ከአንድ ዓመት በኋላ በዑራጓይ አስተጋጅነት ለሚካሄደው የሴቶች ከ17 ዓመት በታች ዓለም ዋንጫ ማጣሪያ የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን (ቀይ ቀበሮዎቹ) ኬንያን ይገጥማል፡፡ በፊፋው የሴቶች ከ17 ዓመት በታች የማጣሪያ ጨዋታ ለቀይ ቀበሮዎቹ በመጀመሪያ ዙር ማጣሪያ ጨዋታ ጥቅምት ላይ ኬንያን እንደሚገጥሙ ካፍ ያወጣው መርሐ ግብር ያስረዳል፡፡
ኢትዮጵያ የመጀመሪያውን ጨዋታ በአዲስ አበባ አድርጋ በኅዳር ከሜዳዋ ውጪ ኬንያን የምትገጥም ስትሆን የሁለቱ አሸናፊዎች ናይጄሪያን ይገጥማል፡፡ የመጨረሻው የማጣሪያ ጨዋታ የካቲት ወር ላይ እንደሚከናወን ታውቋል፡፡
ኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን በአሠልጣኝ አሸናፊ አባተ እየተመራ ዮርዳኖስ ባዘጋጀችው የዓለም ዋንጫ መጨረሻ ዙር ደርሶ 5 ለ 4 በሆነ የፍጹም ቅጣት ምት በካሜሮን አቻው በመረታቱ ከውድድር ውጪ መሆኑ ይታወሳል፡፡ ሊቢያ፣ ጂቡቲ፣ ሴራሊዮን፣ ጋሞቢያ፣ ዛምቢያ፣ ቦትስዋና፣ ኬንያ፣ ኢትዮጵያ፣ ማሊ፣ አልጄሪያ በቀድሞ ማጣሪያ ውስጥ የተካተቱ አገሮች ናቸው፡፡
ጋና፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ሞሮኮ፣ ኢኳቶሪያል ጊኒ፣ ናይጄሪያና ካሜሮን ደግሞ ወደ መጀመሪያው ማጣሪያ ውድድር ውስጥ በቀጥታ ያለፉ አገሮች ናቸው፡፡ ቀይ ቀበሮዎቹ ባለፉት የውድድር ዘመናት በተለያዩ የአፍሪካ ውድድሮች መካፈል የቻሉ ቢሆንም ውድድሩ ከተጠናቀቀ በኋላ መበተን የሁልጊዜም ተግባር እየሆነ ከመጣ ሰነባብቷል፡፡
ጭላንጭል ከታየ በኋላ ብሔራዊ ቡድኑን በማደራጀትና በተለያዩ ዝግጅቶች ጨዋታ ከወዲሁ መዘጋጀት እንዳለበት የአሠልጣኞች አስተያየት ሲሰጥ ከርሟል፡፡
የሴቶች ከ17 ዓመት በታች ፊፋ ዓለም ዋንጫ በየሁለት ዓመቱ የሚደረግ ሲሆን፣ በቀጣይ ለስድስተኛ ጊዜ በዑራጓይ አዘጋጅነት ከኅዳር 11 እስከ ታኅሣሥ 4 ቀን 2010 ዓ.ም. ይከናወናል፡፡
ከስድስቱም አህጉሮች የተወጣጡ 16 አገሮች የሚሳተፉበት ሲሆን፣ ቦሲኒያ ሄርዞ ጎቪኒያ፣ ግብፅ፣ ፈረንሣይ፣ ሰሜን አየርላንድና ስዊድን ሻምፒዮናውን ለማዘጋጀት ፍላጎት ያሳዩ ቢሆንም የፊፋው ፕሬዚዳንት ጃያኒ ጊንፋንቲኖ በዑራጓይ ባደረጉት ይፋዊ ጉብኝት ዑራጓይ እንድታዘጋጅ መወሰኑ ይታወቃል፡፡