የኢትዮጵያ ብሔራዊ የፀረ አበረታች ቅመሞች ጽሕፈት ቤት (ናዶ) ከፌዴራልና ከአዲስ አበባ የምግብ፣ የመድኃኒት ጤና ክብካቤና ቁጥጥር ባለሥልጣን ጋር በመተባበር በአበረታች ንጥረ ነገር (ዶፒንግ) ዙሪያ ለሕክምና ባለሙያዎች ሥልጠና ሰጠ፡፡
ነሐሴ 11 ቀን 2009 ዓ.ም. የተሰጠው ሥልጠና በዋናነት በዶፒንግ ምንነት፣ በዓለም የፀረ ዶፒንግ ሕጎች የአሠራር ሥርዓቶች እንዲሁም የስፖርተኞች ሕክምና አሰጣጥን በተመለከተ ነው፡፡
እ.ኤ.አ. በ2017 በተከለከሉ መድኃኒቶችና ንጥረ ነገሮች ዙሪያ፣ መድኃኒት ቤቶች የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት በተመለከተ መድኃኒቶቹ እንዴት መሸጥ እንዳለባቸውም በሥልጠናው ተካቷል፡፡
በሥልጠናው ላይ የተሳተፉ የሕክምና ባለሙያዎችና አመራሮች ዶፒንግ በመከላከልና በመቆጣጠር ረገድ በየደረጃው በሚካሄደው ዘርፈ ብዙ ጥናት ውስጥ በንቃት በመሳተፍ ስፖርቱንና ስፖርተኛውን እንዴት መታደግ እንደሚችሉ ከሥልጠናው ትምህርት ማግኘታቸውን ገልጸዋል፡፡
ከሳምንት በፊት የእንግሊዙ ዘጋርዲያን የዜና አውታር፣ ከኢትዮጵያ የረዥም ርቀት ሩጫ ጀርባ የኢትዮጵያ መድኃኒት ቤቶች ጥንቃቄ የጎደለው አሻሻጥ አለበት በሚል ዘገባ ማቅረቡ ይታወሳል፡፡ የእንግሊዙ ጋዜጣም ግሸን መድኃኒት ቤትን መጥቀሱ የሚታወስ ሲሆን፣ መድኃኒት ቤቱም በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫም ኢፒኦ አበረታች ንጥረ ነገር መሆኑን አለማወቁን ገልጾ ነበር፡፡
በዚህም መሠረት በእንግሊዙ ጋዜጣ ላይ የቀረበው ዘገባ በጤና ባለሙያዎች ላይ ትኩረት ሰጥቶ ለመሥራት መንገድ እንደፈጠረ ተገልጿል፡፡ ‹‹ሪፖርቱ በጤናው ዘርፍ የበለጠ ትኩረት ተሰጥቶ መሠራት እንዳለበትና እንደሚሠራና ባለሙያውም ትምህርት እንዲሰጠው አድርጎናል፤›› በማለት የኢትዮጵያ ብሔራዊ የፀረ አበረታች ቅመሞች ጽሕፈት ቤት (ናዶ) ዋና ዳይሬክተር አቶ መኰንን ይደርሳል ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
ምንም እንኳ ግንቦት ወር ላይ የሠራውን የምርመራ ዘገባ በለንደኑ ሻምፒዮና መክፈቻ ላይ በማቅረብ የኢትዮጵያን የፀረ አበረታች እንቅስቃሴ ጥላሻት የቀባ ዘገባ የነበረ ቢሆንም፣ በፀረ አበረታች እንቅስቃሴዎች ላይ ትኩረት በመስጠት እንድንሠራ ንቃት ፈጥሮልናል በማለት አቶ መኰንን ያስረዳሉ፡፡
በኢትዮጵያ ሆቴል በተሰጠው ሥልጠና ላይ ከ200 በላይ የሕክምና ባለሙያዎች የተሳተፉ ሲሆን፣ ከፌዴራልና አዲስ አበባ የመድኃኒትና ጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለሥልጣን መድኃኒት እንዴት መሸጥ እንዳለባቸውና መድኃኒት ቤቶቹ የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት በተመለከተም ማብራሪያ ተሰጥቷቸዋል፡፡
ከዚህ ጋር በተያያዘም የሕክምና ባለሙያዎቹና የመድኃኒት ቤት ባለሙያዎቹ ከውጭ አገር የሚመጡት መድኃኒቶች ላይ ቁጥጥር ማድረግ እንደሚገባቸው የተገለጸ ሲሆን፣ ባለሙያዎቹም አያያዛቸውና አሻሻጣቸው ላይ ጥንቃቄ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል፡፡ የበላይ አካሉም በሕገ ወጥ መንገድ የሚገቡ መድኃኒቶች ላይ ቁጥጥር እንዲያደርግ አስተያየታቸውን ሰንዝረዋል፡፡
በተጨማሪም የሚሰጠው ሥልጠና ቀጣይነት እንዲኖረውና በቀጣይ በክልል ለሚገኙ ባለሙያዎች ጭምር መሰጠት እንዳለበት በሥልጠናው ወቅት ተጠቅሷል፡፡
በሚኒስቴሮች ምክር ቤት መጋቢት 15 ቀን 2009 ዓ.ም. ፀድቆ ሥራውን የጀመረው ብሔራዊ የፀረ አበረታች ጽሕፈት ቤት በአገር ውስጥ ከፍተኛ ውድድሮች ላይና በዓለም አቀፍ ውድድሮች አገራቸውን ወክለው የሚሳተፉ ስፖርተኖች ላይ ምርመራ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡
ምርመራው በሁለት ዓይነት መንገድ የሚያከናውነው፣ በውድድር ጊዜና ከውድድር በኋላ ነው፡፡ በዓለም አቀፍ ሻምፒዮና ላይ የሚሳተፉ አትሌቶች ላይ ሁለቱም ዓይነት የምርመራ መንገድን እንደሚከተሉ አቶ መኰንን አስረድተዋል፡፡
ብሔራዊ ጽሕፈት ቤቱ ሥራ ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ በአትሌቲክስ፣ በቦክስ፣ በፓራሊምፒክና በብስክሌት ላይ ባጠቃላይ በ557 ስፖርተኞች ላይ ምርመራ አከናውኗል፡፡