Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ተሟገትሙስናን ተጠየፍነው ወይስ እንደ እንሶስላ ሞቅነው?

ሙስናን ተጠየፍነው ወይስ እንደ እንሶስላ ሞቅነው?

ቀን:

በገነት ዓለሙ

መንግሥት ገዢው ፓርቲ ውስጥ የደረሰበትን ‹‹ቦናፖርታዊ መበስበስ›› እና የመሰንጠቅ አደጋ ከተቆጣጠረ በኋላ በ1993 ዓ.ም. ያወጣው የፌዴራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ሕግ፣ ‹‹ሙስናንና ብልሹ አሠራርን ለመሸከም የማይፈልግና ይህንኑ በብቃት ለመዋጋት ዝግጁ የሆነ ኅብረተሰብ መፍጠር አስፈላጊ›› ነው ብሎ ተነሳ፡፡ የተቋቋመው የሕግና የፍትሕ ሥርዓት ከሚያውቃቸው አስፈጻሚ አካላት በተጫማሪ ሙስናንና ብልሹ አሠራርን ለመመርመርና ለመክሰስ፣ ለመቆጣጠርና ለመከላከል፣ መልካም ሥነ ምግባር በኅብረተሰቡ ውስጥ እንዲስፋፋ በማድረግ ሙስናንና ብልሹ አሠራርን መዋጋት የሚችል ነፃና ራሱን የቻለ መንግሥታዊ አካል አቋቋመ፡፡ ስሙንም የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ብሎ ጠራው፡፡

ሙስናንና ብልሹ አሠራርን ለመሸከም የማይፈልግና ይህንኑ በብቃት ለመዋጋት ዝግጁ የሆነ ኅብረተሰብ የመፍጠር ሥራንም ሙስናን የመመርመር፣ የመክሰስ፣ ወዘተ ሥልጣንንም በፊታውራሪነት የሚመራው ፀረ ሙስና ኮሚሽን ሆኖ በ1997 ዓ.ም. በ2007 ዓ.ም. በተሻሻሉት ሕጎች ጭምር ተጠናክሮ (በሕግ) ቀጠለ፡፡

በ2007 ዓ.ም. አጠቃላይ ምርጫ ውጤት መሠረት በ2008 ዓ.ም. መስከረም መጨረሻ ላይ ሥልጣን የያዘው አምተኛው ፓርላማ የኢፌዴሪ አስፈጻሚውን ዘርፍ አደረጃጀትና ሥልጣንና ተግባር እንደገና ‹‹ልውጥውጡን›› ሲያወጣና ሲወስን እንኳን፣ በፍትሕ ሚኒስቴርና በፌዴራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን መካከል ያለውን ልዩነት በጭራሽ አልነካም ነበር፡፡ እንዲያውም አዲሱ አደረጃጀት የተወሰነበትን ረቂቅ አዋጅ በዝርዝር የሚያብራራውና ከረቂቅ ሕጉ ጋር ለፓርላማው ያቀረበው የጥናት ሰነድ ‹‹የመንግሥት አስፈጻሚ አካላትን አደረጃጀት ሥልጣንና ኃላፊነት አገራችን ከደረሰችበት የዕድገት ደረጃ፣ ከአኅጉራዊና ዓለም አቀፍ ነባራዊ ለውጦች ጋር አጣጥሞ ቀጣይነት ባለው መልኩ ማሻሻል በትኩረት ሊከናወኑ ከሚገባቸው ተግባራት አንዱ ነው›› ሲል የአደረጃጀት ለውጥ ያልተደረገባቸውን የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች በስም ጠቅሶ ነበር፡፡ ከእነዚህ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች መካከል የውጭ ጉዳይ፣ የአገር መከላከያና የፍትሕ ሚኒስቴር ይገኙበታል፡፡

በተለይም ስለፍትሕ ሚኒስቴር በዚህ ኦፊሴላዊ የመንግሥት የጥናት ሰነድ የቀረበው ማብራሪያ፣ ‹‹የፍትሕ ሚኒስቴር በአገራችን ቀደምት ተሞክሮዎችም ሆነ በሌሎች አገሮች ከታየው ልምድ ተነስቶ ስያሜውንም ሆነ አደረጃጀቱን መለወጥ ሳያስፈልግ እንዳለ እንደሚቀጥል ግንዛቤ ተወስዷል፤›› በማለት የመንግሥትን አቋም አረጋግጦ፣ የፍትሕ ሚኒስቴርን ጨምሮ አሥራ አምስት የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶችን ለአዲስ የፓርላማ ዘመን ያዋቀረውና ያደራጀው አዋጅ የፀናው ከኅዳር 2008 ዓ.ም አንስቶ ነው፡፡ ፍትሕ ሚኒስቴር ከሚኒስትሮች ምክር ቤት አባላት ስም ዝርዝር ተርታ የወጣው፣ ያ ከ1993 ዓ.ም. ጀምሮ የተቋቋመው ‹‹ነፃና ራሱን የቻለ መንግሥታዊ አካል›› የሙስና የወንጀል ክስና የምርመራ ሥልጣን አዲስ ለተቋቋመው ለጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የተሰጠው፣ የፌዴራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽንም ከቀፎው የወጣ ኤሊ የሆነው የአስፈጻሚው አካል ማደራጃ ሕግም በዚያው ዓመት እንደገና የተሻሻለው በሚያዝያ 2008 ዓ.ም. ነው፡፡

ሙስናን መዋጋት፣ ሙስናን የሚጠየፍ ኅብረተሰብ ለ‹‹መፍጠር››ም ከዚህ የበለጠ አርቆ ማቀድ አርቆ ማሰብ ያስፈልጋል፡፡

አገራችን ደሃ ናት ጠላቷም ድህነት ነው፡፡ ይህች ደሃ አገር ግን የወገኝነት፣ የብክነትና የግብዝነት ሀብታም ናት፡፡ በአቅም መኖር የማይሆንለት፣ ሥራ አስፈቺነትና ጥሪት አጫራሽ ወገኝነት የሚያጠቃው ኅብረተሰብ አገር ናት፡፡ በብድርና በዕርዳታ በተመሠረተ በጀት ላይ የሚያዘው መንግሥትም ባካናና ለዝርፍያ የተጋለጠ የገንዘብ አጠፋፍና አደፋፍ ክፉ ባህርይና ታሪክ የተጠናወተው ነው፡፡ ብቸኛና ትልቁ ባለሀብት፣ ገንዘብ ሰብሳቢ፣ ግዢ ፈጻሚና ሠራተኛ ቀጣሪ እሱ ነው፡፡ እንደምን አድርጎ ሥነ ምግባር አስተምራለሁ እንዳለ፣ ከዚያም አልፎ ሙስና የሚጠየፍ ኅብረተሰብ ‹‹ልፍጠር›› ብሎ እንደተነሳ የሚገርም ነው፡፡

ዱሮ በደርግ ዘመን ገና መንግሥቱ ኃይለ ማሪያም በ1970ዎቹ መጀመሪያ አፄ ሆኖ ከመውጣቱ፣ ቁጥጥር ኮሚቴ ምንትስ ቢባልም ልሽቀትና ዘረፋ እንደ ወረርሽኝ መባዛት ችሎ ነበር፡፡ ከኢሠፓ ምሥረታና ከ77 ድርቅ ወደዚያ ደግሞ፣ ጠቅላላ ኑሮ በቢሮክራሲያዊ መሰናክሎችና በሥውር ሥራዎች ተጥለቅልቆ ነበር፡፡ የትብትቡ አፈናና የሙስና ሙላቱ የሚቀንስበት ምንም ቀዳዳ አልነበረም፡፡ የነበረው ዕድል በውስጡ መዋኘትና ለአጠቃላዩ ጌታ ንቅዘት መታዘዝ፣ እየነቀዙ ማንቀዝ ነበር፡፡ በኢሕአዴግ ዘመን ይህ አጠቃላይ የንቅዝት ሙላት በስንት ትግል ለመቀነስ ችሎ ነበር፡፡ ዓይን ያወጣው ሙስናም ትንሽ ቆስሎ ነበር፡፡ ከ1999 ዓ.ም. የዋጋዎች መተኮስና የኑሮ መክበድ ወዲህ ግን ቁስሉ ሽሮለት፣ ለፀረ ሙስና ኮሚሽን ጥቆማ በመስጠትና የሥነ ምግባር መኮንን በማቆም፣ በስለላ፣ በሹምሽርና በክስ የማይዝል አጠቃላይ ጉልበተኛ ሆኖ ለመውጣት ኃይልና ብልኃት አሰባስቦ አርፎታል፡፡ ኑሮና ብልኃቱን የማሳካት ዕይታም የተቃኘው ከዚህ ማዕዘን ነው፡፡

የኑሮ ክብደት አመጣሽ ጉልበቱ በተለይ በቤት በኩል ተሟልቶ ትልቅ አዋጅ አውጇል፡፡ የቤት ኪራይም ሆነ የኮንዶሚኒየም ቤት ዋጋ በገቢህ የማይቻል ነውና አዲስ መጥ ወጣት ሁሉ እንዳትጃጃል፣ በየትም በየት ዘረፋና ጉቦን አጡፍ የሚል አዋጅ ያለጥሩምባ ማስለፈፍ ችሏል፡፡ የኢሕአዴግ መንግሥት በየመሥሪያ ቤቱ በሰውና በአሠራር ለውጥ፣ በሥልጠና ሙስናን ለመቀረጣጠፍ ደፋ ቀና ሲል ንቅዘት ጠቅላይ ቢሮውን የኑሮ ጓዳ ውስጥ አቋቁሞና የቤት ውድነትን ዋና የልሽቀት አቡን አድርጎ ሾሟል፡፡ አቡኑ መዝረፍና ጉቦ የመልካም ሕይወት ትክክለኛ መንገድ፣ የማያሳፍር የልባም ሙያ መሆኑን እየሰበከ አዲሱን ትውልድ ማጥመቅ እየተቃናለት ነው፡፡ የአቡኑን ትምህርት ሰምተው ኪስ ውስጥ መግባት የቀራቸው ሙሰኞች በመሆን መሪነቱን የያዙት ደግሞ የፓርቲው ምልምል ወጣቶች ናቸው፡፡ የተዘነጋ የመሰለ ገላጣ መሬት እያደኑ ወይ በቀላል ዋጋ ወደ ገጠር ዳር መሬት እየገዙ ጎጆ ከመቀለስ አንስቶ፣ ቶሎ ቶሎ እየጠፋ የሚያስቸግር መብራትን በሥውር የኃይል ሥርቆት ለመብለጥ መሞከር፣ ከነዳጅ ዋጋ ጋር ከፍ ዝቅ የሚል የአውቶብስ አገልግሎት ዋጋን ተተምኖ ሳንቲም መሸራረፍ ሁሉ የችግር መገለጫዎች ናቸው፡፡

  ሰዎችን በችሎታቸው፣ በትጋታቸውና በጨዋነታቸው መዝኖ የመመልመልና የማሠራት ባህሪይ ያለው፣ ሥልጣን ላይ የወጣውን ፓርቲ ፖሊሲ ማስፈጸምና ለሥልጣንና ለባለሥልጣን እውነቱንና እውነቱን ብቻ መናገር፣ በሙያው ማገልገል ሱሪ በአንገት ማውጣት ያልሆነበት የሲቪል ሰርቪስ ሥርዓት አቅጣጫ ስለጠፋብን፣ የኢትዮጵያ የኑሮ ብልኃት ‹‹ልማታዊ›› አልሆነም፡፡ ትምህርቴን ጨርሼ፣ አሻሽዬ፣ ጥሩ ሥራ ይዤ፣ ይህን የሥራ ዕቅድ ነድፌ፣ ይህንን ጥበብ ወደ ሥራ ቀይሬ ብሎ ከሚወጥነው ይልቅ፣ መንግሥት ቤት እግሬን አስገባና ‹እየፎገርኩ› ዕድገት አግንቼ እሾምና ወፍራም ጉቦ እየዘረፍኩ ብሎ የሚተልመው የበላይነቱን ይዟል የተሳከለትም እሱ ነው፡፡

 ጎሰኛነትንና የመብት ድሎችን መደበቂያ ዋሻ እያደረገና ጨለምላማ ሥፍራዎችን እያነፈነፈነ ንቅዘት ይጠቀምባቸዋል፡፡

በልማት ተዛነፍ ምክንያት የተዘነጋ ብሔረሰብን/የአካባቢ ሕዝብን የኑሮ ሥልት ወደ ሁለገብነት (ወደ ከተማዊ ሕይወት፣ ንግድ፣ ትምህርት፣ መንግሥታዊ ሥራና ፖለቲካዊ ሱታፌ፣ ወዘተ) ለማምጣት ልዩ እገዛዎችና ጉድለት ማስተካካያዎች (አድልኦዎች) ማድረግ አግባብ ይሆናል፡፡ የተወሰኑ ዕድሎችና መብቶች ለተወሰነ ማኅበረሰብ የተመደቡ እስኪመስል ወይም አድልኦ ወይም ቅድሚያ ሕጋዊ መብት እስኪመስል ድረስ ተገትሮ ሲቆይ፣ መብትን፣ ባህልንና ታሪክን አውቆ ከመንከባከብ ንቃትነት አልፎ ብሔርተኛነት እንደ ሃይማኖት ሲሆን (ሁሉን ነገር ከብሔረሰብ ጥግ በማየት ልክ አዕምሮ ሲቀነበብ) ሙስና (ጎሰኝነት) ይደላዋል፡፡ የብሔር መብትንና ቅድሚያን ሽፋን አድርጎ ይነግድበታል፡፡ ‹‹ዴሞክራሲያዊ ብሔረተኝነት›› ከጎሰኝት ጋር አንድ እስኪመስል ድረስ መኖሪያው ያደርገዋል፡፡ በሮችና መንገዶች አንዴ ከተከፋፈቱ ወዲያ የተወዳዳሪነትን አቅም ከሚያሳድግ እገዛ በቀር፣ በመብት ጥበቃ ስም የሚካሄዱ ገደቦችና የመሥፈርት ልዩነቶች ሁሉ መወገድ ይኖርባቸዋል፡፡ ይህ የዛሬዋ ኢትዮጵያ አንዱ ችግር ነው፡፡ 

የኢሕአዴግ መንግሥት ሕዝበኛ ፕሮፓጋንዳና የልማት ትልም ሥልጣንን ለማንም ሳያስነኩ በመቆጣጠር ንድፍ ላይ የተዋቀረ ነው፡፡ መጀመሪያ ትኩረቱ አርሶ አደሩን በመያዝ ላይ ነበር፡፡ በስተኋላ ግን አዲስ የገጠርና የከተማ ሀብታም ከመፍጠር ጋር የተያያዘ ማኅበራዊ መሠረት የመቆናጠጥ ቅያስ ወጥቷል፡፡ በአንድ ወቅት ተዘጋጅቶ ለሥልጠና በዋለ የኢሕአዴግ ሰነድ ላይ እንደተቀመጠው፣ ‹‹በከተማ ከሀብታም አርሶ አደሩ የሚመሳሰል ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ኃይል እንደምንም ተረባርቦ መፍጠርና ፈጥኖ የአመራር ቦታውን እንዲይዝ ማድረግ ከሁሉም ነገር በላይ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው›› (የኢሕአዴግ አገራዊ ለውጦች ቀጣይ ፈተናዎችና አብዮታዊ መፍትሔዎች፣ 2000 ዓ.ም. የተባዛ ጥራዝ፣)፡፡ በከተሞች የተጀመረው የጥቃቅንና የአነስተኛ ሥራዎች ልማት፣ ‹‹ለአብዮታዊ ዴሞክራሲ›› ከማጎንበስ ጋር የጥቅሞች ተስፋን ያዛመደው የአባላት በገፍ ምልመላና የደጋፊ መድረክ መራባትም በዚሁ ቅያስ መሠረት የተካሄደ ነው፡፡ ይህ እንግዲህ መንግሥታዊ አብራክ ያለው (ልማትንና ሌሎች ጥቅማ ጥቅሞችን እንደ ጉርሻ መሣሪያ ያደረገ) ፖለቲካዊ ሙስና ነው፡፡ የተሻለ አቅም ያላቸው ግለሰቦችም በጥቃቅንና በአነስተኛ ሥራዎች ውስጥ የምትገኘዋን የዕፎይታ፣ የቅናሽ ግብርና የገበያ ትስስር ዕድል ለማግኘት መሰስ ለማለት ችለዋል፡፡ በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ዘንድም ኢሕአዴግ አባላቱን አራብቷል፡፡ ያራባቸው ግን ሙስናንና ልሽቀትን በማድከምና በሀቀኝነትና በሥራ ቅልጥፍና ረቡት? አባል ካልሆኑት በለጡ? ወይስ ብልጫቸው በማጨብጨብና ጥቅም በመላፍ? መልሱን ማንም የሚያቀው ነው፡፡ በውጭ የሚኖሩ የኢትዮጵያ ተወላጆችን ድጋፍ ለማግኘትም ሆነ ከተቃውሞ ለመሸበብ፣ የቤት መሥሪያ መሬት የማግኘት ወይም የጋራ ቤት የመሥራት ዕድል ተሠርቶበታል፡፡

የኢሕአዴግና የተቃዋሚዎቹ ከመጠማመድ አለመውጣት ለሙስና ጥቅሙ ነው፡፡ በአንድ በኩል ከሁለት በኩል የታገዘ አሳጭ ሳይገጥመው ተሸፋፍኖ ለመቀጠል፣ ጭራሽ በተለያየ ሥውር ዘዴ ማስመረሪያ አድርጎ ለመበቀልም ይመቸዋል፡፡ በሌላ በኩል፣ ‹‹ፀረ ሕዝብ›› እና ‹‹ነፍጠኛ›› በመታገል ሽፋን እያስመሰሉ ሙስናን ለማጦፍ ያስችላል፡፡ የዚህ ዓይነት ፖለቲካን የተሞላ ማንገላታት በኢንቨስትመንት ላይ ጉዳት ሲያደርስ ታይቷል፡፡ ተቃዋሚን “የጥፋት ኃይል” አድርጎ ከማጥፋፋት ጋር የኢሕአዴግን መስመር በብቸኛ የልማት መንገድነት የማንገሥ ሩጫም ለሙስና ደህና ጨለማ ይፈጥርለታል፡፡ ሙሰኛውም ሙስናን እታገላለሁ ባዩም ልማታዊነትን የሚቆላ አፍ አላቸውና ደህናውን ከጥፉው መለየትና ማጋለጥ ከባድ ይሆናል፡፡ ሌባው ራሱ የሥነ ምግባር መኮንንና ተቆጣጣሪ እስከመሆን ይመሳሰላል፡፡ ፖለቲካው በመጠማመድ ላይ የቆመ እንደመሆኑ የኢሕአዴግ አባል የሆነን ሌባ ከውጭ ሆኖ ማጋለጥ በራስ ላይ ጣጣ እንደማምጣት ‹‹በልማታዊነት ላይ የሚካሄድ የስም ብከላ/የፀረ ልማቶች ደባ›› ወዘተ ተብሎ ራስን ማስነከስ እንዳይሆን ያስፈራል፡፡ አልነቅዝ/አላዘርፍ ያለ የሒሳብ ተቆጣጣሪን ‹‹በለውጥ ማነስ››፣ ‹‹ተባብሮ ባለመሥራት››፣ ወዘተ ስም አጉድፎ በግምገማ ነጥብ አጥቅቶና አስመርሮ እስከማሰደድ ድረስ የሚካሄደው የእንብላው ትብትብና ቡጭሪያ፣ ስም ያለውን የኢትዮጵያ አየር መንገድን ሳይቀር እየታገለ ያለ ችግር ነው፡፡

ባለልዩ ልዩ መልኩ ሌብነት የኑሮ ችግር የመወጣት ወይም ‹‹ሌላው እየፈሰፈሰ እኔስ ለምን ይቅርብኝ?›› የሚል ማመካኛ ብቻ አይደለም ያለው፡፡ ከ1983 ዓ.ም. ሥልጣን በፊትና በስተኋላ የተገኘ ታጋይነትን መሠረት ያደረገ ‹‹ለኢትዮጵያ ልማትና ህዳሴ የተዋደቅሁ›› የሚል ከልዩ ልዩ ብሔረሰብ የወጡ ተዋንያን የሚፏልሉበት የአዲስ ትምክህት ክንፍም አለው፡፡ ይኼኛው ክንፍ ‹‹እንደ ልፋታችን ይችን ታህል መዝገን አይበዛብንም፡፡ በልማቱ ተጠቃሚ መሆን የሚገባው ከእኛ በላይ ማን አለ…›› በሚል ኩራት የተሟሸ ነው፡፡ ወገናዊነቴ ለሕዝብ ነው … የምሠራው ነገር ሁሉ ዓላማው ሕዝባዊ ነው… ለሕዝብ ጥቅም ስል እከነተራለሁ የሚል ሕዝበኝነት አምባገነናዊ የረዥም ጊዜ ገዢነትን ‹‹በሕዝብ ሥልጣን››፣ ‹‹በሕዝብ መሪነት›› ስም ለመሰወር እንደሚያገለግል፣ አፈናንና ግድያን፣ ምርጫ ማጭበርበርንና መሸፈጥን፣ ወዘተ ‹‹ለሕዝብ በመዋደቅ›› አብዮታዊነት ለመተርጎምና በኃፍረት የለሽነት ለመወጠር እንደሚያስችል ሁሉ፣ ትልልቅና ትንንሽ ‹‹አብዮታዊ›› ሌቦችም ‹‹ኪራይ ሰብሳቢዎችን መታገል››፣ ‹‹የኒዮ ሊብራል ጥገኞችን መታገል›› በሚል ከለላ ውስጥ እየተደበቁና እየተሸለከለኩ ለመስረቅና ነውራቸውን በታጋይነት ኩራት ለመጋረድ ጠቅሟቸዋል፡፡

እነዚህ ሁሉ ድንግዝግዞች ተጋግዘው ትልቅ ጨለማና ዝምታ ይፈጥራሉ፡፡ ጨለማና ዝምታ ደግሞ ዋናው የሙስና ዳስና ምሽግ ነው፡፡ በዝምታ ውስጥ ደግሞ አንገት መድፋት፣ እያዩና እየበገኑ ማሳለፍ፣ ምንተዳዬ ባይነት ሁሉ ይገማሸራሉ፡፡ በእነዚህ ውስጥ ግለሰብ ነቀዞች እየተሹለከለኩ ሙስናን በማዛመት የሚያደርሱት የምግባርና የኢኮኖሚ ጥቃት አንድ ጉዳት ነው፡፡ የራስን ቡድን በመተኪያ የለሽነት እየካቡ፣ ተቃዋሚዎችን በዝርፊያ ኃይልነት/በፀረ ልማትነት ሕዝብ እንዲተፋቸው በማድረግ ሥልጣን የማራዘም ሙስና የሚያደርሰው ጉዳት ቶሎ የማይታይ፣ ጠንቁ ግን የከፋ ነው፡፡

የኢሕአዴግ መንግሥት ሙሰኞች እያለ ሰዎችን ሲያነሳና በሌላ ሲተካ ይታያል፡፡ የአሠራር ማሻሻያ ለውጥ ያካሂዳል፡፡ በፕሮፓጋንዳና በሥልጠና፣ በመፈክርም ሙስናን የሚፀየፍ ትውልድ ለመፍጠር ይፍጨረጨራል፡፡ ሕዝብ ሙስናን በማጋለጥ ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርግ ይማፀናል፡፡ ተማፅኖው ግን ሰው አልነቀነቀም፡፡ ሙስናም ሳይደናገጥ ሥራውን እየሠራ ነው፡፡ ችግሩ ምንድነው? ጥቂቶቹን እናንሳ፡፡

ጨለማ/ሰዋራ ሥፍራዎች ካልተወገዱ በቀር እዚያም እዚያም ‹‹ታማኞችን›› በማቆም ሙሰኞችን ጠብቆ መጨረስ አይቻልም፡፡ ትናንትና እንደሆነው ዛሬም እየሆነ እንዳለው ‹‹ታማኞቹን›› ጨለማው እየሰለቀጠ ይውጣቸዋል፡፡ በፀረ ሙስና ኮሚሽን ውስጥ በጥቅም እየነቀዙ የጥቆማ ሚስጥርን ለተጠርጣሪ የማሹለክ፣ የሙስና ፋይል በአግባቡ እንዳይመረመር በማወላከፍና በማዳፈን ኪስን አወፍሮ ዘወር የማለት ችግሮች መታየታቸውም (ሪፖርተር ጋዜጣ የካቲት 2 ቀን 2008 ዓ.ም.) አያስገርምም፡፡ መንግሥታዊ ሥርዓቱ ኮሚሽኑን ዛሬ ድግሞ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉን ከበላይ ተፅዕኖና ከንቅዘት ሊጠብቀው እንደማይችል የታወቀ ነው፡፡ 

ራስን ከማታለል የሚቆጠር ሐሰተኛ ኩሩ ግንዛቤ ሌላው ነው፡፡ ‹‹… በዚህ ዘመን የመንግሥት ሥልጣን ለግል ብልፅግና ማዋል አስነዋሪ አዝማሚያ ተደርጎ ተወስዷል፡፡ ነገር ግን በአገራችን የሚገኙ አብዛኞቹ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች የመንግሥት ሥልጣንን የግል ብልፅግና መሣሪያ የማድረግ አባዜ እንደተጠናወታቸው ይገኛል፡፡›› ኢሕአዴግን ‹‹ያስጨነቀው›› ተቃዋሚዎች ሥልጣን ይዘው መንግሥትን የዝርፊያ መሣሪያ እንዳያደርጉት ነው፡፡ መንግሥት ከባለሀብቱ ነፃ እንደሆነ ቆጥሮ ‹‹የኪራይ ሰብሳቢነትን አረንቋ ደረጃ በደረጃ የማድረቅ ብቃት ይኖረዋል›› ብሎ ማለትም ከቅዠት አይለይም፡፡ መንግሥት ከባለሀብትነት ባህርይ  ነፃ አይደለም፡፡ በአቋራጭ የመክበር ፍላጎትም መንግሥት ቤት አለ፡፡ መንግሥት አንድ የዝርፊያ ዋሻ መሆኑ፣ የፖለቲካ ድጋፍን በጥቅማ ጥቅም በመሳብና በመካስ የሙስና ምንጭና አስተማሪ መሆኑ አልታይ ብሎ ወይስ ሽምጠጣ? ዝርፊያን አስነዋሪ አድርጎ የሚያየው ፓርቲ፣ በ2007 ዓ.ም. የፓርቲዎች ምጥን የምርጫ ክርክር ላይ፣ ተዘርፎ በውጭ ተከማቸ ስለሚባለው በቢሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ ሲነሳበት እንዳልሰማ ከማለፍና ሲደጋገምበት ትንሽ ነው ከማለት ያለፈ መልስ አልነበረውም፡፡ እንኳን ተጠይቆ ሳይጠየቅ ምዝበራው እንዴት እንደተካሄዳና ለማስመለስ ምን እየተሠራ እንደሆነ ለሕዝብ ማብራሪያ መስጠት የሥራ አስፈጻሚነት ግዴታ መሆኑን፣ የተወካዮች ምክር ቤትም አቁሞ መጠየቅ ኃላፊነቱ መሆኑንማ ማን አዙሮ አይቶት! የዚህ ዓይነት ጠያቂነትና ተጠያቂነት እስከሌለ ድረስም ሥልጣን ላይ ማንም ተቀመጠ ማን ለዝርፊያ መግቻ አይገኝለትም፡፡

ኢሕአዴግ የትምክህትና የጠባብነት አስተሳሰቦችን የሚያራምዱ በሥልጣን ላይ እንዳልሆኑ አድርጎም ያስባል፡፡ ተቃዋሚዎቹን አግልሎ እየኮነነ ለራሱ የፈጠረው የኢትዮጵያ ህዳሴና የልማት ኃዋርያነት ለሙስና ከለላ የሆነና በማናለብኝነት የሚንጎማለል የትምክህት ፎቅ ማነፁን፣ ከጠባቦች እለይበታለሁ ባለው ‹‹ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት›› ውስጥ ጎሰኛ ሩጫና መጠቃቀም እየተሹለከለከበት መሆኑ ገና አልተገለጸለትም፣ ወይም ከዕይታ ውጪ ሆኖበታል፡፡

በታጋይነትም፣ በኢሕአዴግ አባል ድርጅትነትም ሆነ በገዢነት (ከፌደራል እስከ ክልሎች) ታላቅና ታናሽ ይንፀባረቅበታል፡፡ በሕዝቡም ግንዛቤ ውስጥ አበላልጦ ማየትና መፍራት አለ፡፡ ይህንን ሀቅ መቀበል ስለት እንደመዋጥ ኢሕአዴግን አስቸግሮታል፡፡ የአደረጃጀት ቅርፁ ከደቡብ ሕዝቦች ውጪ በየብሔረሰብ መዘርዘር ያለበት እንደመሆኑ፣ አደረጃጀቱ ራሱ ከቡድን (ከፓርቲ) ጋር ብሔረሰብን አያያዞ አዕምሮ እንዲመለከት ያስገድዳል፡፡ በዚህም ምክንያት የሥልጣን ሥርጭቱ፣ የግለሰቦች የዘረፋና የሀብት ማጋበስ እሽቅድምድም ሁሉ በብሔረሰብ መብለጥና መበለጥ ሒሳብ ውስጥ ገብቶ መታየት አይቀርለትም፡፡ ኢሕአዴግ የችግሩን ነባራዊ ምንጭ ለይቶ ትክክለኛ መፍትሔ በመፈለግ ፈንታ፣ የግለሰቦች ጥፋትም ሆነ የሀብት አግበስባሽነት በብሔረሰባቸው የመላከኩን ችግር ትምክህተኞችና ጠባቦች የሚያካሂዱት ተንኮል አድርጎ በሥልጠና ስብከት ሊያጥብ ይሞክራል፡፡ ጭራሽ ሲሰብክ እንኳ ዋናው ችግር ላይ በማተኮር ፈንታ በራስ ብሔረሰብ ውስጥ ያለውን ሙስና ደብቆ በሌላው ላይ ግን ጣት የመጠቆምን ፍትሐዊ ያልሆነ አሳጭነት የመተቸት ዝባዝንኬ ውስጥ ይገባል፡፡ ትምክህተኛነትና ጎሰኝት ወገኔ ለሚለው ከማዳላት ውጪ ምን ባህርይ ሊኖረው! ያለ አድልኦ ዝርፊያን መቃወምና ማጋለጥ ከእነሱ የሚጠበቅ ሳይሆን፣ እነሱን የመታገልና የማድከም ውጤት ነው፡፡

ሕዝብ ሙስናን እንዲታገል የሚደረገው የአንደበት ጉትጎታ ልጓም ከማላላት ጋር አለመገናኘቱም ሌላው ትልቅ ችግር ነው፡፡ ሐሳብን በመግለጽ፣ በመሰብሰብና በመቃወም መብቶች ረገድ ያለው እፍንፍን ያለ ሁኔታ፣ ተቃውሞ ላይ ባደሉ ጋዜጦችና በተቃዋሚዎች ላይ ያለው በወጥመድ የተሞላ አያያዝ፣ በየመንደር የሚያጋጥመውና በወሬ የሚናፈሰው ለሥርዓቱ በመታመንና በመታገል ማን አህሎኝ የሚሉ ግለሰቦች የሚያሳዩት የእብሪት ንግግርና  ድርጊት ሁሉ፣ ንቁ ተሳትፎን ከማደፋፈር ይልቅ አደብ መግዛትን የሚያስጠነቅቅ ነው፡፡ በአጭሩ ሥርዓቱ ልዩ መብት የሌለበት መሆኑን፣ ሁሉም በሕግ ሥር እንደሆነ፣ የነፃነት መብቶችም በሕግ እንደሚጠበቁ የሚያሳምን ተግባር ለሕዝብ ማሳየት ተስኖታል፡፡

በ2007 ዓ.ም. በተደረገ አንድ የቴሌቪዝን የምርጫ ክርክር ላይ አንድ የተቃዋሚ ተወካይ በመንግሥት የፖለቲካ ሰው ለሚደርስ በደል ምሳሌ አድርጎ የጠቀሰው፣ ቤተሰቤና እኔ በሌለንበት ሰዓት ካልሆነ በብየዳ/ሙረዳ ጩኸት እንዳትረብሸኝ የተባለ ሰውዬ ሠፈር የቀየረው፣ በመኖሪያ ቤት አጠገብ ጩኸት በመፍጠር መብት ተጋፍቻለሁ ብሎ ሳይሆን የማላሸንፈው ባለጋራ ገጥሞኛል ብሎ ነው፡፡ የሹም ወገን ወይም የገዢ ፓርቲ አባል የሆነ ሰውን ሕገወጥ ድርጊትና ሙስናን ማጋለጥም ያንኑ ያህል መሸማቀቅና ፍርኃት ያለበት ነው፡፡

 መንግሥት ልሽቀትና ሙስናን በቁርጥ መዋጋት ከፈለገ ግምገማው፣ ብጠራው፣ ሹምሽሩ፣ የአሠራር ለውጡና ሥልጠናው ሁሉ ተደርጎ ጨዋነት የተሞላበት ሥራ ለምን ሥር መስደድ አልቻለም? ታታሪነት፣ የግል ተነሳሽነት፣ የሥራ ፍቅርና ተገልጋይ አክባሪነት የማይፍለቀለቁት ምን ጎድሎ ነው? ምዕራብ ዴሞክራሲ ውስጥ የሚታየው የመንግሥት ሠራተኛ ይቅርና የግል ነጋዴ አግባብ ያልሆነ ድርጊት ቢፈጽምበት ለኃላፊ አሳውቆ መብትን የማስከበር የተገልጋይ ልበ ሙሉነት እኛ አገር ሽታውም የሌለው ለምንድነው? ለእነዚህ ጥያቄዎች ትክክለኛ መልስ መስጠት መቻል አለበት፡፡

የምር ፍላጎቱ ካለም የተግባራዊ መልስ ሒደቱን ለመጀመር ከባድ አይደለም፡፡ መጀመርያ ምን የመሰለ ምን ዓይነት ሁኔታ ውስጥ እንደምንገኝ ያውጅ፡፡ አገራችን ውስጥ ዝም ባይነትና የሩቅ አደግዳጊነት መሠልጠኑን፣ የአደባባይ ሕይወታችን በማስመሰል ሥልት መገዝገዙን፣ ሸባ መሆኑን፣ የመንግሥትና የአለቃ ንብረት መሆኑን፣ ያመኑበትን ፊት ለፊት ተናግሮ የመኖር ክብር መጥፋቱን፣ የዝምታ፣ የምን ተዳዬና ሲከፋም የማረጥረጥ ኑሮ ውስጥ መዋጣችንን በአደባባይ ይመስክር፡፡ ይህ መለወጥ አለበት ይበል፡፡ ከዚህ ባርነት ውስጥ ወጥተናል ብሎ ያውጅ፣ ኅብረተሰቡ ዛሬም የአንገት በላዩን በአደባባይ፣ የአንገት በታቹን በየጓዳው በመጫወት ዘይቤ ውስጥ እየዳከረ መሆኑን አውቆ ጥፋቱንና ሽንፈቱን አምኖ ይቀበል፡፡ የጠላትነት ፖለቲካን ያፍርስ፡፡ ለየትኛው ቡድን ሳይወግን የሚያገለግል አውታረ መንግሥት የማነፅ ሥራ ውስጥ ጨርሶ አለመግባቱን ይቀበል፡፡

መንግሥት ሙስናን የሚጠየፍ ኅብረተሰብ ‹‹ይፈጠራል›› ከሚለው ትምክህቱ ወጥቶ አስተዳደርና ልማቱ ያለ ሕዝብና ነፃ ሚዲያ ዓይንና ምላስ ዋስትና የሌለው መሆኑን አምኖ ለዚሁ ይገዛ፡፡ በአገራችን በተለይም አውታረ መንግሥት ግንባታ ውስጥ ያለ ችግር ሰፊና ፅኑ ነው፡፡ ኃላፊነትን የማክበር ጨዋነት ፖለቲካዊ ዝንባሌን በልጦ እስኪፀና ድረስ የዳኝነት፣ የመከላከያ፣ የደኅንነት፣ የዓቃቤ ሕግና የፖሊስ ሰዎች ከፓርቲ አባልነት በተጨማሪ ከየትኛውም የፖለቲካ ተሳትፎ የተገለሉ እንደሆኑ በሕግ መገደብ፣ ፈልገውም (የሙያ ሥነ ምግባራቸው አድርገውም) ወገናዊ ከሆነ አመለካከት ነፃ ለመሆን እንዲጣጣሩ ማሳመን ሳያስፈልግ አይቀርም፡፡

በተጨማሪም በስሙ ማውራት ስለሕዝቡ ሆኖ መወሰን የእነሱ ብቻ አደራ የሆኑት የስም የሕዝባዊ ድርጅቶችና ማኅበራት (አደረጃጀቶች) ብቸኛ የሞኖፖል መብት ቢቀር፣ በአንድ አስተሳሰብ ከመጠርነፍ ወጥተን ብዙ ሐሳቦችን ወደ ማብላላት ብንሸጋገር፣ ሕዝብ ብሶቱንና ፍላጎቱን በይፋ ለመናገር፣ በደልን ለመጋተርና መብቱን ለማስከበር የማይፈራበት የነፃነት አየር ቢለቀቅ፣ በየትኛውም ደረጃ ያለ የመንግሥት የአስተዳደር እርከን ሕዝብን ከየትኛወም ዓይነት ጥቃትና ጉዳት የመጠበቅ ኃላፊነቱን በዝንጉነትም ሆነ በሌላ ምክንያት ሳይወጣ በመቅረቱ ለሚደርስ ጥፋት መጠየቁ የአገር ሕግና ወግ ቢሆን፣ (ለምሳሌ የቂሊንጦ እስር ቤት ቃጠሎ፣ የኢሬቻ ግርግር ያስከተለው ሞት ኃላፊነት ሳይድበሰበስ መቅረት) ረዥም ርቀት የሚሸኙ ማሳያዎች ናቸው፡፡

ያላንዳች ፍርኃትና በኃላፊነት ሕገወጥ ተግባራትንና የሙስና ሥራዎችን የማጋለጥና የመታገል ተግባር ወደ መገናኛ ዘዴዎች ቢስፋፋ፣ መንግሥትም ከየትም ይምጣ ከየት ጥፋቶችን ለማረምና አጥፊዎችን ለመጠየቅ ባያወላውል፣ ማናለብኝነትን፣ ሕገወጥነትንና ሙስናን ፍርኃት ምን ያህል ባከሳቸው! በኢኮኖሚ፣ በማኅበራዊና በፖለቲካ ሕይወታችን ውስጥ ያለ ስንት ጨለምላማ ሥፍራ ጉልህ ብርሃን፣ የጋዜጠኛና የሕዝብ ዓይን በበራበት ነበር፡፡ እዚህ ሒደት ውስጥ የመግባት ነገር ደግሞ በቃ ሳትሳቀቁ ሥሩ የሚል አንድ መግለጫ የመለፈፍ ጉዳይ ሳይሆን፣ አንዱ አልሚ ሌላው አጥፊ፣ አንዱ ጠርጣሪ ሌላው ተጠርጣሪ የሆነበትን ግንኙነት የመናድ ድፍረትን ይጠይቃል፡፡ እስከ ቁንጮ ሹም ድረስ ያለ የሥራ/የተራክቦ ማኀበራዊ ቤታችንን ጣሪያና ግድግዳ መስታወታማ አድርጎ ለመገንባት መቁረጥ፡፡  ዴሞክራሲ! ዴሞክራሲ!!!

 ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊዋን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

‹‹በየቦታው ምርት እየገዙ የሚያከማቹ ከበርቴ ገበሬዎች ተፈጥረዋል››

አቶ ኡስማን ስሩር፣ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር...

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...