Thursday, April 18, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ተሟገትየሐውልቱን ነገር እስኪ እንነጋገር

የሐውልቱን ነገር እስኪ እንነጋገር

ቀን:

በገነት ዓለሙ

የዓመቱ የመጨረሻ ሳምንት፣ እንዲሁም የዓመቱ የመጨረሻና 13ኛ ወር ውስጥ እየገባን ነው፡፡ የምንሰናበተው 2009 ዓ.ም. ከሁሉም በላይ በኦፊሴል የሚታወቀው አስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ ውስጥ የነበርንበት መሆኑ ነው፡፡ ከመስከረም 28 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ ሐምሌ 28 ቀን 2009 ዓ.ም. ድረስ የዘለቀው የአሥር ወራት የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታን አምጦ የወለደው፣ ከኅዳር 2008 ዓ.ም. ጀምሮ አደባባይ የወጣው ታይቶ የማይታወቀው ተቃውሞ ነው፡፡

መጀመሪያ ዙሪያ ከተሞችን ያቀፈ የአዲስ አበባ የልማት ዕቅድን በመቃረን በ2006 ዓ.ም. ተነስቶ የነበረው የኦሮሞ/ኦሮሚያ ተቃውሞ አሸልቦ ቆይቶ፣ በ2008 ዓ.ም. ኅዳር እንደገና አገረሸ፡፡ ብዙ ሥፍራዎችንም እያዳረሰ ለወራት ቀጠለ፡፡ ጥር መግቢያ ላይ ኦሕዴድ ስለኦሮሞ የሉዓላዊነት ውሳኔ አውስቶ ፕሮጀክቱ መታጠፉን ቢለፍፍም፣ ተቃውሞው በመብረድ ፋንታ ብሶበት አረፈው፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

 በተለይ በ2008 ዓ.ም. ክረምት የተቃውሞው ማዕበል ከመንግሥት አያያዝም ነዳጅ እያገኘ የተጋጋለበት፣ የመንግሥት የመቆጣጣር አቅምም ያጠራጠረበት፣ በመንግሥትም ብልኃትና መለኛነት ላይ የተሳለቀለበት ወቅት ነበር፡፡ በተቃውሞው ምክንያት የፈተና ዝግጅት ካላሟሉ አካባቢዎች ወደ ከፍተኛ ትምህርት የሚያስገባው የ12ኛ ክፍል የፈተና ጊዜ ይራዘም የሚል ጥያቄ ሲነሳ፣ ለጥያቄውም ሆነ ፈተናው ተሰርቋል ለሚለው ወሬ ጆሮ አልሰጥም፣ ፈጽሞ ውሸት ነው ያለው መንግሥት ባቀደው ቀን (ግንቦት 22 ቀን 2008 ዓ.ም.) እሽግ ተከፍቶ የፈተና ሒደት ሲያስጀምር፣ ፈተናዎቹ በዋዜማው በስልክ አማካይነት ከተሠራጩት ጋር አንድ መሆናቸውን ‹‹ደርሼበታለሁ›› ይላል፡፡ መንግሥት ፈተና የማራዘም ጥያቄን ቢቀበል ኖሮ በቅን አሳቢነት ይተርጎምለት ይችል የነበረው ጉዳይ ወደ ቅሌት ተቀየረ፡፡ በአጠቃላይ የ2008 ዓ.ም. የሕዝብ ተቃውሞዎች ኦሮሚያ – አማራ – ደቡብ – ኦሮሚያ እያለ ተወዛውዘው በአንዴ ሁሉም ዘንድ ተዳረሱ፡፡ በ2008 ዓ.ም. የሰኔ 28 የቂሊንጦ እስር ቤት፣ የነሐሴ 26 የደብረ ታቦር እስር ቤት ቃጥሎ አያያዙና ‹‹መስተንግዶው›› ጭምር በኢትዮጵያ ‹‹የመልካም አስተዳደር›› ውዳቂ ደረጃ እንኳን አስተዛዛቢና አሳፋሪ ነበሩ፡፡

ምናልባትም ከዚህ ሁሉ በበለጠ ግን መንግሥትን በመፈታተን ከዚያም በላይ በማራድ፣ እንዲሁም አስተዋይነት የጎደለው የማናለብኝና የቢሻኝ ዕርምጃ ምን ያህል መዘዘኛ ሊሆን እንደሚችል በማሳየት ረገድ፣ የመስከረም 22 ቀን 2009 ዓ.ም. የኢሬቻ በዓልን አሳዛኝ አደጋና እልቂት የሚስተካከለው አልነበረም፡፡ ይህን ጉዳይ ዛሬ በዓመቱ የኢሬቻ የ2010 ዓ.ም. በዓል በሚከበርበት የዋዜማ ወር ላይ ሆነን መልሰን የምናስታውሰው ይህን የመሰለ እልቂትና ጥፋት እንኳን የማይበግረው፣ የማይዛለቀውና በማያሰማው ‹‹አይደገመኝም›› የማይል አስተዳደር ያቆመው የቢሾፍቱ ሐውልት ስላስደነገጠን ነው፡፡   

 በ2009 ዓ.ም. በኢሬቻ በዓል መዳረሻ ሰሞን መላው የክረምት ወራት በሙሉ የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ አዋጅ ባይታወጅበትም፣ ውጥረት የተሞላበት ወቅት ነበር፡፡ ገዢው ፓርቲ ከነሐሴ 10 ቀን እስከ ነሐሴ 22 ቀን ድረስ በሥራ አስፈጻሚው ኮሚቴና በድርጅቱ ምክር ቤት ስብሰባ ውሳኔና መግለጫ አማካይነት ለሕዝብ ምሬትና እሪታ ያቀደውን ምላሽ የማያሰማበት ጊዜ ነበር፡፡ በተለይም ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ነሐሴ 24 ቀን 2008 ዓ.ም. በሰጡት ወቅታዊ ሁኔታውን የተመለከተ መግለጫ፣ ‹‹መንግሥት የሕግ የበላይነትን ለማስከበር ሁሉንም አቅሙን ይጠቀማል፡፡ በእኔ በኩል ይህ በሕግ የበላይነት እንዲከበር ለማድረግ ሁሉም የፀጥታ አካሎቻችን የሕግ የበላይነትን እንዲያስከብሩ አዝዣለሁ፡፡ ስለዚህ ሁሉም የፀጥታ አካሎታችን የሕግ የበላይነትን ማስከበር ጀምረዋል፡፡ የጀመሩትንም የሕግ የበላይነት አጠናክረው ይቀጥላሉ፤›› ያሉበት ጊዜ ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን መልስና መረጃ የሰጡት የመንግሥት ሚዲያው ‹‹መንግሥት የሕግ የበላይነት የማስከበር ብቃት እንዳጣ አድረገው የሚመለከቱ ወገኖች ተበራክተዋል››፣ ‹‹በብዙ የማኅበረሰቡ ክፍል ሥጋቱም ጨምሯል›› በማለት ላቀረበላቸው ጥያቄ ነበር፡፡

በዚህ ወቅትና በበዓሉ መዳረሻ ሰሞን ኢሬቻን ዩኔስኮ በቅርስነት እንዲመዘግበው እየተደረገ ስለነበረው ጥረት ይራገባል፡፡ ዋዜማውም በሩጫ ውድድር ደምቋል፡፡ እነዚህና ተያያዥ በመንግሥት አማካይነትና በመንግሥት በኩል የሚከናወኑ ተግባሮች ሁሉ በኢሕአዴግ/ኦሕዴድ ገዢነት ላይ እያሻቀበ የመጣውን የዓይንህ ለአፈር ተቃውሞ የማርገብ መከራዎች ነበሩ፡፡ በመንግሥት በኩል ልዩ ልዩ የሕዝብ በዓላትን ለመንግሥታዊ ድጋፍ መነገጃነት መጠቀም አዲስ አይደለም፡፡ በ2009 ዓ.ም. መስከረም ወር ውስጥ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ እየከበደ የመጣው ተቃውሞ ግን ይህንን እንዳላየ ለማለፍ የፈቀደ አልነበረም፡፡ ተቃውሞው የመንግሥትን የፖለቲካ ንግድ በማክሸፍ ብቻ ሳይወሰን፣ የኢሬቻ ዋዜማን ምሽትን እስከ ዕለተ ቀኑ ድረስ በተቃውሞ መድረክነት ተቆጣጥሮት ነበር፡፡ ባህላዊውና እምነታዊው የኢሬቻ ክብረ በዓል ከየትኛውም የፖለቲካ ጫና ነፃ ሆኖ እንዳይካሄድ ያደረገው የመንግሥትና የተቃዋሚ እኔ አተርፍ እኔ አተርፍ ትንቅንቅ መሆኑ አጠያያቂ አይደለም፡፡ ወጣቶችና አገር የሚመራ መንግሥት የሚኖራቸው የኃላፊነትና የተጠያቂነት ድርሻ ግን ሰማይና መሬት ነው፡፡ ሰላማዊ ሠልፍና ተቃውሞ በተኮላሸበት ሁኔታ ላይ ቆሞ ተቃዋሚዎች የበዓሉን አጋጣሚ ለምን ተጠቀሙበት ብሎ መፍረድ ኅሊናን ይተናነቃል፡፡

 እንደዚያም ሆኖ ክብረ በዓሉ ወደሚካሄድበት የሆራ ሐይቅ አካባቢ ሰው እየተፈተሸ ማለፉ፣ በተሰበሰበው ሕዝብ ፊት የነበሩት ፖሊሶች መሣሪያ አለመያዛቸውና በታጋሽነት መሞላታቸው፣ የትንኮሳ ሰበብ ላለመሆን በፀጥታ ኃይሉ በኩል ዝግጁነት እንደነበር ያሳየ ነው፡፡ የቅዋሜ ሁካታውን በሃይ ሃይታ አስቁሞ ሥነ ሥርዓቱን ማጠናቀቅ እንደማይቻል ለማንም ግልጽ ከሆነ በኋላም፣ የሐይቁን ዳርቻ ጠባብነትና የሰውን ብዛት ግንዛቤ ውስጥ አስገብቶ በአስለቃሽ ጋዝ ተቃውሞን መበተንና እንደገና በዓሉን ማስቀጠልም የሚቻል እንደማይሆን አጢኖ ማቋረጥና ሕዝብ ከሥፍራው እስኪለቅ መጠበቅ ኃላፊነት የሚሰማው ተግባር ነበር፡፡ ይህ ተደርጎ ቢሆን ኖሮም ከተቃዋሚዎቹ ይበልጥ የፖለቲካ ትርፍ ለመንግሥት ባስገኘለት ነበር፡፡ ይህን አዙሮ ማየት ከብዶ ወይም ለተቃውሞ አልሸነፍ ባይ እልህ ያንን ሁሉ ትዕግሥት ገደል ሰዶ አስለቃሽ ጋዝ ይተኮሳል፡፡ ተኩሱ የፈጠረው ድንጋጤና የሽሽት መጋፋትም ዘግናኝ አደጋ ይወልዳል፡፡ ከዚያ በኋላ እየጮሁ ለማረጋጋትና ሰው ለማትረፍ ቢራወጡ፣ ብዙ ሕዝብ ባለበት ገደላማ የሐይቅ ዳርቻ ሥፍራ የከፋ አደጋና እየዬ መድረሱ የት ሊቀር!

በገልለተኛ የመረጃ ምንጭ ችግር የጉዳቱን መጠን በቁጥር መግለጽ ባይቻልም፣ ሰቅጣጭ ጉዳት ለመድረሱ ግን አንድና ሁለት የለውም፡፡ በዕለቱ ማታ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም በሰጡት መግለጫ የታየባቸው ክውታ፣ ተቃውሞን ለጉዳቱ ሁሉ ተጠያቂ አድርገው ከፀጥታ ኃይሉ በኩል አስለቃሽ ጢስ መተኮሱን አለመኖራቸው፣ የደረሰው ጉዳትና ዕልቂት ፀረ ኢሕአዴግ ዝልዘላና ማዕበል ለማስነሳት እንደሚውል በመፍራት እንደሆነ መገመት ይቻላል፡፡ ይሁን እንጂ መረጃ ደብቆ ኃጢያቱን በተቃውሞ ላይ የመደፍደፉ ጥፋት የተፈራውን ከመሆን አላስቀረውም፡፡ በታወቁ የምዕራብ የዜና ማሠራጫዎች ከአስለቃሽ ጭስ ባለፈ ጎማ ጥይት ስለመተኮሱ ተዘግቦ ሳለ፣ አስለቃሽ ጭሱና የተከተለው የሽሽት ትዕይንት በምሥል ተቀርፆ የተላለፈ ሆኖ ሳለ፣ በሪፖርተር ጋዜጣና በአሜሪካ ድምፅ ሬድዮም በኩል አስለቃሽ ጢስ ስለፈጠረው ድንጋጤ የዓይን ምስክር ዘገባ የተሰጠና ይኸውም በወሬ ቅብብል ብዙ ሰዎች ዘንድ መድረሱ አይቀሬ ሆኖ ሳለ፣ የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ተቃውሞን ብቸኛ ተጠያቂ አድርጎ መድረቁ፣ ጭራሽ ተቃዋሚዎቹ ድንጋይ ውርወራ ጀምረው ሕዝብ ከድንጋይ ለመሸሽ ሲሞክር አደጋ ደረሰ የሚል ሽምጠጣ ውስጥ መዘፈቁ፣ በዚህም ቅሌት ጭራሽ ንዴት እያባዛ የተፈራውን የተቃውሞ ማዕበል ማባባሱን አለማስተዋሉ፣ ገደልና ሜዳንም ማየት እስኪሳነው ድረስ ዞሮበት እንደነበር ያሳየ ነበር፡፡

ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ እስከ መስከረም 28 ቀን 2009 ዓ.ም. የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ድረስ ከፍተኛ ቁጣና እልህ ገንፍሎ በመንግሥታዊና በግል የልማት ሥራዎች ላይ ዘረፋንና ቃጠሎን ያካተተ ልዩ ልዩ ጉዳት ሊደርስ ቻለ፡፡ ለአዲስ አበባ ቅርብ በሆነ አካባቢ ውስጥ እንኳ የረባ የተቋማት ጥበቃ ማድረግ ተስኖ በሰበታ ከተማ ውስጥ 1.2 ቢሊዮን ብር የሚገመት የንብረት ውድመት (መንግሥት ጥቅምት 19 ቀን 2009 ዓ.ም. በሰጠው መረጃ መሠረት) ደረሰ፡፡

ለሰው ልጅና ለሰው ልጅነት ክብር በሚሰጡ አገሮች በእንደዚህ ዓይነትም ሆነ በሌላ የቆሼ (መጋቢት 2 ቀን 2009 ዓ.ም. 115 ሰው የሞተበት) ዓይነት ምክንያት ለተቀጠፉ ወገኖች የሐዘን መድረክ ይፈጠራል፡፡ የሐዘን ቀን ይወሰናል፡፡ ሻማ በማብራትና አበባ በማስቀመጥ ሟቾችን የማሰብና የቋሚዎችን ሐዘን የመጋራት የወግ ማዕረግ ሥርዓት ይፈጸማል፡፡ በግድያ ተጠያቂ የመሆን አለመሆን ጉዳይ እንዳለ ለመመርመር ፈጥኖ ይንቀሳቀሳል፡፡ ጉዳዩ ለገለልተኛ የምርመራ ወይም አጣሪ ተቋም ያመራል፣ ይመራል፡፡ ወይም እንደዚያ ያለ ተቋም ይቋቋማል፡፡ ውጤቱም ከእነ ብይኑ ለሕዝብ ይገለጻል፡፡

እኛ እንዲህ ዓይነት ነገር ባይልልንና ባይሆንለንም ሕገወጥ ተቃውሞ ወይም ሕገወጥ ሠልፍ ውስጥ ባይገባ ኖሮ፣ ሕይወትና ንብረት አይጠፋም ነበር የሚል ማማካኛ መስጠቱ ሊያሳፍረን ይገባ ነበር፡፡ ይህ ግን የአገራችን ተጠያቂነትና ‹‹የዴሞክራሲ›› ወግ በጭራሽ አይደለም፡፡ እንዲያውም የተገደሉት ልማቱን ለማደናቀፍና ሁከት ለመፍጠር ሲሞክሩ ነው ከተባለማ የሕይወት መብት ውድነት ይረክሳል፡፡ የሰው ልጅ ደም ደመ ከልብ ይሆናል፡፡ በሕግ በተፈቀደ ሠልፍና ተቃውሞ ጥያቄንና ቅሬታን የማሰማት መብት የተለያዩ ማወላከፊያዎች በመፍጠር፣ ለጥያቄዎችና ለቅሬታዎች ምላሽ በመንፈግ ወደ ሕገወጥነት የገፋ የመንግሥት አካል በቁጣ ለጠፋ ሕይወትና ንብረት ድርሻ እንዳበረከተ፣ ተጠያቂነትም እንደሚጠቀሰው አገራችን ውስጥ የተዘነጋ ሳይሆን ገና ያልተሰማ ወሬ ነው፡፡ ይህ ሁሉ ከሆነና ከዚህ ሁሉ በኋላም ሕገወጥነትንም ሆነ የተቃውሞ እንቅስቃሴን ወይም ለተቃውሞ እንቅስቃሴ የተሰጠ ምላሽ ያስከተለው አደጋ የፈጠረውን ቁጣ የሚያበርድ የፖለቲካ ንግግር በር የሚከፈትለት፣ ገና ኢትዮጵያ ጨረቃ ላይ ሰው ስታሳርፍ ወይም እሱም ካልተሳካ አህያ ቀንድ ስታወጣ ነው፡፡ ባለፈው ሳምንት እሑድ የተሰማው በቢሾፍቱ ከተማ የተመረቀው የኢሬቻ ሐውልት ዜና ያረዳን ይህንኑ ቁርጣችንን ነው፡፡

በኢቢሲ የነሐሴ 21 ቀን 2009 ዓ.ም. የምሽት ዜና በኢሬቻ በዓል አከባበር ወቅት ሕይወታቸው ላለፈ ወገኖች የመታሰቢያ ሐውልት የቆመላቸው መሆኑን ተገልጾ፣ በ2009 ዓ.ም. መስከረም ‹‹የተከበረው የኢሬቻ በዓል ሰላማዊ እንዳይሆን በተወሰኑ አካላት አነሳሽነት ምክንያት በተከሰተ ግርግርና መረጋገጥ ዜጎች ሕይወታቸውን አጥተዋል፤›› በማለት መልሶ ያንኑ ዜማ ያሰማናል፡፡ በዚያው ዜና ውስጥ እንደተገለጸልንም በዓሉ መስከረም 2009 ዓ.ም. ሲከበር ‹‹የዜጎች ሕይወት እንዲያልፍ ያደረገው ጉድጓዳማ ሥፍራ አሁን በዚህ መልክ ተስተካክሏል፡፡ በቀጣይም የቅድመ ጥንቃቄ ሥራዎች ይሠሩበታል፤›› እያለ የመንግሥትን የፖሊሲ መልዕክት ጭምር ይነግረናል፡፡  

‹‹የዜጎችን ሕይወት እንዲያልፍ ያደረገው ጉድጓዳማ ሥፍራ ነው፤››፣ ‹‹በተወሰኑ አካላት አነሳሽነት ምክንያት በተከሰተ ግርግርና መረጋገጥ ምክንያት ሞቱ፤›› ማለት ለሞት ያበቃቸውን ምክንያትና የእሱንም ውጤት፣ ከዚህም የተገኘውን ትምህርት ለዚህም ሆነ ለመጪው ትውልድ አይናገርም፡፡ ተድበስብሶ የቀረበው እውነት መሰል ነገርም ወደፊት እንዲህ ዓይነት ነገር ላለመደገሙ ዋስትና አይሆንም፡፡ ስታዲየም ውስጥ አፉን ከፍቶ የሚውጥ ጉድጓድና ገደል የለም፡፡ ሲኒማ ቤትም እንደዚሁ ነው፡፡ እዚያ ውስጥ ግን እንኳንስ አስለቃሽ ጭስና የጎማ ጥይት መተኮሰ ቀርቶ፣ የተሰበሰበውን ሰው   የሚያንቦዠቡዥ እሳት መጣ ብሎ ያለ ብልኃትም ሆነ ያለመላ ‹‹ማስጠንቀቅ›› አይቻልም፡፡ ይህን ሁሉ ያድበሰበሰ ከሁሉም በላይ ደግሞ ከነጭራሹ ‹‹የዜጎችን ሕይወት እንዲያልፍ ያደረገው ጉድጓዳማ ሥፍራ ነው፤›› እየተባለ የቆመ ሐውልት በጭራሽ ሐውልት አይደለም፡፡

በምንነጋገርበትና ጉዳዩ በተነሳበት በአሁኑ ሁኔታ ሐውልት ማለት ‹‹አፈር ነህና ወደ አፈር ትመለሳለህ›› ለተባለ የሰው ልጅ ሁሉ የሚቆም፣ በዚህም ዓመተ ምሕረት ተወልዶ በዚህ ዓመተ ምሕረት ሞተ የሚል ሐውልት አይደለም፡፡ ከተለያየ የአገሪቱ አካባቢ መጥተው በአሰቃቂ ሁኔታ የሞቱትን እነዚህን (በኦፌሴል የሚታወቀው ቁጥር 55 ነው) ሰዎች ለስም፣ ለመታሰቢያና ለሐውልት እንዲሁም ለጋራ እዝን ያበቃቸውና ከሌላው የሚለያቸው ጉዳይ የጥቃት ሰለባዎች መሆናቸው ነው፡፡ በቸልተኝነት ስለተገደሉ ነው፡፡

የግፍ የጥቃት ሰለባ በመሆናቸውም መንግሥትና ኅብረተሰቡ በዚህ ምክንያት አልሞቱም የማለትን ክህደት ዝምታና ማድበስበስ ተጋትረው፣ የመታሰቢያና የእዝን ሥፍራ ሰጥተው ለትምህርትና ለአገራዊ ግንዛቤና ንቃት መልካም አጋጣሚ ፈጥረው፣ እንዲህ ያለ ነገር ፈጽሞ እንዳይደገም የሚፈጠሙበት ሐውልት ነው፡፡

እርግጥ ነው በኢቢሲ ዜና ውስጥ ሲጠቀሱና ሲናገሩ የሰማናቸው ሐውልቱን የመረቁት የክልሉ መስተዳድር ስለሐውልቱ መታሰቢያነትና ‹‹ማስተማሪያነት›› መናገራቸው ተነግሮናል፡፡ ‹‹ይህ ሐውልት የቆመው በበዓሉ ሕይወታቸውን ያጡት ዜጎች ከዓመት ዓመት እንዲታወሱ፣ እነሱን ከማስታወስም በላይ እንዲህ ዓይነቱ ክስተት ዳግም እንዳይከሰት በማስተዋል ወደፊት ማድረግ የሚገባንን ጥንቃቄ ሕዝባችንም ሆነ የትኛውም አካል እንዲያውቀው ለማድረግ ነው፤›› ብለዋል ሲባል ሰምተናል፡፡

ብለዋል ሲባል ሰምተናል ያልኩበት ምክንያት ያዳመጥኩት የፕሬዚዳንቱ ንግግር የአማርኛ ትርጉሙን በመሆኑ ነው፡፡ ትርጉሙ ደግሞ የዜናው ባለቤት የኢቢሲ ነው፡፡

በዚህ ምክንያት ከተለመደውና ከተባለው በላይ የምናውቀውና እንድናውቀው የተደረገ አዲስ ነገር አላውቅም፡፡ በኢቢሲ ዜና የተጠቀሱትና ዜናው በጠቀሳቸው ልክ የሰማኋቸው የመዳወላቦ አባ ገዳም፣ ‹‹ያጋጠሙ ችግሮች መማሪያ ናቸው፤›› ብለዋል፡፡ ሥፍራው ወይም አካባቢው መሠራቱ እንደሚያስደስታቸው ገልጸው፣ ‹‹. . . ድሮም በብዙ ሺሕ የሚቆጠር ሕዝብ የሚገኝበት ቦታ ላይ አፉን ከፍቶ መቀመጡ በጣም የሚያሳዝን ነው፤›› ሲሉ ሰምተናል፡፡ የነገሩ ሁሉ መደምደሚያ ዞሮ ዞሮ ‹‹ይረገም ይህ ጉድጓድ›› ሆኖ አረፈው፡፡ ‹‹ጉድጓድ ነው ጠላትህ›› የማሳበቢያ መዝሙር ሆነ፡፡ ሳይጠየቁ መቅረት እንዲህ ደልቶትና ተሞላቆ በሚኖርበት አገር ሐውልት የተሠራለት ለ‹‹በጭራሽ አይደገምም››፣ ለ‹‹አይለመደኝም›› ሳይሆን ለራሱ ለሳይጠየቁ መቅረት አይደለምን?

የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ አዋጁ ከተነሳ በኋላ ባሳለፍነው የነሐሴ ወር አጋማሽ ላይ እንደገና ያገረሸበት የኦሮሚያ ክልል ውስጥ የተቃውሞና የሥራ መዝጋት አድማ በቆየበት አጭር ጊዜ ውስጥ፣ የተለመደው ዓይነት የገፍና የጅምላ እስራትና ግድያ አስከተለ ማለትን አልሰማሁም፡፡ ይህ እውነት ከሆነና የኦሮሚያ ክልል እንደሚባለው ሰላማዊ ሠልፍንና ተቃውሞን በጥይት መቀንደብን ተከላክሎና አስቀርቶ ከሆነ፣ ይኼም ከመንግሥቱ የቁርጠኝነት መሀላ ውጪ የሚኖር የሕግ አስገዳጅነት ያለው ባህሪይ ከሆነና ነገ ደግሞ ሌላ ተቃውሞ ሲመጣ ደግሞ ትዕግሥታችንን በፍርኃት የተረጎሙ ተብሎ መንግሥት ወደ አመሉና ጥፋቱ የሚመለስ ካልሆነ ሐውልት ማለት፣ የሐውልት ግንባታ ጅምር ማለት ከሌላው ይልቅ ይኼኛው ነው፡፡ ይኼም እንደተለመደው ‹‹ካልታዘልኩ አላምንም››፣ ‹‹. . . ማመን ቀብሮ ነው›› የሚያሰኝ ነው፡፡ የመታመንም የሥርዓትና የተቋም ግንባታም ጭምር ነው፡፡

የመታመን ጉዳይ ከተነሳ በዚህ የዘመን መሰናበቻና መባቻ አካባቢ መወሳት ያለበት ዓይን ያወጣ የፕሮፓጋንዳ ይሁን የሕዝብ ግንኙነት ሥራ አለ፡፡

ልክ የዛሬ ዓመት በዚህ ወቅት ብዙ የሕይወትና የአካል ጉዳቶች ደርሰዋል፡፡ እስራት፣ እንባና ጩኸት በርክቷል፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሆነን የአዲስ ዓመት መቀበያ የዘፈን ድግስ አዘጋጅቶ አሸሸ ገዳሜ ማለት ህሊናችንን እሺ አይለውም የሚል ነገር በሙዚቃ ሰዎች አካባቢ ብቅ ይላል፡፡ ይህ መባሉ በመንግሥት ላይ ፖለቲካዊ አንድምታ ቢኖረውም ሲበዛ ጤናማ አስተሳሰብ ነበር፡፡

መንግሥት ራሱም ሆነ ማንኛውም ሰው ከዚህ ጤናማ አስተሳሰብ ጋር በጭራሽ ሊጣላ አይገባም፡፡ በተለይ መንግሥት በዚህ ሐሳብ ተስማምቶ ከዚህ ጤናማ አስተሳሰብ ጋር አባሪ ተነባባሪ ሆኖ፣ በየትኛውም ወገን በኩል ለደረሰ የሕይወት መቀጠፍና ጉስቁልና መታወሻ የሚሆን የሙዚቃ ሥራዎች እንዲቀናበሩ አስደርጎ፣ ከተቃዋሚዎችና ከሕዝብ በኩል ቀንድ የሆነ ጎምቱ ግለሰቦች የተሳተፉበት ሐዘንን ከመጋራት ጎን ለጎን ጥያቄዎች ሁሉ ወደ ጠረጴዛ ዙሪያ የሚመጡበትን አዲስ ምዕራፍ የሚያበስር፣ ስለዚህም የአዲስ ዓመት ቅበላው ‹‹ተመስገን››ን ያጎናፀፈና ቁጣ የሚያበርድ እንዲሆን ባደረገ ነበር፡፡

መንግሥት ያደረገው ግን ከዚህ የተለየ ነው፡፡ ዘፈን አንደግስም ባይነትን  ለማክሸፍ መግቢያ በነፃ ብሎ በግዮን ሆቴል መስክ ላይ በነፃ መግቢያ የሙዚቃ ትርዒት አዘጋጀ፡፡ በሐርመኒ ሆቴል የተሰናዳን የዘፈን ድግስ በአዲስ ዓመት ዋዜማ በቴሌቪዥን የቀጥታ ሥርጭት ለቀቀና እንኳን አደረሳችሁ!  እንኳን ደስ አላችሁ! እያለ ብሶትንና ግርግርን የመጋረድ ሥራ እሠራለሁ አለ፡፡

መሰንበቻውን በዜና እንደሰማነው ደግሞ የዚህ ዓመት የዘመን መለወጫ የሙዚቃ ትርዒት በዕቅድ ተይዞ፣ በመንግሥት ኮሙዩኒኬሽንስ ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት አማካይነት በሰፊው መደገሱ ተነግሮናል፡፡

ዝርዝር ፕሮግራሙም እስከተወሰነ የበዓሉ መዳረሻ ወቅት ድረስ ‹‹Embargoed›› ተደርጓል ተብለናል፡፡ የአዲስ ዘመን መለወጫ የዘፈን ድግስን የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ተግባር ማድረግ በዕውቅና በቁጥር ተወስኖ በጀት ሊመደብለት የሚገባ ሥራ ነው? ለፖለቲካ ችግራችንስ መፍትሔ ያዋጣል? ይህስ እንደ ተለመደው የሕዝብ በዓላትን ለመንግሥታዊ ድጋፍ መግዣ ማድረግ ዓምና ኢሬቻ በዓል መዳረሻ ላይ በሰው ፊትና በአደባባይ ያጋለጠን ሕመማችን መሆኑ ቀረ?

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊዋን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...