ሰሜን ኮሪያ ወደ ጃፓን የተቃረበ የመጨረሻውን የሚሳይል መኩራ ካደረገች ስምንት ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ የመጀመርያውን እ.ኤ.አ. በ1998 በኋላም በ2009 ጃፓንን አቋርጠው የተተኮሱት ሮኬቶች የሳተላይት እንጂ የጦር መሣሪያ እንዳልነበሩም በወቅቱ አስታውቃለች፡፡
በወቅቱ የተወነጨፉት ሮኬቶች ፀብ የለሽ በዳቦ በሆነው የኮሪያ ልሳን ምድር እንዳሁኑ የጎላ ትኩረት ባይሰጠውም፣ የሰሜን ኮሪያ አካሄድ ላይ ነጥብ የጣለ ነበር፡፡
ሰሜን ኮሪያ ለሳተላይት ጥቅም የሚውሉ ያለቻቸውን ሮኬቶች የጃፓንን አየር አልፋ ካስወነጨፈችበት ጊዜ በተለየ መንገድ ደግሞ፣ ሰኞ ለማክሰኞ አጥቢያ ለጃፓን የቀረበውንና 15 ደቂቃ ያህል በአየር ላይ የተምዘገዘገውን ሚሳይል አስወንጭፋለች፡፡
ኑክሌር የመሸከም አቅም አለው የተባለው ሚሳይል ከሰሜን ኮሪያ ጃፓን መዳረሻ 2,700 ኪሎ ሜትር እንደተጓዘ ቢቢሲ ዘግቧል፡፡ ከዚህ ቀደም ሰሜን ኮሪያ ካደረገችው የሚሳይል ሙከራ ዝቅተኛ እንደሆነ የተነገረለት ሲሆን፣ አየር ላይ ሦስት ቦታ ተሰባብሮ ሰሜን ፓስፊክ ውቅያኖስ ውስጥ ወድቋል፡፡
ጃፓን ሚሳይሉ ወድቆበታል ለተባለው ሰሜን ፓስፊክ ውቅያኖስ የቀረቡ የሆካኢዶ ነዋሪዎች በሕንፃዎች የምድር ክፍሎች ውስጥ እንዲጠለሉ ማስጠንቀቂያ ከመስጠት ባለፈም፣ ሚሳይሉን መትታ ለመጣል ምንም ሙከራ አላደረገችም ተብሏል፡፡
ጃፓንና አሜሪካ ሰሞኑን በሆካኢዶ በጋራ ያደረጉትን ወታደራዊ ልምምድ ጨርሰው፣ የአሜሪካና የደቡብ ኮሪያ ዓመታዊ የጋራ ወታደራዊ ልምምድ ባለፈው ሳምንት መቀጠሉን ተከትሎ ‹‹በሰሜን ኮሪያ ላይ ወታደራዊ ጥቃት ለመፈጸም ያቀደ ልምምድ›› በማለት ሥልጠናውን የተቃወመችው ሰሜን ኮሪያ፣ ዕርምጃ ልትወስድ እንደምትችልም አስታውቃ ነበር፡፡ በየዓመቱ የሚደረግ የጋራ ወታደራዊ ልምምድ ትንኮሳና ሰሜን ኮሪያን ለመውጋት ያለመ ነው ትላለች፡፡ ባለፈው ሳምንትም ‹‹አሜሪካና ደቡብ ኮሪያ ጠብ እየጫሩ ነው፤›› ስትል ቁጣዋን ገልጻ የነበረ ሲሆን፣ አሁን ደግሞ ቁጣዋን እ.ኤ.አ. በ2017 ካደረገቻቸው የሚሳይል ሙከራዎች በተለየ ለጃፓን ቀረብ አድርጋ አስወንጭፋለች፡፡
የጃፓን ጠቅላይ ሚኒስትር ሺንዞ አቤ ከአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር የተነጋገሩ ሲሆን፣ በሰሜን ኮሪያ ላይ ተጨማሪ ጫና ለመፍጠር መስማማታቸውን ገልጸዋል፡፡ ፔንታጎን የሚሳይል ሙከራው ለአሜሪካ ሥጋት እንዳልሆነ አስታውቆ፣ የመከላከያ ኃይሉ በሰሜን ኮሪያ የሚሳይል ሙከራ ላይ የደኅንነት ክትትል እያደረገ መሆኑን ገልጿል፡፡
ቻይና በበኩሏ አሜሪካና ደቡብ ኮሪያ በተደጋጋሚ የሚያደርጉትን ወታደራዊ ልምምድ ሰሜን ኮሪያ ከምታደርገው የሚሳይል ሙከራ ጋር አብራ ትኮንናለች፡፡
የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሁአ ቹኒንግ አሜሪካና ደቡብ ኮሪያን ወቅሰው፣ በኮሪያ ልሳነ ምድር ያለው ውጥረት ከጫፍ መድረሱን ተናግረዋል፡፡ በሰሜን ኮሪያ ላይ የሚደረግ ጫናም ሆነ ማዕቀብ በኮሪያ ልሳነ ምድር የሚታየውን ውጥረት እንደማያረግበው፣ ሰሜን ኮሪያንም ከድርጊቷ እንደማያቅባት አስታውቀዋል፡፡
የሩሲያ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ራያብኮቭ በበኩላቸው፣ በኮሪያ ልሳነ ምድር ያለው ውጥረት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ መሆኑ እንዳሳሰባቸው፣ የአሜሪካና የደቡብ ኮሪያ ወታደራዊ ልምምድ ፒዮንግያንግን ለማነሳሳት ሚና እንዳለው ተናግረዋል፡፡
ሰሜን ኮሪያ በጃፓን አቅራቢያ ያስወነጨፈችው ሚሳይል ለጃፓን ሕዝብ ትልቅ ሥጋት መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይናገራሉ፡፡ የሰሜን ኮሪያን ድርጊትም ‹‹የቀጣናውን ሰላምና ደኅንነት ያደፈረሰ፤›› ሲሉ ይኮንኑታል፡፡
ሰሜን ኮሪያ በተለይ እ.ኤ.አ. 2017 ከገባ ወዲህ ከዚህ ቀደም ከነበረው በተለየ ቁጡ ሆናለች፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቀድሞ ከጣለው ማዕቀብ በተጨማሪ ሰሞኑን አዲስ ማዕቀብ ጥሎባታል፡፡ ሰሜን ኮሪያ ከውጭ ኃይሎች የሚደርስባትን ጫና የምትመልሰው በድርድር ሳይሆን ወታደራዊ አቅሟን በማሳየት ነው፡፡ ቻይናና ሩሲያም ሰሜን ኮሪያን ወደ ድርድር ለማምጣት ማዕቀብም ሆነ ጫና መፍጠር ዋጋ የለውም ብለው ያምናሉ፡፡ አሜሪካ፣ ጃፓንና ደቡብ ኮሪያ ደግሞ ተጨማሪ ማዕቀብ መጣል ሰሜን ኮሪያን ያስተነፍሳል ይላሉ፡፡
ሁለተኛው የዓለም ጦርነት እንዳከተመ አሜሪካና የቀድሞዋ ሶቪየት ኅብረት ኮሪያን ለሁለት ከከፈሉ በኋላ፣ እ.ኤ.አ. በ1948 መልሶ ለማዋሀድ የተደረገ ጥረት አልተሳካም፡፡ በሁለቱ ኮሪያዎች መካከል እ.ኤ.አ. ከ1950 እስከ 1953 የተደረገው ጦርነት ደግሞ ሁለቱን ኮሪያ መልሶ ለማወሀድ የነበረውን ተስፋ አጨልሟል፡፡
ደቡብ ኮሪያ ነገሮችን በለዘብተኝነት ስታይ ሰሜን ኮሪያ ግን በአንድ ፓርቲ መንግሥት በመመራት ኃያልነቷ እንዳይደፈር ሁሌም ወታደራዊ ብቃቷን የምታዳብር ናት፡፡ አሁን አገሪቱን የሚመሩት ፕሬዚዳንት ኪም ጆንግ ኡንም ሆኑ አባታቸውና አያታቸው ለአሜሪካም ሆነ ለሌሎች አገሮች ያላቸው ምልከታ አዎንታዊ አልነበረም፡፡ አሜሪካም ከሰሜን ኮሪያ ጋር ስትወዛገብ የዘንድሮው የተለየ አይደለም፡፡
በሰሜን ኮሪያና በኮሪያ ልሳነ ምድር እንዲሁም በአሜሪካ መካከል ያሉ አለመግባባቶችን ለመፍታት እ.ኤ.አ. ከ2009 በፊት ተደጋጋሚ ውይይቶች ቢደረጉም ውጤት አልባ ነበሩ፡፡ ከዚህ በኋላ የተደረጉትም እንዲሁ፡፡
ሰሜን ኮሪያ የኑክሌር ባለቤት ከሆነች በኋላ ከማስፈራራት የዘለለ ዕርምጃ ወስዳ ባታውቅም፣ አሜሪካና የአሜሪካ ወዳጆች የሚፈጥሩባት ጫና ዓለምን ከማትወጣበት ጦርነት ሊዘፍቅ ይችላል የሚል ሥጋት ፈጥሯል፡፡ ፕሬዚዳንት ኪምም፣ አሜሪካ ሰሜን ኮሪያን ማስፈራት ካልተወች ወታደራዊ ዕርምጃ ከመውሰድ እንደማይመለሱ ዝተዋል፡፡
በተያዘው ወር መጀመርያም በልሳነ ምድሩ ከሚገኘው የአሜሪካው ወታደራዊ ጦር ሠፈር ‹‹ጉአም›› የተነሱ የጦር ጄቶች ቅኝት አድርገዋል በሚል፣ ጦር ሠፈሩን እንደምትመታ አሳውቃ ለጊዜው ዕቅዷን እንደማትተገብር ገልጻለች፡፡ በቃላት አወራወራቸው የሚተቹት ትራምፕም፣ ሰሜን ኮሪያ ዓለም የማያውቀው እሳት ይወርድባታል ብለው ነበር፡፡
ሰሜን ኮሪያ የቱንም ያህል የውጭ ጫና ቢበረታባት እስካሁን አልተገበረችም፡፡ ሕዝቧ በኢኮኖሚ ተጎድቷል፣ ነፃነት አጥቷል ቢባልም ከኪም አያት ጀምሮ ሲወራረስ የመጣውን የአንድ ፓርቲ ጽንሰ ሐሳብ እንደ አምላክ ቃል እንደተቀበለ ይነገራል፡፡ መሪውንም ‹‹ፍፁም›› በማለት ተቀብሏል፡፡ ይኼ ለሰሜን ኮሪያ የጀርባ አጥንት ሆኗታል፡፡ ከውጭ መንግሥታት ውግዘት ቢገጥማትም አገሬው የውጭ ሚድያዎች እንደሚሉት መብቱ ታፍኖ ይሁን ፈልጎ ገዢዎቹን መንካት አይፈልግም፡፡ ትንሽ የሚንፈራገጥ ካለም የሞት ቅጣት እንደሚጠብቀው ይነገራል፡፡
ሕዝቧን ትበድላለች በምትባለው ሰሜን ኮሪያ ወታደራዊ ትጥቅ ቅድሚያ አለው፡፡ ከዚህ ቀደምም አምስት ጊዜ የኑክሌር ሙከራ ያደረገች ሲሆን፣ በቅርቡ ስድስተኛውን ትሞክራለችም ተብሏል፡፡ ከዚህ ባለፈም የኑክሌር አረር ሊሸከሙ የሚችሉ ረዥም ርቀት ተምዘግዛጊ ሚሳይሎች ሙከራም አድርጋለች፡፡ በጃፓን አቅራቢያ ያስወነጨፈችው ሚሳየል የኑክሌር አረር የመሸከም አቅም ያለው ሲሆን፣ ይኼም በተለይ ጃፓንን አስቆጥቷል፡፡ ደቡብ ኮሪያ ደግሞ ለአፀፋው በመሣሪያ የታጀበ ወታደራዊ ልምምድ አድርጋለች፡፡