የወጪ ንግድን ዓላማ አድርገው ከተቋቋሙት የጨርቃ ጨርቅና የአልባሳት ፋብሪካዎች፣ አብዛኛዎቹ የ2009 ዓ.ም. ዕቅዳቸውን ማሳካት አለመቻላቸው ተገለጸ፡፡
የኢትዮጵያ ጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት የ2009 በጀት ዓመት የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ዕቅድ አፈጻጸምና የ2010 ዓ.ም. ዕቅድን አስመልክቶ ከዘርፉ ባለሀብቶች ጋር ዓርብ ነሐሴ 19 ቀን 2009 ዓ.ም. በተወያየበት ወቅት እንደተገለጸው፣ ከጨርቃ ጨርቅና ስፌት ኢንዱስትሪ ምርቶች ኤክስፖርት በ2009 በጀት ዓመት 271 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ለማድረግ ታቅዶ የነበረ ቢሆንም፣ የተገኘው 89.3 ሚሊዮን ዶላር ሲሆን፣ አፈጻጸሙም 33 በመቶ ነው፡፡
በበጀት ዓመቱ ከየትኞቹም ድርጅቶች በበለጠ ከ60.9 ሚሊዮን ዶላር በላይ ለማስገባት አቅዶ የነበረውና ተስፋ የተጣለበት አይካ አዲስ ቴክስታይል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር፣ ከዕቅዱ ያከናወነው 43 በመቶ ብቻ ነው፡፡ በበጀት ዓመቱ ዕቅዱን ማሳካት የቻለው ካኖርያ አፍሪካ ቴክስታይል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ብቻ ነው፡፡ ካኖርያ 5 ሚሊዮን 424 ሺሕ ዶላር ለማስገባት አቅዶ የዕቅዱን 104 በመቶ መፈጸም መቻሉ ተገልጿል፡፡
የኢንስቲትዩቱ የዕቅድና መረጃ ሥራ አመራር ዳይሬክተር አቶ አበበ ካሴ እንደገለጹት፣ የዘንድሮ ዕቅድ አፈጻጸም አምና ከተገኘው 78 ሚሊዮን ዶላር ጋር ሲነፃፀር የ11.3 ሚሊዮን ዶላር ጭማሪ ቢያሳይም፣ በአጠቃላይ ሲታይ ግን በጣም ዝቅተኛ ነው፡፡ የድርጅቶች አፈጻጸምም ከዕቅዱ ሲነፃፀር የወረደ ነው ብለዋል፡፡
በ2009 ዓ.ም. ዕቅዳቸውን ሊያሳኩ ይችላሉ ከተባሉት ዋና ዋና ድርጅቶች፣ አርቪንድ ላይፍስታይል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር 27 ሚሊዮን 033 ሺሕ ዶላር ለማስገባት አቅዶ አፈጻጸሙ አሥር በመቶውን ብቻ ሲሆን፣ ሺንተስ ኢቲፒ ጋርመንት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ደግሞ 14 ሚሊዮን 954 ሺሕ ዶላር ለማስገባት አቅዶ በአፈጻጸሙ የዕቅዱን 45 በመቶ ማሳካት ችሏል፡፡ ኤምኤንኤስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር 11 ሚሊዮን 088 ሺሕ ዶላር ለማስገባት አቅዶ አፈጻጸሙ 20 በመቶ፣ ኤልሲ አዲስ ቴክስታይል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር 10 ሚሊዮን 112 ሺሕ ዶላር ለማስገባት አቅዶ አፈጻጸሙ 11 በመቶ፣ ቬሎሲቲ አፓራልስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር 9 ሚሊዮን 852 ሺሕ ዶላር ለማስገባት አቅዶ 0 በመቶ፣ ዶንግ ፋንግ ስፒኒንግ ፕሪንቲንግና ዳይንግ 7 ሚሊዮን 812 ሺሕ ዶላር አቅዶ ዘጠኝ በመቶ፣ ኮምቦልቻ ጨርቃ ጨርቅ አክሲዮን ማኅበር 6 ሚሊዮን 768 ሺሕ ዶላር አቅዶ 70 በመቶ፣ ከቢረ ኢንተርፕራይዝ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር 6 ሚሊዮን 200 ሺሕ ዶላር አቅዶ 80 በመቶ፣ ሐይድራሚኒ ጋርመንት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር 5 ሚሊዮን 693 ሺሕ ዶላር አቅዶ 57 በመቶ ፣ አሽተን አፓረል 5 ሚሊዮን 100 ሺሕ ዶላር አቅዶ 29 በመቶ፣ ባህር ዳር ጨርቃ ጨርቅ አክሲዮን ማኅበር 4 ሚሊዮን 558 ሺሕ ዶላር አቅዶ 43 በመቶ እንዲሁም ኢቱር ቴክስታይል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር 4 ሚሊዮን 427 ሺሕ ዶላር አቅዶ አምስት በመቶ መፈጸማቸውን አቶ አበበ አስረድተዋል፡፡
እንደ አቶ አበበ፣ በበጀት ዓመቱ 6.9 ቢሊዮን ብር ካፒታል ያላቸው 23 አዳዲስ ፕሮጀክቶች ወደ ምርት እንዲገቡ ታቅዶ ነበር፡፡ በሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ 14 እና ከዚህ በተጨማሪ አምስት በድምሩ 19 ፕሮጀክቶች ወደ ምርት ገብተዋል፡፡ ወደ ምርት የተሸጋገሩና በመሸጋገር ሒደት ላይ ያሉ ፋብሪካዎችም ለ17,447 ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠራቸው ተወስቷል፡፡
ዘርፉ ለውጭ ምንዛሪ ተስፋ የተጣለበት ቢሆንም፣ ከዓመት ዓመት በችግሮች ሲፈተን የዘርፉ ባለሀብቶችም ዕሮሮዋቸውን ሲያሰሙ ይስተዋላል፡፡ ከዓመታት በፊት ጀምሮ ለዘርፉ ማነቆ የሆኑ ችግሮች በተደጋጋሚ ሲነሱ የከረሙ ቢሆንም፣ ዛሬም ጥያቄ ሆነው ቀጥለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ማኅበር ፕሬዚዳንት አቶ ፋሲል ታደሰ እንደተናገሩት፣ በዘርፉ ላይ በተጋረጡ ችግሮች ምክንያት እ.ኤ.አ. ከ2011 እስከ 2017 ባሉት ጊዜያት የዘርፉ የወጪ ንግድ ገቢ እያሽቆለቆለ ነው፡፡ ለወጪ ንግዱ አፈጻጸም ዝቅተኛ መሆንም በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የሚቀርቡ ድጋፎች ዝቅተኛ መሆን አንዱ ምክንያት መሆኑ ይነገራል፡፡
ለዘርፉ ወጪ ንግድ አፈጻጸም ማሽቆልቆል ኢንስቲትዩቱ እንደ አንድ ምክንያት ያስቀመጠው፣ ፋብሪካዎቹ ወደ ውጭ ከመላክ ይልቅ አገር ውስጥ መሸጣቸውን ቢሆንም አቶ ፋሲል ይህንን አይበቀሉትም፡፡ አገር ውስጥ የሚሸጠውም እዚህ ግባ የማይባል እንደሆነ፣ ይልቁንም አገሪቱ ጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ከውጭ ለማስገባት በዓመት ከነዳጅ ምርት ግዥ ያልተናነሰ የውጭ ምንዛሪ እንደምታወጣ ተናግረዋል፡፡
የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ከኢንዱስትሪ ፓርክ ውጭ ያሉ የአገር ውስጥና የውጭ ባለሀብቶችን ችግር ለመፍታት የሚያደርገው ጥረት በቂ አለመሆን፣ የባለሀብቶች የፋይናንስ አቅም ችግርና በብድር ተዘፍቀው አሁንም ድረስ ዋናውን ሳይሆን ወለዱን እየከፈሉ የሚገኙ መኖራቸው፣ ኤክስፖርትን አዋጭና ሳቢ ለማድረግ ቀጣይነት ያለው ስትራቴጂ ነድፎና በፓኬጅ ማበረታቻ አዘጋጅቶ አምራች ወደ ኤክስፖርቱ እንዲገባ አለማድረጉና የገበያ ቁርኝት አለመፈጠሩ ዘርፉን ከፈተኑ ችግሮች መካከል ተጠቅሰዋል፡፡
ኢንስቲትዩቱ በበኩሉ የዘርፉን ችግር ለመፍታት ድጋፍና ሥልጠና በበጀት ዓመቱ የሰጠ ቢሆንም፣ የዘርፉ ፋብሪካዎች የማኔጅመንትና የቴክኒክ አቅም ውስንነት፣ የጥራት ችግር፣ የማኅበራዊና አካባቢያዊ መሥፈርት አለማሟላትና የማቅረቢያ ጊዜን በማሟላት ተወዳዳሪ አለመሆን የኤክስፖርት አፈጻጸሙ በታቀደው መሠረት እንዳይሳካ ማነቆ መሆኑን ጠቁሟል፡፡
የጥጥ፣ የኬሚካል፣ የቀለማ ቀለምና የአክሰሰሪ አቅርቦት ውስን መሆንም የዘርፉ ችግሮች ናቸው፡፡ በ2010 በጀት ዓመት ችግሮቹን ለመቅረፍና ከዘርፉ የሚገኘውን የውጭ ምንዛሪ 236.2 ሚሊዮን ዶላር ለማድረስ፣ 8.6 ቢሊዮን ዶላር ካፒታል ያላቸው 23 አዳዲስ ፕሮጀክቶችም ወደ ምርት እንዲገቡ ለማስቻልም ታቅዷል፡፡
የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ስለሺ ለማ ‹‹ችግሮችን አብሮ በመድፈን ለበለጠ ውጤት መሥራት ይገባል፤›› ብለዋል፡፡
‹‹ባለሀብቱ ያለውን አቅምና በመንግሥት የሚሰጡ ድጋፎችን በማጣመር በአንድ ላይ ለውጥ እናመጣለን፤›› የሚል እምነት እንዳላቸውም አክለዋል፡፡