Sunday, June 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየመንግሥት ባለ በጀት መሥሪያ ቤቶች ወጪ እንዲቀንሱ ጥብቅ መመርያ ወጣ

የመንግሥት ባለ በጀት መሥሪያ ቤቶች ወጪ እንዲቀንሱ ጥብቅ መመርያ ወጣ

ቀን:

የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር የፌዴራል ባለ በጀት መሥሪያ ቤቶች በቅርቡ ያሠራጨውን የበጀት ወጪ ቅነሳ ማቅረቢያ ቅጽ ሞልተው፣ እስከ ነሐሴ 30 ቀን 2009 ዓ.ም. ድረስ እንዲያቀርቡ አዘዘ፡፡ በመመርያው መሠረት በርካታ አላስፈላጊ ወጪዎችን እንዲቀንሱ ጠበቅ ያሉ ክልከላዎች ተደርገዋል፡፡

በ2010 በጀት ዓመት ተግባራዊ እንዲደረግ ሚኒስቴሩ በቅርቡ ካዘጋጀው የወጪ ቅነሳ መመርያ ጋር አብሮ የወጣው ቅጽ፣ አስፈጻሚ መሥሪያ ቤቶች በጀታቸውን በአግባቡ እንዲጠቀሙ ያዛል፡፡ ሚኒስቴሩ ባለበጀት መሥሪያ ቤቶች በ2010 ዓ.ም. ወጪያቸውን በመቀነስ በጀታቸውን ቁጠባን መሠረት ባደረገ አሠራር እንዲጠቀሙበት አሳስቧል፡፡

ዓመታዊ ፕሮግራም፣ ግብና ውጤትን መሠረት ያላደረገ የበጀት ዝውውርና የተጨማሪ በጀት ጥያቄ መሥሪያ ቤቶች እንዳያቀርቡ መመርያው ከልክሏል፡፡

መመርያው መደበኛ ወጪን በተመለከተ 19 ያህል ግዥዎችና የተለያዩ ወጪዎች ላይ ጥብቅ የሆነ አሠራርና አንዳንዶቹም ላይ ክልከላን አስቀምጧል፡፡

መሥሪያ ቤቶች በየዓመቱ እንደ ቀን መቁጠሪያ ካላንደር፣ አጀንዳዎች፣ የመጽሔት ኅትመትና የደስታ መግለጫ ካርድ ግዢዎችን ከልክሏል፡፡ በተጨማሪም የወረቀት፣ የቶነር፣ የማስታወሻ ደብተርና የእስክሪብቶ ግዢን መቀነስ እንዳለባቸው፣ ነገር ግን የኢንፎርሜሽንና ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ (ICT) እንዲጠቀሙ ያዛል፡፡

ለሠራተኞች በየመሥሪያ ቤቱ የሚከፋፈሉ የፅዳት አላቂ ዕቃዎችን ግዢ በተመለከተ፣ መሥሪያ ቤቶቹ የግዢውን መጠን እንዲቀንሱ ማሳሰቢያ ተሰጥቷቸዋል፡፡

በተለምዶ በየመሥሪያ ቤቱ የሚደረጉ የመስተንግዶ ወጪዎችን በተመለከተ ከአሁን በኋላ ለሚደረጉ ስብሰባዎች፣ ዓውደ ጥናቶችና ሴሚናሮች እንደ ሻይ፣ ቡናና ውኃ ከመሳሰሉት በስተቀር ተጨማሪ ግብዣዎች እንዳይደረጉ ይከለክላል፡፡ የሚደረጉት ስብሰባዎችም በተቻለ መጠን በየተቋማቱ አዳራሾች እንዲደረጉና ለሆቴል የሚወጡ ወጪዎች እንዳይኖሩ ያስገነዝባል፡፡

በተጨማሪም ለስብሰባዎችና ለክብረ በዓላት ቦርሳዎችን፣ ቲሸርቶችን፣ ኮፍያዎችን፣ ስካርፎችንና የተለያዩ የአገር ባህል አልባሳትን መግዛትም በጥብቅ ተከልክሏል፡፡

የውጭ አገር ጉዞን በተመለከተም መመርያ ወጥቷል፡፡ የሚኒስቴሮችና በሥራቸው ያሉ ተጠሪ መሥሪያ ቤቶች ኃላፊዎች ጭምር የውጭ አገር ጉዞ ፕሮግራም ሲኖራቸው የፕሮግራሙ ዓላማ፣ የተሳታፊዎች ብዛት፣ የቆይታቸው ጊዜና ወጪን የሚያሳይ የውጭ ጉዞ መርሐ ግብር በማዘጋጀት ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ቀርቦ መፈቀድ እንዳለበት መመርያው ያሳስባል፡፡

የሠራተኞች የትርፍ ሰዓት ክፍያን በተመለከተም በፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ሚኒስቴር ሲፈቀድ ብቻ መከፈል እንዳለበት ይደነግጋል፡፡

ሌላው ድጋፍና ስጦታን በተመለከተም በመመርያው እንደተገለጸው፣ ባለበጀት መሥሪያ ቤቶች በዩኒቨርሲቲዎች ከሚማሩ የክረምት ተማሪዎችና አካል ጉዳተኞች በስተቀር ለማንኛውም ድርጅት ሆነ ግለሰብ የገንዘብ ድጋፍ ወይም ስጦታ መስጠት አይችሉም፡፡

በተጨማሪም ከተለያዩ አካላት የሚቀርቡ የስፖንሰርሺፕ ጥያቄዎችም በመንግሥት ባለበጀት መሥሪያ ቤቶች እንዳይስተናገዱ በመመርያው ታዟል፡፡

ከካፒታል ወጪ ጋር በተያያዘም በበጀት አዋጁ ከፀደቀው ፕሮጀክት ውጪ ፕሮጀክቶችን ማካሄድ እንደማይቻል፣ የተቀፈዱ ፕሮጀክቶችም በታቀደው ጊዜ፣ ወጪና ጥራት እንዲከናወኑ የፕሮጀክት ማኔጅመንት ሥርዓት ማጠናከር እንደሚያስፈልግ ተጠቁሟል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አወዛጋቢው የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ጉዳይ

በኢትዮጵያ የሕገ መንግሥት ማሻሻል ጉዳይ ከፍተኛ የፖለቲካ ውዝግብ የሚቀሰቀስበት...

 መፍትሔ  ያላዘለው  የጎዳና  መደብሮችን  ማፍረስ

በአበበ ፍቅር ያለፉት ስድስት ዓመታት በርካቶች በግጭቶችና በመፈናቀሎች በከፍተኛ ሁኔታ...

የተናደው ከቀደምቱ አንዱ የነበረው የአዲስ አበባ ታሪካዊ ሕንፃ

ዳግማዊ አፄ ምኒልክ በ19ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ መናገሻ ከተማቸውን...

የአከርካሪ አጥንት ሕክምናን ከፍ ያደረገው ‘ካይሮፕራክቲክ’

በአፍሪካ ከጀርባ ሕመም ጋር በተያያዘ በርካታ ሰዎች ለከፍተኛ የአካል...