የወርልድ ቴኳንዶ ስፖርት በ1970ዎቹ ውስጥ መጀመሩን የብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴ መረጃ ያመለክታል፡፡ ስፖርቱን ለማስፋፋት ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ወደ ተግባር ከገባ በ5 ዓመታት ውስጥ በአገሪቱ ስፖርቱን ለማስፋፋት በርካታ ስፖርተኞችንና ክለቦችን ሊፈሩ ችሏል፡፡ ለኢትዮጵያ ወርልድ ቴኳንዶ ፌዴሬሽን ትልቁ ስኬት በ2006 ዓ.ም. ኮንጎ ብራዛቪል ባዘጋጀችው 11ኛው የመላው አፍሪካ ጨዋታዎች ናርዶስ ሲሳይ የወርቅ ሜዳሊያ ማግኘት ነው፡፡ ከአትሌቲክስና ብስክሌት ቀጥሎ ቴኳንዶ በወርቅ መዝገብ ውስጥ ለመግባት ችሏል፡፡ የወርልድ ቴኳንዶ ስፖርትን በኢትዮጵያ ይበልጥ ለማስፋፋት እንዲያመች የኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዴሚ በአካዴሚው ውስጥ ሥልጠና ለመስጠት ከብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ጋር የመግባቢያ ስምምነት አድርጓል፡፡ ነሐሴ 25 ቀን 2009 ዓ.ም. የጋራ መግባቢያ ሰነዱ የተፈረመው፣ ወጣቶች ለቴኳንዶ ስፖርት ያላቸው ዝንባሌ እንዲያድግ ለማድረግና በዚህ ደረጃ የሚሰጣቸው ሥልጠና ለከፍተኛ ደረጃ እንዲበቁ ለማድረግ ነው፡፡ ስምምነቱን የአካዴሚው ዋና ዳይሬክተር አቶ አምበሳው እንየውና የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ ዳዊት አስፋው ተፈራ (ፎቶ በቀኝ) ተፈራርመዋል፡፡ ስምምነቱ ለብሔራዊ ቡድን ቅድመ ዝግጅት ከመርዳቱም ባሻገር ባለሙያዎችን ለማፍራት እንደሚያስችል አቶ ዳዊት ተናግረዋል፡፡ (በዳዊት ቶሎሳ)