Monday, July 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ይድረስ ለሪፖርተርበስብሰባና ሥልጠና ሽፋን የሚሠሩ ‹‹ሙስናዎች››

በስብሰባና ሥልጠና ሽፋን የሚሠሩ ‹‹ሙስናዎች››

ቀን:

የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ ስለ ሥልጠና፣ ስብሰባና ሙስና ምንነት ትንታኔ ለማቅረብ ሳይሆን፣ በእነዚህ ምክንያት ለሚባክኑ የሕዝብ ገንዘቦችና ንብረቶች የሚመለከታቸው መሥሪያ ቤቶችና ሹመኞች የተዝረከረከውን አሠራር በማጤን የሕግ ሥርዓት እንደዲዘረጉለት (ልግጓም) እንዲያበጁለት ለመነሻ የሚሆን መረጃ ለማቀበል ነው፡፡

በስብሰባ ሥልጠና ስም የሚካሄዱ ሌብነቶችና መገለጫዎቻቸው

የሁሉም መሥሪያ ቤቶች መገለጫ ባይሆንም በየቦታው በስፋት የሚታየው የስብሰባው ዓላማ ይግባውም አይግባውም በጅምላ ተሳታፊ ማድረግ የተለመደ ሆኗል፡፡ በከፍተኛ ወጪ በመንግሥት የተሠሩና ለአገልግሎት የተቀመጡ አዳራሾች እያሉ ከፍተኛ ወጪ በማውጣት በትላልቅ ሆቴል ስብሰባዎች እንዲካሄዱ ማድረግ፣ ተው ባይ የሌለው የበርካታ መሥሪያ ቤቶች የተለመደ አሠራር ነው፡፡

ሌላው አሳዛኝና አሳፋሪ ተግባር ዘጠኝ በመቶ የሚሆኑት የስብሰባ ተሳታፊ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ሆነው ሳለ ለአየር ለውጥ ይሁን ሌላ ስብሰባውን ወደ ሌላ ከተማ በመውሰድ የአገርና የሕዝብ ገንዘብ ለሆቴል መስተንግዶ (አልጋ፣ ቁርስ፣ ምሳና እራት ወዘተ.) ሲሳይ እየሆነ ይገኛል፡፡ አስገራሚው ትርዒት በዚህ ብቻ አይገራም፡፡ በተለይ ባለሥልጣን ከሆኑ ለብቻው በተዘጋጀ ትራንስፖርት ስለሚጓጓዙ ለሾፌርና ለጠባቂዎች በተመሳሳይ ሁኔታ ወጪ መውጣቱ አይቀሬ ነው፡፡

በዚህ ጎጂ ባህል የተነሳ በተለይ በወረዳ፣ በቀበሌና በመሥሪያ ቤት ደረጃ በሚደረጉ ስብሰባዎች አበልን እንደ ተጨማሪ የገቢ ምንጭ የማሰብ አባዜ በመስፋፋቱ ስብሰባን በአበል ምክንያት ይናፍቃሉ፡፡ ስብሰባ ሲዘገይ ቅር ይላቸዋል፡፡ በተለይ ወቅታዊ የሆኑ ጉዳዮች ሲከሰቱ ለስብሰባ መኖር እንደ መልካም አጋጣሚ የሚቆጠሩ ሰዎች ቁጥር ቀላል አይደለም፡፡

አስገራሚና አስደናቂው ነገር ወይም ባህላችን እየተሸረሸረ ከመጣበትና የሞራል ውድቀት መገለጫ መካከል ለስብሰባው በሚል ውኃ፣ ቆሎ፣ ኮፍያና ቲሸርት ወዘተ. ታድሎም ለተሳታፊዎች አበል ካልተከፈለ ሌላው ቀርቶ ከፋዮቸ ከዘገዩ የሚስተዋለው ማጉረምረም፣ መነጫነጭና ማማረር ሰዎች በስብሰባ የሚሳተፉት ለዓላማ ወይስ ለውሎ? የሚያሰኝ ነው፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በ2009 ዓ.ም. በሥሩ የሚተዳደሩ መሥሪያ ቤቶች በስብሰባና በሥልጠና ምን ያህል ገንዘብ እንደወጣ ስታስቲክሱን ቢመለከቱ ለቀጣይ 2010 በጀት ዓመት ጥንቃቄ ለመውሰድ ይረዳል የሚል እምነት አለኝ፡፡

ሙስና ሁለት

አበል ከሌለ ‹‹ስብሰባ ይደብራል›› የሚለው አባባል የተለመደ ቋንቋ ሆኗል፡፡ ስብሰባ አለ ሲባል የብዙዎች የመጀመርያ ጥያቄ አበል አለው? የሚል ነው፡፡ አበል የሚከፈልበት ሁኔታና ሥርዓት እንዳለው ግልጽ ነው፡፡ ይሁን እንጂ በተሳሳተ ግንዛቤ ዛሬ በተለይ ስብሰባ ለማካሄድ አበል ማባባያ ሆኗል፡፡ በየትኛውም ደረጃ በሚካሄዱ አብዛኛዎቹ ስብሰባዎች በተለይ ከአበል ጋር ንክኪ ያላቸው በተጨማሪ ኮፍያ፣ ቲሸርትና ስካርቭ ወዘተ. ማደል እንደ ባህል ተይዟል፡፡ እንደሚባለው ለአነስተኛና ጥቃቅን ኢንተርፕራይዞች ገበያ የመፍጠር ሁኔታ ነው፡፡ ከዚህ ይልቅ የምርት ጥራትን አሻሽለው በገበያ ተወዳዳሪ የሚሆኑበትን አሠራር መዘርጋት ተመራጭ ይሆናል፡፡ የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ ወደፊት አባሎች አልባሳቶችና የምግብ አቅርቦቶች ከሌሉ ማንኛውንም ስብሰባ ለማካሄድ አዳጋች ሊሆን ይችላል የሚል ሥጋት አለው፡፡

ሙስና ሦስት

በስብሰባ የተገኙ ሰዎች በተዘጋጀው የስም መመዝገቢያ ቅጽ ጠዋትና ከሰዓት በኋላ በሚለው ቦታ እንዲፈርሙ ይደረጋል፡፡ ስብሰባው በግማሽ ቀን ቢጠናቀቅም ‹‹የሙሉ ቀን አበል›› መክፈል የተለመደና ከልካይ የሌለው አሠራር ሆኗል፡፡ ይህ ብቻ አይደለም ስብሰባውን የጠራው አካል በመዝጋቢነት፣ ገንዘብ ከፋይነት፣ ሒሳብ ሠራተኛነት፣ አስተባባሪነትና ሾፌር ወዘተ. ከአንድ ሰዓት ላልበለጠ ጊዜ አገልግሎት ሳይሰጡ የሙሉ ቀን አበል ተከፋይ መሆን ከሌብነትና አጭበርባሪነት ተለይቶ ይታያል?

ሙስና አራት

      ስብሰባው ወይም ሥልጠናው ሁለትና ሦስት ቀን የሚወስድ ከሆነ በተለይ ሹማምንትና ካድሬዎች የመክፈቻው ቀን ፊታቸውን አሳይተውና ስማቸውን አስተክለው በመሰወር፣ የስብሰባው ማጠቃለያ (መዝጊያ) ላይ በመገኘት ያለምንም እፍረትና ይሉኝታ አበል ፈርመው ሲቀበሉ መታየቱ አሳዛኝና አሳፋሪ ነው፡፡ በዚህ ተግባር በስፋት የሚታዩት ደግሞ ለሌላ አርዓያ ይሆናሉ የተባሉ የሥራ ኃላፊዎች መሆን፣ ለሌሎች የመጥፎ ሥነ ምግባር ምሳሌነት ተከታይ እንዲሆኑ በር ከፍቷል፡፡

ሙስና አምስት

በየደረጃው በዓሉ የመንግሥት መዋቅሮች የሚካሄዱ ስብሰባዎች፣ ኮንፍራንሶች፣ ወዘተ.  የሚወጣውን ወጪ የቁጥጥርና ክትትል ሲስተሙ ጠንካራ ባለመሆኑ በስብሰባና ሥልጠናዎች የሚሳተፉ ሰዎች የነፍስ ወከፍ መስተንግዶ አጠቃቀም ስለሚለያይ የስብሰባው አስተባባሪዎችና የመስተንግዶ ምግብና መጠጥ አቅራቢዎች ወይም ከባለሆቴሎች ጋር በመመሳጠር የተሳታፊ ቁጥርንና ያልተጠቀሙበትን ፍጆታ ከፍ በማድረግ የሕዝብና የአገር ሀብት የግለሰቦች መጠቀሚያ ለመሆን ዕድሉ ሰፊ ነው፡፡

ከላይ እንደ ናሙና የጠቀሱትን በስብሰባ ሽፋን የሚፈጸሙ ሙስናዎችን መከላከል ወቅታዊ የትኩረት አቅጣጫችን ሊሆን ይገባል፡፡ የመንግሥት ሆነ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚያካሂዷቸው ስብሰባዎችና ኮንፍራንሶች ወዘተ. የተሳታፊዎች ብዛት፣ የስብሰባ ቦታ፣ የሚወስደው ጊዜ፣ የሚያስከትለው ወጪ፣ የፋይናንስ ሕግን በተከተሉ ኃላፊነትና ተጠያቂነት ያለበት አሠራር ሊጠናከር ይገባል፡፡ በአጭሩ ወጥነት ያለው ግልጽነት የተላበሰና ሁሉም የሚያውቀው የጠራ መመርያ ሊኖር ይገባል፡፡

የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ ለስብሰባዎች፣ ለኮንፍራንሶች፣ ለሥልጠናዎች፣ ወዘተ.   ወጪ አይኑር የሚል ጨለምተኛ አመለካከት የለውም፡፡ ይልቁን መሥሪያ ቤቶች ስብሰባዎች፣ ሥልጠናዎችና ኮንፍራንሶች ዕቅድ ይኑራቸው፡፡ በጀቱ የተጠናና የበላይ መሥሪያ ቤቱ ኃላፊ አምኖበትና አፅድቆት ይካሄድ፡፡ ስለ ወጪያቸው አፈጻጸም ተገቢው የቁጥጥር ሥርዓት ይዘርጋላቸው፡፡ ሥልጣናዎቹ ዴሞክራሲን ለማጎልበት፣ ልማትን ለማፋጠን፣ ችግሮችን ለመፍታትና የሥራ ተነሳሽነትን ለመፍጠር መሆናቸው በበላይ መሪዎች ይረጋገጡ፡፡ ፋይዳቸው በጥልቀት ይፈተሽ የሚል ነው፡፡

በስብሰባና ሥልጠና ሽፋን ሙስና እንዳፈጸም እንደ መነሻ መፍትሔ ይሆናሉ ያልኳቸውን እንደሚከተለው እገልጻለሁ፡፡

  1. ማንኛውም መሥሪያ ቤት በበጀት ዓመቱ የሚያካሂዳቸውን ስብሰባዎች፣ ሥልጠናዎች አስቀድሞ የስብሰባውንና ሥልጠናውን ፋይዳ ከማጤን ጀምሮ በምን ርዕሰ ጉዳይ? መቼ? ለምን ያህል ጊዜ? ለስንት ሰው? የት ቦታና ወጪውን በተመለከተ በዝርዝር ዕቅድ በማውጣት በበላይ ኃላፊዎች መፅደቅ አለበት፡፡ 
  2. በዕቅድ የተያዙ ስብሰባዎችና ሥልጠናዎች በተያዘላቸው ፕሮግራም መሠረት ተጨማሪ ጊዜ ሳይወስዱና ሳይሸራረፉ ተግባራዊ ባለመደረጋቸው የመቆጣጠሪያ ሥልት ሊዘረጋ ይገባል፡፡ አስቸኳይና አስገዳጅ ስብሰባዎች ሲከሰቱ በተመሳሳይ ሁኔታ የሚያስከትሉት ወጪ በሰከነ ሁኔታ ሊታይ ይገባል፡፡ ግርግር ለሌባ ይመቻልና!
  3. ስብሰባዎችና ሥልጠናዎች ለይስሙላ ሳይሆን ሰውን ለመቀየር፣ ለለውጥና ለልማት የሚያነሳሱ፣ የተዛቡ ግንዛቤዎችን ማጥሪያ መሆናቸው፣ ከርዕስ መረጣ ጀምሮ ሥልጠና ሰጪዎች /አወያይ/ አቅምን የፈተሸና የተሳታፊዎችን ስብጥር ማጤን አለበት፡፡ ለምሳሌ ስለ ትምህርት ካሪኩለም፣ የማስተር፣ ሥነ ዘዴ በተዘጋጀ ስብሰባ/ሥልጠና/ መምህሩ መሳተፍ ሲገባው የማይመለከተው ጠቅላላ አገልግሎት ሠራተኛ እንዲገኝ ማድረግ ብክነትን (ሙስና) መሆኑን ማወቅ፡፡
  4. ስብሰባዎች በድንገት ሳይሆን ቢያንስ ከሦስት ቀናት በፊት ተሰብሳቢዎች የመሰብሰቢያ ቀንና ሰዓት፣ ቦታውን አጀንዳውን ቢያውቁት፣ ስብሰባው ጠዋት በሦስት ሰዓት የሚጀመር ከሆነ በሰዓቱ ቢጀመር፡፡ ሰዓት አሳልፈው የሚመጡ ወደ ስብሰባው እንዳይገቡ ማድረግና ለምን ሰዓት አክብረው እንዳልተገኙ በመሥሪያ ቤታቸው ኃላፊ ተጠያቂ የሚሆኑበት አሠራር መዘርጋት፣ ሰዎች የስብሰባ ዲሲፕሊን እንዲኖራቸው ያስችላል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ከሁሉ በፊት ግን ስብሰባውን የሚመሩ፣ የሚከፍቱ፣ የሚዘጉ ሰዓት አክብረው በመገኘት አርዓያነት ይጠበቅባቸዋል፡፡
  5. በስብሰባ የሚገኙ ተሳታፊዎች አበል አከፋፈል ተመን በአመቸ ሳይሆን ተመን ሊወጣለት ይገባል፡፡ የተሳታፊዎች ማንነት የሚገልጽ ሙሉ መረጃ መኖሩ እየተረጋገጠ ክፍያዎች ባለፈመጸማቸው የመሥሪያ ቤቱ የበላይ ኃላፊ ተጠያቂነት ያለው አሠራር ሊዘረጋና አፈጻጸሙን የመቆጣጠር የመከታተል ኃላፊነት አለበት፡፡

(ከሰይፈ ወልደ ፃዲቅ፣ አዲስ አበባ)

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...