Sunday, June 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበሙስና ወንጀል በተጠረጠሩ ባለሥልጣናት ላይ ለሦስተኛ ጊዜ የተጠየቀው ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ተፈቀደ

በሙስና ወንጀል በተጠረጠሩ ባለሥልጣናት ላይ ለሦስተኛ ጊዜ የተጠየቀው ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ተፈቀደ

ቀን:

የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቡድን በከፍተኛ የሙስና ወንጀል ተጠርጥረው በታሰሩትና በምርመራ ላይ በሚገኙት ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት የጠየቀው ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ፣ ለሦስተኛ ጊዜ የፍርድ ቤቱን ይሁንታ አገኘ፡፡

ከኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣንና ከገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር ተጠርጥረው በምርመራ ላይ በሚገኙ 26 ባለሥልጣናት ላይ ተጨማሪ 14 ቀናት የምርመራ ጊዜ እንዲፈቀድለት የጠየቀው መርማሪ ቡድኑ፣ ለሚመለከታቸው የመንግሥት ተቋማት ከተለያዩ አካላት የተጻፉ ሰነዶች ኮፒ ተደርገውና በጥራዝ ተዘጋጅተው በተጠርጣሪዎቹ ቤት ማግኘቱን ለፍርድ ቤት አስረድቷል፡፡

መርማሪ ቡድኑ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ሁለተኛ ወንጀል ችሎት ነሐሴ 15 ቀን 2009 ዓ.ም. እንዳስረዳው፣ ከተጠርጣሪዎቹ ቤት ከተገኙት ጥራዝ ሰነዶች በተጨማሪ ሌሎች የሚሰበስባቸው ማስረጃዎች ስላሉት የተጠቀሰው ተጨማሪ ጊዜ እንዲፈቀድለት ፍርድ ቤቱን ጠይቋል፡፡

ፍርድ ቤቱ ምላሽ ከመስጠቱ በፊት መርማሪ ቡድኑ ቀደም ብሎ በተሰጠው 14 የምርመራ ቀናት ምን እንደሠራ እንዲያስረዳ ጠይቆት፣ በሁለቱም የመንግሥት ተቋማት ተጠርጣሪዎች ላይ የሠራውንና የቀረውን የምርመራ ሒደት አስረድቷል፡፡

በቀድሞ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ዛይድ ወልደ ገብርኤል የምርመራ መዝገብ በተካተቱ አሥር ተጠርጣሪዎች ላይ የሠራውን ምርመራ መርማሪ ቡድኑ አስረድቷል፡፡ ተጠርጣሪዎቹ አቶ ዛይድ ወልደ ገብርኤል፣ አቶ አብዶ መሐመድ፣ አቶ በቀለ ንጉሤ፣ አቶ ገላሶ ቦሬ፣ አቶ ገብረ አናንያ ፃድቅ፣ አቶ የኔነህ አሰፋ፣ አቶ በቀለ ባልቻ፣ አቶ ሳምሶን ወንድሙና አቶ ዘለዓለም አድማሱ ሲሆኑ መርማሪ ቡድኑ በተሰጠው ጊዜ በድምሩ 32 ምስክሮችን ቃል መቀበሉን ተናግሯል፡፡

አሥር ምስክሮች የመንግሥት ግዥና ንብረት ማስወገድ ኤጀንሲ ሠራተኞች መሆናቸውንና ከበጀት ዝግጅትና ከዓለም አቀፍ ግዥ ጋር በተገናኘ ሙያዊ ምስክርነት የሰጡ መሆናቸውን፣ 12 ምስክሮች የተጠርጣሪዎች ቤት ሲፈተሽ በታዛቢነት የተገኙ፣ ዘጠኝ ምስክሮች ደግሞ ተቋሙን በቅርብ የሚያውቁና አንድ ኦዲተር መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

ወንጀሉ የተፈጸመው ከአምስት የመንገድ ፕሮጀክቶች ጋር በተገናኘ መሆኑን፣ ባለሥልጣናቱ ከባለሀብቶቹ ጋር በመመሳጠር የነበራቸውን የጥቅም ግንኙነት የሚያሳይ የሰነድና የቴክኒክን ማስረጃዎችን መሰብሰቡንም ገልጿል፡፡ የክፍያ ሰነዶችን ከሁለት ፕሮጀክቶች ማሰባሰቡን የገለጸው መርማሪ ቡድኑ፣ ከ160 በላይ ደብዳቤዎችን ለተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት መጻፉን አክሏል፡፡ ሰነዶቹ የሚገኙት በክልል ከተሞችና በአዲስ አበባ መሆኑን ገልጾ፣ መርማሪዎቹን በመላክ ማስረጃዎችን እያሰባሰበና ቃላቸውን ያልሰጡ ተጠርጣሪዎችን ቃልም እየተቀበለ መሆኑንም ተናግሯል፡፡

መርማሪ ቡድኑ የ27 ምስክሮች ቃል መቀበል እንደሚቀረው፣ የሙያ ምስክሮች ከአዲስ አበባ ውጪ ስላሉ እነሱንም ማነጋገር፣ ቃላቸውን መቀበልና የክፍያ ሰነዶችን መሰብሰብ፣ ለቴክኒክ ምርመራ የተላኩ ሰነዶችን መሰብሰብና በሕገወጥ መንገድ የተገኙ ንብረቶችን ማሳገድ እንደሚቀረው በማስረዳት የጠየቀው ጊዜ እንዲፈቀድለት ጠይቋል፡፡

በሌላ የምርመራ መዝገብ የቀረቡት ከገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር የፋይናንስ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ዓለማየሁ ጉጆ፣ አቶ ሙሳ መሐመድ፣ አቶ መስፍን ወርቅነህ፣ አቶ ታምራት አማረ፣ አቶ አክሎግ ደምሴ፣ አቶ ጌታቸው ነገራ፣ ዶ/ር ወርቁ ዓለሙ፣ አቶ ነገራ መንግሥቱ፣ አቶ ታጠቅ ደባልቄ፣ አቶ ኤልያስ መርዓዊ፣ ወ/ሮ ስህን ጎበና፣ አቶ ተፈታ ፋንታ፣ አቶ ቲጃን አባ ጎጃም፣ አቶ እዮብ በልሁ፣ አቶ ታገል ሞላ (በነሐሴ 12 ቀን 2009 ዓ.ም. የተያዙ) እና አቶ ዋሲሁን አባተ የቀረቡ ሲሆን፣ መርማሪ ቡድኑ በእነሱም ላይ በተፈቀደለት የ14 ቀናት የምርመራ ጊዜ የሠራውን ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡

ሚኒስቴሩ ካወጣው የጨረታ ዋጋ ውጪ ክፍያ የተፈጸመበትን ሰነድ፣ የተከሳሾችን ቃል፣ በተለያዩ ተቋማት የተበተኑ ሰነዶችን፣ ለትርጉም የተሰጡ ሰነዶችን መሰብሰቡን፣ ከታክስና ከቀረጥ ጋር የተገናኙ ሰነዶችን ለኦዲት መስጠቱን፣ ያልተያዙ ግብረ አበሮችን እየተከታተለ መሆኑንና የተወሰኑ ተጠርጣሪዎችን ንብረት ማሳገዱን አስረድቷል፡፡ የሙያ ምስክሮቹንና ቀጥታ ምስክሮችን መቀበል እንደሚቀረው፣ የኦዲት ግኝቶችን መሰብሰብና ለቴክኒክ ምርመራ የተሰጡ ሰነዶችን መሰብሰብ እንደሚቀረውና ሌሎችንም ቀሪ ሥራዎች በመዘርዘር የጠየቀው ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ እንዲፈቀድለት ጠይቋል፡፡

የተጠርጣሪዎች ጠበቆች የመርማሪ ቡድኑን ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ጥያቄ በመቃወም ለፍርድ ቤቱ አቤቱታ አሰምተዋል፡፡

የመንግሥት ኃላፊዎች የምርመራ ጊዜው የተጀመረው ከአሥር ወራት በፊት መሆኑን በመገናኛ ብዙኃን መግለጻቸውን አስታውሰው፣ መርማሪ ቡድኑ ግን ተጠርጣሪዎችን አስሮ ማስረጃ የሚፈልግበት ሕጋዊ ምክንያት ስለሌለ በዋስ ሊፈቱ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ ሌላው ቢቀር ቀደም ብሎ በነበሩት ሁለት ቀጠሮዎች የተሰጠው ቀን ከበቂ በላይ መሆኑን ጠቁመው፣ ይኼ የሚያሳየው ፖሊስ ሥራውን በአግባቡ እየሠራ አለመሆኑን በመሆኑ ተጨማሪ ጊዜ ሊፈቀድለት እንደማይገባ ተናግረዋል፡፡ በተለይ ከገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር ተጠርጥረው ከታሰሩት ውስጥ ስምንቱ ተጠርጣሪዎች ለምን እንደተከሰሱና ለጥርጣሬ ያበቃቸው ነገር እንዳልተነገራቸውም አመልክተዋል፡፡ ከኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን አቶ ሳምሶን ወንድሙ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ከመሆናቸው ውጪ ከግዥም ሆነ ከኮንትራት ጋር የሚያገናኛቸው ነገር እንደሌለ ጠበቃቸው ተናግረው፣ በምን እንደተጠረጠሩ መርማሪ ቡድኑ ለይቶ እንዲናገር ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው ጠይቀዋል፡፡

ፍርድ ቤቱም መርማሪ ቡድኑ እንዲያስረዳ ትዕዛዝ ሰጥቶ መርማሪ ቡድኑ ምላሽ ሰጥቷል፡፡ እንደ መርማሪ ቡድኑ ገለጻ አቶ ሳምሶን የተጠረጠሩት የግል ተሽከርካሪዎቻቸውን ከኮንትራክተሮች ጋር ባላቸው ልዩ ግንኙነት በማከራየት፣ ለኮትራክተር ሙሉ የኮንስትራክሽን ዕቃ ሳይኖረው ያለው በማስመሰላቸውና እሳቸውም በሕዝብና በመንግሥት ገንዘብ ላይ ጉዳት በማድረሳቸው መሆኑን አስረድቷል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ ምርመራ የተጀመረው ከአሥር ወራት በፊት ነው ቢሉም፣ መርማሪ ቡድኑ ግን ሥራ የጀመረው ተጠርጣሪዎቹ ከተያዙ በኋላ መሆኑን ገልጿል፡፡ ከአሥር ወራት በፊት የተጀመረው ድርጊቱ መፈጸሙንም ወይም አለመፈጸሙን የሚያሳይ ጥናት መሆኑን ጠቁሟል፡፡

መርማሪ ቡድኑ በሌሎችም ተጠርጣሪዎች ላይ ያቀረበውን ዝርዝር ቀሪ ሥራ በማስታወስ ዋስትና እንደሚቃወም ገልጾ፣ የጠየቀው ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ እንዲፈቀድለት ጠይቋል፡፡

ሌላው ጠበቆቹ ያነሱት ተቃውሞ በፌዴራል ወንጀል ምርመራ ማዕከል (ማዕከላዊ) ደንበኞቻቸውን ሊያነጋግሩ ቢሄዱም፣ በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥትና ሕጎች መሠረት እንዲሁም ተቀብላ ባፀደቀቻቸው ዓለም አቀፍ ሕጎች መሠረት ደንበኞቻቸውን በነፃነትና በሚስጥር ማነጋገር ሲገባቸው፣ በአንድ ሜትር ርቀት ፖሊስ ስለሚቆም ማነጋገር እንዳልቻሉ አመልክተዋል፡፡

ጠበቆች የፍትሕ ሥርዓቱን ከማገዝ አኳያ ወንጀል ተደብቆ ወይም ተድበስቦ እንዲቀር ፍላጎትም ሆነ ሌላ ዓላማ እንደሌላቸው ተናግረው፣ ደንበኞቻቸው ግን ሳይሸማቀቁ እውነቱን እንዲያስረዷቸው ለብቻቸው ሊያነጋግሯቸው እንደሚገባም አክለዋል፡፡

የግራ ቀኙን ክርክር የሰማው ፍርድ ቤቱ ተጠርጣሪዎች ያለምንም የጥርጣሬ ምክንያት የታሰሩ ሳይሆኑ፣ መርማሪ ቡድኑ ለጥርጣሬ መነሻ ናቸው ያላቸውን ነገሮች አስረድቶና ፍርድ ቤቱም አምኖበት የምርመራ ጊዜ መፈቀዱን አስታውሷል፡፡ በተፈቀደለት ጊዜም የሠራቸውን ፍርድ ቤቱ መመልከቱንና የተከናወኑ ሥራዎች መኖራቸውን ማረጋገጡን ገልጿል፡፡ መርማሪ ቡድኑ ይቀሩኛል በማለት ያቀረባቸውን ዝርዝር የሥራ ዓይነቶችንም ፍርድ ቤቱ ግምት ውስጥ በማስገባት፣ ከተጠየቀው 14 ቀናት ውስጥ 12 ቀናት መፍቀዱንና የዋስትና ጥያቄውን እንዳልተቀበለው አስታውቋል፡፡

ቀጣይ ቀጠሮ የበዓል ቀን ላይ ስለሚውል ወደፊት በመውሰድ ለነሐሴ 29 ቀን 2009 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አወዛጋቢው የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ጉዳይ

በኢትዮጵያ የሕገ መንግሥት ማሻሻል ጉዳይ ከፍተኛ የፖለቲካ ውዝግብ የሚቀሰቀስበት...

 መፍትሔ  ያላዘለው  የጎዳና  መደብሮችን  ማፍረስ

በአበበ ፍቅር ያለፉት ስድስት ዓመታት በርካቶች በግጭቶችና በመፈናቀሎች በከፍተኛ ሁኔታ...

የተናደው ከቀደምቱ አንዱ የነበረው የአዲስ አበባ ታሪካዊ ሕንፃ

ዳግማዊ አፄ ምኒልክ በ19ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ መናገሻ ከተማቸውን...

የአከርካሪ አጥንት ሕክምናን ከፍ ያደረገው ‘ካይሮፕራክቲክ’

በአፍሪካ ከጀርባ ሕመም ጋር በተያያዘ በርካታ ሰዎች ለከፍተኛ የአካል...