Sunday, June 4, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ከፍተኛው ፍርድ ቤት በ69.5 ሚሊዮን ብር ደረቅ ቼክ ላይ የሰጠውን ውሳኔ አገደ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

ቼኩን የጻፉት ግለሰብ ከኃላፊነት እንዲነሱ ተወሰነ
ኢትዮ ሩት ኢንተርናሽናል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ሥራ አስኪያጅ፣ ድርጅቱ ካለው ካፒታል በላይ የ69.5 ሚሊዮን ብር ደረቅ ቼክ ቆርጠው በመስጠታቸው ቼኩ ለተቆረጠላቸው ግለሰቦች እንዲከፈላቸው ቢወስንም፣ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ዘጠነኛ ፍትሐ ብሔር ችሎት ውሳኔው እንዲታገድ ትዕዛዝ ሰጠ፡፡

የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ‹‹ኢትዮ ሩት ኢንተርናሽናል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር በሚል ድርጅት ስም አቶ ሳምሶን አርአያ፣ አቶ ዮሴፍ ከፍያለው፣ አቶ ዮሴፍ አርአያ፣ አቶ ቴዎድሮስ ማሞና አቶ ሚሊዮን መከታን ጨምሮ ዘጠኝ በሚሆኑ ሰዎች የቀረበለትን የደረቅ ቼክ ክስ ተመልክቶ፣ የጠየቁት ገንዘብ ከዘጠኝ በመቶ ወለድ ጋር እንዲከፈላቸው ውሳኔ ሰጥቶ እንደነበር መዝገቦች ያስረዳሉ፡፡

ደረቅ ቼክ የተጻፈላቸው ግለሰቦች በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ክስ የመሠረቱት አቶ ቃለሥላሴ በላይ በሥራ አስኪያጅነት በሚመሩት ኢትዮ ሩት ኢንተርናሽናል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ድርጅት ላይ ሲሆን፣ ውሳኔ ከተሰጠ በኋላ ዕግድ ሊጣል የቻለው ከፍተኛ ባለድርሻ መሆናቸውን በመግለጽ የመቃወሚያ አቤቱታ ለፍርድ ቤቱ ባቀረቡት አቶ ድልአርጋቸው በላይ አማካይነት መሆኑን ፍርድ ቤቱ ገልጿል፡፡

አቶ ድልአርጋቸው በከፍተኛው ፍርድ ቤት የተሰጠውን ውሳኔ ካሳገዱ በኋላ፣ ጉዳዩን ወደ ፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ሰባተኛ ፍትሐ ብሔር ችሎት በመውሰድ ክስ በመመሥረት አቶ ቃለሥላሴ ከሥራ አስኪያጅነት እንዲነሱ ጠይቀዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ የተመሠረተውን ክስ መርምሮ በሰጠው ፍርድ እንዳብራራው ድርጅቱ ኢትዮ ሩት ኢንተርናሽናል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር፣ በደቡብ ክልል ገዋታ ወረዳ፣ የባ ቀበሌ ገበሬ ማኅበር ውስጥ 250 ሔክታር መሬት በሊዝ ወስዶ በቡና ምርት ልማት ላይ የተሰማራ ድርጅት ቢሆንም፣ ባለፉት ሁለት ዓመታት ግን ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ እያደረገ አለመሆኑን ከሳሽ ለፍርድ ቤቱ ማሳወቃቸውን ይገልጻል፡፡ አቶ ድልአርጋቸው ለመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት ባቀረቡት ክስ አቶ ቃለሥላሴ የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ ሆነው ሲሠሩ ከ69.5 ሚሊዮን ብር በላይ ደረቅ ቼክ በመቁረጣቸው፣ ቼክ የተቆረጠላቸው ግለሰቦች በከፍተኛው ፍርድ ቤት ክስ መሥርተው የተወሰነላቸው ቢሆንም ባቀረቡት አቤቱታ ማሳገዳቸውን ፍርድ ቤቱ በፍርዱ ገልጿል፡፡

የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ ቼኮቹን ቆርጠው የሰጡት ለድርጅቱ ማስፋፊያ መሆኑን ለፍርድ ቤቱ የገለጹ ቢሆንም፣ የድርጅቱን የሒሳብ እንቅስቃሴ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ዕግድ ጥሎበት እያለ መሆኑንም ከሳሽ ጠቁመዋል፡፡ የማኅበሩን የቡና ምርት እየሸጡ የገቢ ግብር አለማሳወቃቸውን፣ ከሠራተኞች የሚቀነስ የሥራ ግብርና የጡረታ መዋጮ ለተከታታይ ዓመታትም ገቢ አለማድረጋቸውንም አቶ ድልአርጋቸው በክሳቸው ማካተታቸውን ፍርዱ ይገልጻል፡፡ ድርጅቱ ከስድስት ሚሊዮን ብር በላይ ዕዳም እንዳለበትም አክሏል፡፡

አቶ ቃለሥላሴ ለግለሰቦቹ ቼክ የጻፉት፣ ማኅበሩ የግል ሕንፃ እንዳለውና ኪራይ እየሰበሰበ መሆኑን በመግለጽ መሆኑን ፍርድ ቤቱ ገልጿል፡፡ ሥራ አስኪያጁ ቼክ መስጠታቸውን ያመኑ ቢሆንም፣ የተጻፈላቸው ግለሰቦች ግን ከማኅበሩ ጋር ምን ዓይነት ግንኙነት እንዳላቸው የሚያሳይ ማስረጃ አለመቅረቡንም ፍርዱ ያብራራል፡፡ ቼኮቹ የተጻፉት ለማኅበሩ ማስፋፊያ ለተበደሩት እንደሆነ አቶ ቃለሥላሴ የገለጹ ቢሆንም፣ እሱን የሚያስረዳ ምንም ዓይነት ማስረጃ ማቅረብ አለመቻላቸውን ፍርድ  ቤቱ ገልጿል፡፡ የቼኮቹ አጻጻፍ ከ3,000,000 ሚሊዮን ብር እስከ 10,000,000 ብር በአጭር ጊዜ ከመሆኑ አንፃር ገንዘቡ ወጪ የተደረገው ለማስፋፊያ ቢባልም አሳማኝ አለመሆኑንና ማስረጃም እንዳልቀረበም ፍርዱ ያብራራል፡፡ ቼኮቹ የተሰጡት ማኅበሩ ሒሳብ እንደሌለው እየታወቀ መሆኑን አቶ ቃለሥላሴ ባለመካዳቸው የወንጀል ኃላፊነትን የሚያስከትልባቸው መሆኑንም ገልጿል፡፡

በተጨማሪም አቶ ቃለሥላሴ በሥራ አስኪያጅነት ይመሩት የነበረው ኢትዮ ሩት ኢንተርናሽናል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ከ2004 እስከ 2008 ዓ.ም. ድረስ የኪራይ ገቢ ግብር፣ ተጨማሪ እሴት ታክስ፣ የሥራ ግብርና ጡረታ 6,742,726 ብር ዕዳ እንዳለበት፣ የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ማሳወቁንም በክሱ ጠቅሷል፡፡ ይህም የሚያሳየው ድርጅቱ ሕግን በተከተለ አግባብ አለመመራቱን እንደሆነ ፍርድ ቤቱ ገልጿል፡፡ ሥራ አስኪያጁ በአመራራቸው እምነት ሊጣልባቸው የማይችሉ መሆኑንና ከሳሽ አቶ ድልአርጋቸው ባቀረቡት ‹‹ከሥራ አስኪያጅነት ይነሱልኝ›› ጥያቄ መሠረት ፍርድ ቤቱ በፍትሐ ብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 182፣ በንግድ ሕግ ቁጥር 182 እና በ527(2፣ 3 እና 5) መሠረት ከሥራ አስኪያጅነታቸው እንዲነሱ ፍርድ ሰጥቷል፡፡ ከሳሽ አቶ ድልአርጋቸው በላይንም ሥራ አስኪያጅ አድርጎም ሾሟል፡፡

ኢትዮ ሩት ኢንተርናሽናል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር በ15,240,000 ካፒታል ባላቸው 762 አክሲዮኖች የተከፋፈለ ማኅበር ነው፡፡ አቶ ድልአርጋቸው በእናታቸው ስም 437 አክሲዮኖች ያላቸው ቢሆኑም፣ አቶ ቃለሥላሴ ‹‹የኑዛዜ ወራሽ ነኝ›› በማለታቸው ክስ ተመሥርቶባቸው በመዝገብ ቁጥር 138860 ኅዳር 7 ቀን 2008 ዓ.ም. ለአቶ ድልአርጋቸው መመለሱንም ሰነዶች ያስረዳሉ፡፡ አክሲዮኖቹም ግንቦት 14 ቀን 2009 ዓ.ም. በአፈጻጸም ለአቶ ድልአርጋቸው በሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ኤጀንሲ እንዲመዘገቡ መደረጉም ተጠቅሷል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች