁ ነበሩ፡፡ ማርሽ ባንዱ ከአዲሱ የቴዲ አፍሮ የሙዚቃ አልበም መካከል የሆነውን ‹‹ኢትዮጵያ›› የሚለውን ዘፈን በሚጫወትበት ጊዜ አብዛኛዎቹ ታዳሚያን ኦርኬስትራውን ተከትለው ሲዘፍኑ ነበር፡፡

ሙዚቃውን እንደጨረሱ ‹‹ሆሄ ማለት ስመ ፊደል፣ የፊደል መልክ . . . ወደ ሰፊው ሕይወት የሚያስገባ በር ማለት ነው፤›› በሚል ንግግር መድረክ መሪው አርቲስት ዓለማየሁ ታደሰ ፕሮግራሙን አስጀመረ፡፡ ስለ ቃሉ ትርጓሜ ሙሉ ገለጻ ከሰጠ በኋላም በቃሉ ስለተሰየመው ፕሮግራም ማብራሪያ መስጠት ጀመረ፡፡

ሆሄ የሥነ ጽሑፍ ሽልማት የንባብ ባህልን የማዳበር፣ የደራስያንን ክብር ከፍ የማድረግ ዓላማ ይዞ የተነሳ፣ በየዓመቱ የሚካሄድ የሽልማት ፕሮግራም ነው፡፡ ከመስከረም 1 ቀን 2008 ዓ.ም. እስከ ጳጉሜ 5 ቀን 2008 ዓ.ም. ድረስ የታተሙ ረዥም ልብ ወለዶች፣ የሕፃናት መጻሕፍትና  የግጥም መድበሎች የሚወዳደሩበት የሽልማት ፕሮግራም ነው፡፡

የማኅበረሰቡን የንባብ ባህል ማዳበር፣ ደራስያንም ክብርና በሥራቸው ተገቢውን ጥቅም ማግኘት እንዲችሉ የማድረግ ዓላማ ያለው የሆሄ ሽልማት የተዘጋጀው በሦስት ዘርፎች ነው፡፡ ምርጥ ረዥም ልብ ወለድ፣ ምርጥ ግጥምና ምርጥ የልጆች መጻሕፍት የመወዳደሪያ ዘርፎቹ ነበሩ፡፡ ለንባብ መዳበር አስተዋጽኦ ላደረጉ ግለሰቦችና ተቋማትም በአምስት ዘርፎች ዕውቅና ሰጥቷል፡፡

በምርጥ የልጆች መጽሐፍ ዘርፍ ሦስት መጻሕፍት ዕጩ ሆነው ቀርበዋል፡፡ በአስረስ በቀለ የተጻፉ ዋናተኛዋ ሶሊያናና የቤዛ ቡችላ፣ እንዲሁም የታለጌታ ይመር የአይጦችና የድመቶች ሠርግ ዕጩዎቹ ነበሩ፡፡ አሸናፊ ሆኖ የዓመቱን የሆሄ ሽልማት የተቀዳጀው ምርጥ የልጆች መጽሐፍም የኮሜዲያን አስረስ በቀለ ሥራ የሆነው የቤዛ ቡችላ የተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡

ኮሜዲያን አስረስ በቀለ በልጆች የቴሌቪዥን ፕሮግራም የቼሪን ገጸ ባህሪ በመጫወት ተወዳጅነትን ያተረፈ ባለሙያ ነው፡፡ ነሐሴ 22 ቀን 2009 ዓ.ም.  ሰኞ በብሔራዊ ቴአትር ተዘጋጅቶ በነበረው የሽልማት ሥነ ሥርዓት ሽልማት ሲቀበል ‹‹ይህንን ታሪክ አባባ ተስፋዬ ኖረው ቢያዩልኝ ደስ ይለኝ ነበር፤›› በማለት ስሜቱን ገልጿል፡፡

በምርጥ የግጥም መጽሐፍ ዘርፍ የኤፍሬም ሥዩም ኑ ግድግዳ እናፍርስ፣ የትዕግሥት ማሞ የጎደሉ ገጾች፣ የበላይ በቀለ ወያ እንቅልፍና ሴት፣ የአበረ አያሌው ፍርድና እርድ እንዲሁም የበድሉ ዋቅጅራ (ዶ/ር) ሥራዎች በዕጩነት ቀርበው ነበር፡፡ የዓመቱ የሆሄ ሽልማት አሸናፊ ሆኖ የተመረጠው ግን የአበረ አያሌው ፍርድና እርድ ነው፡፡ ‹‹ያልጠበቅኩት ነገር ነው፡፡ በመጀመሪያ ሥራ ማሸነፍ ደግሞ ትልቅ ነገር ነው›› በማለት ሽልማቱ ያልጠበቀውና ይበልጥ እንዲሠራ የሚያነሳሳው መሆኑን ተናግሯል፡፡

በረዥም ልብ ወለድ መጽሐፍ ዘርፍ በዓለማየሁ ዋሴ (ዶ/ር) የተጻፈው ዝጎራ፣ የአዳም ረታ የስንብት ቀለማትና ሌሎችም በዕጩነት የቀረቡ ሲሆን የ2008 ዓ.ም. ምርጥ ሆኖ የተሸለመው የአዳም ረታ የስንብት ቀለማት ነበር፡፡ ደራሲው በቦታው ባለመገኘቱ ተክቶት ሽልማቱን የተቀበለው ወንድምየው ነበሩ፡፡

መጻሕፍትን ለዓይነ ሥውራን በብሬይልና በኦዲዮ በበቂ ማቅረብ በአገሪቱ የመማር ማስተማር ሥርዓት ትልቅ ክፍተት እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ብዙዎቹ ዓይነ ሥውር ተማሪዎችም በጉዳዩ ቅሬታቸውን ሲገልጹ ይሰማል፡፡ ለዚህ ችግር መፍትሔ የሚሰጥ ላይብረሪ ያዘጋጀው አዲስ ሕይወት የዓይነ ሥውራን ማዕከል ለዓይነ ሥውራን መጽሐፍ ተደራሽ በማድረግ ዘርፍ የዚህ ዓመት የሆሄ ሽልማት አካል ሆኗል፡፡

በረዥም ዘመን የሥነ ጽሑፍ ሐያሲነት የሥነ ጽሑፍ ባለውለታ ዘርፍ ደራሲ አስፋው ዳምጤ፣ በሕይወት ዘመን የሥነ ጽሑፍ የላቀ ባለውለታ ዘርፍ አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ተሸላሚ ሆነዋል፡፡ አለቃ ኪዳነ ወልድ መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ በሚል መጽሐፋቸው በብዙዎች ዘንድ ይታወቃሉ፡፡ ይህንን ሥራቸው በያዘው ጥልቅ ሐሳብ አንፃር ያዩት አንዳንድ ባለሙያዎች ከኢንሳይክሎፒዲያ ጋር ያመሳስሉታል፡፡

በረዥም ዘመን ጋዜጠኝነት ደግሞ ጋዜጠኛ ደጀኔ ጥላሁን ለንባብ መዳበር አስተዋጽኦ በማድረግ ተሸላሚ ሆኗል፡፡ በረዥም ዘመን የትምህርት መስፋፋት ባለውለታ ሽልማት ዘርፍ አቶ ማሞ ከበደ ሸንቁጥ ተሸላሚ ሆነዋል፡፡ አቶ ማሞ በትምህርት ዘርፍ ለረዥም ዓመታት ያገለገሉ ሲሆን፣ የተለያዩ የትምህርት መጣጥፎች አዘጋጅተዋል፡፡ በመሠረት ትምህርት ዘመቻዎች በተደጋጋሚ ጊዜ ተሳትፈዋል፡፡ ትምህርት በሬዲዮ በማዘጋጀትም ይታወቃሉ፡፡

‹‹በትምህርቱ ዘርፍ ለዓመታት በመሥራቴ ደስተኛ ነኝ፡፡ አሁን አርጅቻለሁ፡፡ በሥራዬ በመሸለሜ ደስተኛ ነኝ፡፡ ሽልማቱ ሌሎችን ያነቃቃል፤›› በማለት ደስታቸውን ገልጸዋል፡፡ አሸናፊዎቹ የተመረጡት 80 በመቶ በዳኞች ድምፅ፣ 20 በመቶ ደግሞ በማኅበረሰቡ ድምፅ ነው፡፡ በውድድሩ በሥነ ጽሑፍ የበቁ የተባሉ ዘጠኝ ዳኞች ተሳትፈውበታል፡፡

ኖርዝ ኢስት ኤቨንትስ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና ከብሔራዊ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት ኤጀንሲ ጋር በትብብር ያዘጋጁት ሆሄ የሥነ ጽሑፍ ሽልማት ፕሮግራም ሲካሄድ ይህ የመጀመርያው ሲሆን፣ ከዚህ በኋላ በየዓመቱ እንደሚካሄድ አስተባባሪው አቶ ኤፍሬም ብርሃኑ ተናግረዋል፡፡

አቶ ኤፍሬም  ‹‹የንባብ ባህላችን ኋላ ቀር ነው ይባላል፡፡ ከ300 እስከ 5,000 የሚሆን የመጽሐፍ ዕትም ተሸጦ ለማለቅ እስከ ሁለት ዓመት ሊፈጅ ይችላል፤›› በማለት ደራሲው የልፋቱን ለማግኘት ብዙ እንደሚቸገር ተናግረዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በርካታ አዳዲስ ደራስያን እየወጡ ነው፡፡ ብዙ መጻሕፍትም እየታተሙ ነው፡፡ ይህንን ማስተናገድ የሚችል የተጠናከረ የኅትመት ኢንዱስትሪ እንዲኖር ማድረግና የንባብ ባህል እንዲዳብር ጥረት ማድረግ እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡

በመድረኩ ሀሁ የዳንስ ቡድን በንባብ ዙሪያ የሚያጠነጥን ዳንስ አሳይቷል፡፡ ባህላዊና ዘመናዊ ዳንስ የተካተተበት ትዕይንቱ ወጣትና አንጋፋ አርቲስቶችን ያሳተፈ ነው፡፡ ዳንሱ ወጥነት ያለው መልዕክት ከማስተላለፉ ባሻገር አዝናኝም ነበር፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አወዛጋቢው የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ጉዳይ

በኢትዮጵያ የሕገ መንግሥት ማሻሻል ጉዳይ ከፍተኛ የፖለቲካ ውዝግብ የሚቀሰቀስበት...

 መፍትሔ  ያላዘለው  የጎዳና  መደብሮችን  ማፍረስ

በአበበ ፍቅር ያለፉት ስድስት ዓመታት በርካቶች በግጭቶችና በመፈናቀሎች በከፍተኛ ሁኔታ...

የተናደው ከቀደምቱ አንዱ የነበረው የአዲስ አበባ ታሪካዊ ሕንፃ

ዳግማዊ አፄ ምኒልክ በ19ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ መናገሻ ከተማቸውን...

የአከርካሪ አጥንት ሕክምናን ከፍ ያደረገው ‘ካይሮፕራክቲክ’

በአፍሪካ ከጀርባ ሕመም ጋር በተያያዘ በርካታ ሰዎች ለከፍተኛ የአካል...